አባይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በቁጭት የሚጠቀስ ወንዝ ሆኖ ኖሯል። ይህንንም በግጥሞች፣ በቅኔዎች፣ በምሣሌያዊ አነጋገሮች ሲገልጹ ነው የኖሩት።
አባይን በታንኳ ሲሻገሩ ባይ፤
በእግሬ ገባሁበት አበሣዬን ላይ።
ከአባይ እስከ አባይ ዱር በሙሉ ሲጓዙ፣
ያገር ዋስ ሆኑና በዳሞት ተያዙ።
ዐባይ በጣና ላይ ሲሻገር አየና፣
ልጄ ጣና ገባ እንደ አባይ ሆነና።
አባይ ኢትዮጵያውያንን ሲጎዳ እንደነበር በቅኔ የተገለፀበት ነው። ከዚህ እንጉርጉሮ ለመውጣትም ኢትዮጵያውያን ብዙ ደክመዋል። ኢትዮጵያውያን በዚህ ታላቅ ወንዛቸው ላይ ግድብ በመሥራት ለመጠቀም ጥናቶች ማሠራት የጀመሩት በንጉሱ ዘመን ቢሆንም ወደ ግንባታ ለመቀየር ግን ብዙ ፈተናዎች አጋጥመው ቆይተዋል። ከፈተናዎቹ መካከል ደግሞ የውጭ ሀይሎች ተጽዕኖ ነው። አባይን ያህል ወንዝ ገድቦ ለመጠቀም ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ለዚያውም የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል። ግብጾች የቅኝ ግዛት ሥምምነቶችን / ለዚያውም ኢትዮጵያ የሌለችባቸውን ሥምምነቶች / በመጥቀስ የውሃው አድራጊ ፈጣሪ እኛ ሲሉ ኖረዋል። በዚህ የተነሣ ኢትዮጵያ ወንዙን ለመጠቀም የምታደርጋቸውን ማናቸውንም ጥረቶች ሲያኮላሹ ኖረዋል።
ኢትዮጵያውያን ይበልጥ ቁጭት ይከታቸው የነበረው አንድም ይኼ ተጽዕኖ ነበር። ኖሮ ኖሮ ግን ቁጭት የወለደው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን ሆነ። ቁጭታቸው ትልቅ አቅም ይዞላቸው ከተፍ አለ። በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም በአፍሪካም በዓለምም ተጠቃሽ ግድብ መሥራት ውስጥ ከገቡ ከ10 ዓመት በላይ ሆናቸው። ይህ ግድባቸው በራሳቸው በኢትዮጵያውያን ሀብት የሚገነባ ነው። የግድቡ ግንባታ መጀመር የአባይ ውሃ ቅኝቱን ቀየረው። እንጉርጉሮው በቃና ተሥፋ ተሠነቀ። የሙሉ ገበየሁ ቅንብር የሆነው እንጉርጉሮ ይብቃ ሥንኞች ይህንኑ ነው የሚያመለክቱት ።
‹‹…እንጉርጉሮ ይብቃ፤ ይገባል ውዳሴ
ጉዞውን ጀምሯል ዓባይ በሕዳሴ
ትውልድ እንደ ጅረት የተቀባበለው
ቁጭት ፀፀት ሥጋት ዛሬ ሊቋጭ ነው
ቁጭት ፀፀት ሥጋት ሀይ ባይ ሊያገኝ ነው…››
የግድቡ ግንባታ ልዩ ልዩ ምዕራፎችን አልፏል። ከምዕራፎቹ አንዱ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት በዚሁ ወር መካሄዱ ይታወሣል። በቅርቡ የተጀመረው የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትም ተከናውኗል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታው የተጀመረው በመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጉባ በረሀ በይፋ በጣሉት መሠረት ነበር። ጉባ ከአዲስ አበባ 800 ኪ.ሜ የሚርቅ ረባዳማ አካባቢ፣ ከሱዳን ድንበር 40 ኪሜ ርቆ የሚገኝ ነው። ሕዳሴ ግድብ ተገድቦ ሰው ሠራሽ ሐይቅ የምናየውና የኤሌክትሪክ ኃይል ከሀገራችን አልፎ ለኢትዮጵያ ጎረቤቶች ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው ከዚሁ አካባቢ ነው።
ግድቡን ለመገንባት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ታስቦ በአሜሪካ ጥናት ተካሂዶ ከተጠናቀቀ በኋላ የዓለም ባንክ ለኃይል ማመንጫ የሚስፈልገውን ገንዘብ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። በወቅቱ ንጉሡ አንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ አቅም ዕውቀት ሲያገኝ ይገነባዋል ብለው ተናግረዋል። የግድቡ ዕቅድም ንጉሡ በብር ላይ ታትሞ እንዲወጣ አድርገው ነበር። እንዳሉት አልቀረም ይኸው ሁለተኛው የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ዘንድሮ ሐምሌን ሣናጋምስ ተገባዶ የምሥራች ሰማን።
እናም “አባይ ማዞሪያ የለውም ግንድ ይዞ ይዞራል” የሚለውን ምሣሌያዊ አባባል፤ አባይ ማደሪያ አለው፤ ማደርያውም ሕዳሴ ግድብ ሆኗል።
የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት አገራችን እንዳታድግ በብሔር፣ በእምነት ልዩነት እየፈጠሩ እርስ በርስ እንድንጫረስ ግንባታ ቆሞ እንደራደር ሲሉ ለነበሩ “ወዳጅ” ተብዬ ሀገሮች እና ባንዳዎች ልፋት ሁሉ ከንቱ መሆኑን ማሣያ ነው።
ኢትዮጵያውን ጉዳቱን እንጂ ጥቅሙን ሣያገኙበት ለዘመናት ፍዳ ሆኖባቸው የኖረው አባይ ፋይዳ ሊያመጣላቸውና ወደ ብልጽግና ሊወስዳቸው እየነጎደ ነው። ግድቡ እውን እንዲሆን የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች፣ ተማሪዎች፣ እናቶች፣ አዛውንቶች፣ ዲያስፖራዎች እና ድርጅቶች ጭምር ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን አሣርፈው ታሪክ ሠርተዋል። በሕዝብ ላብ እየተገነባ ያለ ግድብ ነው።
የአባይን ጉዳይ በግጥም ብለን ዘልቀን አንጨርሰውም፤ እንዲያው ብዙ ከማይታወቁት ግጥሞች እንጠቀስ በሚል ነው። ተረትና ምሣሌው አባይን በጭልፋ እንደሚለው ማለት ነው።
ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ዘመን አይሽሬ በሆነው ሙዚቃዋ የሕዝብን ቁጭት ገልፃበታለች።
የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማነጥፍ – በዘመን የጠና
ከጥንት ከፅንሰ አዳም – ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ – ፈልቆ ከገነት
ግርማ ሞገስ አባይ
አባይ ለጋሲ ነው በዚህ በበረሀ
አባይ – አባይ – አባይ
አባይ ወንዛ ወንዙ
ብዙ ነው መዘዙ
ጂጂ አባይ ወንዛ ወንዙ ብዙ ነው መዘዙ እንዳለችውም ለኢትዮጵያ ተኝተው የማያድሩ ወገኖች የእርስ በርስ ግጭት ሲደግሱልን ኖረዋል። ሕልም ተፈርቶ ሣይተኛ አይታደርም እንደሚባለው፤ ግድቡን ገድበን እንጠቀማለን፤ ገና ለገና ይከሱናል፣ ይወቅሱና ብለን አናቀላፋም፤ በፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ዘንድሮ ድል በድል የሆነችው፤ የኒኩሊየር ማብለያ ሣይሆን ኃይል ማመንጫ የምንገነባ መሆኑን ሚኒስትር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በማስረዳት ሙያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግዳጃቸውን ስለፈፀሙ ነው።
የበረሃው ሲሳይ ትለዋለች፤ ዛሬ ታሪክ የሚቀየርበት ወቅት ላይ ደርሰናል፤ የበረሃው ሲሳይ ማለት የበረሃው ምግብ ማለት ነው፤ ለሱዳንና ለግብጽ፤ ለእኛም ምግብ ሊሆነን አለሁላችሁ ብሎ ፈጣሪም አግዞን የግድቡ ሙሌት ደረጃ በደረጃ እየተፈፀመ ነው፤ ቀጥሎ ደግሞ ኃይል እናመነጭበታለን። የቱሪዝም መስህብ እንፈጥርበታለን፤ ብቻውን እንደ አክሱምና ላሊበላ ሐረርና ጎንደር የቱሪስቶች መዝናኛ መጎብኛ ቦታ ይሆናል።
አባይ ከእንጉርጉሮ ወጥቷል፤ ባለብዙ ውለታ ሊሆን ተቃርቧል፤ ያኔ ደግሞ እንደ ባለብዙ ውለታነቱ ብዙ ሥንኝ ይደረደርለታል፤ ይገጠምለታል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013