
ግብር ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ ነው። ይሁን እንጂ ግብር ከፋዩ በተገቢው መንገድ በታማኝነት ማሳወቅና መክፈል ካልቻለ የታሰበው ዕድገት ሊመጣ አይችልም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮም በ2013 ዓ.ም ለከተሞች ዕድገት ዋነኛ ሞተር የሆነውን የገቢ ግብር አሰባሰብ ውጤት ገምግሟል። በበጀት ዓመቱ 61 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ገልጾ ከዚህም ውስጥ 56 ቢሊዮን ብር ከገቢ ግብር የሰበሰበ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የተገኘ መሆኑን አመልክቷል።
ከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ሊያከናውናቸው ያሰባቸውን የልማት ግቦች ለማሳካትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማከናወን በተለይም የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን የተለያዩ ተግባራትን በማከናወኑ ተጨማሪ ውጤት መመዝገቡን ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ገቢዎች ቢሮ ዋና ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ እንዳብራሩት፤ በበጀት ዓመቱ የተጣለውን የገቢ ዕቅድ መቶ በመቶ ማሳካት ተችሏል። ለዕቅዱ መሳካት የከተማ አስተዳደሩ የበላይ አመራሮች ባለሙያዎች እንዲሁም ትልቁን ሚና የተጫወቱትና ግብር በመክፈል ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የከተማዋ ግብር ከፋዮች ናቸው።
ቢሮው የዕቅዱን መቶ በመቶ መፈጸም እንዲችል አምስት የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ተንቀሳቅሷል። ይህም የላቀ አገልግሎት መስጠት፣ ተቋማዊ ሪፎርም ማድረግ፣ የላቀ ገቢ በሁሉም መስክ ማግኘት፤ በቅንጅት ውጤታማ ሥራ መስራትና የህግ ማስከበር ነው ። ከህግ ተገዥነት አኳያ የአስተምህሮ ስራዎች በቀጣይ ግብር ከፋይ በሆነው ትውልድ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እየተሰራ ይገኛል።
ከተማ አስተዳደሩ 418 ሺ ግብር ከፋዮች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሰፊ ቁጥር ያላቸውና 298 ሺ 964 የሚደርሱት የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ናቸው። እነዚህ ግብር ከፋዮች ግብር በሚከፍሉበት ወቅት ረጃጅም ሰልፎችን የሚያስተናግዱና ለከፍተኛ እንግልት የተጋለጡ በመሆናቸው ባሉት ወረዳዎችና ቅርንጫፎች እንዲሁም በማዕከላት ጭምር ደረጃ አንድ የመረጃ ቋት ተደራጅቷል።
በመሆኑም የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ግብሮቻቸውን ለማወቅ ቅርንጫፍ ድረስ ሳይሄዱ በእጅ ስልካቸው አማካኝነት ምን ያህል ገንዘብ የት ሄደው መክፈል እንደሚችሉ በ7075 የኤስ ኤም ኤስ መልዕክት ይደርሳቸዋል። በዚህ መሰረት ሁሉም የደረጃ ‹‹ሐ›› ያለእንግልት ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው በመሆኑ ከዚህ ቀደም የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ በግማሽ የሚያሻሽል ይሆናል።
በበጀት ዓመቱ 98 በመቶ የሚደርስ የታክስ ቅሬታዎችን በየደረጃው መፍታት ተችሏል። ቅሬታ ሲቀርብባቸው የነበሩና ባልተገባ መንገድ የተንቀሳቀሱ ባለሙያዎችን ከቦታ ቦታ የማዘዋወርና ከቦታቸው የማንሳት ሥራ ተሰርቷል። ይህም ከፍተኛ ገቢ ለመሰብሰቡ አይነተኛ ሚና ነበረው።
ከፍተኛ አፈጻጸም ለነበራቸው 187 ግብር ከፋዮች ዕውቅና በመስጠት የማበረታታት ሥራ ተሰርቷል። ኮቪድ 19ኝ ወረርሽኝ ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ ድቀት ምክንያት በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ በወሰነው ውሳኔ መሰረት 6700 የሚደርሱ ግብር ከፋዮች የዕዳ ምህረት ተጠቃሚ ሆነዋል። በዚህም የከተማ አስተዳደሩ 10 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ አጥቷል።
ከደረሰኝ ጋር ተያይዞ የሀሰተኛ ደረሰኞችን አሳትሞ ማሰራጨት፣ ከቀረበው ዋጋ በታች በደረሰኞች ላይ መጻፍ እንዲሁም ያለደረሰኝ በመሸጥ 22 ሺ የሚደርሱ አጠራጣሪ ደረሰኞች ቀርበው ውድቅ ተደርገዋል።በእነዚህ ምክንያት ለማጭበርበር የተሞከረውን ማክሸፍ ተችሏል።
ከታክስ ኦፕሬሽን አኳያ በበጀት ዓመቱ በሁሉም ዘርፍ በቂ ንቅናቄዎችን ማድረግ የተቻለ ሲሆን ግብር ከፋዮች የሚያነሷቸውን ችግሮች ቀረብ ብሎ ለመረዳት ብዙ መድረኮች ተፈጥረዋል። በዚህም የተሻለ አፈጻጻም ተመዝግቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ 418 ሺ 133 ግብር ከፋዮች ሲኖሩ በደረጃ ‹‹ሀ›› 73 ሺ 294 በደረጃ ‹‹ለ›› 45 ሺ 875 በደረጃ ‹‹ሐ›› 298 ሺ 964 ግብር ከፋዮች ናቸው። በዋነኛነት እነዚህ ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ጥቅምት 30 ግብሮቻቸውን የማሳወቅና የመክፈል ሥራ መስራት አለባቸው። ስለዚህ ሁሉም ግብር ከፋዮች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ ግብራቸውን በታማኝነት እንዲያሳውቁና የተጣለባቸውን ግብር እንዲከፍሉ ቢሮው ያበረታታል።
የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የአንድ ወር ጊዜ ያላቸው በመሆኑ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ግብራቸውን የማሳወቅና መክፈል ሲኖርባቸው የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን እስከ እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም በድምሩ በ65 ቀናት ውስጥ ማሳወቅና መክፈል ይኖርባቸዋል። የደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች አራት ወራት ከአምስት ቀን ጊዜ ያላቸው ሲሆን ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2014 ዓ.ም ይሆናል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮም ግብሩን ለመሰብሰብ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል። በተለይም የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ሙሉ ለሙሉ በስልኮቻቸው ከ70 -75 በሚደርሳቸው መልዕክት መሰረት ምን ያህል ገንዘብና በየትኛው የንግድ ባንክ አካውንት ማስገባት እንዳለባቸው ይደርሳቸዋል። በዚህም አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋና ምቹ ይሆናል። በቀጣይም ቴክኖሎጂውን በማበልጸግ የደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮችም እንዲሁ ተካታች ይሆናሉ። ቢሮው በቀጣይ አራት የግብር መሰብበሰቢያ ወራት 20 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013