
አዲስ አበባ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ሦስት ክፍለ ከተሞች ለመከላከያ ሠራዊት የተለያየ ድጋፎችን አደረጉ።
የአራዳ፤ የኮልፌ ቀራኒዮና የልደታ ክፍለ ከተማ የኮሚውኒኬሽን ፅህፈት ቤቶች እንዳስታወቁት፤ የክፍለ ከተማዎቹ ነዋሪዎች ከተለያዩ አከላት ገንዘብ በማሰባሰብ ለመከላከያ ሠራዊት ስንቅና ሌሎች ድጋፎች አድርገዋል።
አራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሀና የሽንጉስ እንዳስታወቁት፣ በክፍለ ከተማው ከሚገኙ 10 ወረዳዎች ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ ለመከላከያ ሠራዊት የስንቅ ድጋፍ ተደርጓል ።
የአራዳ ክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ከ300 በላይ በጎችን፣ 18 ሰንጋዎችን፣ ፓስታ፣ መኮሮኒ ፍርኖ ዱቄት፣ ላርጎ፣ ዘይት፣ በሶ፣ ሩዝ ማዘጋጀቱን የተናገሩት ስራ አስፈፃሚዋ፣ የሌሎች ክፍለ ከተሞችን ጨምሮ እንደ አዲስ አበባ ለመከላከያ ሚኒስቴር የማስረከብ መርሐ ግብር በቅርቡ እንደሚኖር አስታውቀዋል።
በተየያዘ ዜና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ግምቱ 12 ሚሊዮን ብር የሆነ የበሬና በግ ድጋፍ አድርገዋል።
ከክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የተሰባሰበው 42 በሬዎች እና 1500 በጎች ሲሆኑ፤ ድጋፉን በትናትናው እለት ለመከላከያ ሠራዊት ተወካዮች ያስረከቡት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙቀት ታረቀኝ በርክክብ ወቅት እንደተናገሩት፤ “ኢትዮጵያን በልቡ አንግቦ በግንባር ለተሰለፈው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንም የደጀንነት ሚናችንን ለመወጣት ቆርጠን ተነስተናል›› ብለዋል።
በሌላ ዜና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ለ2ኛ ዙር እየተሳባሰበ ባለው ድጋፍ የልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚሆን በገንዘብና በአይነት ከ50 ሚሊዬን ብር በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ ነው ። ባለፉት 15 ቀናት ብቻ ከ2 ነጥብ 5ሚሊዬን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ቁሳቁስና 10 ሚሊዬን ብር በጥሬ ገንዘብ አሰባስቧል።
አስተዳደሩ ትናንት 200 የሚጠጉ በጎችን ጨምሮ ሌሎች ለምግብነት የሚውሉ ግምታቸው ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዬን ብር በላይ የሆኑ ግብዓቶችን ያስረከበ ሲሆን ፤ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች፣ ባለ ሃብቶችና አመራሮች ካላቸው ላይ ቀንሰው በራስ ተነሳሽነት ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሽታዬ ሙሃመድ ጠቁመዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ድጋፉን ላሰባሰቡና ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና ከማቅረባቸው በተጨማሪ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች መከላከያ ሰራዊትን በማንኛውም መንገድ ለመደገፍ ያለው ተነሳሽነት የሚበረታታ መሆኑንና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለመደው መልኩ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል::
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013