
የኢድአልአድሃ ወይም የአረፋ በዓል በእስልምና ሀይማኖት ከሚከበሩ ሶስት ታላላቅ በዓላት አንዱ ነው። የእስልምና እምነት እንደሚያስተምረው ዐረፋ የሚለው ቃል በዐረብኛ “አወቀ” እንደማለት ነው። ይህም ታሪክ አለው። አዳምና ሔዋን ወይንም አደምና ሃዋ ከጀንነት ወደ ምድር ከወረዱ በኋላ ለብዙ ዘመናት ተጠፋፍተው ነበር። ለረጅም ጊዜ ሲፈላለጉ ከቆዩ በኋላ በዚህ ዕለት በሳዑዲ ዐረቢያ ባለው የአረፋ ተራራ ላይ ተገናኙ። እዚያም “ዐረፍቱከ… ዐረፍቱኪ” ተባባሉ። “አወቅኩህ! አወቅኩሽ” ማለታቸው ነው። ይህንን ታሪክ ለመዘከር ሲባል ነው የዐረፋን በዓል ማክበር የተጀመረው” ይህ በዙልሂጃ ዘጠነኛው ቀን የሚከበር በዓል ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢድ አል አድሃ ወይም አረፋ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን በአላህ ትእዛዝ ለመስዕዋት ሲያዘጋጁ በምትኩ ሙክት በግ መቅረቡን የሚያስታውስ በመሆኑ የመስዋዕት በዓል ተብሎም ይከበራል።
ኢድ አልአድሃ የመተሳሰብና የመረዳዳት በዓል ከመሆኑም ባሻገር ሙስሊሞች የመስዋዕትነት በዓሉን እርድ በመፈጸም፣ በጋራ በመጸለይ እና ከፈጣሪ ምህረትን የሚያስገኙ በጎ ተግባራትን በማከናወን ያሳልፉታል።ይህም ያጡ ወገኖች የሚደገፉበትና መረዳዳትና መደጋገፍ የሚታይበት በመሆኑ በዓሉ የተለየ ገጽታ ይዞ ይከበራል።
ኢድ አልአድሃ የነብዩ ኢብራሂምና ልጃቸውን የእስማኤልን ታሪክ መነሻ በማድረግ ኢድ ይከበራል። በዓሉ የመስዋዕት፣ የእርድ በዓል ነው። በተለይም የሐጅ ጸሎት የሚፈጽም ሰው በዚህ ቀን ከብት የማረድ ግዴታ አለበት። የተቀረውም ሙስሊም ዕለቱን አቅሙ በፈቀደ ከብት በማረድ ከቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ጋር ያሳልፈዋል። ለኢድ አል አድሃ አንድ ሰው ከሚያርደው ከብት ሲሶውን ብቻ ለራሱ እንዲወስድ ነው ደንቡ። የተቀረው ሲሶው ለዘመድ አዝማድ፣ ሲሶው ደግሞ አቅም ለሌለው ደሃ እንዲከፋፈል እስልምና ያዛል።
ይህንንም መሰረት በማድረግ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች በበዓሉ ዕለት ሰዎች ድሃ ጎረቤቶቻውን ይዘይራሉ፤ ያላቸውን ያቋድሳሉ፤ የታረዙትን ያለብሳሉ፤ የተጠሙትን ያጠጣሉ። በተለይም ወላጅ አልባ ሕጻናት ከፍተኛ ትኩረትና እንክብካቤ ያገኛሉ። ስለዚህም በዓሉን ተደስተው ያሳልፋሉ።
ከዚሁ ጎን ለጎንም በበዓሉ ዕለት ሙስሊሞች ክርስቲያን ጎረቤቶቻቸውን በመጥራት እና ማዕድ በመቋረስ በዓሉን በድምቀት ያሳልፋሉ። ስለሀገራቸው ሰላምና አንድነት ይጸልያሉ፤ እብሮነታቸውንም ያጠናክራሉ።
አረፋ የአብሮነት በዓል ነው፡፤ በአረፋ በዓል ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ በዓሉን በጋራ ያሳልፋል፤ አብሮነት ይደምቃል። ከዚህ በሻገር ግን ከጥንት በኢትዮጵያ ያለው የአረፋ በዓል አከባበር ለየት የሚልባቸው እሴቶች አሉት። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችን በጻጋ የተቀበለችና የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ተከባብረው የሚኖሩባት የተለየች ሀገር ነች። አረፋን በመሳሰሉ የበዓል ወቅት ደግሞ በክርስትና በዓላት እንደሚደረገው ሁሉ የክርስትና አምነት ተከታዮች የሆኑ ጎረቤቶችን በመጥራት በዓሉን በጋራ ማሳፍለፍ የተለመደ ነው። ይህ አንዱ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ሲሆን ለዘመናትም ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ የደረሰ ድንቅ መገለጫችን ነው።
ነብዩ ኢብራሂም በእስልምና ሀይማኖት በነበራቸው አስተምህሮት የሰው ልጆች ያለ ዘርና ሃይማኖት ልዩነት የምድር ፍጡራን ሁሉ እኩል መሆናቸውን ሲያስተምሩ የቆዩ በመሆኑ ዛሬ በዘር፤ በጎሳና በኃይማኖት ልዩነት እየተናጠች ለምትገኘው ሀገራችን አስተምህሮቱ ከፍተኛ ትምህርት ይሰጣል። ሕዝበ ሙስሊሙም ልዩነትን፤ መገፋፋትና መወቃቀስን በማስወገድ ለሀገሩ አንድነትና ሰላም የሚሠራበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሚገኝ መረዳት አለበት።
በተለይም ነብዩ ኢብራሂምና ልጃቸው እስማኤል ያሳዩት ታዛዥነት ለዛሬው ትውልድ ከፍተኛ ትምህርት ይሰጣል። ታናሽ ለታላቁ ታዛዥ መሆን አለበት፤ ሕዝብ ለመሪዎች ታዛዥ መሆን አለበት፤ ምዕመናን ለኃይማኖት አባቶች ታዛዥ መሆን አለባቸው። ይህ ሲሆን ፉክክር ይጠፋል፤ በምትኩም መተዛዘንና መረዳዳት ይነግሳል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት አንዱ የበዓሉ ዕሴት ነው። የእስልምና እምነት ድሆችን ማብላትና ማጠጣት እንዲሁም በዓላትን እኩል በደስታ እንዲያሳልፉ በአማኞች ላይ ግዴታ ጥሎባቸዋል።ከእነዚህ ትዕዛዞች አንዱ ያጡና የተቸገሩ ወጎኖች መርዳትና መደገፍ አንዱና ዋነኛው ነው።
የእምነቱ ተከታዮች በዓላትን እራሳቸው ብቻ ተደስተው እንዲያሳልፉ አይፈቀድላቸውም።ይልቁንም በዓላት ድምቀት የሚኖራቸውና በፈጣሪም ዘንድ ተቀባይነትን የሚያጎናፉት ከተቸገሩ ወገኖች ጋር አብሮ ማሰላፍ ሲቻል ነው።ስለዚህም ሙስሊሞች የአረፋ በዓልን ሲከብሩ ለተቸገሩ ወገኖች ማዕድ ከማጋራት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ሊሆን ይገባል።
በአረፋ መረዳዳትና መደጋገፍ ቢስታውልም በዚህ ወቅት ሚስተዋለው መደጋገፍ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚከናወን ተግባር ሊሆን ይገባል። የደካሞችን ቤት በማደስ፣ ለጦም አዳሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን ማቅረብ ፤የታረዙትን ማልበስና ወላጅ አልባዎችን መጎብኘት በኢድ አልአድሃ የሚወደድ ተግባር ቢሆንም በሌሎችም ቀናት እነዚህ በጎ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው ናቸው።
ማኅበረሰቡ በበዓል ወቅት ከመረዳዳት ባሻገር ሀገራዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በጋራ መቆምም ይጠበቅበታል።ሰዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ጉዳት ሲደርስባቸው፤ ከአካባቢያቸው ሲፈናቀሉ፤ ሲራቡና ሲጠሙ ዝም ብሎ መመልከት ከእስልምና አስምሮ አንጸር የሚያስጠይቅ ነው።በተለይም ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት በርካቶች ቤት ንበረታቸውን ጥለው የተሰደዱበትና የተፈናቀሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህም የኢድ አልአድሃ በዓልን ስናከብር እነዚህን ወገኖች በመጎበኝነትና ወገናዊ ፍቅር በመስጠት ሊሆን ይገባል።
ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፎ ሌሎች ወገኖችን መቀበል እና መርዳት ጭምር ያውቁበታል። ታሪካቸውም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
ኢትዮጵያ ስደተኞችን የመቀበል ታሪኳ የሚጀምረው ከመካ ተሰደው የመጡ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ተቀብላ ከማስተናገዷ ጋር በተያያዘ ነው። ነብዩ መሃመድ የእስልምና እምነትን ለማስፋፋት ሲነሱ በመካ የነበሩ የባዕድ እምነት ተከታዮች ተቃውሟቸው እስከማሳደድና የአማኞችንም ሕይወት እስከማጥፋት የደረሰ ነበር።
በዚህ የጭንቅ ወቅት ነብዩ መሃመድ ተከታዮቻችን ለሁለት ጊዜ ያህል ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ከባዕድ አማኞቹ ጨካኝ በትር ማዳን ችለዋል። ይህን ዓለም አቀፋዊ መልዕክት መሠረት ለመጣል በወቅቱ እንደ ሀገር፤ እንደ መንግሥትና እንደ ሕዝብ መስዋዕትነት የከፈለ ከሐበሻ በቀር ማንም የለም።
ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ሐበሻን ‹‹የእውነት ምድር» ብለዋታል፣ ይህ አባባል ምንም እንኳ መካ የተከበረው የአላህ ቤት የሚገኝበት ቢሆንም በወቅቱ ፍትህና እውነት ስለጠፋ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) እና ተከታዮቻቸው ለስቃይና ችግር ተጋልጠው ነበር። የሚፈለገው ፍትህና እውነት ግን በሐበሻ መሬት በጊዜው ተግባራዊ መሆን ችሏል። ስለዚህ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ሲታገሉለት የነበረው ፍትህና እውነት ከመካ ከ16 ዓመት በፊት በሐበሻ ምድር ተረጋግጦ ነበር። ለዚህ ነው ሐበሻ የፍትህና የእውነት ምድር በመሆን መካን የቀደመችው።
ከኢትዮጵያውያን አስደናቂ ስብዕናዎች አንዱ የስደተኞችን ባሕል እና ኃይማኖት አክብረው እንዲኖሩ መፍቀዳቸው ነው። ቀደም ሲል ከመካ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ስደተኞች ከሐበሻ ጋር ቋንቋ፣ ብሔር፣ ባሕል፣ ወግ፣ ቀለም የተለዩ ቢሆኑም ባደረጉት የ16 ዓመት ቆይታ፤ በእነሱ ላይ የተፈፀመባቸው ግፍም ሆነ በደል ፈፅሞ አልነበረም። እምነታቸውን በነፃነት ተግባራዊ እያደረጉ ከመንግሥትም ሆነ ከሕዝቡ አስፈላጊ ድጋፍ፣ ድጐማና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መቆየት ችለዋል።
የስደት ቆይታቸውን ጨርሰው እስከሚመለሱ ድረስ ከነሱ ውስጥ አንድም ቅሬታ ያቀረበ ስደተኛ አልነበረም። እንዲያውም ለሐበሻ ምድር፣ ለንጉሱና ለሕዝቧ ከፍተኛ ፍቅርና ክብር ነበራቸው። ባሕል እና ኃይማኖታቸው ተከብሮላቸው በመኖራቸው ሁልጊዜም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍ ያለ ክብር አላቸው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማኖርና እምነታቸውንም በነጻነት እንዲያከናውኑ በማድረግ ደማቅ ታሪክ ያላት ሀገር ነች። የአይሁድ፤ የክርስትና እና የእስልምና ኃይማኖቶችን ተቀብላ በአንድትና በወንድማማችነት በሀገራቸው እንዲኖሩ ያደረገች ድንቅ ሀገር ነች።
የኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት ዘመን የማይሽረው ነው። ዛሬም ድረስ የተለያዩ ሀገራት ሲቸገሩ የሚመጡት ወደ ኢትዮጵያ ነው። የጎረቤት ሀገራትም ሆኑ የሩቅ ሀገራት ግጭት፤ ጦርነት እና ስደት ሲያጋጥማቸው የሚመጡት ወደ ኢትዮጵያ ነው። ከኢትዮጵያ የተሻለ ሀብት እና የኑሮ ደረጃ ያላቸው እና ሊያሳድዷቸው የሚችሉባቸው የቅርብ ሀገራት እያሉ በርካታ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ምርጫቸው የሚያደርጉት ኢትዮጵያን ነው።
የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ኢትዮጵያን የሚመርጡት ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ ነው። ከዚህም በሻገር ማንኛውም ስደተኛ ባሕሉ እና እምነቱ ተከብሮለት የመኖር መብት የምትሰጠው ኢትዮጵያ ብቻ ነች። ሌሎች ሀገራት በቂ ሀብት ቢኖራቸውም መጀመሪያውኑ ስደተኞችን የመቀበል ፍላጎት የላቸውም። ቢያስገቡ እንኳን የስደተኞችን ባሕል እና እምነት እንዲሁም የተለያዩ የአኗኗር ዘይቤዎችን ማክበር ይሳናቸዋል።
እንደመንግሥትም የኢትዮጵያ መሪዎች ለስደተኞች ልዩ ክብር ይሰጣሉ። ከራሳቸው ዜጋ ባልተናነሰ መልኩ እንዲኖሩ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ። የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፤ ስደተኞች በሰላም እንዲኖሩም ጥበቃ ይደረግላቸዋል።
ኢትዮጵያ ለብዙዎቹ ሀገራት የጭንቅ ጊዜ መጠለያ ናት። ከ25 ዓመታት በፊት ሶማሊያ ውስጥ ባጋጠመው ግጭት በርካታ ሶማሊያውያን ለስደት ተዳርገው ነበር። ሕዝቡ የፈለሰው ወደ ሳኡዲ፤ የመን ወይም ጅቡቲ አይደለም። ወደ ኢትዮጵያ ነው። በአሁኑ ወቅትም በሱዳን ፤ በደቡብ ሱዳን ባለው ግጭት እና ጦርነት መጠጊያ የሆነችው ኢትዮጵያ ነች።
ሱዳን በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር የድንበር ውዝግብ አላት። ሆኖም በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ ሀገራት ሲቸገሩ፤ በጦርት እና በግጭት ሲጎዱ ተቀብላ ታስጠልላለች እንጂ ስደተኞችን አልቀበልም አትልም። ወይም ደግሞ ሀገራት ሲቸገሩ የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ ሙከራ አታደርግም። በሥነምግባር የታነጻ ሕዝብ እና መንግሥት ያላት ጥንታዊ ሀገር በመሆኗ የምትፈጽማቸው ድርጊቶች በከፍተኛ ስብዕና የሚገለጽ ነው።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር አላት፤ በዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ሁኔታ ምክንያት የኑሮ ውድነት እና የኢኮኖሚ ችግር አለ። ይህም ሆኖ ግን ስደተኞችን ከመቀበል ተቆጥባ አታውቅም። በዚህም ላይ ለስደተኞች የሥራ ዕድል ከመፍጠር እና ነገሮችን ከማመቻቸት በስተቀር ከስደተኞች የምትፈልገው ገንዘብ የለም። ግብጽን የመሳሰሉ ሀገራት ከእያንዳንዱ ስደተኛ እስከ 3ሺ ዶላር ይቀበላሉ። ኢትዮጵያ ለቪዛ እና መሰል ጉዳዮች የምትጠይቀው ከ10 ዶላር ያነሰ ነው።
በሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በርካታ ሱዳናውያን ወደ ግብጽ ለመሰደድ ሞክረው ነበር። ሆኖም ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎች እንደሚናገሩት 3ሺዶላር በመጠየቃቸው ወደ ግብጽ ሊገቡ አልቻሉም። 3ሺ ዶላር ለአንድ ስደተኛ ከፍተኛ ገንዘብ ነው። ከየትም አምጥቶ ሊከፍል አይችልም። በየትኛው ሀገር ያለ ስደተኛ የቆይታውን ጊዜ ሲያራዝም ከፍተኛ ገንዘብ ይከፍላል። ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን እያስከፈለች ያለችው ከ10 ዶላር ያነሰ ነው። ይህም የሚያመላክተው ከፍ ያለ ሰብአዊነት የሚታየው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን መረዳት ይገባል።
ከዚሁ ባሻገር ከኢትዮጵያ በስተቀር ስደተኞች እንዲለምኑ የሚፈቅድ ሀገር የለም። ሌሎች ሀገራት የደህንነነት ስጋት ናቸው በሚል እንዲዘዋወሩ አይፈቅዱላቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታየው በየመንገዱ እና በየመስኪዱ ስደተኞች እየለመኑ እራሳቸውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ፖሊሶች እኮ ለስደተኞች ከማዘናቸው የተነሳ የማይገባ ቦታ ሁሉ ሲለምኑ እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉ በጎ ስብዓና የተላበሱ ባለሙያዎች ናቸው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ እንግዳ የመቀበል እና እንደ ባሕላቸው እና ኃይማኖታቸው እንዲኖሩ የመፍቀድ ስብዕና ዛሬም ደረስ ቀጥሏል። በተለያዩ ሀይማኖቶች መካከል ያለውም የእርስ በርስ መስተጋበር እንደ ደመቀ ዛሬ ላይ ደርሷል። ነገም ይቀጥላል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም