የተፋሰስ ልማት የተራቆተ መሬት እንዲያገግም፣ የተመናመነ ደን መልሶ እንዲለማ ለግብርና ሥራ ምቹ በመሆን፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ በተለይም ከ80 በመቶ በላይ ኢኮኖሚዋ በግብርና ሥራ ላይ ለተመሰረተ ኢትዮጵያ ወሳኝ ከመሆኑ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ የኃይል ምንጯም በተመሳሳይ ውሃን መሠረት ያደረገ በመሆኑ የተፋሰስ ልማቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። የዓለም ሥጋት የሆነውን የአየርንብረት ለውጥንም ለማሻሻል የተፋሰስ ልማት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ባለሙያዎችም ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ።
‹‹የተፋሰስ ልማት ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ያስፈልጋሉ። እነርሱም የመጠቀም፣ የመንከባከብ፣ የመጠበቅ ሂደቶች ናቸው። እነዚህ ተግባራት አካባቢን፣ማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማዕከል አድርገው ወይንም ተዋህደው ሲከናወኑ ዘላቂ የሆነ የተፋሰስ ልማት ሂደት ይኖራል። ተጠቃሚ ባልሆነ ህብረተሰብ ውስጥ ልማት ማከናወን ለጊዜው ያማረ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ዘላቂነቱ አስተማማኝ አይሆንም።ተጠቃሚነቱ በተለያየ መንገድ እስከተረጋገጠ ድረስ ግን አስተማማኝ የሆነ ልማት ይኖራል።›› በማለት የተፋሰስ ልማትን አስፈላጊነትና ጥቅም ያስረዱት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ላንድ ሪሶርስ ማኔጅመንት ኤንድ ኢንቫይሮሜንታል ፕሮቴክሽን (የመሬት ሀብት አጠቃቀም እና የአየርንብረት ለውጥ) ትምህርት ክፍል፣ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ሥር በሚገኙ የአየር ንብረትና የህብረተሰብ ጉዳዮች የጂኦ ኢንፎርሜሽንና አርዝ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ውስጥ የሚሰሩት ዶክተር አትክልት ግርማ ናቸው።
እንደ ዶክተር አትክልት ማብራሪያ ተጠቃሚነት ወሳኝ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ልማቱን የሚያከናውኑት የህብረተሰብ ክፍሎች ካለሙት ልማት መልሰው በመጠቀም ገቢ ሊያገኙና ኑሯቸውን ሊለውጡ ወይንም ሊያሻሽሉ ይገባል። ያለሙትን መልሰው መጠቀም ሲችሉ የባለቤትነት ስሜት ይፈጠራል። የተፋሰስ ልማት የአንድ ወቅት ሥራ ብቻ አይደለም። ተከታታይ ሥራዎች አሉት። የደን ሀብቱን መንከባከብ፣ የተለያዩ የጥገና ሥራዎችን ማከናወን፣ ኢኮኖሚ የሚያመነጩ ተጨማሪ ተክሎችን መትከልና መንከባከብ፣ ሌሎችም የማሻሻያ ሥራዎች ይጠበቃሉ። ተፋሰስ ልማትን ለማከናወን ቀድመው የሚታሰቡ ወይንም በዕቅድ የሚቀረጹ ፕሮጀክቶች ሳይቆራረጡ አንዱ ሌላውን እየተካ የሚሄድ እንዲሆን ማድረግ ከቁልፍ ተግባራት መካከል ይጠቀሳል። የመንግሥት የትግበራ መዋቅር መኖር ይኖርበታል። እንዲህ ያለው መዋቅር ሲዘረጋ ልማቱ ዘላቂ ይሆናል።ዶክተር አትክልት ለዘላቂ ልማት ማረጋገጫ መልካም ማሳያ ነው ብለው የጠቀሱት የተከዜ ጽራሬ ግድብ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ተምሳሌትነት እንዳስረዱት፤ የተፋሰስ ልማቱ በከፊል አማራና ትግራይ አካባቢዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ በልማቱ ወደ 14 ወረዳዎች ተካትተዋል። ከነዚህም በትግራይ በኩል በአላማጣ ኦፍላ ወረዳ፣ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ የጊዳንና ላስታ፣ ጋዝግብላ፣ ሰቆጣ ከተማና ወረዳ ዙሪያዎች ዝቋላ ወረዳና ሌሎችንም አካባቢዎች እንዲሁም ከተፋሰሱ ወጣ ያሉ ደሃና፣ ሰሃላ፣ ሰየምት ጣንቋበርገሌ፣ አላጄ፣እንዳመሆኒ፣ ህጣሎወጀራት ይጠቀሳሉ። በጥቅሉ የተከዜ ተፋሰስ ልማት 60 በመቶ በሚሸፍን ቦታ ላይ ነው የተከናወነው። ተከዜ ጽራሬ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ሲጀመር በስድስት ወረዳዎች ውስጥ ለመሥራት ነበር። ይሁን እንጂ ፍላጎት ከፍ እያለ በመምጣቱ ሌሎችም ወረዳዎች ተካትተው ሰፊ ሥራ ለመሥራት ተችሏል።
ፕሮጀክቱ የታለመለትን ዓላማ በማሳካት ምን ያህል ርቀት እንደተጓዘ ዶክተር አትክልት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በተከናወነው የተፋሰስ ልማት በዕፅዋት የጽድቀት መጠን ላይ የመጣውን ለውጥ ማየት የመጀመሪያው ሥራ ነበር። በወቅቱም የዕፅዋት ሽፋን መጠኑ ከፍተኛ መሆኑ ነበር የተረጋገጠው። ማሳያውም በአካባቢው ላይ ውሃ የመያዝ አቅም መሻሻል ነው። የመጣው ለውጥ ከፕሮጀክቱ በተጨማሪ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት ጭምር በተከናወኑ ሥራዎች በመሆኑ ውጤቱ የጋራ ነው። ሌላው ለውጥ ከአፈር መከላት ጋር ተያይዞ የነበሩ ክፍተቶች መሻሻል መታየታቸው ነው። ለውጡንም በሥፍራው ተገኝቶ ሞዴል የሆኑትን ለአብነት በማሳያነት በመጠቀም ማረጋገጥ ተችሏል።በሶስተኛ ደረጃ በለውጥነት የተወሰደው ከአካባቢው የሚወጣውን የውሃ መጠን ወይንም የውሃ ሀብት በማሻሻል የተገኘው ውጤት ነው። በዚህ ረገድም አመቱን ሙሉ የሚፈስና በአንድ ወቅት ብቻ የሚታይ የውሃ መጠን ላይ ያለውን ልዩነት ለማየት ነበር የተሞከረው።የታየው መሻሻል ውሃው ቀስ እያለ በመሬት (አፈር) ውስጥ እየሰረገ አመቱን ሙሉ የሚፈስ ሆኖ መገኘቱ ነው። የተገኘውን የውሃ ሀብትም ለመስኖ፣ ለመጠጥ፣ ለተለያዩ ተግባራት በመጠቀም በአካባቢው ይስተዋል የነበረውን የውሃ እጥረት ማሻሻል ተችሏል። ከውሃ ሀብቱ በተጨማሪ በእርሻው ላይ የታየው ለውጥም ይጠቀሳል። የአካባቢው አርሶ አደር ቀደም ሲል ይጠቀም የነበረው ከሁለትና ሶስት ያልበለጠ የሰብል ዝርያ ወደ16 ከፍ ብሎ የተለያዩ አዝርእቶችን ለመጠቀም አስችሏል። ይሄ ደግሞ አርሶአደሩ የተለያዩ የምርት ውጤቶችን ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆኑ በተጨማሪ እራሱም የተለያየ ምግብ ለማግኘት አግዞታል። የተመጣጠነ ምግብ ያገኘ ማህበረሰብ አምራች ኃይልም ለመሆን የሚያግዝ በመሆኑ ጠቀሜታው ዘርፈብዙ ነው። በእንስሳት፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ የታየው ለውጥም እንዲሁ መልካም የሚባል የፕሮጀክቱ አካል ናቸው። ፕሮጀክቱ የአቅም ግንባታንም ያካተተ በመሆኑ የአመለካከት ለውጥ በማምጣትና ግንዛቤን በማሳደግ ማገዙ ተረጋግጧል። እነዚህን ለውጦች ማረጋገጥ የተቻለውም በፕሮጀክቱ በተከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ ተጠቃሚ የሆኑና ያልሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመጠየቅ፣ የለማና ያልለማ አካባቢዎችን በማነጻፀር በተከናወነ የጥናት ሥራ ነው። በስድስት አመት የፕሮጀክት ሥራ ቆይታ የታየው ለውጥ ለቀጣይ ተግባራት የሚያነሳሳና የሚያበረታታ ሆኖ ተገኝቷል።የተከዜ ጽራሬ ፕሮጀክት የተፋሰስ ልማት ተሞክሮ እንደሀገር ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚተርፍ መሆኑ ብዙ ማሳያዎች እንዳሉትም በጥናት ሥራው ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ማረጋገጣቸውን ዶክተር አትክልት ተናግረዋል።
እንዲህ ያለ መልካም ተሞክሮ ያለው ፕሮጀክት ወደ ኋላ የሚመለስበት አጋጣሚ ስለመኖሩ ዶክተር አትክልት ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ አንድ ክፍተት ከሚታዩት የአንድ ፕሮጀክት ሥራ ተጠናቅቆ ሥራውን አካባቢው እንዲረከበው ሲደረግ ተከታትሎ የሚከናወኑ ሥራዎች ይዳከማሉ። ከፕሮጀክቱ በኋላ ያሉ ሥራዎችም ቅድመ ጥናቱ ላይ በደንብ አይመላከትም። የጥገና ወጭ ቢያስፈልግ ማነው የሚሸፍነው የሚል በግልጽ አይታወቅም። ጥገናው ብቻውን በቂ አይደለም። ከደኑ የሚጠቀም አካል በመፍጠር እንዲንከባከበው ባለማድረግ በሚፈጠር ክፍተትም ጉዳት ይደርሳል። አዲስ ፕሮጀክት ሲጀመር እንደሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ ፕሮጀክቱ ሥራውን ጨርሶ ሲወጣ ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ወደኋላ መመለሱ አይቀርም›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ተከዜ ላይ የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሊኖረው ስለሚችለው ተሞክሮ ዶክተር አትክልት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤በግድቡ አካባቢ የተፋሰስ ልማቱ በሥፋት በመከናወን ላይ ነው። ሥራዎቹም ይደነቃሉ።የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተፋሰስ ሰፊ በመሆኑ ሥራውም በዚያው ልክ ሰፊ እንደሚሆን ይገመታል። በመሆኑም በተለያዩ አካላት ተሳትፎ የተጠናከሩ የልማት ሥራዎች ማከናወን ይገባል። በተለይም ደለልን ለመቀነስ ተፋሰሱን ከወዲሁ ማልማት ያስፈልጋል።የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ደለሉን ለመቀነስ ብቻም መሆን የለበትም። የአካባቢውን ማህበረሰብ ኑሮ ለማሻሻልም መሆን ይኖርበታል። በዚህ መልኩ ሲከናወን ታች ያለው፣ለላይኛው መተሳሰብ ይፈጠራል። እኩል ተጠቃሚነት ሲኖር ቸልተኝነቱ አይኖርም።ግድቡም ከደለል ይጠበቃል።
ተከዜ ጽራሬ አነስተኛ ፕሮጀክት ቢሆንም የተለያዩ ሥራዎች በማከናወን ጥረት ተደርጓል።የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ አቅም ግንባታ፣ የመንገድ ሥራ፣ ለሰውና ለእንስሳት የጤና አግልገሎት፣ የችግኝ ጣቢያዎችን ማጎልበትና ማሻሻል ይጠቀሳሉ። የተፋሰስ ልማቱ መጠናከር ወደ ግድቡ የሚገባውን የደለል መጠን ለመቀነስ እጅግ ይጠቅማል። ሌላው ከተሰራው ሥራ አንዱ ጥናት ማከናወን ይገኝበታል። የተከዜ ግድብ የደለል መጠን ለ13 አመታት ያህል አልተጠናም። ግድቡን ለመሥራት በተያዘው ቅድመ ዕቅድ ላይ ግድቡ እስከ 50 አመት ያገልግሎት ዘመኑ ወደ 30 ሚሊየን ሜትሪክ ኪዩቢክ ደለል ሊገባ እንደሚችል ነው የተገመተው። መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች ስብስብ በግድቡ ውስጥ የሚገኘውን የደለል መጠን ለማጥናት ባደረጉት እንቅስቃሴ በደለሉ ውስጥ የገባውን የደለል መጠን ለማወቅ ችለዋል። የጥናት ግኝቱም እንደሚያመለክተው ወደ ግድቡ በዓመት የሚገባው የደለል መጠን ወደ 24 ሚሊየን ሜትሪክ ኪዩቢክ ነው። ከቅድመ ዕቅዱ ግምት ወደ አምስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ደለል መጠን ቅናሽ መኖሩ በጥናቱ ተረጋግጧል። ቅድመ ግምቱን የሚያሻሽል ውጤት የተገኘው በአካባቢው የተከናወነው የተፋሰስ ልማት አስተዋጽኦ ነው። ይህ ተሞክሮ በተመሳሳይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ቢተገበር ስጋቶችን ከወዲሁ መቀነስ እንደሚቻል እንደ አንድ የዘርፉ ባለሙያ ይመክራሉ። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ መያዣ ክፍል (ሪዘርቫየር) ውስጥ የሚገባውን ደለል በየጊዜው በመከታተል ጥናት በየጊዜው ቢካሄድ ይጠቅማል። በጥናት የተደገፈ ክትትል ማድረጉ ቀድሞ በመተንበይ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያግዛል።
‹‹የህዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት በመሆኑ የምንኮራበት የሁላችንም ሀብት ነው። በመሆኑም ግድቡ ተጠናቅቆ ከመነሻው የታለመለትን ግብ አሳክቶ ማየት የሁላችንም ጉጉትና ምኞት ነው። ምንም እንኳን ጉዳዩ የብሄራዊና የኢትዮጵያ ቢሆንም በተፋሰሱ ውስጥ ያሉትም ሆኑ ከተፋሰሱ ውጭ የሚገኙትም እንደሆነ አይካድም›› ያሉት ዶክተር አትክልት ይህን ብሄራዊ ኩራት የሆነውን ግድብ ሁሉም ከዳር ለማድረስ የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል። ጥረቱ ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ከማውጣት ባለፈ ሊንከባከበውና ሊጠብቀው እንደሚገባ፣ ጥበቃውም በአካባቢው የተፋሰስ ልማት በማከናወን መሆን እንዳለበት ገልጸዋል። እርሳቸው እንዳሉት የተፋሰስ ልማት ተሳትፎው ከአካባቢው የወረዳና የቀበሌ አስተዳደር፣ ከፍ ብሎም በዞንና በክልል ደረጃ በተቀናጀና በተደራጀ ሁኔታ መከናወን ይኖርበታል። በአካባቢ የተደራጀ ሥራው ሲጠናከር መዋቅሩ እስከ ሀገር ደረጃ ደርሶ አመርቂ ውጤት ይመዘገባል። የተለያዩ የልማት አካላትም የየራሳቸው አስተዋጽኦ ስላላቸው ተጨማሪ ተሳትፎ ያስፈልጋል። ለአብነትም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትምህርት ግንዛቤን ከፍ በማድረግ፣ ተመራማሪዎች ደግሞ በተከታታይ ጥናትና ምርምር ያልታወቁ ነገሮችን ለይቶ ውጤቱን ለህብረተሰቡ ማሳወቅ፣ በደንናዱር እንስሳት ዘርፍ የሚሰሩትም እንዲሁ ኃላፊነታቸውን በመወጣት አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።በተለይም የቤት እንስሳት ደንን ከማጥፋት (ከማውደም) ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው ለእንስሳቱ የሚሆን ቦታን በማዘጋጀትና የደን ሀብቱ ከእነርሱ እንዴት መጠበቅ አለበት የሚለውም ከዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብሩ ጋር ጎን ለጎን የእንስሳት ስምሪት ወይንም የግጦሽ ቦታ አጠቃቀም ታሳቢ ተደርጎ መከናወን ካለባቸው ተግባራት መካከል መሆን ይኖርበታል።በእንስሳት ዘርፍ ላይ የተሰማራው የጥናትና የልማት አጀንዳዎችን በመያዝ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስተካከልና በማረም ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል። ወደፊት የአየርንብረት ለውጥ ንብረት ይቀየራል የሚል እሳቤ በመኖሩ በአካባቢ፣ ደን፣ የአየርንብረትና ለውጥ ላይ የሚሰሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ሆኑ ተመራማሪዎች የአየርንብረት ለውጡ ከምን ወደ ምን እንደሚቀየር፣ የሚቀየርም ከሆነ ምን አይነት ዝግጅት መደረግ እንዳለበት፣ የትኞቹ ሀገሮችና አካባቢዎች ተሞክሮ አላቸው የሚለውንም ልምድ በመቀመር ማሳየትና ማሳወቅ ይጠበቃል። እንዲህ ያሉ ተግባራት ወደፊት ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ችግሮች መጠበቅ የሚቻልበትን፣ ችግሩንም አውቆ ተቋቁሞና ተዋህዶ ለመኖር የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በቀጥታ በተፋሰስ ውስጥ ተሳትፎ የሌለው ደግሞ የጥናት ግኝቶችን በማዳረስ፣በገንዘብ በመደገፍና በተለያየ መልኩ የተለያዩ ተግባራት መከናወን ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማት ስታከናውን ቆይታለች። አሁንም አጠናክራ ቀጥላለች። ለመሆኑ በተፋሰስ ለማ የሚባለው ምን አይነት ልማት ሲከናወን ነው? ለሚለው ጥያቄ ዶክተር አትክልት በሰጡት ማብራሪያ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ስለተከናወኑ ወይንም የዛፍ ችግኝ ተከላ ስለተከናወነ ብቻ ለምቷል ማለት አይቻልም። ሲለማ የማህበረሱ ተጠቃሚነት፣የተፈጥሮ ሀብቱን የያዘው አፈር፣ ውሃ፣ ተክሎችን፣ ዕፅዋቶችንና የአየሩን ሁኔታና ሌሎችንም አጠቃልሎ የያዘው የአካባቢ ነባራዊ ሁኔታ አቀናጅቶ በመያዝ ሁለንተናዊ የሆነ ልማት ሲከናወን ለምቷል ብሎ በድፍረት መናገር የሚቻለው። አስፈላጊ ናቸው ተብለው ከተቀመጡት ሶስት ነገሮች መካከል አንዱ እንኳን ከጎደለ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ የሆነ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው። እኛም በመልዕክታችን መልካም ተሞክሮዎች ይጎልብቱ እንላለን።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2013