ለዛሬው ትዝብቴ መነሻ የሆነኝ እጅግ ኋላ ቀር የሆነውና ኢትዮጵያን ለኪሳራ እየዳረጋት ያለው የመንግሥትና የማኅበረሰብ አንቂዎች (አክቲቪስቶች) የመረጃ አሰጣጥ፣ አያያዝና አመራር ጉዳይ ነው፡፡ አገሪቱ መረጃን በወቅቱና በተገቢው ሁኔታ ለሕዝብ የሚያደርስ ጠንካራ ተቋም አለመገንባቷ ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡ ይህ ዋጋ የመክፈሏ እዳዋ ለብዙ ዓመታት ሸክም ሆኖባት ቢቆይም በተለይ ከትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወዲህ እያስተናገደችው ያለው ኪሳራ ደግሞ እጅግ አሳሳቢና የሚያስቆጭ ሆኗል፡፡ ያለንበትን ጊዜ ጨምሮ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ‹‹የመረጃ ባለቤት ነን›› ብለው መረጃ የሚያቀርቡ ግለሰቦችና ቡድኖች ከመረጃ አያያዝና አቀራረብ ስርዓት ጋር የማይተዋወቁ፣ የውሸት መረጃ በማሰራጨት የተካኑ እንዲሁም የመረጃን ትርጉምና አስፈላጊነት የማያውቁ ናቸው፡፡
የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ ወዲህ በአክቲቪስቶች በኩል ሲሰራጩ የቆዩት መረጃዎች በውሸት የታጨቁ፣ ብሔራዊ ጥቅምንና ወቅታዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ያላስገቡ እና ማኅበረሰባዊ እሴቶችን የጣሱ የጥራዝ ነጠቆች ፕሮፖጋንዳዎች ሆነው ታዝበናል። መንግሥትም የሕግ ማስከበር ዘመቻው በተካሄደባቸው ስፍራዎች ስለተፈጠሩ ክስተቶች፣ በአሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ትና በዓለም አቀፍ ተባባሪዎች በኩል ስለሚጠቀሱ ውንጀላዎች እንዲሁም ሕዝቡ ስለጠየቃቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠበት አካሄድ የዘገየ፣ በሚገባ ያልተብራራና የጠላትን ፕሮፖጋንዳ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማክሸፍ አቅም የሌለው ሆኖ አይተናል፡፡ እነዚህ የአክቲቪስቶችና የመንግሥት ስህተቶች ደግሞ ኢትዮጵያን ለበርካታ ጫናዎች ዳርገዋታል፡፡
ከባንዳ ያልተሻሉ ቂል አክቲቪስቶች
‹‹አክቲቪስት›› እየተባሉ የሚጠሩት ግለሰቦች ምን ዓይነት መረጃ በይፋ እንደሚነገርና እንደማይነገር እንኳ ለይተው የማያውቁ ቂሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ሲያሻቸው ‹‹የዩኒቨርሲቲ መምህር››፣ ሲፈልጉ ‹‹ዳያስፖራ››፣ ሌላ ጊዜ ‹‹አክቲቪስት››፣ ‹‹ጋዜጠኛ … ነን›› የሚሉ አካላት ናቸው፡፡ ይባስ ብሎም አንዳንዶቹ በመንግሥት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ተቀምጠው ያሉ ‹‹የሹም ዶሮዎች›› ሆነው ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ግንዛቤ መሰረት መረጃን ከእነርሱ በስተቀር የሚያውቅ ሌላ ግለሰብ የለም፤የምስጢራዊ መረጃዎች ባለቤቶች፣ የመረጃዎቹ ተንታኞችና የመረጃዎቹን ውጤት ወሳኞች እነርሱ ናቸው፤‹‹ከውስጥ ሰው የደረሰን ነው› በማስባልም ከደህንነት ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸውም ያስወራሉ፤መረጃው ሐሰት እንደሆነ እየታወቀ እንኳ ‹‹እውነት ነው›› ብለው ድርቅ የሚሉ አስገራሚ ፍጡራን ናቸው፡፡
‹‹አክቲቪስት›› ተብዬዎቹ ግለሰቦች መረጃዎች እንዴትና መቼ ይፋ መደረግ እንዳለባቸው ፈፅሞ አያውቁም፡፡ ለጠላት ብዙ ጥቅም የሚያስገኙ መረጃዎችን እነርሱ እንደዋዛ በአደባባይ ይናገሯቸዋል/ይጽፏቸዋል፡፡ ‹‹ … በዚህ ስፍራ የወገን ጦር እየተጠቃ ነው … የተላከው ኃይል ወደ ግዳጅ ቀጠና እየሄደ ነው …›› ብለው ቦታ ጭምር የሚጠቅሱና ወታደራዊ ምስጢሮችን የሚያባክኑ ከባንዳ ያልተሻሉ ጥራዝ ነጠቆች ናቸው፡፡ በየደቂቃው የሚቀያየረው አስተሳሰባቸው ደግሞ ምን ዓይነት አቋምና እሳቤ እንዳላቸው ለማወቅ ያስቸግራል፡፡
እውነትም ይሁን ውሸት ከሌላ ሰው ያገኙትን መረጃ ያለምንም ማጣሪያና ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡ መረጃዎቹ በሕዝብ ደህንነት ላይ ስለሚፈጥሩት ጫና አያስጨንቃቸውም፡፡ ለእነዚህ ሰዎች የፌስቡክ ላይክ (Like) እና ሼር (Share) እንዲሁም የዩቲዩብ ተመልካች ቁጥር ከሕዝብ ደህንነትና ከአገር ጥቅም የበለጠ ዋጋ አለው፡፡
የእነዚህ ‹‹አክቲቪስት›› ተብዬዎች ሌላው መገለጫቸው ደግሞ ውሸታምነታቸው ነው፡፡ ግለሰቦቹ የውሸት መረጃ በማሰራጨት ይታወቃሉ፡፡ ያልተደረገውን እንደተደረገ፤ ያልተባለውን እንደተባለ አድርገው የሚናገሩና የሚጽፉ የውሸት ቋቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ አክቲቪስቶች ‹‹ … ሞተ፣ ተደመሰሰ፣ ተቃጠለ፣ ተቆጣጠረው …›› ያልተባለ ነገር የለም፡፡ ዓይናቸውን በጨው አጥበው ውሸት የሆነውን ‹‹እውነት ነው›› ብለው ይሟገታሉ፡፡
እጅግ የሚያሳዝነውና ተስፋ አስቆራጭ የሆነው ደግሞ እነዚህ ‹‹አክቲቪስቶች›› በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ባለቤቶች መሆናቸውና ተከታዮቻቸውም ከእነርሱ የባሱ አላዋቂዎች መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ‹‹አክቲቪስቶች›› በተከታዮቻቸው ዘንድ እንደታማኝ የመረጃ ምንጭ ይቆጠራሉ፡፡ በተደጋጋሚ የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ ተከታዮቻውና ደጋፊዎቻቸው እነርሱን ከመምከርና ከመተቸት ይልቅ ይባስ ብለው የማበረታታቸውና እንደጀግና የመቁጠራቸው አሳዛኝ እውነት ሲደመርበት ደግሞ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
‹‹እነዚህ ‹አክቲቪስቶች› እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን የሚያሰራጩበት ዓላማና ምክንያት ምንድን ነው?›› ብሎ መጠየቅ የጉዳዩን ውል ለመያዝ የሚደረገውን ጉዞ ቀለል ያደርገዋል፡፡ መቼም የውሸትና ለአገር ጥቅምና ለሕዝብ ደህንነት አደገኛ የሆኑ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ሰዎች የድርጊታቸው መነሻ/ዓላማ ቀላል ነው ብሎ አለመገመትና ማሰብ ሞኝ አያስብልም፡፡
ከምክንያቶቻቸው መካከል አንዱ አላዋቂነታቸው ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት እነዚህ ግለሰቦች የመረጃ አስተዳደርና አቀራረብ እውቀት የላቸውም፡፡ አክቲቪስቶቹ በስሜት የሚነዱ እንጂ በስሌት የሚመሩ አይደሉም፡፡ የተከታዮቻቸው አላዋቂነት ተጨማሪ ሞራል የሚሰጣቸው የዝቅተኛ አስተሳሰብ ደረጃ ባለቤቶች ናቸው፡፡ በምክንያታዊነት ደጅ ደርሰው አያውቁም። ሃሳብን መፈተሽ፣ መመርመርና መመዘን እንደሰማይ ይርቃቸዋል፡፡ ሌላው ይቅርና ምን እንደተፈጠረ እንኳ በውል መረጃ ሳይኖራቸው ተቃውሞ ለማሰማትና ድጋፍ ለመስጠት ጊዜ አያባክኑም፡፡
ሌላው ምክንያታቸው ደግሞ በእነርሱ ጥላ ተከልለው የራሳቸውን ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀም የሚፈልጉ አካላትን (የውጭ ኃይሎች እና በመንግሥት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ያሉ) ዓላማ የማስፈፀም ተልዕኳቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ተግባራቸው የሚበረከቱላቸው ቁሳዊና ሌሎች ጥቅሞችና ማታለያዎች ደግሞ በዚሁ የይሆናል መላምት ስር የሚጠቃለሉ ገፊ ምክንያቶች ተደርገው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ግለሰቦቹ ራሳቸው የሚያራምዱትን አቋም ማስፈፀምም ሌላኛው ምክንያት ነው ተብሎ ይገመታል። ይህኛው ምክንያት አደገኛና የሐሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩት ግለሰቦች የሌሎች ተልዕኮ አስፈፃሚዎች ከመሆን ተሻግረው የራሳቸውን ዓላማና አቋም የሚያሳዩበትና የሚተገብሩበት መንገድ ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ግምቶች በተጨማሪ ሌሎች ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
በእርግጥ ምክንያቶቻቸው ሁሉንም ሰው ላያስማሙ ይችላሉ፡፡ አንድ የማይካድ ሃቅ ግን አለ፤ ይኸውም ከሌሎች በተቀበሉትም ይሁን በራሳቸው ፍላጎት፣ እነዚህ አካላት አደገኛና የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ መጣላቸው ነው፡፡
ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ ‹‹በምርጫ ተወዳድረን፣ አሸንፈን አገር እንመራለን›› ብለው ሲደነፉ የነበሩ የፓርቲ አባላትና አመራሮችም በዚህ የዘቀጠ ተግባር ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ትልልቅ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጭምር ከመረጃ አያያዝና አቀራረብ መርህ ርቀው መገኘታቸውም ያስገርማል፡፡
በመንግሥት በኩል የመረጃ አሰጣጥ ዝርክርክነት
መንግሥት ወቅታዊ፣ ተዓማኒና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎች የሚመጥን መረጃ መስጠት እጅግ ከብዶታል። ሕዝቡ የየትኛውን ወገን መረጃ ማመን እንዳለበት ግራ ገብቶታል፡፡ የጥራዝ ነጠቅ አክቲቪስቶችን መረጃ ከተመለከተና ካዳመጠ በኋላ፣ መንግሥት መረጃ ይሰጠኛል ብሎ ተስፋ ቢያደርግም የመንግሥት ነገር ‹‹ቄሱም ዝም፤መጽሐፉም ዝም›› እንደሚባለው እየሆነ ነው፡፡ ሕዝቡ የውሸት መረጃዎችን የሚያሰራጩና መረጃዎች እንዴትና መቼ ይፋ መሆን እንዳለባቸው የማያውቁ ‹‹አክቲቪስቶች››ን በመረጃ ምንጭነት የሚጠቀመው ትክክለኛ መረጃ የሚሰጠው ሁነኛ የመንግሥት አካል ባለመኖሩ ነው፡፡
የመንግሥት ተገቢውን መረጃ በፍጥነት የማሳወቅ ችግር ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ወዲህ በጉልህ ታይቷል። የሕግ ማስከበር እርምጃው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ (የውጭ) መገናኛ ብዙኃን ስለጉዳዩ የሚያሰራጩት ዘገባ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ተገቢ ያልሆነ ነው፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ስለጉዳዩ ያላቸው ግንዛቤ ከእውነታው በእጅጉ የራቀ ሆኖ ታዝበናል፡፡ ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለጉዳዩ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ (እንዲኖረው) አድርጓል፡፡ ይህ የውሸት መረጃን የማሰራጨትና የተሳሳተ ግንዛቤን የመያዝ ችግር የተፈጠረው በመንግሥት ድክመት እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት እንዲሁም በመንግሥታት ዓላማና የግል ፍላጎት ምክንያት ነው፡፡ መንግሥት ስለጉዳዩ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልፅ ከማሳወቅ አንፃር የሰራው ስራ በቂ የሚባል አልነበረም (በእርግጥ መንግሥት ሁሉንም ኃላፊነት ብቻውን ሊወጣ አይችልም፤አይገባምም፡፡ በተለይ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ የዘመቻና የቅስቀሳ ስራ በሚፈልጉ ተግባራት ላይ የምሁራን፣ የተቋማት በአጠቃላይ የዜጎች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው)፡፡
‹‹በለው፣ ፍለጠው፣ ቁረጠው ፣ ተደመሰሰ …›› የሚሉ ጥራዝ ነጠቅ ‹‹አክቲቪስቶች›› የመረጃ ምንጭ እንዲሆኑ ፈቅዶላቸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የመንግሥት አካላት የሚናገሯቸው መረጃዎች መሬት ላይ ካለው ተቃራኒ የሆኑና ግራ የሚያጋቡ ሆነው ታዝበናል፡፡ ይህ አሳዛኝ አካሄድ ደግሞ ሕዝብ ግራ እንዲጋባ፣ ተስፋ እንዲቆርጥና አገሪቱም ከፍተኛ ኪሳራዎችን እንድታስተናግድ እያደረገ ነው፡፡ መንግሥት አደገኛ የሆኑና የውሸት መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ ፍላጎትም የለውም፡፡
መንግሥት የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እጅግ አደገኛ የሐሰት መረጃዎች ሲሰራጩ ዝምታን መምረጡ የሚያስገርምና ተስፋ የሚያስቀርጥ ቢሆንም ሕዝቡም የራሱ ኃላፊነት አለበት፡፡ የመረጃዎቹን ምንጮች ታማኝነት መገምገም፣ ምንጮቹ ከዚህ ቀደም ስለነበራቸው ልምድ/ታሪክ ማጣራት፣ የመረጃዎቹ ዓላማዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰላሰል፣ የታወቀ የመንግሥት አካል ማረጋገጫ እስከሚሰጥ ድረስ መረጃዎቹን ለሌሎች አለማጋራት እንዲሁም አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት ማድረግ ከሕዝቡ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የመፍትሄ እርምጃዎች ሐሰተኛ መረጃዎቹ ሊፈጥሩ የሚችሏቸውን አደጋዎች ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይችሉ እንኳ አደጋዎቹን ለመቀነስ ግን ያስችላሉ፡፡ በተጨማሪም ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ማለት በሐሰት መረጃ የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል!
በእርግጥ ‹‹አክቲቪስቶቹ›› የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ ከመምከርና ከመተቸት ይልቅ ይባስ ብለው እነርሱን የሚያበረታቷቸውና እንደጀግና የሚቆጥሯቸው ተከታዮቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ግን የሐሰት መረጃዎችን ለማጣራት የሚያስችል ብቃትና ዝግጅት አላቸው ተብሎ አይታሰብም፡፡
ሕዝብ ለማገልገል ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ስላለበት ስለአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ እውነታውን ለሕዝብ ማስረዳት አለበት። ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ግልጽነት በተግባር እየታየ ነው›› ተብሎ ቢጠየቅ ምላሹ አጥጋቢ አይደለም ነው፡፡ በርካታ ጥያቄ የሚነሳባቸው ጉዳዮች ምላሽ ባለማግኘታቸው እንቆቅልሾች በዝተዋል፡፡ መንግሥት የአገርን ሁኔታ በግልጽ ማስረዳት ሲያቅተው ምላሽ የሚሹ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ተነስተዋልም፡፡
በሕዝብና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት በመተማመን ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ለዚህም መንግሥት አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ከሚሆኑባቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው የግልጽነት መጥፋት ነው፡፡ ግልጽነት ሲጠፋ መተማመን አይኖርም። የመንግሥት አሠራር ግልጽ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ካለበት የሴራ ፖለቲካ ሥፍራ አያገኝም፡፡ ይህ አካሄድ መግባባትን ይፈጥራል፡፡ ይህ መግባባት ደግሞ በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ የአገር ግንባታ (Nation Building) ለማከናወን ያስችላል፡፡
ዋናው ጉዳይ ጠንካራ፣ ታማኝና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ያስገባ ጠንካራ የመረጃ አያያዝና አሰጣጥ ስርዓት መፍጠር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደካማ በሆነ የመረጃ አስተዳደርና የፕሮፖጋንዳ ስልት ምን ያህል ኪሳራ እንደደረሰባት እየተመለከትን ነው፡፡ መንግሥት ግልጽና ትክክለኛ መረጃን በየወቅቱ ለሕዝብ ይስጥ፤ጥራዝ ነጠቅ ‹‹አክቲቪስቶችን››ም አደብ ያስይዝ!
ስለመረጃ አያያዝና አቀራረብ ምንም እውቀት በሌላቸው ጥራዝ ነጠቅ ‹‹አክቲቪስት›› ተብዬዎችና መንግሥታዊ ዝርክርክነት የተነሳ ኢትዮጵያ ዋጋ መክፈሏ ሊቆም ይገባል!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013