አዲስ አበባ፡- በ150 ሚሊዮን ብር የተገዙት አዳዲሶቹ ዘመናዊ የደረቅ ወደብ ማሽኖች፤ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አሰራርን ከዘጠኝ እጥፍ በላይ እንደሚያሣድጉት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለፀ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሮባ መገርሣ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ አዳዲሶቹ ማሽኖች ባሳለፍነው ጥር ወር በሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ተመርቀው ሥራ ጀምረዋል፡፡
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው ለአገልግሎት የበቁት እነዚህ ማሽኖች የዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍ የተወሰደ ቁርጠኛ እርምጃ ነው ብለው ይህም የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ እና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡
አዳዲስ 13 የኮንቴይነር መጫኛና ማውረጃ ሪች ስታከሮች እና 21 ፎርክ ሊፍቶች መሆናቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ ማሽኖቹ በአንድ ጊዜ 45 ቶን ክብደት ያለው ኮንቴይነር የማንሳት አቅም ይዘው በሰዓት ከ20 በላይ ኮንቴይነሮችን ያነሳሉ ብለዋል፡፡ ፎርክ ሊፍቶቹም 20 ቶን የሚደርስ ክብደት የማንቀሳቀስ አቅም እንዳላቸውም ተጠቁሟል፡፡
ማሽኖቹ የደረቅ ወደቦቹን የማስተናገድ አቅምን መሰረት በማድረግ ተደልድለዋል ያሉት አቶ ሮባ በዚህም ሞጆ አስር፣ መቀሌ አንድ፣ ኮምቦልቻ አንድ እና ቃሊቲ አንድ እንደተመደበላቸው አመልክተዋል፡፡
በዚህ ደረቅ ወደብ ሲያስተናግዱ የነበሩ መጫኛ እና ማውረጃ ማሽነሪዎች ስምንት ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ስድስቱ የሚሠሩ ናቸው ብለው ለረዥም ጊዜ ሁለት ማሽኖች ብቻ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰው፤ በዚህም ደንበኞች ከአስር ቀናት በላይ እቃቸውን ለማስፈተሽ እንዲቆዩ ሲገደዱ ቆይተዋል፡፡
በመሆኑም የእነዚህ ማሽኖች መገዛት በዋናነት ሎጅስቲክ አገልግሎቱን ያቀላጥፋል፤ ፈጣን አገልግሎት መስጠት ያስችላል፤ ወጪንም በመቀነስ ደንበኞች እቃቸውን ለማስፈተሽ ከአንድ ቀን ባነሰ ጊዜ መስተናገድ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡ ይህም በመቶኛ ሲሰላ ከዘጠኝ መቶ ፐርሰንት በላይ አድጓል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የአገሪቱ ደረቅ ወደቦች የማስተናገዳቸው አቅም በቂ ደረጃ ላይ አልደረሰም ተብሏል፡፡
አቶ ምትኩ አበበ የሞጆ ደረቅ ወደብ ትራንዚተር በበኩላቸው የአዳዲስ ማሽኖቹ መገዛትና ሥራ መጀመር የአሰራር ጥራትን፣ ቅልጥፍና በመጨመር በአዳዲስ ማሽኖቹ ብቻ ችግሩን መቶ በመቶ መቅረፍ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው፡፡
የኢትዮጵያ ጉምሩክ አስተላላፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሀብቴ ጴጥሮስ እንዳስታወቁት፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የዘመናዊ ማሽኖች እጥረት በአጠቃላይ የሎጂስቲክስ ሥራው ላይ ከፍተኛ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል፡፡
በማሽን ችግርና በጉምሩክ አሰራር መጓተት ፈጥሯል የሚሉት አቶ ሀብቴ በዚህ ምክንያት ደንበኞች ለአላስፈላጊ የመጋዘን ወጪ እና እንግልት ሲዳረጉ ቆይተዋል፡፡ እንደ አቶ ሀብቴ ገለፃ በጋራ የተቋቋመው የሎጅስቲክስ ኮማንድ ፖስት ችግሩን ይፈታል የሚል እምነት ተይዟል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
ሙሀመድ ሁሴን