የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ‹‹የገጠምነው ጠላት የኢትዮጵያ ነቀርሳ የሆነውን ጠላት ነው። ጁንታው ያገኘውን የፖለቲካ ሥልጣን የገዛ ሀገሩን ለማፍረስ የተጠቀመ ምናልባት በታሪክ ብቸኛው ቡድን ነው። አብሮ የኖረ ሰይጣን በቶሎ አይነቀልም እንደሚባለው በግራ በቀኝ መፍጨርጨሩ አይቀርም። በርግጠኝነት ግን ጁንታው መልሶ እንዳይበቅል ሆኖ ይነቀላል። ይህ የሚሆነው ሁላችንም እንቦጩን ለመንቀል ከተረባረብን ነው። በሂደቱ ውስጥ እዚህና እዚያ ግለሰቦች ሊሳሳቱ ይችላሉ። ሐሳብ የሚከፋፍሉ መረጃዎች ሊሰሙ ይችላሉ። በግብ አንድ ሆነን የአካሄድ ክርክር ይፈጠር ይሆናል።
ያም ሆነ ይህ ከግባችን አያናጥበንም። የኢትዮጵያ ልጆች ከአራቱም ማዕዘን የጁንታውን ዕቅድ ለመቀልበስ ተነስተዋል። ይህ በራሱ ድል ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ጠላታቸው ማን እንደሆነ ለይተውታል። እርሱንም ምን ማድረግ እንዳለባቸው አውቀዋል። ያንንም ያደርጉታል። ይህ አንድነታችን ያስፈራቸው ኃይሎች የሚከፋፍል የመሰላቸውን ነገር ሁሉ ያደርጋሉ። ዓይነ መዓታችንን ከእነርሱ ላይ አንስተን በገዛ ወገኖቻችን ላይ እንድንተክል ያሤራሉ። ፈጽሞ አናደርገውም።
አሁን የፈጠርነው አንድነት የጁንታውን የጥንት ሤራ ያፈረሰ፤ ቀጥሎም የሤራውን ባለቤት የሚያፈርስ፤ በመጨረሻም የተሤረባትን ሀገር በአንድነት የሚያድስ ነው። መከላከያ ኃይላችንና የክልል ኃይሎቻችን ተገቢውን ቦታ እየያዙ ነው። ያንን ለማወክ ትንኮሳ ይኖራል። ለዚያ ለራሳችን ቃል የገባነውን የተኩስ አቁም እያከበርን ተገቢውን ምላሽ ይሰጠዋል። ምንን፣ ለምን፣ እንዴት፣ የትና መቼ ማድረግ እንዳለብን ጥብቅ ዕቅድ አለን። ውጤቱን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወዳጅም ጠላትም ያየዋል። ሠራዊታችን አስፈላጊ ሲሆን እጅን በአፍ ላይ ለሚያስጭን ተልዕኮ ተዘጋጅቷል። አረሙ እንዲነቀል አድርገን እንሠራለን። አረሙን ስንነቅል ግን ስንዴውን እንዳንጎዳው የሚቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ እናደርጋለን። በሀገራችን አረም በደቦ ነው የሚነቀለው። የኢትዮጵያ ልጆችም እርሱን እያደረጉት ነው።›› በማለት አስፍረዋል።
በአገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ክልሎች የአሸባሪውን ህወሓት ለማጥፋት የክተት ጥሪ ከማስተላለፍ ባሻገር ልዩ ኃይላቸውን ወደ ግንባር እየላኩ ይገኛሉ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማው ለሚገኙ ወጣቶች የክተት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ይህን ጥሪ በመቀበል ወደ ግንባር የሚሄዱ ወጣቶች ማክሰኞ ሀምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ለወሰኑ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በመስቀል አደባባይ የአስተዳደሩ አመራሮች እና የመከላከያ ሚኒስትሩ በተገኙበት ሽኝት ተደርጎላቸዋል። በወቅቱም አስተዳደሩ ለመከላከያ ሠራዊት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የስንቅ ድጋፍ አድርጓል።
በሥነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለዘማቾቹ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ወጣቶቻችን ኮርተንበችኋል። በታላቅ የሀገራዊ ፍቅር በማለዳው እዚህ መርሃ ግብር ላይ የተገኛችሁ ዘማቾች እና የህክምና ባለሙያች ዝቅ ብዬ አመሰግናችኋለሁ›› ብለዋል። አሸባሪው ህወሓት ለ27 ዓመታት ያህል የፈፀመውን ወንጀል ተወት በማድረግ በጋራ ለመሥራት ብዙ ጊዜ እንደተለመነ እና እንደተሞከረ ተናግረዋል። አሁን ላይ የከፈተውን ትንኮሳ ተከትሎ ዛሬ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ጥሪ በተደረገላቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመቻውን ለመቀላቀል ያሳዩት ቁርጠኝነት ታሪክ እንደማይረሳው ጠቅሰዋል።
‹‹ዛሬም ለትግራይ ሕዝብ ጥሪ እናደርጋለን›› ያሉት ከንቲባዋ፤ ‹‹ውድ የትግራይ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንወዳችኋለን። ልጆቻችሁ ኢትዮጵያን አሳልፎ ለጠላት ለሚሰጥ ኃይል ጥንካሬ መሆን የለባቸውም›› በማለት ሁሉም የትግራይ ወላጆች ልጆቻቸውን ከእልቂት እንዲቆጥቡ ጥሪ አድርገዋል። ዘማች ወጣቶቹ በድል እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀንዓ ያደታ፤ ህወሓት ጁንታ ቡድን ኢትዮጵያን እያፈረሰ የኖር አሁንም ሀገርን ለማፍረስ እየሠራ ያለ የጥፋት ቡድን ነው ብለዋል። ጁንታው ባለፉት 27 ዓመታት ጥፍር እየነቀለ ኖሯል፤ ሠራዊቱን ከጀርባው የወጋ እሱም አልበቃ ብሎት ሕፃናትን ለጦርነት አየማገደ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ላደረጉት ድጋፍ፤ ወጣቶች ደግሞ ሠራዊቱን ለመቀላቀል በመወሰናቸው በሚኒስቴሩ ስም አመሰግነዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል ሽኝት ከተደረገላቸው ወጣቶች መካከል ከቦሌ ክፍለከተማ የመጣው ሰሞን አዲስ አስማረ አንዱ ነው፡፡ የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ ቀድሞ የነበሩ አባቶች ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ዋጋ ከፍለው ያቆሟትን አገር አሁን ያለችበት ችግር ላይ መውደቅ የለባትም፡፡ ሁሉም ቤተሰቤ በውትድርና ዓለም ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በእነሱና በአገሪቷ በተከሰተው ሁኔታ በመነሳሳት ለመዝመት ተዘጋጅቻለሁ፡፡
በአገሪቱ የሚታየው የሰላም መደፍረስና የርስበርስ ግጭት አስጊ ሲሆን፤ በዘርና በሃይማኖት ተቧድኖ ግጭት ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ የአሸባሪውን ቡድን ደግፈው እየተዋጉ የሚገኙ ወጣቶች ከገቡበት የተሳሳተ አመለካከት ወጥተው ወደ አንድነት እንዲመጡ እመክራለሁ፡፡ ሁሉም ወጣት ለአንድ አገር እንዲቆምና በመስማማት ላይ በተመረኮዘ ሰላም እንዲመጣ ማስቻል ይገባል፡፡ አሁንም እርቅ በማድረግ ወደ ሰላምና መግባባት ሊመጣ ይገባል፡፡ የውጭ ጠላት መከላከል በሚገባ ሰዓት ወደ እርስበርስ ግጭት መገባት አስፈላጊ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያስተላለፈውን የዘመቻ ጥሪ በመቀበል ወደ ጦር ሜዳ ለመሄድ ተዘጋጅቷል፡፡
ከጎጃም የመጣው ወጣት ገብሩ በየነ በበኩሉ እንደሚናገረው፤ የዘመቻ ጥሪውን እንደሰማ ለአገሩ ሰላም ለማስጠበቅ ወደ ዘመቻው መቀላቀሉን ይናገራል። የቀድሞ አባቶች የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ ወደ ትውልድ አሸጋግረዋል፡፡ ወደ ዘመቻው ለመቀላቀል ቀደም ብሎ ሲያስብበት እንደነበር የሚናገረው ወጣት ገብሩ፤ ወደ መከላከያ ለመቀላቀል የትምህርት ደረጃው ሳይፈቅድለት ቀርቶ አለመግባቱን ያስታውሳል፡፡ ነገር ግን አሁን የተፈጠረውን የክተት አዋጅ በመጠቀም ወደ መከላከያ መቀላቀሉን ይናገራል፡፡
እንደ ወጣት ገብሩ አባባል፤ ከሁሉም በፊት የአገር ሰላም ይቀድማል፡፡ የአገርን ሰላም ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል ውስጥ የሚመጣውን ለመቀበል ዝግጁ ነው፡፡ ወጣቱ ወደ ዘመቻ ሲገባ ምንም ዓይነት ፍራቻ ውስጥ ሳይገባ መንቀሳቀስ አለበት፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት ብርሃኑ በቀለ እንደሚናገረው፤ በተያዘው ዓመት የአሸባሪው ህወሓት ኃይል በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት መንግሥት የህግ ማስከበር ዕርምጃ እንደወሰደበት ይታወቃል። በዚህም የአገር ደህንነት ችግር ውስጥ እንዳይገባና ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር እንዲሁም በትግራይ ክልል የሚገኙ አርሶአደሮች እንዲያርሱ በተጨማሪም በተፈጠረው ጦርነት ወጣቱ ሂይወቱ እንዳይቀጠፍ መንግሥት መከላከያ ሠራዊቱን አስወጥቷል፡፡ ነገር ግን አሸባሪው የህወሓት ኃይል ይህን አጋጣሚ በመጠቀም መንግሥትን አሸንፌያለሁ በማለት ወጣቱን ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል፡፡ ሕፃናትን ወደ ጦርነት በመላክና መንገዶችን በማፈራረስ እንዲሁም አፍራሽ ተግባራትን በማከናወን ወጣቱ በሽብር ተግባር ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ነው፡፡
‹‹ይህ የሚያሳየው አገሪቱን እየመራ የሚገኘው መንግሥት ምን ያህል ትዕግስተኛ መሆኑን ነው።›› የሚለው ወጣት ብርሃኑ፤ አሸባሪው ቡድን በሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የውጭ ዲፕሎማችን በማሳመን እንደተበደለና እንደተጨቆነ በማስመሰል ማቅረቡን ይናገራል፡፡ ቀደም ብሎ ህወሓት በስልጣን በነበረበት ወቅት ወጣቶችን በመግደልና በማሰር እንዲሁም በመዝረፍ የሚታወቅ ነው፡፡ በተመሳሳይ በአሁን ወቅትም ወጣቱን በመግደልና ሽብር በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ብዙ ንፁሐን ዜጎች የሞቱበት ሁኔታ አለ፡፡ አሸባሪ ቡድኑ ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ በመሆኑ ሊጠየቅ ይገባል፡፡ ነገር ግን የአሸባሪው ቡድን አመራሮች ወንጀለኛ መሆናቸውን ዘንግተው ለህዝብ ተቆርቋሪ መስለው እየቀረቡ ናቸው፡፡ በአሁን ወቅት በተለያዩ ድንበር አካባቢ በመሄድ ንፁሐን ዜጎችን በሽምቅ ውጊያ እየገደሉ መሆናቸውን ይናገራል፡፡
እንደ ወጣት ብርሃኑ አባባል፤ ስለዚህ አገሪቱን ከዚህ አሸባሪ ቡድን ለማዳን መንግሥት እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ትክክለኛና ወቅታዊ ነው፡፡ ወጣቱ በዚህ ወቅት ግንባር ቀደም ሆኖ አገሩን ማዳን አለበት፡፡ አገሩን የሚወድ ማንኛውም ወጣት እራሱንና አገሪቱን ለማዳን መዘጋጀት አለበት፡፡ ወጣቱ በአገር መከላከያ ውስጥ ተቀላቅሎ ወታደር በመሆንና በመሰልጠን ጦር ሜዳ በመሄድ መዋጋት አለበት፡፡ አሸባሪው ኃይል እስኪጠፋ ድረስ መዋጋት አለበት፡፡ በየቦታው ሸምቆ የሚገኘውን የአሸባሪው ቡድን ማጥፋት የወጣቱ ሥራ መሆን አለበት፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወጣቱ ወደ መከላከያ ከተቀላቀለ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ ወንጀለኛ ከነበረበት ዋሻ እየወጣ መደምሰስ ያለበት እየተደመሰሰና መታሰር ያለበት እየታሰረ አገሪቱ ወደ ነበረችበት ሰላም ትመለሳለች፡፡
ወጣቱ ወደ መከላከያ እንዲቀላቀል ሊጉ ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፤ በሊጉ ስር ከሃያ ሺህ በላይ ወጣቶች አሉ፡፡ አብዛኛው ወጣት ወደ መከላከያ እየተቀላቀለ ይገኛል፡፡ ሊጉ እንቅስቀሴዎችን በማድረግ ወጣቱ መከላከያን እንዲቀላቀል እየተደረገ ይገኛል፡፡ ወጣቱ ለአገሩ እንዲቆም ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ማንኛውም የአገሪቱ ተወላጅ ወጣት በአሁን ወቅት ወደ መከላከያ እንዲገባ ጥሪ እየተደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ሊጉ እንደ አገር የሚሠራ በመሆኑ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ወጣቶች ወደ ውትድርና እየገቡ ናቸው፡፡ ሊጉ የማስተማርና የመቀስቀስ ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን፤ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ወጣቱ መከላከያን ተቀላቅሎ አገሩን ማዳን አለበት የሚል ጥሪ ሊጉ እንደሚቀርብ ወጣት ብርሃኑ ያብራራል። ወጣቱ አገሩን ሰላም ለማድረግ ሲዘምት መንግሥት ለወጣቶቹ አጭር የውትድርና ስልጠና በመስጠትና አስፈላጊ ግብአት በማሟላት ወጣቱ አሸባሪዎች ላይ እንዲዘምት ማድረግ አለበት፡፡ አስፈላጊ ድጋፎችንም ማድረግ አለበት፡፡ ወጣቱ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ እየተሳተፈ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ አስፈላጊ ግብዓት ለመከላከያው በማቅረብና ስልጠና በመስጠት እንዲሁም የሞራል ግንባታ በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ያስረዳል፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2013