የምስራቅ አፍሪካ ዕንቁ፣ የምድር በረከት መገኛ፣ የጥቁር ሕዝቦች ደማቅ ስም ኢትዮጵያ፡፡ ይህች አገር ነጻነትና ጀግንነት ሲወሳ፣ ስሟ ከሌሎች ቀድሞ ይመዘዛል ፡፡ ዘመናትን በራሷ ባህልና ቋንቋ ተሻግራለች፣ ዓመታትን በነጻነት ኖራ ድንቅ ሕዝቦችን አፍርታለች፡፡ ማህጸነ ለምለሟ አገር ሁልጊዜም ድንቅነቷ አይደበዝዝም። ከዓመት እስከዓመት የሚፈሱት ታላላቅ ወንዞቿ ምድሯን ያረሰርሳሉ፡፡ በሆዷ ያሉና ገና ያልተወለዱ ማዕድኖቿ ባዕዳንን ያስጎመጃሉ፡፡ በርካታ ብሔርና ቋንቋን ታድላለች፡፡ ስስታም አይደለችም። ካላት አካፍላ ጎረቤት አብልቶ ለማጥገብ እጆቿ ሰፊ ናቸው፡፡
ዓለም ያወቀው፣እውነት የመሰከረው ጀግንነቷ በወርቅ መዝገብ ተጽፎ ትውልድን ሲያኮራ ዘልቋል፡፡ በየዘመናቱ ውበትና ሀብቷን አይተው ፣ሊዘርፉ፣ማንነቷን ሊያወርዱ የመጡ ጠላቶቿን አሳፍራ መልሳለች፡፡ በውስጥና በውጭ ኃይሎች ለሚሰነዘርባት ጥቃት እጅ ሰጥታ አታውቅም፡፡ ዛሬም ቢሆን ይህ እውነታ የዚህች ታሪካዊ አገር መገለጫ ነው፤አሁንም በርካቶች በሰላም ውላ ማደሯን አይመኙም፡፡ ማንነቷ ያሰጋቸው ዕድገት ብልጽግናዋ ያላማራቸው ምዕራባውያን በየሰበቡ ህልውናዋን ለመናድና አቅሟን ለማዳከም ሲሮጡ ያድራሉ ፡፡
ወደኋላ መለስ ብለን የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነትን ስንቃኝ የመነሻው ምንጭ ከአንድ እውነታ ያደርሰናል፡፡ ይህ እውነት የምዕራባውያኑን የግል ጥቅምና ራስ ወዳድነትን ይመሰክራል፡፡ ይህ የራስወዳድነት ክፉ አባዜ የበርካታ አገራትን ታሪክ ቀይሯል፡፡ የመላ አፍሪካውያንን ህልውና አፋልሷል፡፡
ዘመኑ በርካታ ምዕራባውያን በቅኝ የገዟቸውን አገራት እንደፈረሶቻቸው ‹‹ቼ..›› እያሉ የሚጋልቡበት ነበር ፡፡ ጥቁሮች በማይፈታ ሠንሰለት ታስረው ህይወትና ጉልበታቸውን እንዲገብሩ የተገደዱበት፣ ወራሪ ኃይሎች ተዝቆ በማያልቅ የአፍሪካ ሀብት እንዳሻቸው የፏለሉበት የቅኝ ግዛት ዘመን፡፡
የዛኔ አገር ቆርጠው፣ ወንዝ አቋርጠው የሚመጡ ነጮችን በጀግንነት የሚመክት የጥቁር አገር ሕዝብ አልነበረም፡፡ በገዛ አገሩ መሬቱን ወርሶ፣ አገሩን ነጥቆ ትውልዱን በግፍ ከሚመራ ኃይል ለመውጣት የሚሞክር ካለም ክፍያው የውርደት ሞት ይሆናል፡፡
ዓይነ ግቧ ኢትዮጵያም ብትሆን ከዘመኑ ወራሪ ኃይሎች እይታ አልዳነችም፡፡ ለምነቷን እንደማር ጥዕምና የለዩት እንግሊዝና ጣሊያን ከእጃቸው ሊያስገቧት ቢሹ የጋራ ጥቅማቸውን የሚያስከብር የውል ስምምነት ተፈራረሙባት፡፡
ሁለቱ አገራት እንደኤሮፓውያን አቆጣጠር በመጋቢት 1891 የተዋዋሉት ስምምነት ብቻ አልበቃቸውም፡፡ ከሶስት ዓመታት በኋላም ዳግመኛ የጋራ ጥቅማቸውን በሚያስከብርና የግል ጥቅሞቻቸውን እንዳይነካ በሚያስችል ውል .‹‹አንግሎ ኢጣሊያ አግሪመንት›› በሚል ተስማሙ፡፡
ይህ ውል የሌላዋን ኃያል አገር ፈረንሳይ ጥቅም እንዲያስከብር ሆኖ ዳግም በ1894 በሶስትዮሽ የጋራ ጥቅም ላይ ተመስርቶ ተጠናከረ፡፡ ሶስቱ ኃያላን ተብዬ አገራትም ከኢትዮጵያ ጋር የቅኝ ግዛት ወሰንተኞች በመሆን በጋራ ጥቅማቸው ጉዳይ እርስበርስ እንዳይጋጩ ከስምምነት ደረሱ፡፡ የዚህ ስምምነት ዋንኛ ፍሬ ኢትዮጵያ ብትሆንም ፣በስምምነቱ መሳተፍ ቀርቶ በወጉ እንድታውቅ አልተደረገም ፡፡ በወቅቱ ሶስቱ ኃያላን በአገሪቱ ገብተው ጥቅማቸውን ማስከበር የሚችሉበትን ውል ለማሰር ያገዳቸው አልነበረም፡፡
የዛኔ የተፈጸመው የውሉ ዓላማና ግብ ሲጠናም ከአባይ ውሀ መፍለቂያ እስከ ሱዳንና ኢትዮጵያ መውጫ ድረስ ያሉ ወሰኖችን የሚመለከት ሀቅ ስለመሆኑ ልብ ይሏል፡፡
በጊዜው ፈረንሳይና ኢጣሊያ ለእንግሊዝ በሰጧት ማረጋገጫ ግብጽና ሱዳን የውሀ እጥረት ስለሚያገኛቸው ጥቅሟ የሚነካ ስለመሆኑ ይሁንታቸውን ቸሩ፡፡ በአንጻሩም እንግሊዝና ኢጣሊያ ለፈረንሳይ በሰጡት ማረጋገጫ ከጂቡቲ አዲስ አበባ የተዘረጋው የባቡር ሀዲድ በሙሉ የግል ሀብትና ንብረቷ ስለመሆኑ መሰከሩላት፡፡
ፈረንሳይም ሁለቱን አገራት አቋርጦ የሚያልፈው ረዥሙ የባቡር ሀዲድ የእሷና የእሷ ብቻ ስለመሆኑ ፊርማ ባደመቀው ውል አረጋግጣ ተቀበለች ፡፡ የሶስቱ ኃያላን አገራት ውል ለሶስት ዓመታት እንደዘለቀ በ1922 ሌላ ተጨማሪ አንቀጽ ታከለበት፡፡
ይህ አንቀጽ እንግሊዝ ጣና ሀይቅ አጠገብ ግድብ እንድትሰራ ይፈቅዳል፡፡ ለዚህም የኢጣሊያ መንግስት በዲፕሎማቲክ ረገድ ድጋፉን እንደሚሰጥ ያረጋግጣል። ይህ ሁሉ ሲሆን ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር…የሆነባት ኢትዮጵያ አንዳች አስተያየት እንድትሰነዝር እንኳን ዕድል አልተሰጣትም፡፡ በራሷ ድንበርና ወሰን ላይ ሁለቱ አገራት ጥቅማቸውን እያሰሉ በስምምነት ተደራደሩ፤ በሙሉ ስልጣንና ይገባኛል ባይነትም ግዛት ለማስፋት ጋብቻ ፈጸሙ፡፡
የአገራቱ ስምምነት መነሻ የጋራ ጥቅምን በማስጠበቅ ‹‹ኢትዮጵያ›› የተባለችውን ታላቅ አገር በቅኝ ግዛት ለማንበርከክ የታሰበ ነበር፡፡ ውሉ እንደጠፋበት ክር በየጊዜው የሚወሳስቡት ስምምነትም በ‹‹እናውቅልሻለን›› እሳቤ ለህጻን ብስኩት ሰጥቶ ህይወትን እንደመንጠቅ ነበር፡፡
የምዕራባውያኑ ሴራና ተንኮል ግን እንደሌሎቹ አፍሪካ አገራት በኢትዮጵያ ላይ አልሰመረም። በተለያዩ ጊዜያት መልክና ይዘቱን እየለወጡ አገርን አጥብቆ ለመጠፈር የሚፈጽሙት የወረቀት ላይ ጀግንነት ድል አልሆናቸውም፡፡ ሉዓላዊቷ አገር ኢትዮጵያ እስከዛሬ በጽኑ ማንነቷ ስትገዳደርቸው ቆይታለች፡፡ ታሪካዊ ስምምነት አለን ለሚሉት ታሪካዊ ጠላቶቿም ታሪክ የማይረሳው ትውልድ የማይዘነጋው ደማቅ አሻራ የማኖር ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡
አዎ! ታሪካዊ ጠላቶቻችን አልተኙም፡፡ ዛሬም አገራችን ጥርሳቸውን ባሾሉ የውጭ ኃይሎች ተከባለች። እስከአሁን እንዳደረጉት በየቀኑ ውደቀቷን፣ሞትና ቀብሯን ያመቻቻሉ፡፡ በምክንያትና በሰበብ ከዕድገት መንገዷ ተጋርጠው ዕንቅፋትና ጋሬጣ ይሆናሉ፡፡
ባለ ረጃጅም እጆቹ ምዕራባውያን በአፍሪካ ውሎ ከማደር ባለፈ የሌሎች አህጉራትን ጓዳ ለመፈተሽ የሚያህላቸው የለም፡፡ ድርጊታቸው ደግሞ በቀላሉ አይቋጭም፤ያሰቡትን እስኪያገኙ በእርዳታና ሰብዓዊነት ሽፋን አገር አስከ ማፍረስ፣ ሕዝብ እሰከመበተን ይደርሳሉ ፡፡
በማር የተለወሰ መርዝ ያላቸው ምዕራባውያን ወዳሰቡት አገር ጣልቃ ለመግባት ጠብ መጫርና ጦር መስበቅ የመጀመሪያ ምርጫቸው ላይሆን ይችላል፡፡ እነሱ በችግር መሐል መፍትሄ፣ በረሀብ ውስጥ ምግብ፣ በጦርነት ሰላም ለመፍጠር ዘዴና መንገዳቸው የረቀቀ ነው ፡፡ ይህን ሀቅ ለማጣቀስ የአገረ ሶርያን የቀደመ ታሪክና አሁን ያለችበትን እውነታ ማሳየቱ ብቻ በቂ ነው።
እንደኤሮፓውያን አቆጣጠር በመጋቢት 2011 የሶሪያ ዜጎች ዴሞክራሲ ይስፈን ፣ሙስናም ይብቃ ሲሉ በአደባባይ ሰልፍ ወጡ ፡፡ በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በነበሩት በሽር አላሳድ ላይ የተነሳውን ተቃውሞም ብዙዎች ተቀላቀሉት ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ግጭቱ ተባብሶ እስከዛሬ መቋጫ ያልተገኘለት ጦርነት አስነሳ፡፡
በሶርያ ውስጣዊ ጉዳይ እጃቸውን ያስገቡት ሀያላኑ አገራት የጦርነቱ አካል በመሆን እሳቱን ቆሰቆሱት። እነ አሜሪካን ወታደራዊ ስልጠና በመስጠትና ለዘብተኛ የሚባሉ ቡድኖችን በማገዝ፣ ጦርነቱን አገዙ። ሩስያ የአየር ጥቃቱን በመምራት ክንዷን አሳየች። ቱርክ፣ዮርዳኖስና ኢራንም የጦር አቅርቦትና የፖለቲካ ድጋፍ በማድረግ ተሳተፉ ፡፡ ሄዝቦላህና የሺአ ሙስሊም ታጣቂዎች ጭምር ታሪካዊቷን የመካከለኛ ምስራቅ አገር በጦርነት ለማውደም አለን ሲሉ ተነሱ፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው በአገሪቱ ለተነሳው የእርስ በእርስ ግጭት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አልነበረም፡፡ በሽር አላሳድን አስወግዶ ሌላ መሪ የመተካት ፍላጎትም አይደለም፡፡ ለዚህ ሁሉ ውድመትና ብጥብጥ የመነሻ ምስጢር የየአገራቱ የግል ጥቅም ስለመሆኑ ዓለም ሁሉ ያውቀዋል፡፡
ሶርያ በነዳጅ ሀብቷ የበለጸገች አገር ናት፡፡ የዛሬን አያድርገውና ሕዝቦቿ ባላቸው በቂ ገቢ ራሳቸውን ማሳደርና ሌሎችን ማስተዳደር የሚችሉ ናቸው፡፡ በወቅቱ መንግሥታቸውን የተቃወሙ ኃይሎችን በጎን በመደገፍ ግጭቱን ያሞቀችው ጣልቃ ገቧ አሜሪካ ነበረች፡፡ በወቅቱ የሰጠችው ሰበብም የአልሳድን የጭካኔ ድርጊት መታገስ አልችልም የሚል ነበር፡፡
ሌላዋ ኃያል አገር ሩሲያ ብቸኛውን የሜዴትራሊያን የባህር ኃይልና የአየር ጦር ማዘዣን በሶርያ በኩል የማግኘት ዕድሏ የሰፋ ነው፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉትም በጦርነቱ ዋንኛ ተሳታፊ መሆኗ በመካከለኛው ምስራቅና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ያግዛታል፡፡ ይህ ግላዊ ፍላጎቷም በሶርያ ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ ሆኗ እጇን እንድታነሳ አድርጓታል፡፡
ባለፉት ዓመታት አይኤስን በመዋጋት የቆየችው አሜሪካም ከግል ጥቅሟ ባለፈ ፕሬዚዳንት አሳድን ከስልጣን ለማውረድ አልጣረችም፡፡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ ላለቁባትና በሺዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦቿ በየአገሩ እንደጨው ለተበተኑባት ሀገረ ሶርያ የፈየደችው መላ አልተገኘም፡፡
ዛሬም በሶርያ የሕዝቦች ታሪክ ሞትና ስደት ሆኗል። አሁንም የትናንቷ ደማቅ ከተማ ደማስቆ በፍርስራሽ ቅሪት ተሞልታ በ‹‹ነበር›› ቀርታለች፡፡ የአገሪቱ ነዳጅና ጥሬ ሀብት የሚያስጎመጃቸው ምዕራባውያን ግን በራሳቸው መላና ዘዴ ጥሬ ሀብቷን ለመዝረፍ፣ ዕንቅልፍ ይሉትን አያውቁም፡፡
የሀያላን አገራት ጣልቃ ገብነት ሲወሳ የሊቢያን ጉዳይ ሳያነሱ ማለፍ ይቸግራል፡፡ ሊቢያ በአሁኑ ጊዜ በሁለት ሀያላን ፈርጣማ እጆች እንደተወጠረ ቆዳ ትመሰላለች፤ፍላጎታቸው የበረከተ ተቃዋሚዎች፣የወቅቱ ገዢዎችና ዙሪያዋን የከበቧት የውጭ ኃይሎች አፍሪካዊቷን አገር ለውድመት ዳርገዋታል፡፡
ከዓመታት በፊት ከስልጣናቸው በውርደት ከተወገዱት ሙአመር ጋዳፊ ውድቀት በኋላ በአገሪቱ ከፍተኛ የሚባል ውጥረት ነግሷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትር ፈይዝ አልሲራጅ መንግሥትና በጄኔራል ካሊፍ ሀፍታር የሚመራው አማጺ ቡድን ሊቢያን የሁለትዮሽ ወጥረዋታል፡፡ ይህ እውነታም በርካታ ዜጎችን ለሞት፣ለአስከፊ ድህነትና ለስደት ዳርጓል፡፡
የአምባገነኑ ጋዳፊ ሥርዓት ከተገረሰሰ በኋላ የሊቢያ ዜጎች መልካም ህይወትን ናፍቀው ቆይተዋል። ከዓመታት በፊት መንግሥታቸውን ሲያስወግዱ በራሳቸው ፍላጎትና ለውጥ ፈላጊነት ነበር፡፡ ይህን ሲያደርጉ የሌሎች አገራትን ጣልቃ ገብነትና ‹‹እናውቅላችኋለን›› ባይነትን አስበው አልነበረም፡፡ ለራሳቸው ችግር ራሳቸው መፍትሄን የሻቱት ዜጎች ግን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ዋጋ አስከፈላቸው፡፡ ‹‹በአንደበታችሁ እንናገር በማዕዳችሁ እኛ እንቁረስ›› ባዮቹ አማጺያንን አደራጅተው የፍላጎታቸው መዳረሻ የዕቅዳቸው ግብ አደረጓቸው፡፡
እነሆ ዛሬ በምድረ ሊቢያ ዙሪያ ገባውን ካሉ የአረብ አገራት ባሻገር እንደ ሞስኮ የመሳሳሉ አገራት እጃቸውን ማስገባታቸው ይነገራል፡፡ የሊቢያ ጉዳይ ያገባኛል ባይዋ ፈረንሳይና የቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ኢጣሊያም በጄኔራሉ የሚመራውን ጦር የመቀላቀል ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡
ለማንም ግልጽ እንደሆነው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያለባት አገር ነች፡፡ ይህ ባለቤትነቷም የዓለም ገበያውን በስፋት እንድትቆጣጠር ሲያደርጋት ቆይቷል፡፡ የዚህ ወርቃማ ጥቅም ተጋሪ መሆን የሚሹት ምዕራባውያን ታዲያ የልባቸውን ክፋት በልባቸው ከልለው በእርዳታና ሰብዓዊነት ሽፋን ጭምር አገሪቷን እያመሷት ይገኛሉ፡፡
አስገራሚው ጉዳይ የምዕራባውያኑ ገራገር መሳይ ልብ ሲፈተሽ የሚገኘው ዥንጉርጉር ገጽታ ነው ፡፡ እነሱ ሁሌም ቢሆን እንደ ካብ ላይ እባብ ውስጥ ውስጡን ተሽሎክላኪዎች ናቸው፡፡ ያሰቡትን እስኪያገኙም መልካቸው ብዙ ድርጊታቸው እልፍ ነው፡፡
ሲሻቸው እርዳታ ለጋሾች፣ አልያም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሆነው ለመቆም የሚቀድማቸው የለም፡፡ ይህን ሲደርጉ ኃያልነታቸውን እንደታላቅ ጋሻ ይጠቀሙበታል፡፡ ስማቸውን ከፍ አድርገው በሚፈጽሙት መልካም መሳይ ተግባርም በችግር ብዙ አገራትና ሕዝቦቻቸው ዘንድ የሚያገኙት አመኔታ ከፍ ያለ ነው፡፡
ምዕራባውያኑ የአፍሪካውያንን ልቦና አሳምረው ያውቁታል፡፡ ከዘመናት በፊት አገራቸውን ወርሰው፣ ማንነታቸውን ነጥቀው ሲጫወቱባቸው ኖረዋል፡፡ ይህ እውነታም ጭቃ አቡክቶ ሸክላ እንደሚሰራው ባለሙያ ሲደርጋቸው ቆይቷል፡፡ ሸክላ ሰሪው የእጁን ጥበብ
ቢሻው ማፍረስ፣ አልያም መልሶ መስራት ይቻለዋል። አፈሩና ሙያው በእጁ ነውና እንዳሻው የፍላጎቱን ቢያደርስ ከልካይ የለበትም፡፡ ምዕራባውያኑም የአፍሪካውያንን አገር እየሰሩ ፣ለማፍረስ የሸክላውን ጭቃ ያህል ሲያቀሉትና በገሀድ ሲሞክሩት ኖረዋል፡፡
ወደአገራችን አሁናዊ እውነታ እንመለስ። በኢትዮጵያ በአሸባሪው የህውሓት ቡድን ጠብ አጫሪነት ወራትን ያስቆጠረ ጦርነት እየተካሄደ ነው፡፡ ይህ በተንኮልና ሴራ የተዋቀረ ዕቅድ መነሻውን በሰሜን ዕዝ ወታደሮችና በማይካድራ ጭፍጨፋ ላይ አድርጎ አስከዛሬ ዘልቋል፡፡
የሕዝቦችን ሰላምና አብሮነት ፣የማይሻው የህወሓት ቡድን ‹‹ግፍና በደል በቃን›› ባሉ አገር ወዳዶች ስልጣኑን ከተቀማ ወዲህ በገባበት ዋሻና ጉድጓድ ሆኖ አገር የማፍረስ ዓላማውን እየተገበረው ይገኛል። ይህን እውነታ ከጅማሬው አሳምረው የሚያውቁት ምዕራባውያንም ከአገርና ሕዝብ ህልውና ይልቅ ለጥፋት ቡድኑ መወገናቸውን በገሀድ እያሳዩን ነው፡፡
ቀደም ሲል ምዕራባውያኑ ከህወሓት ጋር የነበራቸው ዕዛዊ ሰንሰለትና የአብሮነት ጨዋታ አሁን ዓይናቸውን በጨው አጥበው ነውርን ህጋዊ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአገርና ወገን አይበጅም ሲል በሽብርተኝነት ለፈረጀው የሕዝብ ጠንቅም የለመዱትን የሰብዓዊነት ድንቅ ዜማ ማቀንቀን ይዘዋል፡፡
እነሱ ከበሯቸውን አድምቀው ዜማውን ይደጋግሙት እንጂ ነገሩ ሁሉ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› መሆኑን እናውቀዋለን፡፡ ለዘመናት በአባይ ውሃ ጉዳይ ጥርስ ሲነክሱብን የኖሩት ኃይሎች ወቅቱን ተጠቅመው ሊያዳክሙን መሞከራቸው ግልጽ ነው፡፡
እነሱ በብድርና እርዳታ ሰበብ እጃቸውን አርዝመው ያሻቸውን እንደሚዘግኑ ይታወቃል። በእቡይ ልባቸው አሲረው በእሾሀማ እጆቻቸው ለአፍሪካ የሚበትኑትን የእርዳታ ስንዴ ሳይቀር ማስፈራሪያ ሲያደርጉት ኖረዋል። አሁን ደግሞ በግልጽ አገርና ሕዝብን እየወጋ ለሚገኘው ሽብርተኛ ቡድን እነ አሜሪካን አጋርነታቸውን ያሳዩት ያለምንም ሀፍረትና ነውር ሆኗል፡፡
ዛሬ የእነሱ አንደበት የተለመደውን እንጉርጉሮ እያስደመጠን ነው ፡፡ ይህ ደግነት ይሉት ክፋታቸው ግን ለሌሎች ሲዘረጋ አይታይም፡፡ በሰሜን ዕዝ ወታደሮች ላይ ግፍ ሲፈጸም፣በማይካድራ ነዋሪዎች ላይ ጭፍጨፋ ሲካሄድ ምዕራባውያኑ በእርግጥም ሰምተው ነበር፡፡ የኤርትራውያን ስደተኞች፣ ሲገደሉና፣ ሴቶቻቸው ሲደፈሩም በትክክል ያውቃሉ ፡፡ ዜጎች ቤትና ንብረታቸው ተዘርፎ ለመከራና ስደት መዳረጋቸውንም አይተው ሰምተዋል፡፡
የመንግሥትን ለውጥ የደገፉ በአደባባይ በጥፋት ቡድኑ ሲገደሉና አካላቸው ለአውሬ ሲሰጥም ከእውነታው አልራቁም፡፡ አሁን ድረስ ለተራቡ ወገኖች እንዲደርስ የሚላክ የእርዳታ እህል ከመንገድ እየታገተ መቅረቱን ጭምር አይተው አረጋግጠዋል፡፡
ምዕራባውያን ሆይ! የእናንተ ዓይንና ጆሮ የሚሰላው ለፍትሐዊ ጦርነቱ ብቻ መሆኑ በእርግጥም ያስገርማል። ዛሬ ስለህጻናት መብትና በጎ ህይወት የሚተጋው አንደበታችሁ ወዴት ሄደ? አሁን እኮ የህወሓት መንደር ህጻናት ከቤታቸው የሉም ፡፡ በርካቶቹ በሱስ ናውዘው፣ መሳሪያ ታጥቀው፣ ጦርሜዳ ውለዋል፡፡ ምስኪን የትግራይ እናቶች በግዳጅ ልጆቻቸውን ለጦርነት እያዋጡ ነው፡፡ የጓዳቸውን እህል የመቀነታቸውን ሳንቲም ለነጣቂዎቹ እያራገፉ ነው፡፡
አዎ! ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም ዝምታ የመምረጣችሁበት ምስጢር ግልጽ ነው፡፡ እናንተ አፍሪካን አንድ የሚያደርግና ነጻነትን የሚሰብክ ቆራጥ መሪን አትሹም፡፡ ከዓመታት በፊት ይህን እውነት በአደባባይ ያሳዩ እነኩዋሜ ኑክሩማንና ቶማስ ሳንካራ በእናንተ የጥፋት ጥርሶች ታኝከዋል፡፡ አገራችን ከሌሎች አገራት ልቃ አንድ እርምጃ እንድትቀድም ፍላጎታችሁ አይደለም፡፡
ዛሬ አፍሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያ የጀመረችውን ግስጋሴ ዕውን ለማድረግ ነጋሪ አያሻትም፡፡ ፈጣን እርምጃዋ ይቀጥላል፣ የልማት ግቧ አይቀንስም። ምዕራባውያን ሆይ! አሁንም ከዚህች ድንቅ አገር እሾሀማ እጃችሁን አንሱ፡፡ የክፋት ልባችሁንም አክሙ።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013