ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን በሚቀጥለው ሳምንት ቬትናም ላይ ተገናኝተው መምከራቸውን በጉጉት በሚጠብቅበት ሰዓት፣ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በበኩላቸው ከሰሜን ኮሪያው መሪ ጋር ለመምከር ፍላጎት እንዳላቸው እየተዘገበ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ከኪም ጆንግ-ኡን ጋር በመምከር አገራቸው ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን የቆየ አለመግባባት መፍታት ይፈልጋሉ ተብሏል፡፡ የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታና ሰሜን ኮሪያ ከዓመታት በፊት ያገተቻቸው ጃፓናውያን ጉዳዮች የሁለቱ አገራት ውዝግብ መነሻ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ እ.አ.አ በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ 13 ጃፓናውያንን ማገቷንና ከነዚህም መካከል አምስቱ ወደጃፓን መመለሳቸውን እ.አ.አ በ2002 ገልፃ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ጃፓን ያለፈውን ‹‹መጥፎ ጊዜ›› በመተው ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ፍላጎት እንዳላት ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ሰሜን ኮሪያ ያገተቻቸውን ጃፓናውያንን በተመለከተ ጉዳዩን በሁለትዮሽ ድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም አለን፡፡ ከአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይናና ሩስያ ጋር በመተባበር የኑክሌር ጦር መሳሪያውንና የታጋቾችን ጉዳይ ዳር ለማድረስ ጥረት እናደርጋለን›› ብለዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አቤ የሰሞኑ መግለጫ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ባለፈው ሰኔ ወር ሲንጋፖር ላይ ከመገናኘታቸው አስቀድሞ ከሰጡት የቀደመ አስተያየት ተቃራኒ የሆነ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለመገንባት የምታደርገውን ሙከራ ‹‹ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ የሕልውና አደገኛ ስጋት›› ብለውት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ትራምፕና ኪም ጆንግ-ኡን ሲንጋፖር ላይ ተገናኝተው ታሪካዊ ነው የተባለውን ውይይት ካደረጉ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ስለሰሜን ኮሪያ ሲሰነዝሯቸው የነበሩትን አስተያየቶች አቀዝቅዘው ስለድርድርና የሁለቱን አገራት ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ስለመፍታት መናገር ጀምረዋል፡፡ ባለፈው መስከረም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የአለመተማመን ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ እንደሆኑና ከኪም ጆንግ-ኡን ጋር ለመወያየትም ፍላጎት እንዳላቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ግን ከደቡብ ምስራቃዊቷ ጎረቤታቸው ጋር ለመነጋገር ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም፡፡ የሰሜን ኮሪያ መንግሥታዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ (KCNA) በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ባሰራጨው ዘገባ ጃፓንን ‹‹በሰው ልጅ ላይ እልቂት የፈጸመች ወንጀለኛ›› እንዲሁም ‹‹ሞራል ያልፈጠረባት አገር›› በማለት ወርፏታል፡፡
ከሳምንት በኋላ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ጋር ሁለተኛ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ የያዙት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ምርት ሙከራ ነፃ ሆና ለማየት እንደማይቸኩሉና አገሪቱ ባሊስቲክ ሚሳይሎችን ለመተኮስ እንዳትሞክር ዋስትና ብቻ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ግን አካባቢው ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ነፃ መሆንን ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለሚደረግ ማንኛውም ድርድር እንደዋነኛ ቅድመ ሁኔታ ያዩታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አቤ አማካሪና መቀመጫውን ቶኪዮ ያደረገው የብሔራዊ የፖሊሲ ጥናት ድኅረ ምረቃ ተቋም (National Graduate Institute for Policy Studies) ባልደረባ የሆኑት ናሩሽጌ ሚቺሺታ፣ ‹‹ውይይቱ ሰሜን ኮሪያ ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ነፃ የምትሆንበትን ሂደትና የጊዜ ሰሌዳ በግልፅ የሚያስቀምጥ ስምምነት የሚደረስበት መድረክ ሊሆን ይገባል›› ይላሉ፡፡
የሲንጋፖሩ ውይይት ሰሜን ኮሪያ ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ነፃ ስለምትሆንበት ሂደት በግልፅ ያስቀመጠው ነገር እንደሌለም ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ መሪዎች ግልፅና ጠንካራ ስምምነት ቢፈራረሙ እንኳ ‹‹ሰሜን ኮሪያ ለስምምነቱ መሳካት ፈቃደኛ ትሆናለች ወይ›› የሚለው ጥያቄም አጥጋቢ ምላሽ የማግኘቱ ነገር አጠያያቂ እንደሆነም አማካሪው ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ከአሁን ቀደም ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ ማዕከሎቿን ለማፍረስና ቀጣናውን ከኑክሌር ስጋት ነፃ ለማድረግ ሁለት ጊዜ ቃል ገብታ ነበር፤በተግባር የታየ ተጨባጭ ነገር ስለመኖሩ ግን ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡
በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል የሚፈረሙ ስምምነቶች የስምምነቶቹን አፈፃፀም የሚያሳዩ አቅጣጫዎች (ሂደትና የጊዜ ሰሌዳ) ከተካተቱባቸው የጃፓንና የሰሜን ኮሪያ ግንኙነትም መሻሻል የማያሳይበት ምክንያት አይኖርም›› ብለዋል፡፡ የጃፓን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ (NHK) በቅርቡ በሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት፣ 67 ከመቶ የሚሆኑት አስተያየት ሰጪዎች በሃኖይ በሚደረገው የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ውይይት ሰሜን ኮሪያን ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ነፃ ማድረግን በተመለከተ አዲስ ነገር ይኖራል ብለው እንደማይጠብቁ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቹኒቺ (Chunichi)›› የተባለው የጃፓን ጋዜጣ ባለፈው ወር ባሳተመው ጽሑፍ የሲንጋፖሩ ውይይት ግልጽና የተፃፈ ስምምነት የሌለው እንደነበር ጠቅሶ፤ ድርድሮቹ ውጤት ያመጣሉ ብሎ ተስፋ ማድረግ አስፈላጊ እንዳልሆነ አትቷል፡፡ ጋዜጣው ‹‹አሜሪካ ለራሷ ደኅንነት ስትል የሰሜን ምስራቅ እስያን ጉዳይ ችላ በማለት ለአህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይል ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥታ ልትደራደር ትችላለች›› ሲል አስነብቧል፡፡
ዕለታዊው የጃፓን የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ‹‹ጃፓን ታይምስ (Japan Times)›› ጃፓን የቤጂንግ ኤምባሲዋን ጭምር በመጠቀም ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለመነጋገር ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ባለፈው ጥር ባወጣው ሪፖርቱ አመልክቶ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በእጅጉ እየሻከረ የመጣው የጃፓንና የደቡብ ኮሪያ ግንኙነት ሴዑል ቶኪዮንና ፒዮንግያንግን አስማምታ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ልታመጣቸው ትችላለች የሚለውን ተስፋ ውሃ ቸልሶበታል፡፡
እ.አ.አ ከ1910 እስከ 1945 ጃፓን በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ዘርግታው የቆየችው አምባገነናዊ የቅኝ ግዛት አስተዳደር እንዲሁም የድንበር ውዝግብ የጃፓንና የደቡብ ኮሪያ ግንኙነት እንዲሻክር አድርገውታል፡፡ ጃፓን ከሁለቱ ኮሪያዎች ጋር እንዲሁም ሁለቱ ኮሪያዎች ደግሞ እርስ በእርሳቸው የገቡበት ውጥረት ለቀጣው ሰላምና መረጋጋት አደጋ በመሆኑ ችግሮቻቸውን በድርድር መፍታት ለአገራቱ አማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነ ናሩሽጌ ሚቺሺታ ያስረዳሉ፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ጎረቤት አገራት በመሆናቸው በሁለቱ መካከል የሚፈጠር አለመግባባት በጋራ ጥቅሞቻቸው ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ቻይና በቀጣናው ያላት ተፅዕኖ እየጨመረ መምጣቱ ደግሞ ለሁለቱ አገራትና ጉዳዩ ትኩረታቸውን ለሳባቸው አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ሌላ የቤት ስራ ይሆናል፡፡
ስለሆነም ጃፓን ከደቡብ ኮሪያ ጋር የገባችበት ውዝግብ ተደራራቢ ችግሮች እንዲፈጠሩ ስለሚያደርግ ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለአገራቱና ለቀጣናው ሰላም ዘላቂ መሰረት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አሜሪካ ከቀጣናው አገራት ጋር ያላት ግንኙነትም በጃፓንና በሰሜን ኮሪያ ግንኙነት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ ሚቺሺታ እንደሚሉት፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በደቡብ ኮሪያ ከሚገኙት የአሜሪካ ወታደሮች መካከል የተወሰኑትን ያህል ለመቀነስ ያላቸው ፍላጎት ጃፓንን ያስጨንቃታል፡፡
‹‹በእርግጥ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሲንጋፖሩ ውይይት በኋላ አሜሪካ በደቡብ ኮሪያ ካሏት ወታደሮች መካከል የተወሰኑትን የመቀነስ ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸው ለጃፓን ቀጥተኛ ስጋት አይሆንም፤ይሁን እንጂ ውሳኔውን ተከትሎ በኮሪያ ልሳነ ምድር ሊፈጠር የሚችለው ውጥረት ለጃፓን ጥሩ አይሆንም›› ይላሉ፡፡ ያም አለ ይህ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ከአምስት ቀናት በኋላ በቬትናም የሚያደርጉት ሁለተኛ ዙር ውይይት ጃፓን ከአካባቢው አገራት በተለይም ከሰሜን ኮሪያ ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አይካድም፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
አንተነህ ቸሬ