
18ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ከነገ በስቲያ መነሻና መድረሻውን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በማድረግ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትናንት በሰጠው መግለጫ እንደተጠቆመው፣ ፌዴሬሽኑ የውድድሩን ደረጃ ከፍ ለማድረግ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ በማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል።
የፌዴሬሽኑ የውድድርና ሥነ ሥርዓት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ፣ የሃያ አንድ ኪሎ ሜትሩን ሀገር አቀፍ ውድድር ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። በቀጣይ ውድድሩን ዓለም አቀፍ ለማድረግም ከወዲሁ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ውድድሩን ዓለም አቀፍ ለማድረግ ከሚታዩ ጉዳዮች መካከል ውድድሩ የሚካሄድበት (የኮርሱ) ምቾት፣ የተለካበት መንገድ፣ ምን ያህል ዓለም አቀፍ ዳኞችን አሳትፏል ወዘተ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አስፋው፣ በዚህ ረገድ የውድድሩ ርቀት (ኮርስ) በፌዴሬሽኑ ዓለም አቀፍ ሙያተኞች መለካቱን ተናግረዋል። ለመጀመሪያ ጊዜም የእያንዳንዱ አትሌት ሰዓት በዘመናዊ መንገድ (ቺፕስ ታይም ሲስተም) ይመዘገባል ብለዋል። ስልሳ ዓለም አቀፍ ሥልጠና የወሰዱ የፌዴሬሽኑ ዳኞችን ጨምሮ 150 ባለሙያዎች ውድድሩን እንደሚመሩም አክለዋል። የቀድሞዋን የዓለም ማራቶን ሻምፒዮን ጎይተቶም ገብረሥላሴን ጨምሮ ሞገስ ጥዑማይና ሌሎችም ስመ ጥር አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ተሳታፊ እንደሚሆኑ አቶ አስፋው ጠቁመዋል።
የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ በበኩላቸው፣ የውድድሩ ዓላማ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የክለቦችና ተሳታፊ ተቋማት አትሌቶች የጎዳና ላይ የውድድር ዕድል እንዲያገኙ መሆኑን ተናግረዋል። አትሌቶች የሀገር ውስጥ የውድድር ልምድ እንዲያዳብሩ፣ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራትና በውድድሩ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ አትሌቶችን በሽልማት ማበረታታትም የውድድሩ ዓላማ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህም መሠረት ከ1-6 ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች የገንዘብና የስፖርት ትጥቅ ሽልማት ተዘጋጅቷል። ለቡድን አሸናፊዎችም ከዋንጫ በተጨማሪ ከ80ሺ እስከ 16ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥ ይሆናል።
ቀደም ሲል ከግማሽ ማራቶን ውድድሩ ጎን ለጎን ሕዝብ የሚሳተፍበት የአምስት ኪሎ ሜትር ውድድር ለማካሄድ ፌዴሬሽኑ ሃሳብ እንደነበረው ይታወሳል። ይሁን እንጂ በውድድሮች መርሐ ግብር መደራረብና በሌሎች ምክንያቶች ፌዴሬሽኑ በዚህ ውድድር ሕዝብ የሚሳተፍበትን የሩጫ ውድድር ተግባራዊ ለማድረግ እንዳልቻለ አቶ ዮሐንስ አብራርተዋል። በቀጣይ ግን ይህን ለማሳካት ፌዴሬሽኑ የቤት ሥራ ወስዶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የፌዴሬሽኑ የኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ መሐሪ ነጋሽ በበኩላቸው፣ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስኅን ጀምሮ ሥራ አስፈፃሚ አባላት ውድድሩን ዓለም አቀፍ ለማድረግ ብዙ ጥረቶች እንዳደረጉ በመግለፅ፣ የዘንድሮው ሻምፒዮና ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት የተለየና በደረጃም ከፍያለ እንደሚሆን ተናግረዋል። ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። ውድድሩ ከማለዳው 12:00 ጀምሮ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፣ ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ ሲካሄድ ሃያ አንድ ክለቦችና ተቋማት እንዲሁም ሦስት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ ይሆናሉ። በአጠቃላይ 535 አትሌቶች ተፎካካሪ ሲሆኑም 156ቱ ሴቶች፣ 389ኙ ደግሞ ወንዶች ናቸው። ይህም ቀደም ሲል ከተካሄደው ውድድር አንፃር በከፍተኛ ቁጥር ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል።
በብዙዎቹ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ትልቅ ስም ያላቸው አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ከተገለፀ በኋላ ይወዳደራሉ የተባሉ እውቅ አትሌቶች ውድድሩ ላይ የማይታዩበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በዚህ ረገድ አቶ አስፋው ማብራሪያ ሲሰጡ፣ “እኛ ይሳተፋሉ ብለን የምንገልፀው ክለቦች ወይም ክልሎች ይሳተፋሉ ብለው በሚልኩልን ዝርዝር መሠረት ነው፣ እኛ ታዋቂ አትሌቶች በሀገር ውስጥ ውድድሮች እንዲሳተፉ እንፈልጋለን፣ ግን አይሳተፉም። ለዚህ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል፣ አሁንም ደግመን እናሳስባለን” ያሉ ሲሆን ታዋቂ አትሌቶች በመሰል ውድድሮች መሳተፋቸው ለወጣትና ተተኪ አትሌቶች ትልቅ ተነሳሽነትን እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም