የእርዳታ ነገር እንደ ዘንድሮ ግራ አጋቢ ሆኖ አያውቅም። እርዳታ ሰጪ ነን የሚሉ አካላት ዋነኛ ችግር ፈጣሪ የሆኑበት እና እርዳታው በእርግጥ እርዳታ ነው ወይ የሚል ጥያቄ በህዝብም በመንግስትም ዘንድ ያስነሳበት ወቅት ዘንድሮ ነው። በትግራይ ለተፈጠረው ሰብአዊ ችግር ሰብአዊ እርዳታ እንሰጣለን ብለው የገቡት ሀይሎች ከሚያስፈልገው እርዳታ 30 በመቶውን ሰብአዊ እርዳታ ብቻ እየለገሱ 70 በመቶውን ግን ፖለቲካዊ ችግር በመፍጠር ላይ ተሰማርተው ሲታዩ የተፈጠረው አግራሞት ለየት ያለ ነው። ምናልባትም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ዘንድሮው የእርዳታ ድርጅቶች ጭንብላቸው ወልቆ ያየበት ጊዜ ያለ አይመስልም።
በእርግጥ ዘንድሮ ጭንብላቸው ተገፈፈ እንበል እንጂ ከዚህ ቀደምም እነዚህ እርዳታ ሰጪ ነን የሚሉ ሀገራት እና ተቋማት ሲሰሩ የከረሙት አስነዋሪ ስራ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይታወሳል። ወትሮም ቢሆን ሲፈልጉን እንጂ ስንፈልጋቸው የማይደርሱልን እነዚህ “ለጋሾች” ኢትዮጵያ የጭንቅ ጊዜ ላይ በነበረችበት ጊዜ በሙሉ አናውቅሽም ብለዋታል።ለዚህም ምስክሩ በሁለቱም የጣሊያን ወረራ ወቅት ይዘውት የነበረው አቋም ነው።በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ መወረሯን አቤቱታ ባሰሙት አጼ ሀይለስላሴ ላይ የሳቁት ሳቅ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወስ ነው። ከዚያም በኋላ በዘመነ ደርግ በተከሰተው የ1977ቱ ረሃብ ወቅት ሰብአዊ እርዳታ እንሰጣለን ብለው ቢመጡም ነገር ግን በእርዳታ ሽፋን ዛሬ ሀገርን ለሚያምሰው ህወሃት ደርግን የሚጥልበትን መሳሪያ አስታጥቀው ነው የተመለሱት።በወቅቱ በረሀብ ለተጎዳው ህዝብ ሲላክ ከነበረው እህል 95 በመቶው ተሸጦ የጦር መሳሪያ እንደተገዛበትም የዛሬው የጁንታው አፈቀላጤ ማርቲን ፕላውት ከአመታት በፊት ለቢቢሲ በሰራው ዘገባ አጋልጦ ነበር።
እነዚህ ሁሉ ታሪኮች እንዳሉ ሆነው ዛሬም እነዚሁ ሀይሎች በእርዳታ ስም ሊሞት አንድ ሳምንት የቀረውን ህወሓት የተሰኘ ሽፍታ ወደ ህይወት ለመመለስ እየተንደፋደፉ ነው። መንግስትም በተከታታይ በሰጠው ማሳሰቢያ ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከሳምንታት በፊት ለህዝብ እንደተናገሩት እነዚሁ ለጋሾች ከ40 አመት በፊት የተጠቀሙበትን መንገድ ሊጠቀሙ እየሞከሩ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንንም መንግስት እንዲህ አይነት ነገር እንደማይታገስ አሳውቀዋል። የእሳቸው ምክትል የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው እርዳታ በመስጠት ስም ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ከዚያ የተለየ እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን መንግስት ለማባረር እንደሚገደድ አስጠንቅቀዋል።
ይህ ሁሉ ማስጠንቀቂያ እና ማሳሰቢያ አላማው አንድም ታሪክ በደንብ የሚያስታውሰው ደግሞም መሪዎች በየቀኑ የሚያዩት በሰብአዊነት ካባ ስር የተደበቀ ስውር ደባ ስላለ ነው። ይህን ደባ ማወቅ እና መጠንቀቅ ደግሞ ከብዙ አደጋዎች ያድናል። ለመሆኑ እርዳታ በምን በምን መልኩ ለረጂ ሀገራት ጥቅም ይውላል? የሚለውን በተወሰኑ መንገዶች እንመልከት
እርዳታ እንደ ፖሊሲ መሳሪያ
ሰብአዊ እርዳታም ይሁን የልማት እርዳታ አሁን በምናውቀው መልክ መከናወን የጀመረው ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ነው። ጀማሪዋም አሜሪካ ናት። በሁለተኛው የአለም ጦርነት አውሮፓ በተለይም ጀርመን እና በዙሪያዋ ያሉ ሀገራት ከባድ የኢኮኖሚ ድቀት አጋጥሟቸው ነበር። በዚህም የተነሳ በወቅቱ በጦርነቱ ብዙም ያልተጎዳችው አሜሪካ ማርሻል ፕላን የተባለውን የእርዳታ እቅድ አዘጋጀች። በወቅቱ አሜሪካ 13 ቢሊየን ዶላር /በዛሬው ተመን ከ114 ቢሊየን ዶላር/ በላይ ለ17 የአውሮፓ ሀገራት የሰጠች ሲሆን ይህም ይፋዊ አላማው ሀገራቱ ከገጠማቸው ፖለቲካዊ ድቀት ቶሎ እንዲያገግሙ እና ኢኮኖሚያቸው እንዲነሳ ሲሆን ድብቅ አላማው ደግሞ የኮሚኒዝምን መስፋፋት መመከት ነበር። እንግዲህ የወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ጆርጅ ማርሻል እቅድ የሆነው እና በስማቸው የተሰየመው ይህ እቅድ ከጅማሮውም ውስጣዊው እና ዋነኛ አላማው ፖለቲካዊ እንደነበር ከዚህ መረዳት እንችላለን።
ከዚያ በኋላ በተከተሉት አመታት በሙሉ የነበረው የእርዳታ ታሪክ በፖለቲካዊ አጀንዳዎች እና በሰጥቶ መቀበል ሸፍጥ የተሞላ ሲሆን በተለይም የቀዝቃዛው ጦርነት መጀመር ሀገራት እርዳታቸውን በሙሉ በርእዮተ አለም ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል።ምእራባውያኑ በተለይ ሁለተኛው የአለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ያቋቋሟቸው እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፤ የአለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍን የመሳሰሉ ተቋማት እርዳታዎች ፖለቲካው አላማ እንዲይዙ ለማድረግ ተጠቅመውበታል።
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው እርዳታዎች የተለያየ አይነት ቅርጽ እና ስያሜ እንዳላቸው ነው። ዋነኞቹ ግን የልማት እርዳታ እና የሰብአዊ ድጋፍ የሚባሉት ናቸው። የልማት እርዳታ በሚባለው ውስጥ ብዙ አይነት ድጋፎች ያሉ ሲሆን ዋነኛ አላማቸው ድህነትን መቀነስ ላይ ያተኮረ ነው።ሰብአዊ እርዳታ በሚባለው ውስጥ ደግሞ ተፈጥሮአዊም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲፈጠሩ እነሱን ለመቀነስ እና የሚያስከትሉትን ቀውስ ለማስቀረት የሚደረግ ርብርብ ነው። ሁለቱንም አንድ የሚደርጋቸው ነገር ቢኖር ታዲያ ሁለቱም ከጀርባቸው ተንጠልጥሎ የሚመጣ የሰጪው ፖለቲካዊ ፍላጎት መኖሩ ነው።
ምእራባውያን እርዳታን ለፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ተጠቅምውበታል ፤ አሁንም እየተጠቀሙበት ነው። ሰብአዊ እርዳታም የሚሰጠው ከብዙ ቅድመ ሁኔታዎች ጋር ነው። እንዲሁ የሚመጣ ሰብአዊ እርዳታ የለም። በአደባባይ መግለጫቸው እርዳታው የሰዎችን ሰቆቃ ለማስቀረት የሚደረግ ነው ቢሉም እንኳን ከጀርባ ግን እያንዳንዷ ኪሎ ስንዴ እና እያንዳንዷ ሊትር ዘይት አብሯት የሚመጣ ቅድመ ሁኔታ አለ።ሁሉም ቅድመ ሁኔታ የነሱን ጥቅም የያዘ ነው።ሰብአዊ ድጋፍ የሚሰጡት ለተቸገረ ሁሉ አይደለም ፤ ለመረጡት እንጂ። የሚመርጡት ደግሞ ለነሱ ፖለቲካው ፍላጎት ቅርብ የሆነውን ነው።ለዚህ ደግሞ ጥሩ ማሳያ ያለፉት ሶስት አመታት የኢትዮጵያ ሁኔታ ነው። በትግራይ ከተከሰተው በመጠን ቢያንስም በባህሪ ብዙም የማይለያይ ችግር በሶማሌ ፤ በኦሮሚያ ፤ በቤኒሻንጉል ፤ በአማራ ተከስቷል። ማናቸውም ሰብአዊ ቀውስ ተፈጥሯል ላግዛችሁ አላሉም። በትግራይ ግን ቸግሩ ገና ችግር የሚባልበት ደረጃ ላይ ሳይደርስ እና መንግስት ከበደኝ ሳይል ሁሉም እርዳታ ለመስጠት ካልገባን የሚል ጩከት ነበር።
በእርዳታ ስም ሲገባ አብሮ የተከተለም ብዙ ጥያቄ ነበር። መንገድ ይጠረግልን ፤ ኔትወርክ ይከፈትልን ፤ መብራት ይብራልን ወዘተ…የሚሉ ማለቂያ የሌላቸው ጥያቄዎች ነበሩ። በአደባባይ ካለው ጥያቄ ባለፈ ደግሞ በውስጥ መስመር መንግስት በትግራይ ክልል የሚከተለውን ፖሊሲ እንዲቀይር የሚደረግ ውትወታዎች ነበሩ። በእርዳታ ስም ገብተው የዲፕሎማሲ ስራ የሚሰሩ ነበሩ። ህወሓትን የሚያሞካሽ ፕሮፓጋንዳ የሚያቀናብሩትም በርካቶች ነበሩ። ለእርዳታ ስራ ይዘው የገቡትን የሳተላይት ስልኮች ለህወሓት ሰዎች መገናኛ ያቀበሉም አሉ። ብዙ ነገር ተሰርቷል። ሁሉም አላማው በመንግስት ላይ ጫና በማድረግ መንግስት እነሱ በጦርነቱ ዙሪያም ሆነ በሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ መጠምዘዝ ነው። ይህ ያለ ቅድመ ሁኔታ መሰጠት የሚገባው ሰብአዊ እርዳታ ላይ ይህን ያህል እጅ የመጠምዘዝ ስራ ከተሰራ በሌሎቹ ከአለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ እንዲሁም ምእራባውያን መንግስታት ጋር በሚደረጉ የልማት እርዳታዎች እና ብድሮች ላይ ምን ያህል እጅ ጥምዘዛ እንዳለ መገመት ይቻላል። እርዳታ ለምዕራባውን የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ናቸው።
እርዳታ እንደ ማሰሪያ
ብዙ የሀገራት መሪዎች የሚስማሙበት አንድ ነገር አለ። እሱም በእርዳታ ያደገ ሀገር እንደሌለ ነው። እንዲያውም ብዙ ሀገራት ብዙ እርዳታ በተቀበሉ ልክ በዚያው መጠን ከድህነት የሚያመልጡበት ቀዳዳ እየጠበበ እንደሚመጣ ነው።ይህን ደግሞ ከግራም ሀንኩክ በላይ በሚገባ ያብራራው ሰው የለም። ሰውየው ሎርድስ ኦፍ ፖቨርቲ / የድህነት ጌቶች/ በተባለው መጽሀፉ የእርዳታ ስራው ምን ያህል የተበላሸ እንደሆነ በብዙ ማስረጃዎች ይሞግታል።በመጽሀፉ እንደሚታየው የእርዳታ ገንዘብ በአብዛኛው ጥቂቶችን ለማደለብ እንደሚያገለግል በተለይም ደግሞ በእርዳታ ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ግለሰቦች በእርዳታው እንዴት ወደሚሊየነርነት እንደተሻገሩ ያሳያል።እስኪ ከመጽሀፉ አንዲት አንቀጽ እንውሰድና እንመልከት። ”በአመት 60 ቢሊየን ዶላር የሚንቀሳቀስበት የእርዳታ ስራ ችግር ለመፍጠር በቂ ነው።የእርዳታ ዘርፉ ለድሆች እጅግ አደገኛ ሲሆን ፍጹም ሊጠቅማቸውም የማይችል ነው። የእርዳታ ዘርፉ የብዙዎችን ህይወት ያመሳቀሉ እና ምድርን ክፉኛ የጎዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተፈጠሩበት ፤ ፍጹም አምባገነናዊ ስርአቶች የሚደገፉበት እና ህጋዊነት የሚያገኙበት ፤ ራሳቸውን የሚያገለግሉ ግብዞች የተሰገሰጉበት ግዙፍ ቢሮክራሲዎች የሚዘረጉበት ፤ የተራ ዜጎች ተነሳሽነት እና ፈጠራ ተደምስሶ የታይታ ሀሳብ ከውጭ የሚሸመትበት፤ በታዳጊ ሀገራት ያሉ የስራ ፈጠራዎችን እና ፈጣሪዎችን ምርታማ ወዳልሆነ የአስተዳደር ስራ በመጎተት ለፍቶ እና ደክሞ ሀብት ማፍራትን በስጦታ የሚተካ ስርዓት ነው” ይላል።
እንግዲህ ከዚህ በላይ የእርዳታን አሳሪነት አመልካች አይገኝም። ላለፉት 27 አመታት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተቀበለችው እርዳታ እና በሱ የተከናወነውን ልማት ስንመለከትም የምንደርስበት ድምዳሜ ተመሳሳይ ነው። በእርዳታው ገንዘብ ብዙ የእርዳታ ድርጅት መሪዎች ህይወታቸው ተቀይሯል።እንደ ሀገር በሩብ ክፍለ ዘመን ውስጥ ከ25 ቢሊየን ዶላር በላይ በእርዳታ ተቀብለን ያንኑ ያህል ገንዘብም ተመዝብሮ ወደ ምእራባዊያኑ ባንክ በባለስልጣናት እና ልጆቻቸው ስም ገቢ ሆኗል።እርዳታ ሰጪዎቻችን እና አበዳሪዎቻችን ይህንኑ እያወቁ በላይ በላይ ብድር ይጨመሩልናል።ለምን? ሀገሪቱን በእዳ አስሮ ለማቆየት ነው መልሱ። እርዳታ ሰጪዎቻችን ኢትዮጵያን ከልመና እንድትወጣ የሚያደርጉ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሳሰሉ ፕሮጅከቶችን አይደግፉንም። ያለንን ነዳጅ ወይም የማእድን ሀብት ወይም የግብርና አቅም እንድናጎለብት እና እንድንጠቀምበት አይለግሱንም። የሚለግሱን ቢሮክራሲው ላይ የሚፈስ እና ለውጥ የማያመጣ ገንዘብን ነው። የጦር መሳሪያ ሊያስታጠቁንም ቁርጠኛ ናቸው።እሱንም ቢሆን የሚያደርጉት የምንወጋው አካል እነሱ እንድንወጋው የሚፈልጉት ከሆነ ብቻ ነው።በጥቅሉ እርዳታ ማለት ሰጪዎች ተቀባዮችን በድህነት ገመድ ረዘም አድርገው የሚያስሩበት ነው። ተቀባዩ የሚያድግ ይመስለዋል እንጂ ከተሰመረለት መስመር አልፎ ከፍ አይልም።
እርዳታ እንደ ግጭት ማቀጣጠያ
እርዳታን እንደ ግጭት ማቀጣጠያ በመጠቀም ረገድ ብዙ ርቆ መሄድ አያስፈልግም።የ1977ን ታሪክ ማስታወስ በቂ ነው። ያ እርዳታ አንድ ሀሙስ የቀራትን ህወሓትን ነፍስ የዘራባት ነው። እንዲህ አይነት ታሪኮች በሌሎች ሀገራትም የተለመዱ ናቸው። እርዳታ ሰጪዎች ለነሱ የፖለቲካ አላማ የሚቀርባቸውን ሀይል ቀለብ እየሰፈሩ ፤ መሳሪያ እያስታጠቁ ፤ ስልጠና እየሰጡ ፤ በሞራል እያነቃቁ በጦርነቱ እንዲበረታ የሚያደርጉበት ብዙ ታሪክ አለ። በ2017 እ.ኤ.አ የደቡብ ሱዳን መንግስት መሳሪያ አሾልከው ሲያስገቡ ነበር ያላቸውን 6 የአለም አቀፉ ድንበር የለሽ ሀኪሞች ቡድን አባላት አስሮ ነበር። ግሪክ በ2018 እ.ኤ.አ 30 የእርዳታ ሰራተኞች በህገወጥ መልኩ ስደተኞችን ወደ ሀገር ውስጥ ሊያስገቡ ሲሞክሩ ፤ ህገወጥ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ ፤ ሰነድ ሲያጭበረብሩ እና መሰል ስራዎችን ሲሰሩ አግኝቻቸዋለሁ ብላ አስራ ነበር።ሌሎችም መሰል ክሶች በየጊዜው ብቅ ይላሉ።
አፍሪካን በተመለከተ የእርዳታ ሰራተኞች በድብቅ የስለላ፤ የመሳሪያ ዝውውር ፤ የሰው ዝውውር እና ሌሎች ተግባራትን እንደሚፈጽሙ የሚታወቅ ሲሆን ቢሆንም ክስ እንዳይቀርብባቸው ላኪዎቻቸው አስቀድመው ሽፋን ስለሚሰጧቸው ብዙ መሰል ታሪኮች ተዳፍነው ቀርተዋል።ኢትዮጵያን በተመለከተ የእርዳታ ሰራተኞቹ ወደፈለግነው የትግራይ አካባቢ ስንንቀሳቀስ ማንም እንዳይከተለን ፤ እንደ ፈለግን እንድንገባ እና እንድንወጣ ይፈቀድልን ፤ ምን እንደጫንን አትፈትሹን ሲሉ አለመጠርጠር ሞኝነት ነው። እርዳታ እና እርዳታ ሰራተኞች ሁከት በማቀጣጠል እና ግጭት እንዲስፋፋ እና እንዲራዘም በማድረግ ያላቸው ታሪክን የሚያውቅ ሰው ለዚህ አይነት ህገወጥ ጥያቄ ፊት አይሰጥም።
ስናጠቃልለው ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ካለችበት ድህነት አንጻር ብዙ ወዳጆች እና ብዙ እርዳታዎች ትፈልጋለች። ይህ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ነገር ግን ነገራችን ሁሉ “በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እንዳይሆን እርዳታውን ብቻ ሳይሆን ከእርዳታው ጀርባ “ወዳጆቻችን” የማሱልንንም ገደል ማስተዋል አስፈላጊ ነው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013