የበጎ ፈቃድ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጠውና በአገልግሎቱም ጥራትና ተደራሽነት አንፃር ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባሳዩት የበጎነት ልብ እና ተሳትፎ ምክንያት ሌሎች አመራሮችም ለተግባሩ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ሰፋፊ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኙ የሚታይ ነው፡፡ ይሁንና ከተለመደው የበጎ ፈቃድ ተግባር ባሻገር ዘመናዊ በሆነ መልኩ በጎነትን ለመከወን በሚያስችል መልኩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ትስስር መረብ ዲጂታል ቮለንተሪዝም የተሰኘ ልዩ የበጎ ፈቃድ እድል ኢንስፓየርድ ኢትዮጵያ ዮዝ አሶሴሽን ለህብረተሰቡ ይዞ መጥቷል፡፡ አሶሴሽኑ ከበጎ ፈቃደኝነት በዘለለ ወጣቱን በአዕምሮ የማጎልበት ስራዎች ላይም የነቃ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ለዚህም የእውቀት ኮንሰርት ዝግጅት ተጠቃሽ ነው፡፡ የአሶሴሽኑ መስራችና መሪ ከሆነው ወጣት ልዩነህ ታምራት ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢንስፓየርድ ኢትዮጵያ ዮዝ አሶሴሽን ምን ምን ስራዎችን ለማከናወን ተመሰረተ?
ወጣት ልዩነህ፡– በዚህ ማህበር ስር ብዙ ስራዎች የሚከናወኑበት ሲሆን በዋነኝነት አላማ አድርጎ የያዘው አዕምሮ የታደሰ ወደፊቱን የታለመ ባለ ራዕይ ወጣቶች እንዲፈጠሩ መስራት ነው፡፡ የሚለውጥና ወጣቱን ለተሻለ ነገር የሚያነሳሱ እሳቤዎችን እየፈጠረና እያሳተፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ተነሳሽነት ፕሮግራም ሲሆን ወጣቱ በመማርና በመለማመድ መሪነትን እንዲሰለጥኑ ወደ ፊት ኢትዮጵያን የሚረከቡ ወጣቶች የተማሩና የተለማመዱ እንዲሆኑ በበጎ ፈቃድ ላይ ወጣቶች የመሪነት ተነሳሸነት መፍጠር በሚል ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም ከሁለት ሺህ በላይ ወጣቶች ተሳትፈው አሁን በበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴዎች ላይ እየተሳተፉ ናቸው፡፡
ሁለተኛው ስራ ደግሞ የወጣቶች ትስስር (ዮዝ ኔትወርክ ኢትዮጵያ) ሲሆን በዲጅታል ወጣቱ በየትኛውም የአለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በበጎ ፈቃደኝነት እንዲሳተፉ የምናነቃቃበት መርሃ ግብር ነው፡፡ በዚህም ወጣቶች ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ በአነቃቂ ስልጠናና በዲጅታል ስራዎች አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ እንዲሁም በራስ ማብቃት ዙሪያ ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን የማማከርና ሌሎች ስልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡ በነዚህ ውስጥ 12 ሺህ 850 የሚሆኑ ወጣቶች ይሳተፉበታል፡፡ በዚህ በዲጅታል እንቅስቃሴ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ወጣቶች እየተሳተፉ ኢትዮጵያዊነትን በሰላምና በአብሮነት አንፃር እየተሰራ ይገኛል፡፡
የእውቀት ኮንሰርት ወጣቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው የተማሩትም የበቁትን በተግባር መሬት ላይ ለማውረድ እውቀቱ መድኃኒትና ብርሃን እንዲሆን የምናነቃቃበት ወይም ደግሞ እውቀቱ ለውጥ እያመጣ ነው የሚለውን የሚያይበት እድል የተፈጠረበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህም ‹‹እውቀት ያዝናናል›› በሚል መሪ ሀሳብ እየተሰራ ሲሆን እውቀት ጭንቀት የሚሆንባቸውን ወጣቶች እውቀት ብርሃን እንዲሆን የስኬት ስልጠና ይሰጣል፡፡ እውቀት ለህብረት፣ ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለአንድነት መሰረት ነው በሚል በሚያዝናና መልኩ ለህብረተሰቡ እየቀረበ ይገኛል፡፡ የሰላማዊ እውቀት ለአብሮነት የሚጠቅም ሲሆን ኢትዮጵያዊ እውቀትን በማጎልበት ለወጣቱ በእውቀት ኮንሰርት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
የእውቀት ኮንሰርት በግሌ ለራሴ ለአገሬ ያቀረብኩት ነው ብዬ አስባለው፡፡ የእውቀት ኮንሰርት ሁሉም ሰው አለኝ የሚለውን እውቀት ወይም በተመረቀበት ዘርፍ ዝም ብሎ ከሚቀመጥ እውቀቴ መድኃኒት ሆኗል ወይ፣ እውቀቴ ለውጥ አምጥቷል ወይ፣ እውቀቴ ለአገሬ ለቤተሰቤና ለራሴ መፍትሄና ብርሃን ሆኗል ወይ የሚለውን የሚለካበት ነው፡፡ በኮንሰርቱ የተለያዩ ሰዎች መጥተው ምን ላይ ለውጥ እንዳመጡ ለታዳሚው ያቀርባሉ፡፡ ሌላው በኮንሰርቱ የሰው እውቀት የሚባሉ ማለትም የተማረም ያልተማረም የሚኖራቸው እውቀት ለሰላምና ለአንድነት የሚኖራቸውን ጥቅም ማስገንዘቢያ ይሰጥበታል፡፡ ይህ ሁኔታ ሰዎች ከሚሰጧቸው ተቀፅላዎች ማለትም የብሄርና የሃይማኖት ሁኔታዎች በመተው ሁሉም በኢትዮጵያዊነት ክብር ተዋደውና ተፋቅረው በሰላምና በአብሮነት የሚቀራረቡበትና የሚዋደዱበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ሌላው እየሰራሁት ያለው የዲጅታል በጎ ፈቃደኝነት ስራ ነው፡፡ ይህ ስራ በአገሪቱ የመጀመሪው ሲሆን ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ስራ እንዲሳተፉ ያደርጋል። በዚህም 13 ሺህ ወጣቶችን በማሳተፍ ኢትዮጵያን እናልብሳት በሚል በመርሃ ግብር ላይ ለማሳተፍ ታስቧል፡፡ በዚህም የጊዜ ገደብ ሳይኖር ከየትኛውም ቦታ ሆነው በበጎ ፈቃድ ስራ ላይ እንዲሳተፉ የዲጅታል ፕላትፎርም ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ፕላትፎርም ከየትኛውም አገር ሆነው ወጣቱ ተሳትፎ ማድረግ ይችላል፡፡ በዚህም ላይ ብዙ ወጣቶች ተሳትፎ እያደረጉ ሲሆን ልምዳቸውን እየተካፈሉ ይገኛሉ፡፡
ድርጅቱ በማህበራዊ ትስስሮች ላይ የሚገኙ አላስፈላጊ ነገሮችን ‹‹ድረገፄን አጥባለው›› የሚል ዘመቻ በመክፈት በማህበራዊ ሚድያዎች ላይ የርስበርስ ግጭት የሚፈጥሩ አላስፈላጊ ሰዎችና ገፆችን ማስወገድ ላይ ያተኩራል፡፡ ስለ አገሬ መልካም ሀሳብና ንግግር አለኝ የሚል ማህበረሰብ ለመፈጠር ታልሞ እንቀስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ሁሉም ህብረተሰብ ማህበራዊ ሚዲያዎቹን ካለስፈላጊ ነገሮቸ ማፅዳት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡– በበጎ ፈቃደኝነት ዙሪያ የወጣቱ ተሳትፎ እንዴት ይታያል?
ወጣት ልዩነህ፡– አሁን ባለው ሁኔታ እኛ በያዝነው የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ወጣቶች እየጎረፉ ይገኛሉ፡፡ የመጡት ወጣቶች በጣም ደስተኛ ናቸው። በሙሉ ፈቃዳቸው የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ የሚተጉ ናቸው፡፡ በጣም ከፍተኛ ተነሳሽነትና ፍላጎት አላቸው፡፡ እንዴትና መቼ በምን አይነት ሁኔታ መሳተፍ አለባቸው የሚለው ጉዳይ ቢመቻችላቸው ከፍተኛ የሆነ ተነሳሽነት ያለው ወጣት በብዛት አለ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ በመንግስትና በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ድርጅቶች አንፃር ህብረተሰቡ ጊዜውና ሀሳቡ በበጎ ፈቃድ ለመሳተፍ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተነሳሽነት ያሳየበት ሁኔታ አለ፡፡
የኢለመንተሪና የሀይስኩል ተማሪዎችን ከማስጠናት አንፃር በርካታ በጎ ፈቃደኞች የተሰማሩ ሲሆን በዲጂታል ቮለንተሪዝም አንፃር ቤተሰብ፣ ተማሪው፣ አስጠኚው የሚካተቱበት ይሆናል፡፡ ይህንንም በማድረጋችን በክረምት ወቅት ከፍለው የትርፍ ጊዜ የትምህርት ድጋፍ ማግኘት ለማይችሉ ወገኖቻችን እንደርሳለን። ወጣቶች ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎችን እንዲሁም አለም አቀፋዊ ቋንቋዎችን መማር አስፈላጊ ነው እንላለን፡፡ ቋንቋዎች የሚያቀራርቡን የሚያስማሙን የሚያዋድዱን እንጂ የሚያጣሉን መሆን የለባቸውም፡፡ በዚህ ሀሳብ የተነሳው የኢትዮጵያ ወጣቶች ትስስር መረብ በዲጂታል ቮለንተሪዝም የቋንቋ ስልጠናዎች በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይም በታቀደው የክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃግብር ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎችን በስፋት በመማር ሀገራዊ አንድነትና ሰላም ላይ የበኩላችንን አሻራ እናበረክታለን፡፡
በኢትዮጵያ ወጣቶች ትስስር መረብ የዲጂታል የበጎ ፈቃድ ሂደት ውስጥ ሌላው እና ዋነኛው በበጎ ፈቃድ ልንሰጥ የተዘጋጀነው የአዕምሮ ውቅር እና የአመለካከት ለውጥ ስልጠና እንዲሁም የግል ስብዕና ግንባታ ስልጠናዎች ነው፡፡ በዚህ የሁለት ወር የክረምት የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ በዲጂታል አኳኋን ወጣቶችን፣ ህብረተሰባችንን ከላይ የተዘረዘሩትን ስልጠናዎች እንሰጣለን፡፡ የሴቶች ማጎልበት (ወይም ሴትን ማጎልበት የተሰኘው ስልጠና) ሴቶችን የማብቃት ሂደት ነው፡፡ የሴቶችን አመለካከት ለውጥ ላይ መስራት አቅማቸውን ማጎልበት በትምህርት፣ በግንዛቤ፣ በማንበብ እና በስልጠና ከፍ ማድረግን ጨምሮ በበርካታ መንገዶች በመጠቀም በተለይም ልምዱን ዝግጅቱ ባላቸው በጎ ፈቃደኞች ሴቶችን የማጎልበቻ ስልጠና እንዲሁም የማማከር ስራን እንሰራለን፡፡ ሴቶችን ማጎልበት ሴቶች ሕይወትን የሚወስኑ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– የእውቀት ኮንሰርቶች ሲዘጋጁ ብዙ አላማ ይዞ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ላይ የሚስተዋሉት ችግሮች ምንድን ናቸው?
ወጣት ልዩነህ፡– በመጀመሪያ እውቀት የመረጃ ጥርቅም ነው ይባላል፡፡ እኛ ደግሞ ያልተተገበረ እውቀት በመረጃ ላይ የቀረ እንጂ ወደ ተግባር የወረደ አይደለም ብለን እናምናለን፡፡ ሰዎች ክፍተታቸውን ሲያዩ በጣም ደስተኛ ይሆናሉ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ተስፋ ሰንቀው ነገ ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚደርሱ ትልም ያስቀምጣሉ። አሁን በእውቀት ኮንሰርት እየተሰራ ያለው ሰላማዊ፣ ባለራዕይ፣ ስኬታማ፣ አብሮነትን የያዘ ህብረተሰብ ለመገንባት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ወጣቱ ትውልድ በጣም በደስተኛነት እየተከታተለ ነው፡፡ ከዳንስና ከጭፈራ በተለየ እውቀትን በኮንሰርት ማቅረብ ወጣቱን ይስባል ወይ ቢባል መልሱ አዎ ነው፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ወጣቱ እየተሳተፈ ሲሆን በኮንሰርቱ የሚቀርቡ ፕሮግራሞችን በአፅንኦት እየተከታተለ ይገኛል፡፡ የእውቀት ኮንሰርትን በሬድዮ ፕሮግራምነት እየተዘጋጀ ሲሆን ብዙ ወጣቶች እየተከታተሉት ይገኛል፡፡ በክልል የሚገኙ አድማጮችም የእውቀት ኮንሰርቱ ወደ እነሱ እንዲመጣ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ስራ የተስተዋለው ነገር ወጣቱ ለውይይት ፍላጎት እንዳለው የታየበት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በወጣቱ ዙሪያ ማህበሩ ላለፉት አስር ዓመታት የስብዕና ስልጠና ሲሰጥ ነበር፡፡ በዚህ ስራ ወጣቱ ላይ ምን ለውጦች ታይተዋል?
ወጣት ልዩነህ፡– ማህበሩ በበጎ ፈቃደኝነት ላይ ስራዎችን ሲጀምር ወጣቱ የሚወዱት የሚፈልጉት ከፍተኛ እንቅስቀሴ ነበር፡፡ ለአገራቸው በማንኛውም መስክ አስተዋፅኦ ለማድረግ ፍላጎት ስለነበራቸው ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በየጊዜው ቦታውን እየቀየረ ደረጃውንም እያሳደገ አሁን በተደራጀ መልኩ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ስራው ዘመናዊ በሆነ መንገድ የሚከናወን ሲሆን ብዙ ለውጦች ማምጣት ተችሏል፡፡ በስራው የሚሳተፉ ሰዎች እየጨመሩ ሲሆን የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ እየሠፋ ይገኛል፡፡ ለውጡ አዎንታዊና ለውጥ ያመጣ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ወጣቱ አሁን ባሉት የበጎ ስራዎች ይሁን እሱን በሚፈልጉ ዘርፎች ላይ በምን አይነት መንገድ መሳተፍ አለበት?
ወጣት ልዩነህ፡– በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት በስኬት ያጠናቀችበት ጊዜ ነው፡፡ አገሪቱ ጨለማ የሚመስል ነገር ውስጥ የሆነች ብትመስልም እየነጋላት ይገኛል፡፡ አሁን ወጣቱ ተስፋ ያለው መሆን አለበት፡፡ ተስፋ ያለው ሰው ደስታና ሰላም ይኖረዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ደስተኛና ሰላማዊ መሆን ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አገሪቱ ተስፋ ያለው ሰው እንዲኖራት ማድረግ ይገባል፡፡ በመንግስት ደረጃ በህብረተሰቡና በወጣቱ እየተደረገ ያለው ደስ የሚል፣ የሚበረታታና የሚደነቅ መስመር የያዘ ነገር እየተሰራ ነው፡፡ ከወጣቱ የሚጠበቀው ነገር የተቀመጠውን ራዕይና አላማ በአወንታዊነት ተቀብሎ መከታተልና መደገፍ አለበት፡፡ በተጨማሪም ከመንግስት ጎን ሆኖ መስራት ይገባል፡፡
አሁን ላይ ችግሮች ላይ በማውራትና በመፍራት ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ አስፈላጊው ነገር የሚጠቅመንን ሊያንፀን የሚችለውን እንደ ማህበረሰብ አንድ የሚያደርጉንን ሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከመንግስት ጎን መቆም ይገባል። አገሪቱ ላይ ያሉት ችግሮች ይታወቃሉ፡፡ ችግሮቹን መንግስት ይፈታቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም ወጣቱ በአወንታዊነት መሳተፍ ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ለሰጠኸን ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ወጣት ልዩነህ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2013