ታታሪና ለፍቶ አደር ናቸው ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይ ከባህላዊ የወርቅ ማምረት ስራ ጋር በተያያዘ ስማቸው ጎልቶ ይነሳል ። የባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበር በማቋቋም የክልሉ ተወላጆች በማህበሩ ውስጥ ገብተው እንዲደራጁ በማድረግ ከምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑም አድርገዋል ። ከመሰረቱት ማህበር ከወጡ በኋላም በቤተሰባቸው በመሰረቱት ሌላ የባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበር በኩል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በዋናነት ደግሞ በጉሙዝና ሸርቆሌ ወረዳ አካባቢ በርካቶችን በማህበር አደራጅተው የሙያና ሀብት ድጋፍ በማድረግም ለውጤት አብቅተዋል ። ከትግል ግዜ ጀምሮ እስከ 2004 ዓ.ም በተለያዩ የመንግሥት ሥራዎች ላይ ተመድበው በመስራትም በተማሩበት የትምህርት መስክ ክልላቸውን አገልግለዋል ።
ቤተሰባቸውን በማሰባሰብ ያቋቋሙት ባህላዊ የወርቅ አምራች ማህበር በትንሽ ተነስቶ ዛሬ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ካፒታል እንዲያካብትና ለበርካታ ዜጎችም የሥራ እድል እንዲፈጠር አስችለዋል ። በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ወደ ዘመናዊ የወርቅ አምራች ማህበር ለመሸጋገር በሚያስችለው ቁመና ላይ እንዲገኝም አድርገውታል ። ወርቅን በቀጥታ ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብም አገሪቱ የውጪ ምንዛሪ እንድታገኝም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል ። የገያፅ ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አህመድ መሀመድ።
አቶ አህመድ መሀመድ ውልደትና እድገታቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሸርቆሌ ወረዳ ልዩ ቦታው ጊዘን በሚባል ቦታ ነው ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው በተወለዱበት አካባቢ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተከታትለዋል ። ይሁንና በትጥቅ ትግል ወቅት ለአስራ ሶስት ዓመት ያህል ትምህርታቸውን ካቋረጡ በኋላ በ1991 ዓ.ም እንደገና ካቆሙበት ቀጥለው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረዋል ።
በአዲስ አበባ ከተማ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር እድል በማግኘታቸው እስከ አስረኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል ። የአስረኛ ክፍል የማትሪክ ፈተና ከተፈተኑ በኋላ በመጣላቸው ውጤት በአሶሳ ግብርና ኮሌጅ ገብተው በ2003 ዓ.ም በፕላንት ሳይንስ በዲፕሎማ ተመርቀዋል ። በዛው ዓመትም በግላቸው በአልፋ ዩኒቨርሲቲ የርቀት ትምህርት መርሐ ግብር ተከታትለው በሰው ሀብት አስተዳደር ዲፕሎማ አግኝተዋል ።
ከትግል ግዜ ጀምሮ እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የመንግሥት ስራዎች ላይ የቆዩት አቶ አህመድ፤ በክልሉ የወረዳ ዋና ጸሐፊ በመሆንም አገልግለዋል ። የክልል ምክር ቤት አባልም ሆነው ሰርተዋል ። ለስድስት ዓመታትም በተለያዩ ወረዳዎች የአስተዳደር ሥራዎችን ሰርተዋል ። በመቀጠልም በተማሩባቸው የሙያ መስኮች በመጀመሪያ በቤኒሻንጉል ክልል ሸርቆሌ ወረዳ አስተዳደር በንብረት ጠቅላላ አገልግሎት የሥራ መደብ ለሁለት ዓመት ያህል ሰርተዋል ። በኋላ ላይ ደግሞ በትራንስፖርት አስተዳደር ለሁለት ዓመት ያህል በዛው ወረዳ አስተዳደር ስራ ላይ አሳልፈዋል ።
አቶ አህመድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በወርቅ ሃብቱ የሚታወቅ ቢሆንም ቀደም ባሉት ዓመታት አንድም ጊዜ ሕዝቡ ከሀብቱ ተጠቃሚ ሲሆን አላዩም ። በቀድሞ ጊዜ እንዳውም ሰዎች ከሱዳን መጥተው ወርቁን አውጥተው ይጠቀሙበት እንደነበር መስማታቸውን ያስታውሳሉ ። የሱዳኑ ትልቁ የሜሮይ ግድብ ከቤኒሻንጉል በተወሰደ የወርቅ ሀብት እንደተገነባም በታሪክ ሲነገር አዳምጠዋል።
እነዚህንና መሰል ነገሮችን ሲሰሙና ቁጭት ሲያንገበግባቸው ያደጉት አቶ አህመድ በመጀመሪያ በሸርቆሌ ወረዳ ላይ መልሄር የተሰኘ ባህላዊ የወርቅ አምራች ማህበር መሰረቱ ። ከተለያዩ ቀበሌዎች ሰዎችን በማሰባሰብም ስለማህበሩ ጠቀሜታ ትምህርት ሰጥተው ወደማህበሩ እንዲቀላቀሉ አደረጉ ። ስልሳ አምስት የሚሆኑ ሰዎችን ከመዘገቡ በኋላ ሰላሳ ሰው ጨምረውበት የአባላቱን ቁጥር ወደ ዘጠና አምስት አደረሱት ። ማህበሩ ጥሩ ደረጃ ላይ በመድረሱም ተሽከርካሪም እስከመግዛትም አበቁት። የእነርሱን ማህበር ተሞክሮ በማየትም በአንድ ሳምንት ውስጥ አስራ ዘጠኝ ቀበሌዎች በባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበርነት ተደራጁ ።
አቶ አህመድ በዚሁ ማህበር ውስጥ ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ የማህበሩ አባላት ለሥራ ዝግጁ መሆን ስላልቻሉ ማህበሩን ለቀው በመውጣት ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን በሸርቆሌ ወረዳ ሃልሞ ቤቤ ልዩ ስሙ በምባክ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የራሳቸውን የባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበር በ2007 ዓ.ም አቋቋሙ ።
ማህበራቸው ሥራውን የጀመረው በአስር የቤተሰብ አባላትና በሰባት ሺ ብር መነሻ ካፒታል ሲሆን ወርቅን በባህላዊ መንገድ በጉልበት ያመርት ነበር ። በሂደት ግን በ120 ሺ ብር የድንጋይ መፍጫ ማሽን ገዛ ። እንደገና በ90 ሺ ብር ተጨማሪ ማሽን ደገመ ። በ2009 ዓ.ም የማህበሩ ካፒታል 350 ሺ ብር ሲገባ ከጥቃቅንና አነስተኛ ባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበር ወደ ልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራች ደረጃ ተሸጋገረ ።
ማህበሩ ወደ ልዩ አነስተኛ የባህላዊ ወርቅ አምራች ደረጃ ከተሸጋገረ በኋላ በአሁኑ ጊዜ ወርቅ በማምረት ለብሔራዊ ባንክ ያቀርባል ። እስከ 25 ሜትር ጥልቅ ጉድጓዶችን በመቆፈርም ድንጋይ ያወጣል ። ድንጋዩን በማሽን በመፍጨትም ወርቅ ያመርታል ። አርባ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ጉድጓድ ለሚቆፍሩ 250 ሰዎችም ሌላ የስራ እድል መፍጠር ችሏል ። በተጨማሪም ሴቶችን ጨምሮ ከ500 በላይ ለሚጠጉ የጉልበትና በተመላላሽነት ለሚሰሩ ዜጎችም በተመሳሳይ የሥራ እድል ፈጥሯል ።
በአሁኑ ግዜም ማህበሩ አንድ ትራክተር የገዛ ሲሆን፣ አንድ የጭነት ተሽከርካሪና ስድስት የድንጋይ መፍጫ ማሽኖች አሉት ። ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ምርት የሚሰጡና የማይሰጡ የወርቅ ማውጫ ጉድጓዶችም ባለቤት ነው። ከነዚህ ጉድጓዶች መካከል የሚወጣውን ድንጋይ በመፍጨት እንዲሁም የተፈጨውን ድንጋይ በማጠብና የማጣራት ሂደቱን በመከተል ወርቅን ለይቶ ያወጣል። የወርቁን የካራት ደረጃ እያየም የተለያዩ ዋጋዎች ወጥተውለት ለብሔራዊ ባንክ ይቀርባል ።
ከፍተኛ ካራት ያለው ወርቅ ዋጋው ከፍ ሲል ዝቅተኛ ካራት ያለው ደግሞ ዝቅ ይላል ። ማህበሩ ወርቅ በሚያመርትበት አካባቢ በአብዛኛው የሚገኘው ወርቅም 20 ካራት ያለው ነው ። በ2012 ዓ.ም መጨረሻና በ2013 ዓ.ም መጀመሪያ ማህበሩ የተሻለ የወርቅ ምርት ያገኘ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ሰባት መቶ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ችሏል ። በዚሁ በጀት ዓመት መጨረሻ ደግሞ ስድስት ኪሎ የሚሆን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማስገባት ትልቅ ሪከርድ አስመዝግቧል።
የማህበሩ አጠቃላይ ካፒታል በአሁኑ ወቅት 12 ሚሊዮን ብር ተጠግቷል ። ወደ ዘመናዊ ወርቅ አምራች ደረጃ የሚሸጋገር ከሆነም ከዚህ የበለጠ ወርቅ ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል። በ2014 ዓ.ም በኪራይም ቢሆን ስካቫተርና ማጠቢያ ማሽኖችን ጨምሮ ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም ወርቅን በዘመናዊ መልኩ በማምረት ምርቱን የማሻሻል እቅድ እንዳለው ይናገራል። ሙሉ በሙሉ ወደ ዘመናዊ ወርቅ አምራች ደረጃ ለመሸጋገር እቅዶ እየሰራም ይገኛል ። ከክልሉ አስተዳደርና ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመሆን ወርቅን በዘመናዊ መልኩ ለማምረት የሚረዱ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ጥረት በማድረግ ላይም ሲሆን በቀጣዩ አምስት ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደ ዘመናዊ የወርቅ አምራች ደረጃ የሚሸጋገር ከሆነና ቆፋሪ ካገኘ በየዓመቱ ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርበውን የወርቅ መጠን ከ20 እስከ 30 ኪሎግራም የማሳደግ ውጥን አለው።
ቀደም ሲል በሌላ ማህበር ውስጥ ሲሰሩ የነበረውን ሁኔታ አሁን ካለው የራሳቸው ማህበር ጋር ሲያነፃፅሩት የምድርና የሰማይ ያህል ልዩነት እንዳለው የሚገልፁት አቶ አህመድ፤ በአሁኑ ግዜ ራሳቸውን ጨምሮ የቤተሰባቸውን ህይወት በእጅጉ ማሻሻል እንደቻሉ ይናገራሉ ። አንድ ልጃቸውን አስተምረው እንዳስመረቁና አንድ ሌላ ልጃቸውን ደግሞ ዩኒቨርሲቲ አስገብተው እያስተማሩ እንደሚገኙም ይገልፃሉ። ሌሎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሴት ልጆች እንዳሏቸውም ይጠቅሳሉ።
ቀደም ሲል ከጥቃቅንና አነስተኛ እስከ ልዩ አነስተኛ የባህላዊ ወርቅ ማምረት ደረጃ በመስራት በተለይ ወርቅን በቀጥታ ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ የውጪ ምንዛሪ እንዲገኝ በማድረግ ከራሳቸው አልፈው አገራቸውን መጥቀም እንደቻሉ የሚናገሩት አቶ አህመድ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘም የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በያዝነው አመት ባዘጋጀው የእውቅናና ሽልማት ፕሮግራም እርሳቸውም ተሸላሚ እንደነበሩ ያስታውሳሉ ። ይህም ለበለጠ ትጋትና ጥረት እንዳነሳሳቸው ይጠቁማሉ።
ሰው በሁሉ ነገር ወሳኝ ከሆነ የማይቻል ነገር እንደሌለ ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት የሚናገሩት አቶ አህመድ፤ መጀመሪያ ላይ በመሰረቱት የባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበር ሲሰሩ ትልቅ ትምህርት ማግኘታቸውንና በርካታ ውጣውረዶችም አጋጥመዋቸው እንደነበር ይገልፃሉ ። በተለያዩ የክልሉ ዞኖች በመንቀሳቀስም ከወርቅ ማምረት ሥራ ጋር በተያያዘ ለሌሎች ትምህርት በመስጠት በማህበር የተደራጁ ሰዎች እንዳሉም ይጠቅሳሉ ።
ከራሳቸው ልምድና ተሞክሮ በመነሳት በጉሙዝ አካባቢ በርካታ ማህበራት በባህላዊ ወርቅ ማምረት ስራ እንዲደራጁ ማድረጋቸውንም ይናገራሉ ። እርሳቸው ባሉበት ሸርቆሌ ወረዳ አካባቢም ለአነስተኛ የባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበራት የሃሳብና የሀብት ድጋፎችን እያደረጉ እንደሚገኙም ያስረዳሉ ። በዚህም በርካቶች ራሳቸውን ወደመቻል ደረጃ እንደተሸጋገሩም ይጠቁማሉ። ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም መትረፍ እንደቻሉ ይናገራሉ ።
አቶ አህመድ ራሳቸውን ለመለወጥ ብዙ ጥረዋል። እውቀታቸውን ለማሻሻልም የተለያዩ ትምህርቶችን ተምረዋል ። የክልላቸው ሕዝብ የወርቅ ሀብት ቢኖረውም እስከዛሬ ድረስ ሳይጠቀምበት በመቅረቱ ቢያንገበግባቸው ማህበር አቋቁመው ወርቅን በባህላዊ መንገድ ለማምረት ተነስተዋል ። በዚህም ተሳክቶላቸው በርካቶች በማህበር ተደራጅተው ወርቅን በባህላዊ መንገድ በማምረት ውጤታማ እንዲሆኑ አድርገዋል ። በራሳቸው ቤተሰብ የፈጠሩት ባህላዊ የወርቅ አምራች ማህበርም ከአነስተኛና ጥቃቅን ተነስቶ ዛሬ ላይ ወደ ዘመናዊ የወርቅ አምራች ማህበር ለመሸጋገር ከጫፍ ደርሷል ።
እኛም አቶ አህመድ ጥረው ግረው ዛሬ ላሉበት ደረጃ የበቁበትን ሂደት በማድነቅ ሌሎችም ከእርሳቸው ህይወት በመማር ከፍ ወዳለው ደረጃ መድረስ እንደሚችሉ በዚህ አጋጣሚ መጠቆም እንወዳለን። ሰላም!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2013