በተለያዩ ዓለም ሀገራት የሚኖረው ዲያስፖራው ስለሀገሩ ጉዳይ ዘወትር በንቃት ይከታተላል፡፡ በውጭ ሆኖ በሀገር ውስጥ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅ ጥረት ያደርጋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ የሚዘግቡት የተሳሳተ ዘገባ መበራከት ቁጭቱን እንዲጨምር አድርጓታል፡፡
የእነዚህ ሚዲያዎች የተሳሳተ ዘገባ ለመመከትም ሆነ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ጫና ለማርገብ መሬት ላይ ያለው ነባራዊ እውነታ ምን ይመስላል የሚለውን በአካል ተገኝቶ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም በአሜሪካ የሚኖሩ ከተለያዩ ሲቪክ ማህበረሰቦች ፣ ከምሁራን እና ከተለያዩ ድርጅቶች የተውጣጡ አስር አባላት ያሉት የአሜሪካ ዲያስፖራ የሰላም ጓድ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተመልክቷል፡፡ የሰላም ጓዱ አባላት በኢትዮጵያ የነበራቸው ቆይታ እና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ከቡድኑ አባል አቶ ዳዊት ጌታቸው ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አቶ ዳዊት ጌታቸው እንደሚሉት፡- የሰላም ጓዱ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ያነሳሳው ኢትዮጵያን በሚመለከት በተለይ በሶሻል ሚዲያ በርካታ የተዛቡ ነገሮች መኖራቸው እና ሀገር ውስጥ ያለው ውጥረት እየተካረረ በመምጣቱ ምክንያት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገው ከፍተኛ ጫና መበራከቱን ተከትሎ ነው፡፡ የሰላም ጓዱ በመሬት ላይ ያለውን ነባራዊ እውነት በመመልከት ለዲያስፖራው እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት ሀገራችን ላይ የሚደረገውን ጫና ለማርገብ በማሰብ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የቡድኑ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉት ዜጎችን ለመጎብኘት እድሉን አግኝተዋል፡፡ በሰሜን አጣዬና ከሚሴን፤ በደቡብ ኮንሶ አካባቢ የሚገኙ ተፈናቃዮችን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለተፈናቃዮቹ የሚወራውንና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ከመመልከታቸው በላይ አሁንም በሀገሪቱ ያለውን ጠቅላላ ሁኔታ የተገነዘቡ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ምን መደረግ አለበት የሚለውን ለዲያስፖራው ሆነ የዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ትክክለኛውን ኢትዮጵያን የማይጎዳ መረጃ ለመስጠት የሚያስችል ሥራ ለመሥራት የሚረዳቸውን መረጃ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በእርግጥ ተፈናቃዮችን ስንመለከት በጣም አዝነናል ያሉት አቶ ዳዊት፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉት እነዚህ ዜጎች ብንመለከት፤ ለአብነት የኮንሶ አካባቢ ተፈናቃዮች የመሬት አጠቃቀም ላይ የተነሳ ግጭትን ምክንያት በማድረግ ሌሎች ከጀርባ መጥተው ግጭቱን በማባባስ ከ4ሺ በላይ የሆኑ ዜጎች ቤታቸው ተቃጥሎ እንዲፈናቀሉ መደረጉን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ ህጻናት ፣ አዛውንቶች እና ነፍሰ ጡር ሴቶች ከቀዬአቸው ተሰደው በመጠለያ ውስጥ ልጆች ወልደው ያሉበት ሁኔታ መመልከታቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው ጠቅሰው፤ ሁለቱም ወገኖች በሀገር ሽማግሌ ቢታረቁም ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ እንደሆነ ለመገንዘብ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
የሰላም ጓዱ ጅማሮ በዓለም አቀፍ ሆነ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ እና በአሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካም የሚኖሩትን የዲያስፖራውን ማህበረሰብ የሚያስተሳስር እና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አንድ አይነት ነገር ለመስራት የሚያስችለንን አቋም ለመያዝ የሚረዳ ነው ያሉት አቶ ዳዊት፤ እኛ መሠረት ጣዮች ነን፤ ሀገራችን በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች እኛ ቁጭ ብለን አናይም ብለን የመጣን የመጀመሪያ ፈር ቀዳጆች ነን ይላሉ፡፡ ወደፊት ይህን ዓላማ በተለያዩ ሀገሮች እንዲሰርጽ በማድረግ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ዲያስፖራው አንድ ሆኖ ሀገራችን ልናሳድግ የምንችልበትና ግጭቶች የሚቀሩበትን እንዲሁም ሰላም የሚወርድበት ሁኔታ ለማምጣት ጥረት የሚያደርጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዲያስፖራው አብዛኛው ውጭ ይኖሩ እንጂ ልብ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚሉት አቶ ዳዊት፤ ዲያስፖራው የህዳሴ ግድብ ከድጋፍ ባሻገር ግድብን ለማጥቃት በሚደረግ ሙከራ ሁሉ ከፍተኛ ተቃውሞ በማቅረብ እየደገፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ምንም ሰው በራሳችን ገንዘብ የምንገነባውን ግድብ ሊያጠቃብን ፤ ማንንም በማይጎዳ መልኩ ውሃችንን ለመጠቀም እንዲያቆመን አንፈልግም›› ይላሉ፡፡ ከዚህ በፊትም ለግደቡ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገ መሆኑን ጠቁመው ፤አሁንም በየትኛውም መንገድ የሚፈለገውን ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዲፕሎማሲም አኳያ በሚፈለግብንን ሁሉ በመወጣት አባይ የኛ ውሃ ነው፤ ግድቡም የኛ ነው የምለው ሌሎቹን ሀገራት ለማስጠማት ሳይሆን በጋራ ለመጠቀም በመሆኑ ያንን ሀሳባችንን በተሳሳተ መንገድ መንዘረው በሀገራችን ላይ ጠፋት እንዲፈጸም ባያደርጉ ጥሩ ነው የሚሉት አቶ ዳዊት፤ ይህንንም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን
ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በውጭ ያለው ዲያስፖራ በማስተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እና በዲፕሎማሲ በመረዳዳት ለወደፊት ለሀገራችን ትልቅ መሠረት በመጣል ልማታችንን የሚፋጠንበትና ከአደጉት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ እንድትሰለፍ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሰላም ያጣውን ህዝብ ሰላሙን እንዲጎናጸፍ እና ሰላማዊ ሀገር ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት እስከመጨረሻ ለማስቀጠል እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡
ሌላው ሀገራችን በዓለም አቀፍ ሚዲያ በሚያሰራጩት የተሳሳተ ዘገባ እየተጠቃች ትገኛለች፡፡ በዚህም ረገድ ዲያስፖራው ከፍተኛ የቲውተር ዘመቻ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ልጆቻችንን ሳይቀር እንዲሳተፉ በማድረግ ያለውን ነባራዊ ሁኔታና ትክክለኛ መረጃ ለዓለም ለማሳወቅ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህንንም አጠናክሮ በማስቀጠል ኢትዮጵያን የሚወዷት አካላት ሁሉ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለማሳወቅ ተረባርበው የሚሰሩበት ሁኔታ በማመቻቸት እናስቀጥላለን ብለዋል፡፡
የሰላሙ ጓዱ ከኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እና ነባራዊ እውነታ ምን ይመስላል የሚለውን እና የተመለከተው ተጨባጭ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያሳወቅ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዳዊት፤ ለዚህም ዲያስፖራውን በማስተባበር በገንዘብ፣ በእውቀት እና በዲፕሎማሲው እንዲሁም በሁሉም መስክ ኢትዮጵያን የምንረዳበትን መንገድ ቀይስን እንሰራለን ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም