በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ተሳታፊ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ለውጤት የምትጠበቅበት የአትሌቲክስ ውድድር በመጪው አርብ ቢጀመርም በወርልድ ቴኳንዶ እና ብስክሌት ስፖርቶች ተካፋይ ሆና በኦሊምፒኩ የሚኖራት ቆይታ ካለ ምንም ሜዳሊያ ተደምድሟል፡፡ ብቸኛዋ የብስክሌት ተወዳዳሪ ሰላም አመሃ ባለፈው እሁድ 137 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ውድድሯን ስታቋርጥ በወርልድ ቴኳንዶ ብቸኛው ተወዳዳሪ የሆነው ሰለሞን ቱፋ ባለፈው ቅዳሜ በሁለተኛው ዙር ተሸንፎ ከሜዳሊያ ፍልሚያ ውጪ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ሰለሞን ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ባዶ እጁን ወደ አገሩ አይመለስም፡፡ ሰለሞን ቱፋ በውድድሩ የዲፕሎማ ተሸላሚ በመሆን በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው አትሌት ሆኗል፡፡
ሰለሞን ዲፕሎማውን ያገኘውም በተካፈለበት የ58 ኪ.ግ ውድድር ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ በመቻሉ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት አገሩን የወከለው ሰለሞን በውድድሩ ወቅት ጉዳት አስተናግዶ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፍ ባይችልም እግሩ እየደማ ውድድሩን ቀጥሎ ያደረገው ተጋድሎ በበርካቶች ዘንድ እንዲመሰገን አድርጎታል፡፡
ከሌሎች ስፖርቶች በተለየ ላብን ከማፍሰስ አልፎ ደምን እስከ ማፍሰስና አጥንትን እስከ መስበር ድረስ መስዋዕትነት መክፈል በሚፈልገው የፍልሚያ ስፖርት ሰለሞን ሜዳሊያ ማስመዝገብ ባይችልም በእልህ አስጨራሽ ፍልሚያ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረቡና የዲፕሎማ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ ስሙ በወርቅ ቀለም እንዲፃፍ አድርጎታል። አሰልጣኙ ማስተር አዲስ ኡርጌሳም በተመሳሳይ የታሪኩ ተጋሪ መሆን ችሏል፡፡
የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያውን ባለፈው ቅዳሜ በ58 ኪሎግራም ከጃፓኑ ሱዚኪ ሰርጂዮ ጋር ያደረገው ሰለሞን ፍልሚያውን በጥሩ የአጨዋወት ስልት በበላይነት ተቆጣጥሮ ማሸነፉ አይዘነጋም። በሩብ ፍፃሜው ውድድር ከቱኒዚያዊው ጀንዱቢ መሐመድ ካህሊል ጋር የተገናኘው ሰለሞን እልህ አስጨራሽ ፉክክር ቢያደርግም በነጥብ ተሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ሰለሞን በሩብ ፍፃሜው ፍልሚያ እግሩ እየደማም እስከ መጨረሻው የተፋለመ ሲሆን በቀጣዩ በሬፔሻዥ (ለነሐስ ሜዳልያው ግጥሚያ ለማለፍ በተደረገ ፍልሚያ) ከመወዳደር ወደ ኋላ አላለም፡፡ በዚህም በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አርማ ስር በተወዳደረው ሩሲያዊው ሚካኢል አርታሞኖቭ ቢሸነፍም ለዚህ ደረጃ መብቃቱ በራሱ ሊደነቅ እንደሚገባ በርካቶች አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡
ሰለሞን አጠቃላይ ውድድሩን ከተካፈሉት አስራ ስድስት ተወዳዳሪዎች ሰባተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል፡፡ በውድድሩ ላይ ሰለሞንን ያሸነፉት ካህሊል እና አርታሞኖቭ የብር እና የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ በመሆን ውድድሩን ሲያጠናቅቁ ጣልያናዊው ቪቶ ዴል አኩዊላ በፍፃሜው ካህሊልን በመርታት የወርቅ ሜዳልያውን ወስዷል፡፡ ሰለሞን ቱፋ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪክ በወርልድ ቴኮንዶ ስፖርት ለመጀመርያ ጊዜ ያገኘውን የሰባተኛ ደረጃ በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያው ደስታውን ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን›› በማለት ገልጿል።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ በወርልድ ቴኳንዶ ከ61 አገራት የተውጣጡ 131 የዓለም ምርጥ ስፖርተኞች በስምንት የተለያዩ ኪሎ ግራሞች ተከፋፍለው በሁለቱም ፆታ የሚፋለሙ ይሆናል።
ከተጀመረ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን በያዘው 32ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ አገራት በርካታ ሜዳሊያዎችን በአንድ ጊዜ የሚያፍሱባቸው እንደ አትሌቲክስ አይነት ውድድሮች ባይጀመሩም በርካታ አገራት በተለያዩ ውድድሮች ሜዳሊያ በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ። እስከ ትናንት አመሻሽ አሜሪካ 22 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፤ ከእነዚህ መካከል 9ኙ የወርቅ፣ 5ቱ የብር እንዲሁም 8ቱ የነሐስ ሜዳሊያዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛ ደረጃን የያዘችው ቻይና በተመሳሳይ 9 ወርቅ መሰብሰብ ስትችል፣ 5ብር እና 7ነሃስ አግኝታ በድምሩ በ21 ሜዳሊያዎች ትከተላለች፡፡ አዘጋጇ አገር ጃፓን በበኩሏ 9የወርቅ 3የብር እና 5የነሃስ በድምሩ 17 ሜዳሊያዎችን በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ ሶስተኛዋ አገር ሆናለች፡፡ የሩሲያ አትሌቶች ደግሞ አገራቸው ከውድድሩ ብትታገድም ገለልተኛ ሆነው እያካሄዱ በሚገኙባቸው ውድድሮች 5የወርቅ 7የብር እና 4የነሃስ በጥቅሉ 16 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ፈረንሳይ፣ ኮሶቮ እና ጣሊያን ደግሞ እስከ አስር ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም