ብዙ ግዜ መስራት ያለብንን ሳንሰራ የምንቀረው መሆን ያለብንን ሳንሆን የምንቀረው ውስጣችን በሚፈጠር ፍርሀት ተሸብበን ወደ ሙከራ ስለማንገባ ነው። በዚህም ነገሮች ካለፉ በኋላ ምን ነበር እንዲህ ባደርገው፣ እንዲህ ብሆን ኖሮ ብለን ስንቆጭ እንታያለን። ለመሆኑ ፍርሃት ምንድን ነው ምክንያታዊና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ፍርሀትን እንዴት ልናስወግድ እንችላለን ስንል የማህበራዊ ሳይንስና አመራር ባለሙያ የሆኑትን አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ባለሙያው እንደሚያብራሩት ፍርሃት ከውጭ ዓለም ሲፈጠር መረጃን ከሚያቀብለን የስሜት ህዋሳቶቻችን፤ ከውስጥ አዕምሮ ሲመነጭ ደግሞ ከእውቀት ወይም ከተሞክሮ ጋር ተዋህዶ የሚፈጠር ነው። ከየትም ይመንጭ ግን አዕምሮ ውስጥ ተቀምጦ አዕምሮ ውስጥ የሚፈጠር ነው። ስለዚህ ነጥለን ፍርሃትን ስሜት ወይም እውቀት ነው ከማለት ይልቅ ፍርሃት መረዳት ነው ብንል ይሻላል። ፍርሃት መረዳት ነው ስንል ደግሞ መረዳት ከግለሰብ ግለሰብ የሚለያይና የሚበላለጥ ከመሆኑ በተጨማሪ መረዳት ስሜት ሲደመር እውቀት የሚፈጥሩት ሁለቱንም አጣምሮ በመያዙ ነው።
ሰዎች ለምን ይፈራሉ?
- እርግጠኛ ካለመሆን ይመጣል (ነገ ምን ይሆን፤ እሆን) ከሚል፤
- መረጃን አብዝቶ ከመከታተልና ከማመን። ይህ ስሜት መር በመሆን የሚመጣ ነው፤
- እምነት ማጣትም ፍርሃትን ያመጣል፤ ስንጠራጠርና ስንገምት ከእምነት ይልቅ ፍርሃት ይነግስብናል፤
- ሁኔታን መታመን ፍርሃትን ያመጣል። ትላንት ወይም አሁን ያለንበትን ማንኛውንም አስቸጋሪ ሁኔታ ይቀጥላል/አይለወጥም ብለን ስናምን እንፈራለን። (በቃ አለቀልኝ አይነት መረዳት፤
- በሌሎች ላይ መለጠፍ፣ መደገፍና መታመን እንዲሁም
በራስ ደግሞ አለመተማመን ፍርሃትን ያመጣል፤
• አዳዲስ ነገርና ሁኔታ ልንገባ ስንል እንፈራለን። ይህም አሮጌውን የለመድነውን ልንተው ስንል ፍርሃት ይመጣል (ትዳር ልንይዝ፣ ቤት መቀየር፣ ስራ መቀየር፣ እንግዳ ሲመጣብን)ና የመሳሰሉት።
• ቀድሞ የደረሰባቸው ማንኛውም አሉታዊ ገጠመኝ በማስታወስ ብቻ ሰዎች ይፈራሉ (መጥፎ ትዝታና ትውስታ ፍርሃትን ይወልዳል)፤
ከፍርሃት ጠቀሜታዎች መካከል
1ኛ. ደህንነታችን እንድንጠብቅ ይረዳናል። ፍርሃት ልክ እንደውስጥ የአደጋ ጊዜ አላርም ነው። ይህም እንድንጠነቀቅና ቀድመን እርምጃ እንድንወስድ ያስችለናል። ለምሳሌ መንገድ ስናቋርጥ፣ መኪና ስናሽከረክር፣ ስራ ስንሰራ ወዘተ ሁሉ ፍርሃት ስለሚሰማን ጉልበት፣ ትኩረት፣ ፍጥነት ወይም ጥንካሬ እንዲኖረን ያደርገናል።
2ኛ. ክብደት ለመቀነስ ይጠቅማል። ጥቂት የምትባል ፍርሃት ብዙ ካሎሪዎችን እንድናቃጥል ያስችለናል። ስንፈራ ሰውነታችን ስኳርና ስብን ያቀልጣል። በለንደን ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች እንዳጠኑት አንድ ሰው አስፈሪ የሆነ የሆረር (የጭራቅ) ፊልም ሙሉውን ሲመለከት በአማካኝ 113 ካሎሪ – ይህም አንድ ሰዓት ከግማሽ ደቂቃ በእግር በመጓዝ ሊያቀልጠው ከሚችለው ካሎሪ እኩል ክብደት ይቀንሳል።
3ኛ. ጊዜያዊ በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራል። በ2009 በዩ/ኪ/ኮቨንተሪ ዩኒቨርሲቲ የተሰራ ጥናት እንደሚያሳየው አንድ ቡድን የሆረር ፊልም እንዲመለከት ተደረገና ከመመልከታቸው በፊትም ሆነ በኋላ የደም ናሙና ተወስዶ በላብራቶሪ ሲታይ በስነ-ልቦናዊ ፍርሃት የተነሳ ከፊልሙ በኋላ ነጭ የደም ሴላቸው በፍጥነት መራባቱን ማረጋገጥ ችለዋል። ነጭ የደም ሴል ደግሞ በሽታ ተከላካይ እና የተጎዳ የሰውነትን አካል ጠጋኝ ነው።
የፍርሃት ጉዳቶች (ይህም ከፍተኛ ፍርሃት ሲነግስብን የሚደርስብን ጉዳቶች ናቸው።)
- ወደ የምንፈልገውና የምንወደው ከመሻገር ይልቅ የማንፈልግና የምንጠላው እስረኞች፣ ባሪያዎችና ተገዥዎች ያደርገናል፤
- እድልና ገጠመኝን ከመጠቀም ያስተጓጉላል፤
- ጨካኝና አውሬ ከማድረግ ባለፈ ለሰብዓዊነት ከፍታ የምናደርገውን ጥረት ይገድላል።
- ለውጥረት፣ ጭንቀትና ድባቴ በመዳረግ እራስን እስከማጥፋት ያደርሰናል፤
- ለጥላቻ፣ ለፈራጅነት፣ ቅናት፣ ለበቀለኝነት፣ ለቂመኝነት ይዳርገናል፤
- ስሜትን መቆጣጠሪያ ክፍሎቻችንን ይጎዳል። ይህም ውሳኔ የመወሰን ችሎታችንን በመጉዳት ለጠቅላላ ሕይወታችን ጤና መናጋት ይዳርገናል።
- ማህበራዊ ህይወትን ይበጠብጣል (ትዳርን፣ ጓደኝነትን፣ ቤተሰባዊነት ወዘተ)፤
ፍርሃትን ለማሸነፍ (ይህም 80 በመቶ የሆነውን ፍርሃትን ለመቀነስ የሚረዱ ናቸው)
1ኛ. በራስ መተማመን። ሰው የራሱ በሆነው ባለው እውቀት፣ ችሎታ፣ ክህሎት፣ ብቃት፣ ተሞክሮ መሰል የውስጥ የአዕምሮ ሃብቱ ላይ እምነቱን ሲጥል ወይም ሲታመን ፍርሀቱን መቀነስ ይችላለል።
2ኛ. የተግባር ሰው መሆን። ለማድረግ፣ ለመፈፀም፣ ለመስራትም ሆነ ለመሆን የፈለግነውንና የወደድነውን በቅድሚያ በደንብ በተገቢው መልኩ ዲዛይኑን በአዕምሮ ውስጥ መጨረስ። ከዚያ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟላን በኋላ በፍጥነት ወደ ተግባር መለወጥ ተመካሪ ነው።
3ኛ. ሃላፊነትን መወጣት ሃላፊነትን መወጣት ከአሉታዊ ሃሳብና መረዳት ነፃ ስለሚያወጣ ፍርሃት ይቀንሳል።
4ኛ. ራስን ለፈተና ማዘጋጀት። ትልቁ የፍርሃታቸን ምንጭ ይገጥመናል ብለን አስበን የምንገምተው ማንኛውም አይነት ፈተና ነው። ይህም ያለመቻል፣ የመበላሸት፣ የኪሳራ፣ የውድቀት ወዘተ ከፊታችን ያስቀመጥነው የፍርሃት ፈተና ነው። ስለዚህ ያስፈራንን ፈተና በደንብ ለመረዳት፣ ለማወቅና ለመመዘን በመሞከር የሚያደርስብንን ጉዳት ወይም ለማለፍ የሚያስፈልገንን ዝግጅት ቀድመን በማሰናዳት ለፈተና ስንዘጋጅ ፍርሃታችን ይጠፋል።
- 6ኛ. የውሳኔ ሰው መሆን። መወሰን የማይችሉ ሰዎች ለእዛ ላልወሰኑለት ጉዳይ ሲፈሩ መኖራቸው ግልጽ ነው። አለመወሰን ፍርሃትን ያበረታል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013