አንድ ሰው ጤንነቱ ቢታወክ በሕክምና ተፈውሶ ወደ ቀድሞ አቋሙ ሊመለስ ይችላል:: ሀብቱና ንብረቱ ቢወድምም በርትቶ ከሰራ፣ በተስፋ መቁረጥ ካልራደና የነበር ቁዘማን ሳይሆን የዛሬን እውነታ ተቀብሎ ከተጋም አንሰራርቶ ከውድቀቱ ለማገገም ዳግም ዕድል ሊያገኝ ይችላል:: ዕድሜ ከባከነና ጊዜ “ከፈሰሰ” ግን መመለሻም ሆነ መካሻ ዘዴና ብልሃት በፍጹም ሊኖረው አይችልም፡፡
የአንድ ትውልድ ዕድሜ ምን ያህል ነው? መገለጫውስ ምንድን ነው? በሚሉት የፍልስፍና ጥያቄዎች ዙሪያ ለመራቀቅ ወቅታዊ ብሶታችን አይፈቅድልንም:: መልሶቹ ምንም ይሁኑ ምን ዛሬ በሕይወት ያለነው አብዛኞቹ ነፍስ አወቅ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ዕድሜያችን በከንቱ አልባከነም ብለን ለመከራከር ድፍረት አይኖረንም:: ዘመናችን በክፉ ክስተቶች ተዘርፎ መራቆታችንንም ብንሸሽግ አያምርብንም:: እንዴት ተዘረፍን? ማንስ ዘረፈን? በምን ምክንያትስ ተዘረፍን? የሚሉትን የአድማስ ጥግ ጥያቄዎች ለመመለስ ወደ ጥቁምታዎቹ ዘልቀን የምንገባው የጸሐፊውን የዕድሜ ዘመንና የዘመነ አቻዎቹን ዜና መዋዕል እንደ አንድ “የትውልድ አብነት” በመዋስ ይሆናል፡፡
ይህ ጸሐፊ የተወለደበት ዓመት የክብር ዘበኛ ሠራዊት በንጉሡ ላይ አምጾ ሀገሪቱ በደም አበላ የጨቀየችበት ወቅት ነበር:: ጄኔራል መንግሥቱ፣ ወንድማቸው ገርማሜ ነዋይና የአመፁ ተባባሪ ጓዶቻቸው የንጉሡን መኳንንት በያኔው ቤተመንግሥት (የዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስድስት ኪሎው ዋናው ግቢ) ውስጥ ሰብስበው ደማቸውን ደመ ከልብ ባደረጉበት ወር እና ሳምንት ውስጥ ስለነበር በወታደራዊ ሙያ የተካነው ቤተሰቡ ብዙ ትዝታ አለው:: የጦር ሠራዊቱና የክብር ዘበኞች ተቃቅረው ደም መቃባታቸው በወቅቱ በስፋት ተስተውሏል:: የመፈንቅለ መንግሥቱ ነቅናቂዎችም በአልባሌ አሟሟት ፍጻሜያቸው መደምደሙ በሀዘንና በቁጭት ተጋኖ ተወርቷል:: እነዚህ አሰቃቂ የሞት መርዶዎች የእኔንና የመሰል ጨቅላዎችን ቤተሰቦች አንገት ያስከፉ ታሪኮች ነበሩ:: ከሟቾቹ ጋር የደም ሀረግ ባይሳሳቡም በኢትዮጵያዊነት ዝምድና ብቻ እናቶቻችን የሀዘን ማቅ፣ አባቶቻችን የክንድ ላይ ጥቁር ቱቢትና የሀዘን ኮፍያ ለብሰው ስለፈሰሰው የሀገር ደም በየአደባባዩና በየጓዳው እምባቸውን እንደ ጎርፍ በማፍሰስ አልቅሰዋል:: በዚህ ወቅት እኔና የዕድሜ አቻዎቼ ሕጻናት እንኳንስ በፍቅር እሹሩሩ እየተባልን ልንሞላቀቅ ቀርቶ የልጅነታችን ጆሮ እያደመጠ ለዳዴ የበቃነው የእናቶቻችንን የምሬትና የሀዘን እንጉርጉሮ በማድመጥ ነበር፡፡
ጥቂት ከፍ ብለን በታዳጊነት ዕድሜ ላይ ስንደርስም የኮሌጅና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች “ንጉሡን ለመገልበጥ” እያሴሩ ነው የሚል ጉርምርምታ በስፋት ይደመጥ ጀመር:: ከፍ እያልን ስንሄድም እነዚያው ተማሪዎች አመጻቸውን በስፋት አቀጣጥለው “ለእስራት፣ ለስቃይና ለሞት ተዳረጉ” የሚሉ ዜናዎችን መስማት የእለት ተእለት ዜናዎቻችን ነበሩ:: ወላጆቻችንም የታላላቅ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ፎቶግራፎች አቅፈው “ምነው ባልተወለዳችሁ ኖሮ” እያሉ ማማጣቸውን አንዘነጋም፡፡
በተለየ ሁኔታ ይህ ጽሑፍ በዋነኛነት ትኩረቱን የሚያደርግበት ክስተት ግን በመጀመሪያዎቹ የአሥራዎቹ ዕድሜዎቹ ይህ ጸሐፊ ያደምጣቸው የነበሩ የሹክሹክታ ወሬዎችና ተግባራቱን የተመለከተ ይሆናል:: የሹክሹክታው ቅብብሎሽ ይፋ ተገልጦ የአደባባይ ዜና ወደ መሆን የተሸጋገረው ትህነግ የሚባለው (የትግራይ ነፃ አውጭ ነኝ ባይ ቡድን) በዋቢ ሸበሌና በማዘጋጃ ቤት ላይ ፈንጂ ጥሎ የሽብር ተግባር መፈጸሙ ነበር:: ከዚያ በኋላማ ምኑ ይጠየቃል:: ይህ በጉተና ዕድሜ ላይ ያለው አሸባሪ ድርጅትና እንደ “ጅብ ጥላ” በብዛት የተፈለፈሉት እርሱን መሰል የወቅቱ የፖለቲካ ቡድኖች ሀገሪቱን በመከራና በእዮታ አንቀረቀቧት ማለቱ ይቀላል:: እኒህን መሰል መከራዎች እያየን ስላደግንም የልጅነታችንንና የታዳጊነታችንን ዕድሜ በወጉ ሳናጣጥም በከንቱ እንደፈሰሰ ውሃ እብስ ብሎ ሲያልፍ አልታወቀንም፡፡
በበሳል የወጣትነት ዘመናችንም ቢሆን በድምቀት ሳይሆን በክስረት፤ በብርታት ሳይሆን በሃፍረት እየተሸማቀቅን ማለፋችንን አንክድም:: የዕድገት በኅብረት ዘመቻ፣ የነጭና የቀይ ሽብር አመፅ፣ የሀገራችን ምሥራቃዊና ሰሜናዊ ጦርነቶች ወዘተ. የወጣትነት ዕድሜያችንን የተገዳደሩ፣ በብሔራዊ ውትድርና እየታፈስን እንድንሳቀቅ፣ በመወለዳችንም ተስፋ ቆርጠን እንድንጸጸት ክፉ የሥነ ልቦና ቀውስ አሳርፎብን አልፏል::
በሽብርና በጦርነት ከረገፉት የዕድሜ እኩዮቻችን መካከል እኔን መሰል ጥቂቶች ለምን መከራ ተሸካሚና ቆዛሚ ሆነን ለምስክርነት እንድንተርፍ ፈጣሪ ፈቀደ በማለትም መንፈሳዊ ግጭት ውስጥ በመስመጥ ብዙዎቹ “አምላክ የለሽ” በመሆን የኮሚኒስታዊ አይዲዮሎጂ ካዳሚዎች ለመሆን ተገደዋል:: የወጣትነት ዕድሜያችንን እንዲህ እያየነው ጥሎን እብስ ማለቱን አንኳን ለማስታወስ እፎይታ አልነበረንም፡፡
በሀገሪቱ ላይ የወረደው መልከ ብዙ አበሳ በሕይወት የተረፉትን ወጣቶች ለጅምላ እስርና ለስደት ስለዳረገ የወጣትነት ዕድሜ ብርቅ እስከ መሆን መድረሱም አይዘነጋም:: የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችና የኮሌጅ መማሪያ ክፍሎች በተማሪ ቁጥር ሳስተው በአንጻሩ ወታደራዊ ካምፖችና እስር ቤቶች በዕድሜ እኩዮቻችን የተጣበቡበትም ዘመን ነበር:: የልጆቻቸው የግፍ እልቂትና መሰወር የሚያንገበግባቸው እናቶችና አባቶች እኛን በፈጣሪ ርዳታ ከሞት አፋፍ ተነጠቀንና በተዓምራት የተረፍነውን ጥቂት ወጣቶች ስናልፍና ስናገድም ባዩን ቁጥር “የእኔም ልጅ ይሄኔ ቢኖር ኖሮ…” እያሉ እንባቸውን ሲያፈሱ ደጋግመን አስተውለናል:: ወጣትነታችንን ብቻም ሳይሆን መኖርን ራሱን ተጠይፈንም የአብሮ አደጎቻችን ክፉ እጣ ለምን ሊያልፈን እንደቻለ በስቅቅና በፀፀት እያስታወስን በህሊና ህመም መሰቃየትን የእለት እህታችንን አድርገን ኖረናል::
ፈጣሪ ጓደኞቻችንን ነጥቆን እኛን ለምን ለጉድ መጎለት እንደፈለገ እያማረርንም አምተነዋል:: የተዘረፈብን የወጣትነት ዕድሜያችን ትዝ ሲለንም በከንቱ ለረገፉት “አበቦች” የስሜት ማቅ እንደለበስንና በውስጣችን እንዳነባን ከእህታችን ፋታ ሳናገኝ “የሀዘን ፍራሽ ላይ እንደተቀመጥን” ዕድሜያችን ወጣትነትን ተሸጋግሮ ወደ ጉልምስና ሲንደረደር ሳይታወቀን ዛሬን ደርሰናል፡፡
ዛሬም የመከራችን ጉም አልተገፈፈም፤
ለዚህ ሁሉ ሀገራዊ አበሳና አሳር በዋና ተዋናይነት የሚጠቀሱት ቡድኖች በርካታ ቢሆኑም የአሸባሪውን የትህነግን ያህል የትውልድ ነቀርሳ የሆነ ደዌ በምድራችን ላይ የተፈጠረ ስለመሆኑ ያጠራጥራል:: ህወሓት/ ኢህአዴግ ከበረሃው ጎሬ ወጥቶ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በሀገርና በሕዝብ ላይ የፈጸማቸውን እኩይ ድርጊቶች ዘርዝሮ ለመጨረስ የአንድ ሺህ አንድ ሌሊት ተረክ ይበቃው አይመስለንም:: “ሀ” ብሎ የጀመረው የጥፋት ተግባር በረጂም ዘመናት ሂደት ውስጥ በዲስፕሊንና በጠንካራ ተቋማት ሲገነባ የኖረን ጀግና የመከላከያ ሠራዊት ገና ከጠዋቱ በትኖ አባላቱ ጀግኖቹ ላይ መሳለቅ ነበር:: በመግባባት፣ በሰላምና በመነጋገር ልዩነቶችን እየፈቱ አብሮ መኖር እየተቻለ ሀገሪቱን አስገንጥሎ በድንበር ውዝግብና በወደብ አልባነት ችግር ውስጥ እንድትዘፈቅ ማድረጉም ሁለተኛው ክፋቱ ነው:: የክፍተኛ ትምህርት ተቋማትን፣ በሳል የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎችን፣ አይተኬ ተመራማሪዎችን እንዳልባሌ ዕቃ ወርውሮ ማወረዱን መዘርዘሩ ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል፡፡
በአጭሩ የኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያን መንፈስ አከርካሪ ሰብሮ በጎጠኝነትና በዘውጌነት እንዲረገጥና እንዲዋረድ አድርጓል:: የኢኮኖሚውን በረከት ለብጤዎቹ አከፋፍሎና ደልድሎ የሀገሪቱን የሀብት መቅኒ ሙጥጥ አድርጎ እርቃኗን አስቀርቷል:: በዚህ እኩይ ቡድን እያለቀሱ የእንባና የደም ዋጋ ሲከፍሉ የኖሩት ሕዝቡና ሀገሪቱ በእኩልነት ነው፡፡
ይህንን አሳፋሪ ሀገራዊ ክስተት ያስተዋልነው የጎልማሳነት ዕድሜ ላይ ደርሰን ጋሼና አባባ፣ እትዬና እማዬ ለመባል በደረስንበት ማምሻ ዕድሜያችን ላይ ከደረስን በኋላ ነው:: ለልጆቻችን እየነገርን ያለነውና እነርሱም በተራቸው ለልጆቻቸው እንዲነግሩና እንዲተርኩ እየመከርን ያለነውም እኒህን መሰል ዕድሜያችንን የዘረፉትንና የሞራል እርቃን ላይ ያደረሱንን በደሎችና መሰል ሀገራዊ መከራዎች በትዝታ ብቻ ሳይሆን በኑሯችንም ጭምር እየተገለጠ እንዳለ በማሳየት ነው:: ለመሆኑ እኒህን መሰል መራራ ታሪኮች በዘመናቸው ወይንም በአባቶቻቸው ዘመን ስለመፈጸሙ የሚነግሩን ሌሎች ሀገራት ይኖሩ ይሆን? እርግጠኛ መሆን
ያዳግታል፡፡
ይህ ቡድን ዛሬም አላረፈም:: ዘመናችንን ቅርጥፍ አድርጎ መብላቱና ዕድሜያችንን ከል እንዳለበሰ መኖሩ አላጠረቃ ብሎት ዛሬም በንጹሐን የደም ግብር ለመኖር መጨከኑ የሰብእናውንና የሞራል ዝቅጠቱን የሚያሳይ ነው:: “ሀገሪቱን ካላፈራረስኩ” እያለ ከመንፈራገጥ በላይ ምን ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል:: በትግራይ ሕጻናት ደም ከመቆመሩ በላይስ ምን ማሳያ ሊኖር ይችላል:: የጥይት አረር ሽታ ሱሱ አልለቅ ብሎትና ብረት ተንተርሶ ካልተኛ እንቅልፍ የማይወስደው ይህ ቡድን ሰይጣናዊው መገለጫ በጋዜጣ ጽሑፍ ተዘርዝሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡
ከሃዲው የጥቂቶች ስብስብ ቡድን የትግራይን ሕዝብ ከተቀረው ወንድምና እህት የኢትዮጵያ ወገኖቹ ለመለያየት እየፈጸሟቸው ያሉት ድርጊቶች የመሰሪነቱ ዋና መገለጫዎች ናቸው:: የትግራይ ሕዝብስ ቢሆን ስንት ዘመን ልጆቹን እየገበረ እንዲኖር ይፈቅድለታል:: በራሱ ወዝና ላብ አርሶና ነግዶ ከመብላት ይልቅስ የባዕዳንን የእርዳታ እጅ እንዲጠብቅ ግድ ሲሉትስ እንዴት አሜን ብሎ ይቀበላቸዋል:: “ኢትዮጵያን አፈራርሳለሁ!” እያለ ሲንፈራገጥስ እንዲያርፍ ለምን አይገሰጽም:: ለነገሩ እነርሱ እንደሚቃዡት ሆኖላቸው “ኢትዮጵያ ብትፈራርስ” የትግራይ ሕዝብ ብቻ እንዴት በሰላም ይኖራል ተብሎ ይገመታል:: የእነዚህን መልከ ብዙ የእንቆቅልሽ ጥያቄዎች ለመፍታት ከምንግዜውም ይልቅ ዛሬ የትግራይ እናቶችና አባቶች፣ የሃይማኖት ክህነት ያላቸው “ባለስልጣናት”፣ የሽበት ባለጸጎች፣ ምሁራንና ወጣቶች አጥብቀው ቢመክሩበት ሳይሻል አይቀርም፡፡
ከውቂያኖስ ማዶ ተቀምጠው ንፁህ ምግብ እየተመገቡ፣ ንፁህ ውሃ እየተጎነጩ፣ ንፁህ አየር እየማጉና በተዘረፈ የሀገር ሀብት እየተንቀባረሩ “ግፋ በለው” በማለት ለሚያቅራሩት ልጆቹ ጆሮውን ነፍጎ “አልሰማችሁም እምቢዮ!” ለማለትስ ለምን አቅም አጣ? ለትግራይ ሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው የትራዤዲ ተውኔት የሚከውኑ ባዕዳን ዜጎች ሴራስ እንዴት ሊገለጽለት አልቻለም:: የሀገራት እርዳታና ብድር የሰብዓዊነት መደጋገፊያ መገለጫዎች እንጂ የሉዓላዊነት መደርመሻ “አካፋና ዶማ” ሊሆኑ ያለመቻላቸውስ እንዴት ይጠፋዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ሲያወድምና ሲያጠፋ የኖረው ቁሳዊ ሀብታችንን፣ ሥነ ልቦናዊ አቋማችንን፣ ብሔራዊ ክብራችንን፣ ማሕበራዊ ትስስራችንንና አብሮነታችንን ብቻም ሳይሆን ዘመናችንንና ዕድሜያችንን ጭምር ቅርጥፍ አድርጎ በልቶብናል:: ብዙዎቻችን ከልጅነት እስከ ሽበት የኖርንበት ሕይወት አሸባሪው ቡድን በተበተባቸው ሴራዎች እየተጠለፍንና እየተላላጥን በመደነቃቀፍ እንደሆነ የተዥጎረጎረው ተሞክሯችን ምስክር ነው::
እናስ ይህ እኩይ ቡድን በሀገሪቱ ላይ መኖሩ ለጥፋቱ ዕድሜ ከመጨመር ውጭ ምን ፋይዳ ይኖረዋል:: ለዚህም ነው ከሀገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆ! ብሎ በመዝመት ሊፋለመው ቆርጦ የተነሳው:: ይህ ሕዝባዊ ዘመቻ የትግራይንም ሆነ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚታደግ ስለሆነ ዘማቹን ሕዝባዊ ሠራዊት በሆት ግባ! ብለን በመመረቅ በኋላ ደጀንነት እንደምንደግፈው ቃል የምንገባው ቡድኑ ዳግም እንዳያንሰራራ በጽኑ በመሻት ነው:: ሰላም ይሁን፡፡
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም