ኳ..ኳ…ኳ.. በሩ ከልክ በላይ ሲደበደብ በድንጋጤ ተፈናጥሬ ተነሳሁ። እኔ ከተኛሁበት አልጋ ጋር በተደራቢነት የተሰራው አልጋ ላይ ቁጭ ብሎ ወረቀቶችን ሲያገላብጥ የነበረው ሶሌማን ለበሩ ድብደባ “ሰውየው እንቸክልበታ፤ አትበጥብጠና” በማለት ምላሽ ሰጠ። ሶሌማን እንቸክልበት ያለው እናጥናበት ለማለት ነበር። እዚያ ግቢ ውስጥ ለእያንዳንዱ ተግባር ተማሪው በተለምዶ የሚጠቀምበት የራሱ የሆኑ ስያሜዎችና መጠሪያዎች አሉት።
እኔ ምሽቱን ሳነብና ከእኔ ጥናት ጋር የሚዛመዱ ሌሎች ጥናቶችን ስመለከትና ለጥናታዊ ፅሁፌ ቀረቤታ የሚጠቅመኝን ልምምድ በራሴ ሳደርግ ነው ያደርኩት። ጠዋት አይኔን እየጠራረግሁና እየተንገዳገድኩ የተማሪዎች ካፌ ሄጄ እንደ ነገሩ ቀማምሼ ነበር የተኛሁት። ከእቅልፌ ስነሳ የመኝታ ክፍሌ ተጋሪ ተማሪዎች ሶሌማን አያሌውና መቻል ለጥናታቸው የሚጠቅማቸውን ሰነድ በማንበብና በመዘጋጀት ላይ ነበሩ። የበሩ ድብደባ ቢቆምም በሩን የደበደበው “ ውጡ ካፌ ካፌ…” የሚል ድምፁን ስሰማ ካሳሁን መሆኑን አወኩኝ።
ካሳሁን ከሁላችንም ጋር የሚግባባ የትምህርት ክፍላችን ልጅ ነው። ክፍል ውስጥ ስንማር አልፎ አልፎ በሚያደርጋቸው ንግግሮቹ ሁሉም ተዘጋጅቶ ከእሱ ቃል የጠበቀ ያህል ይስቃል። የፌዙን ያህል ቁም ነገረኛም ነው። ተማሪዎች ሲቸገሩና አንዳንድ ከባድ ጉዳዮች ሲገጥማቸው ከተማሪዎች መዋጮ የሚጠይቀውና የሚሰበስበው እሱ ነው። ክፍሉ በሙሉ ይወደዋል። በትምህርት ብዙም ጎበዝ ባይሆንም ለአራት ዓመታት ግቢ ውስጥ ቆይቶ ከእኛው ጋር ሊመረቅ ያዘጋጀውን ጥናታዊ ፅሁፍ ማቅረብ ብቻ ይቀረዋል።
እሁድን እንደምንም በጭንቀትም በዝግጅትም ውለን ሰኞ ጠዋት ላይ የምረቃ ፅሁፋችንን ልናቀርብ ዲፓርትመንት አካባቢ ተገኘን። ለወራት የደከምንበትን ስራ አማካሪዎቻችን ፊት አቅርበን ስንወጣ የተሰማኝን እረፍት ልገልፀው አልችልም። ሌሎች ጓደኞቼም ተመሳሳይ እረፍት እንደተሰማቸው ነገሩኝ። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለን የትምህርት ቆይታ በዚሁ የጥናት ፅሁፍ ማቅረብ ተጠናቀቀ። የደወልኩት እዚያው ዩኒቨርሲቲ ተዋውቀን በጥሩ መተሳሰብና ፍቅር አብሬያት የቆየኋት ፍቅረኛዬ ፌቨን ጋ ነበር።
ስልኩን አንስታው ከሰላምታ ቀድማ “ማሬ ስላንተ ስጨነቅ ነበር። ምን ሆነልህ?..እንዴት ነበር አስተያየትና ምልሻቸው? …እንዳልደውልልህ እረብሻለሁ ብዬ..”ችግር የለም ውዴ በጣም ምርጥ ነበር። እንደውም አጨብጭበውልኛል። ስልህ “የኔ ቆንጆ፤ እኔ ሁሌም እንደምኮራብህ ታውቅ የለ፤ የጠበኩት ነው” አለችኝ። “አሁን የት ላግኝሽ?” ብያት ቦታውን ተነጋግረን ተገናኘን።
ፌቨንን የነብሴ ያህል እወዳታለሁ። እሷም ተመራቂ ተማሪ ናት፤ በእርግጥ የተለያየ ትምህርት ክፍል ላይ ነው ተምረን የጨረስነው። የጥናት ፅሁፍዋን ከእኛ ቀድማ አቅርባ ነበርና ቀድማን እፎይ ብላለች። የዚያን ቀን ከዩኒቨርሲቲው ራቅ ብለን በተለየ ሁኔታ በፍቅር ልዩ ቀን አሳለፍን። ከፌቨን ጋር ስራ እንደተቀጠርን ልንጋባ ቀጠሮ ይዘናል። እኔ የአዲስ አበባ ልጅ ስሆን እስዋ የአዳማ ልጅ ናት።
ከተመረቅን በኋላ አዲስ አበባ ስራ ፈልጋ እንደምትቀጠርና አብረን መኖር ብሎም ተጋብተን ቤተሰብ እንመሰርታለን ተባብለናል። እስከ ህይወታችን ማብቂያ ድረስ ላንለያይ ቃል ተጋብተናል። ፌቨን አባትዋን አታውቀውም። እናትዋ በአንድ አጋጣሚ ከተዋወቀችው ሰው እንደፀነሰችና ሰውየው ማርገዝዋን ስትነግረው አድራሻውን ደብቆ እንደጠፋባት ከዚያ በኋላ አግኝታው እንደማታውቅ ለማግኘት ጥረት አድርጋ እንዳልተሳካላት እናትዋ እንደነገረቻት ነው ለእኔ የነገረችኝ። አብዝታ “ፍቅረኛም አባትም እንድትሆነኝ እፈልጋለሁ” ትለኛለች። እኔም ሁለቱንም ለመሆን ቃል እገባላታለሁ።
እስከ ምርቃት ቀን ድረስ ከፌቨን ጋር ፍቅራችንን በነፃነት ያለማንም ከልካይነት ተለዋወጥን። ወደፊት እንዴት መኖርና በምን ሁኔታ ህይወታችንን መምራት እንዳለብን እቅድ አወጣን። የምርቃታችን ቀን ሲቃረብ አባቴ ደውሎ ድሬዳዋ ለእኔ ምረቃ እንደሚመጣ ሲነግረኝ እጅግ ተደሰትኩ። የፌቨን እናትም ልጅዋን ልታስመርቅ እንደምትመጣ ቀድሜ አውቅ ነበር። እኔ ከአባቴ ጋር በግልፅ ስለማወራ ፍቅረኛ እንዳለኝ ተመራቂ እንደሆነች ነግሬው ስመጣ ታስተዋውቀኛለህ ብሎኛል።
ፌቨን ከእናትዋ ጋር በጣም ሚስጥረኞች ናቸው። እኔንም ከእናትዋ ጋር በስልክ እስተዋውቃኛለች ። ወደኛ የሚመጡ ቤተሰቦቻችንን ስንጠብቅና ፍቅራችንን ስናጣጥም ቆይተን ለምረቃችን አንድ ቀን ሲቀረው ጋወናችንን ከየትምህርት ክፍሎቻችን ወስደን ለበነጋታው መዘገጃጀቱ ተያያዝነው። ከሰዓት በኋላ እኔም አባቴን ፌቨን እናትዋን ልንቀበል ከዩኒቨርሲቲው በር ላይ ባጃጅ ይዘን ወደ ከተማ ወጣን። የሚመጡት የእስዋ እናት ከናዝሬት የእኔ አባት ደግሞ ከአዲስ አበባ ስለሆነ ምሽት ላይ እንደሚደርሱ ስምናውቅ አንድ ካፌ ቁጭ ብለን ስናወራ ቆየን።አብረን እዚያ እንሂድ እንጂ ያለቅድመ ዝግጅት አንደኛችን የአንደኛችንን ወላጆች ማግኘት እንደሌለብን እናውቃለን። ቀድሞ ድሬዳዋ ገብቶ የደወለ ወላጁን ይዞ ዩኒቨርሲቲው ለቤተሰብ ወዳዘጋጀው ቦታ ይሄዳል።
በመሀል ፌቨን አንድ ሀሳብ አቀረበች።“ቆይ ማሬ እ አባትህን ልተዋወቃቸው ነው ፤አንተም የእኔን እናት ልትተዋወቅ ነው አይደል?”አለችኝ “አዎ ምነው አልኳት። “ታዲያ እነሱንስ ለምን አናስተዋውቃቸውም” ስትለኝ፤ አላቅማማሁም። በእርግጥ የእስዋ እናትና የእኔም አባት ዘመናዊ ናቸው ብናስተዋውቃቸው ምንም አይደለም ብዬ ስላመንኩበት ነው።
ከትንሽ ቆይታ በኋላ የፌቨን እናት መግባታቸውን ለሄለን ስልክ ደውለው ነገርዋት። እየፈራሁ አብሬያት ሄጄ ተቀበልኳቸው። ብዙም አይከብዱም፤ ሳቂታና ተጫዋች ናቸው። መጀመሪያ የፈራሁትን ያህል ሳገኛቸው ቀለለኝ። ፌቨን ሁሌም ወሬዋ ስለኔ መሆኑና ሁሉ ነገር እንደሚያው ነገሩኝ። አንገቴን ደፍቼ የሚያወሩልኝን ፈገግ ብዬ እየሰማሁ ቆየሁ። መክሰስ ነገር በልተን እጃችንን እየታጠብን ሳለ ስልኬ ጠራና ከኪሴ አውጥቼ አየሁት ፤ አባቴ ነው።”ፌቨን መጡ ፋዘር፤ ሂድ በቃ ይዘሀቸው ና” አለችኝ። አንገቴን በመነቅነቅ እሺታዬን እየገለፅኩ ስልኩን አንስቼ ወደ መውጫ በሩ አቀናሁ። ተመልሼ ፌቨንን ጠርቻት።
“ፌቪዬ አሁን እዚሁ ይዤው ልምጣ ወይስ ነገ ጠዋት እናስተዋውቃቸው?” ስላት “አቦ ማሬ አታካብድ፤ ይዘሀቸው ናና አብረን ተያይዘን እንሄዳለን” አለችኝ።
ለምን እንደሆነ ባላውቅም ወደመናኸሪያ ሲሄድ የሆነ ለየት ያለ ስሜት እየተጫጫነኝ ነበር። የአባቴ መምጣት አስደስቶኝ ይሁን፤አልያም ማስተዋወቁ ላይ ቸኮልኩ ብዬ በመፀፀት አላውቅም ለራሴ አልገባህ ያለኝ ስሜት ውስጥ ገባሁ። አባቴን ሳገኘው ደስታ ተሰማኝ። እሱም ሲያገኘኝ “የኔ ጀግና ልጅ አኮራኸኝ..በድል ወደ ቤቴ ይዤህ ልመለስ ነው”ብሎ ተጠመጠመብኝ። ውስጤ አንዳች ልዩ የደስታ ስሜት ወረረው።
ይዤው እነ ፌቨን ያሉበት መናኸሪያው ጋር ያለው ሬስቶራንት እስክንደርስ ድረስ ስለቤተሰብ ስናወራ ነበር። በር ላይ ስደርስ አስቆምኩትና ነገርኩት። ትንሽ አሰብ አደረገና። “ችግር የለም ፤እዚህ ናቸው እንግባ ፤እንተዋወቃለና ደስ ይለኛል” አለኝ። ይዤው ስገባ ፈራ ተባ እያልኩኝ ነበር።
ውስጥ እንደገባን አይኔ ፌቨን ላይ ነበር። እንደማፈር ብላ አቀረቀረች። እናትዬውን ስመለከት ፊታቸው ተለዋውጦ አየሁት። ግራ ተጋባሁ። አባቴን ሳይ ደግሞ ይበልጥ ግራ ገባኝ። የፌቨን እናት “ሳህሉ” ሲሉ አባቴ “ታየች” ተባባሉ።
የፌቨን እናት ሌላ ቃል ሳይጨምሩ ፈዘው ቆዩና እንባ አንቋቸው በተረበሸ ገፅታ ተነስተው ወደ ሬስቶራንቱ መታጠቢያ ሲያመሩ ፌቨን ቀና ብላ በምታየው ነገር እንደኔው ግራ መጋባት ጀመረች። ቆይቼ በሰማሁት ነገር ሀፍረት ተሰማኝ፤መሬት ተሰንጥቃ ብትውጠኝ መረጥኩ። አባቴ በአንድ አጋጣሚ አዳማ ሄዶ የተዋወቃትና አረገዝኩ ስትለው የጠፋው የፌቨን አባት ሆኖ ተገኘ። ተፈፀመ
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013