የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የጤና፣ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ በተለይ ወረርሽኙ ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተከትሎ በርካታ የንግድ ተቋማትና አምራች ኢንዱስትሪዎች በመዘጋታቸው ብዛት ያላቸው ሰዎች ከስራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ክስተቱ ማህበራዊ ርቀትን የሚጠይቅ ከመሆኑ አኳያም ሌሎች በስራ ላይ ያሉት ደግሞ ስራቸውን ከቤታቸው ሆነው ለመስራት ተገደዋል፡፡
እነዚህ ሰዎች በቤታቸው ሆነው ስራቸውን ሲያከናውኑ ታዲያ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የግድ ብሏቸዋል፡፡ ኮቪድ ካመጣቸው ክስተቶች ውስጥም አንዱና እንደበጎ ጅምር ሆኖ የታየው የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በርቀት ሆኖ ስራን ማከናወን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ቴክኖሎጂ ጋር ያልተገናኙና እድሜያቸው አርባ አምስትና ከዛ በላይ የሆኑ በመካከለኛ የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ትልቅ የስራ አጥነት ቀውስ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አዲስ ጥናትን ዋቢ በማድረግ ሲ ኤን ቢሲ ኒውስ በድረ ገፁ አስፍሯል፡፡
ዘገባው የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ በእድሜ በገፉ ሰዎች ላይ ያሳደረው የስራ አጥነት ጫና እንዳለ ሆኖ አርባ አምስትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሥራ አጥነት ቀውስ ጋር በተያያዘ ከፍተኛውን ጫና ሊሸከሙ እንደሚችሉ ከጥናቱ የወጣው ሪፖርት ማመላከቱን አስታውቋል፡፡
‹‹ጄኔሬሽን›› ከተሰኘውና ለትርፍ ካልተቋቋመ የሰራተኞች ድርጅት በወጣው የጥናት ሪፖርት መሰረት በወረርሽኙ ወቅት ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የነበረው መላመድ ስራዎችን በእጅጉ ማቀላጠፉን ነገር ግን በመካከለኛ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ስራቸውን ለማከናወን ከባድ አድርጎት እንደነበርም አስታውሷል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ “Meeting the world’s midcareer challenge,” በሚል ርእስ በተሰራው በዚህ ጥናት ከ45 እስከ 60 የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ በስራ መጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ሰራተኞች በቀጣሪዎቻቸው በኩል በሚደርስባቸው መድሎ ምክንያት ተደራራቢ ችግሮች እያጋጣማቸው እንደሚገኝና በራሳቸው በሰራተኞቹ በኩልም አዳዲስ ክህሎቶችን ለመልመድ ቸልተኝነት እንደሚታይባቸው በጥናቱ መረጋገጡን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሞና ሞርሼድ የጥናቱ ሪፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ የስራ እድሜን በሚመለከት በቁጥር ማብራሪያ ማስቀመጡን ጠቁመው፤ ሰዎች የእድሜ ከፍታ ላይ ሲደርሱ ስራ ለማግኘት እንደሚቸገሩ ያሳየ መሆኑን መናገራቸውንም አስታውቋል፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከመጋቢት እስከ ግንቦት 2021 ተካሂዶ የነበረው ይህ ጥናት እድሜያቸው ከ18 እስከ 60 የሚሆኑ 3 ሺ 800 ተቀጣሪዎችና ስራ አጦች እንዲሁም ከሰባት ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺ 404 ስራ ቀጣሪ ማናጀሮችን ያካተተ መሆኑም በዘገባው የተነገረ ሲሆን፤ ምንም እንኳን ላለፉት ስድስት አመታት በመካከለኛ የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰራተኞች የረጅም ግዜ የስራ አጥነትን ከፍተኛውን ደረጃ ቢይዙም በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የስራ ስነ ምህዳሮች እንዳሉ ሆነው ከአሜሪካ እስከ እንግሊዝ ከህንድ እስከ ጣሊያን ድረስ የሚያሳዩት የጥናቱ ግኝቶች ተመሳሳይና ከ 45 እስከ 60 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰራተኞች በጣም ችላ የተባሉ ስለመሆናቸውም ተገልጿል፡፡
ጥናቱ በሁሉም ሀገራት ያሉ የቅጥር ማናጀሮች አርባ አምስትና ከዘ በላይ እድሜ ያላቸውን ሰዎች ስራን ለማመልከት ያላቸው ዝግጁነትን፣ ቅልጥፍናቸውንና ቀደምት ልምዳቸው እጅግ ደካማ ሆኖ ማግኘቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በእድሜ የገፉ ሰዎች ላይ ከሚታዩ ትልቅ ችግሮች ውስጥ እምቢተኝነትና ቸልተኝነት መሆኑንም ጥናቱ ጠቅሶ፤ በጥናቱ በተካሄደባቸው ሰዎች ላይ 38 ከመቶ ያህሉ ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመሞከር ዝግጁ ያለመሆን፣ 27 ከመቶ ያህሉ አዲስ ክህሎት መማር አለመቻል እንዲሁም 21 ከመቶ ያህሉ ላይ በአነስተኛ የእድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር የመስራት ችግሮች እንዳሉ ማብራራቱንም ጠቁሟል፡፡
በእድሜ የገፉ ሠራተኞች ብዙውን ጊዜ ወጣት እኩዮቻቸውን በስራ እንደሚበልጡ የሚያሳዩ ማስረጃዎች መኖራቸውንም ጥናቱ ማሳየቱን የጠቀሰው ዘገባው፤ ከአስሩ ዘጠኙ ወይም 87 ከመቶ ያህሉ የቅጥር ማናጀሮች እነርሱ የቀጠሯቸው አርባ አምስት እና ከዛ በላይ እድሜ ያላቸው ሰራተኞች ከወጣት ሰራተኞች የተሻሉ መሆናቸውን መናገራቸውንም አመልክቷል፡፡
የጥናቱ ግኝቶች በስራ ቦታ ላይ መሰረታዊ አድሏዊነትን እንደሚያሳዩም የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሞረሽድ መናገራቸውንም ጠቅሶ፤ ለምሳሌ በቅጥር አስተዳዳሪዎች በኩል ተቀጣሪዎችን በእድሜያቸው የመምረጥ ዝንባሌ መኖሩን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ መግለፃቸውንና በተቀጣሪዎች አጭር መረጃ ሊስት ላይ የተመረኮዘ ቃለ ምልልስ ተወዳዳሪዎች ክህሎታቸውን ለማሳየት ከባድ አድርጎታል ሲሉ ማብራራታቸውን ዘገባው
አስታውቋል፡፡
አሁንም ድረስ ስልጠናዎችን ለመውሰድ ግድ የለሽ መሆን እድሜያቸው አርባ አምስትና ከዛ በላይ በሆኑ ስራ ፈላጊዎች በኩል የሚታይ ችግር ቢሆንም ለዚህ ችግር ስልጠና አንዱ መፍትሄ መሆኑን ጥናቱ በዘገባው አመልክቷል፡፡ በጎ ያልሆነ የትምህርት ልምድ መኖር፣ ከግል ሃላፊነት ጋር ግጭት ውስጥ መግባባት፣ ለመካከለኛ ደረጃ ሰራተኞች በቂ ፕሮግራምና የፋይናንስ ድጋፍ አለመኖር ከግምት ውስጥ ገብቶ ከግማሽ ወይም ከ57 ከመቶ በላይ የሚሆኑት የመግቢያ እና የመካከለኛ ደረጃ ሥራ ፈላጊዎች ክህሎታቸውን ዳግም ለማሻሻል ፍላጎት አለማሳየታቸውንና አንድ ከመቶ ያህሉ ብቻ ስራ ሲፈልጉ ስልጠና በራስ መተማመናቸውን ከፍ እንዳደረገላቸው መናገራቸውን ስራ አስፈፃሚዋ እንደጠቀሱ በዘገባው ሰፍሯል፡፡
ይሁንና ስልጠና ትክክለኛ ጠቀሜታ እንደሚያጎናፅፍ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አጥብቀው የተናገሩ ሲሆን ሶስት አራተኛ ወይም 73 ከመቶ የሚሆኑ እድሜያቸው አርባ አምስትና ከዛ በላይ የሚሆኑ ስራ የቀየሩ ሰዎች ስልጠና መከታተላቸው አዲስ የስራ መደባቸውን ለመያዝ እንዳስቻላቸው፣ መናገራቸውን ዘገባው በመቋጫው አስቀምጧል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም