
‹‹ፈጣሪ ይመስገን ከፀሐይና ዝናብ በተለይም ከዘራፊ ተጠብቂያለሁ። ወገቤ እስኪንቀጠቀጥ መቆምም ቀርቶልኝ ዘና ብዬ መቀመጥ ችያለሁ። አሁንማ አየር መንገድ ያለሁ ነው የሚመስለኝ›› ሲሉ ከልብ በመነጨ የደስታ ስሜትና ፈገግታ ሀሳባቸውን ያካፈሉኝ በመርካቶ አውቶብስ ተርሚናል ያገኘሁዋቸው አቶ ረጀብ ደሊል ናቸው።
አቶ ረጀብን ያገኘናቸው በተርሚናሉ በታችኛው የአንበሳ አውቶብስ ድርጅት የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ወለል ላይ ባለው ምቹ ወንበር ተቀምጠው የሰበታን አውቶቡስ ሲጠባበቁ ነው። የተሰራውን ተርሚናል ምቹነትና ዘመናዊት ሲገልጹም፤ ወንበሩ ከአዲስ አበባ ምድር ባቡር ጋር ቢመሳሰልም ደረጃው የአየር መንገድ ዓይነት ነው። ማጋነን ሳይሆን በትክክልም የተርሚናሉ አጠቃላይ ይዘትም ከአንበሳ አውቶቡስ ጋር ሳይሆን ከአየር መንገድ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ምቾቱ ውጡ ውጡ አይልም። መርካቶ ውስጥ በንግድ ስራ እንደሚተዳደሩ የገለፁልንና መኖርያቸው ሰበታ መሆኑን የነገሩን ወይዘሮ ዘሀራ አብዱልመጅድ በየቀኑ ወደ መርካቶ የሚመላለሱ በመሆናቸው ዘወትር አገልግሎቱን ይጠቀማሉ። ለተሳፋሪው መፀዳጃን ጭምር የተዘጋጀውን ተርሚናል ምቾትና ዘመናዊነትን በፊት ከነበረው ችግር ጋር ሲያነፃፅሩት ያሳለፉት ጊዜ ስቃየ እንደነበር ይናገራሉ። አሁን ወንበር ላይ ተቀምጦ አውቶቡስ መጠበቅ በራሱ ትልቅ እድል መሆኑን ይናገራሉ። ወረፋ የሚጠብቁት በስነስርዓት ግፊያ፣ ሲራራጡ መውደቅና በነጣቂ መዘረፍ የሚል ስጋት ሳይኖር መሆኑ ከብዙ ነገር ስጋቱ ቀንሶላቸዋል። አውቶቡሱ ውስጥ ከገቡም በኋላ ቢሆን በወንበር ተቀምጦ የመሄድ ሰፊ መኖሩን ያስታውሳሉ። በተለይ የሰበታ ጉዞ ተገልጋዮች ረጅም መንገድ እንደመሄዳቸው እግራቸው እስከሚንቀጠቀጥ የሚቆሙበትን በማስቀረት ከወገብ በሽታ ታድጓቸዋል። በመፀዳጃ በኩል በተለይ እሳቸውን ጨምሮ ብዙ ሴቶች በአካባቢው እንደ ወንዶች እንኳን የሚፀዳዱበት በማጣት ሽንታቸውን እየቋጠሩ ለኩላሊት ህመም የሚዳረጉበት አጋጣሚ አንዳለም ሳይጠቅሱ አላለፉም።
አብዛኛው የአንበሳ አውቶቡስ ተጠቃሚ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ዜጋ እንደሆነ የሚጠቅሱት ወይዘሮዋ የተሳፋሪው ቁጥር ስለሚበዛ ግፊያ ስለሚኖር በግፊያ ወቅት ዝርፊያ እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን ላይ ግን ተርሚናሉ አውቶቡስ ተራ በነበረበት ጊዜ እንደነበረው ግፊያንና ዘረፋ የለም። ቢሆንም የሰበታዋ አውቶቡስ ቶሎ ቶሎ ስለማይመጣ በተረጋጋ ቦታ ቁጭ ብለው የሚጠብቁበት ሁኔታ እንዳለ ይናገራሉ።
ሌላዋ በላይኛው የተርሚናሉ ወለል ላይ በተዘጋጀው መቀመጫ ተቀምጠው የጀሞ አንድ የሸገር አውቶብስን ሲጠባበቁ ያገኘናቸው አቶ ዳኛቸው ላቀው እንዳሉን፤ የዘመናዊው ተርሚናል አገልግሎት አሰጣጥ አስደሳች ነው። ተራ መጠበቂያው የመቆሚያ ቦታ እንደ ባቡር የተለየ ስለሆነ ተሳፋሪውን ለአደጋ የሚያጋልጠው ነገር አይገጥመውም።
ዘመናዊ አገልግሎት በመጀመሩ እርሳቸውም የአውቶብስ ተጠቃሚ ሆነዋል። ይህም አገልግሎቱ ከመጀመሩ በፊት በየቀኑ ለታክሲ ያወጡት የነበረውን ከ20 እስከ 30 ብር ወጪ አስቀርቶላቸዋል። አውቶቡሶቹ በተገልጋዩ ስነስርዓት ጉድለት መስመር ዘግተው ብሎም መጫን ከጀመሩ በኋላም አቋርጠው የሚሄዱበትን እና በዚህ ምክንያት ከሹፌርና ትኬት ቆራጮች ጋር የሚፈጠረውን ግጭት ያስወገደ ነው። ዱላና ግብግቡን ሁሉ አስቀርቷል ሲሉ ይገራሉ። ሆኖም ግን ከተሳፋሪዎች በኩል ያሉ ችግሮችን ሳይጠቅሱ አላለፉም። ‹‹ ተሳፋሪው በኔነት ስሜት ጥንቃቄ እያደረገ አይደለም። አገልግሎት መስጠት በጀመረ አንድ ወር ውስጥ የተርሚናሉ ፅዳት ጉዳይ ዕድሜውን ዘላቂ የሚያደርገው አይመስልም። ከወረቀትና ትኬት ጀምሮ የሙዝ ልጣጭና ፌስታል ወረቀት በወለሉ ላይ ተዝረክርከው ይታያሉ። አንዳንዴ መጥፎ ጠረን ያመጣል። ይሄ ለራስ ካለማሰብ የሚመነጭ በመሆኑ ሁሉም ሰው እንደራሱ ንብረት ጥንቃቄ ሊያደርገ ይገባል›› ብለዋል።
ባለፈው ግንቦት 7/2013 ዓ.ም በይፋ የተመረቀውና ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ ወደ አገልግሎት የገባው የመርካቶ የከተማ አውቶቡስ ተርሚናል ፅዳት ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን የገለፀችልን ደግሞ የሸገር የብዙሃን አገልግሎት ድርጅት የሰራተኞች ተቆጣጣሪና የስምሪት ኦፊሰር ወጣት እየሩስዓለም መኮንን ነች።
‹‹እኛ በመስተንግዶ ወለሉ ላይ ተጥሎ ያየነው ብዛት ያለውና ጥቅም ላይ የዋለ የአውቶቡስ ትኬት፣ የበቆሎ ቆረቆንዳ፣ የሙዝ ልጣጭ፣ አልፎ አልፎም ፌስታል ነው። ይሄ ጥንቃቄ በጎደላቸው ተሳፋሪዎች በወለሉ ላይ ተጥሎና ተዝረክርኮ ይስተዋላል።›› በመሆኑም እሷና ባልደረቦቿም በዚህ በኩል ተገልጋዩን ስርዓት ለማስያዝ ሳይታክቱ ትምህርት ይሰጣሉ። ትምህርቱ በቋሚ ተገልጋዮች ዘንድ ለውጥ አምጥቷል። ሆኖም አዳዲስ በሆኑት ዘንድ ዘላቂ ለውጥ እንዲያመጣ አሁንም መስራት አለባቸው። ተሳፋሪውም የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አለበት። ንብረቱ ሁሉም የራሱ አድርጎ የሚጠቀምበት ሲያልፍም ለትውልድ የሚያስተላልፈው በመሆኑ ለተጠቃሚዎች በየጊዜው ትምህርት ሊሰጥ ይገባል የሚል እምነት አላቸው።
የጽዳቱን ጉዳይ አንድ በሉት የሚላቸው ብዙ ነው። በተለይ ከምቾትና ጊዜን ከመቆጠብ ጋር በተያያዘ በጊዜ ወደ ቤቴ መግባትና ጊዜዬን መጠቀም ችያለሁ፤ ከዘረፋ፣ ከፀሐይና ዝናብ ተጠብቄያለሁ በማለት እስከ ቢሯቸው ዘልቆ የሚያመስግናቸው ተገልጋይ ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ድሮ ግን በሰልፍም የተጣላና ንብረቱን የተዘረፈ አብዝቶ ይማረርባቸው እንደነበር አትዘነጋም። አንዳንዴ ቁጭቱን ሊወጣባቸው የሚሞክርበትና ግጭት የሚፈጥርበት ሁኔታ ነበር። ለስድብና ዱላ የሚጋበዝን እንደነበር ታስታውሳለች። ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ከገንዘብ ተቀባይነት አንስቶ ከዚህ ዓይነቱ ተገልጋይ ጋር በቀጥታ በሚያገናኛት ሥራ ስትሰራ ቆይታለች። አሁን ላይ አዲሱ የመርካቶ ተርሚናል ይሄን ዓይነቱን የተገልጋዩን ባህርይ መቀየር መቻሉንም በግልፅ ማስተዋል ችላለች።
በዚሁ ድርጅት የሰራተኛ ተቆጣጣሪና የስምሪት ኦፊሰር ወጣት ዳርሜለሽ አስፋው የሺ ደበሌ (ቀራንየው) ልኳንዳና እሷ ምትሰራባቸው መስመሮች ተገልጋዮች አሁን ባለው ሁኔታ ደስተኞች መሆናቸውን ትናገራለች። እነዚህ አካባቢዎች በፊት ረጃጅም ሰልፍ ይታይ ነበር። ሁከትና ረብሻ ብሎም ንጥቂያና ዘረፋ ይበዛባቸው ነበር። የአውቶብሶቹ ሹፌሮችና ትኬተሮች በዚህ በመማረር ስርዓት አስከባሪ ከመጥራት ጀምሮ ለብዙ ችግሮች መፍትሄዎችን በመፈለግ ጊዜያቸውን ያባክኑ ነበር። በተለይ እስከ ልኳንዳ የደረሰ ረጅም ሰልፍ ያስተናግድ የነበረው ልኳንዳ አካባቢ በዚህ የታወቀ ነው። ብዙ ተሳፋሪዎች ሲማረሩበት ነው የኖሩት። ሆኖም አሁን ይሄ መስመር ወረፋው በስነስርዓት በመያዙ፣ ተሳፋሪውም በወንበር ቁጭ ብሎ የሚስተናገድ በመሆኑና ከግፍያና ዝርፊያ መሻሻል በማሳየቱ ተገልጋዩ ደስተኛ መሆኑን እየመሰከረና እየተናገረ ይገኛል።
ወጣት ተወዳጅ ማቲዎች በአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የሸጎሌ ዲፖ ሠራተኛ ሲሆን ድርጅቱ ወደ ዲፖ የላከው የማስተናበር ሥራ እንዲሰራ መሆኑን ነግሮናል። ወጣቱ የሸጎሌ፣ የመካኒሳና የየካ መኪናዎች ዲፖ የ91 እና 26 ቁጥርና ሌሎች አውቶቡሶች በየመስመራቸው ወደ ተርሚናሉ መጥተው ይስተናገዳሉ። የእሱ ሥራ የነዚህን አውቶቡስ ተገልጋዮችና አውቶቡሶች ማስተናበር ነው። ሰልፍ በማስያዝ ስርዓት ያስከብራል። አውቶቡሱ ሲመጣም በሰልፍ እንዲገቡ ያደርጋል።
ከቀድሞ ሲል በነበረው ሁኔታ የከተማ አውቶብስ ተገልጋዩ ውጪ ፀሐይና ዝናቡን ችሎ አውቶብስ ለመጠበቅ ይገደድ ነበር። ለትኬት ቆራጭም ቢሆን በተለይ በክረምት አስቸጋሪ ነው።አሁን ተገልጋዮች ተርሚናሉ ውስጥ ከዝናብ ተጠልለውና ቁጭ ብለው አውቶቡሱ የሚጠብቁበት ሁኔታ ነው ያለው ።በበዙ ሳይንገላቱ ወደ ቤታቸው የሚመለሱበት ዕድልም ተፈጥሯል።
በአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት ትኬት ቆራጭ ወጣት መሐመድ አብረሃም እንደሚለው፤ በአስተናባሪነት የሚሰሩት ወንዶች ናቸው። ምክንያቱም ተርሚናሉ የሚገኘው ብዙ መጨናነቅና ወከባ እንዲሁም ሌብነትና ማጭበርበር በሚበዛበት መርካቶ ገበያ መካከል ነው። ከዚህ አንፃር ተገልጋይ መስሎ ለዘረፋ የሚገባ አይጠፋም። ትኬት ቆርጦና ተሳፋሪ መስሎ ሊገባ የሞከረ በተግባር የተያዘበት ሁኔታ አለ። የሦስት ብር ትኬት ቆርጠው የስምንት ብር መንገድ የሚጓዙ ብልጣብልጥ ተገልጋዮችም ተይዘው ያውቃሉ። በመሆኑም ከበር ጀምሮ አውቶቡሱ ውስጥ እነዚህን የመለየት ስራ ይሰራሉ። በዚህ መካከል ቡጢ የሚሰነዝር የሚገፈትርና የሚጋፋ ግብግብ የሚገጥም ሊኖር ስለሚችል በሥራው የሚመደቡት ሊቋቋሙት የሚችሉ ወንዶች መሆናቸው ትልቅ ፋይዳ አለው።
አቶ ጅጋር ላቀ የመካኒሳ ዲፖ የብዙሃን ትራንስፖርት ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ተርሚናሉ ካለፈው ሰኔ ወር አንስቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ጀምሮ የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉትን 18 መስመሮች አስተዋውቋል። አገልግሎት እየሰጡባቸው ከሚገኙት ከነዚህ መስመሮች መካከል ከዓለም ባንክ አውቶቡስ ተራ መርካቶ ተርሚናል፣ ከአየር ጤና መርካቶ ተርሚናል፣ ከካራ ቆሬ መርካቶ ተርሚናል ይጠቀሳሉ። በተርሚናሉ የሚሰጠው አገልግሎት ከበፊቱ ጋር ሲነጻፀር ለየት ያለና ዘመናዊ ነው። አሁን ትኬት ተቆርጦ ነው የሚገባው። ትኬት ለመቁረጥ የነበረውን ግፊያና ዘረፋም ቀንሷል። መፀዳጃ ቤት፣ ሻወር ቤት፣ ቢሮዎችም አሉት።
ድርጅታቸው ቀድሞ በምእራብ መርካቶ ላይ በሁለት መስመሮች ስምንት አውቶቡሶችን ያስገባ ነበር። አሁን ላይ ከ21 እስከ 28 መደበኛ አውቶቡሶችን በማስገባት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። እርሳቸው አንድ ማዕከል ላይ ሆነው አገልግሎት መስጠት በመቻላቸው ደስተኛ ናቸው። ከ10 ሰዓት ጀምሮ የተርሚናሉ መቀመጫ ስለሚጠብ ተሳፋሪው ወደ ውጪ ይወጣል። ይሄ የሚሆነው ተገልጋዩ ሥራ ጨርሶ አንዴ ስለሚወጣ ነው። ይሄን ጫና ለመቀነስ በተቻለ መጠን አውቶቡሶቹ ቶሎ ቶሎ እንዲመጡ እየተደረገ ይገኛል። ተገልጋዩ ተጨማሪ መስመር እንዲከፈትም ይጠይቃል። በመሆኑም ድርጅታቸው ከተርሚናሉ ወደ ሽሮ ሜዳ፣ የካ አባዱ፣ በካዛንቺስ መገናኛ፣ ወደ ሜክሲኮ ቢከፈቱ አዋጭ መሆኑን አጥንቷል። ለመክፈትም እየተዘጋጀ ነው።
እስካሁን ባለው ሁኔታ የሸገር ባስ 35 ተሳፋሪዎችን በወንበርና 35 ቱን ደግሞ ቆመው እንዲሄዱ ይደረጋል። ሆኖም ሕብረተሰቡ በወንበር ተቀምጦ መሄድ ስለለመደ ተሳፋሪ ሲበዛ ቆሞ ለመሄድ ፈቃደኛ አይደለም። ስለዚህ ሸገር ባስ 35 ሰው ብቻ ጭኖ ነው ከተርሚናሉ እየወጣ ያለው። ችግሩን ለመፍታት ከከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር እየተነጋገረ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ስጦታው አከለ እንዳሉት፤ የከተማ አውቶቡስ ተርሚናል በመርካቶ አካባቢ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ በአንድ ሰዓት 6 ሺህ፤ በቀን ደግሞ እስከ 80 ሺህ ተገልጋዮችን በማጓጓዝ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው። እኛ እንዳስተዋልነው ተርሚናሉ በአንድ ጊዜ ለ20 አውቶቡሶች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሲሆን የራሳቸው መግቢያና መውጫ ያላቸው ሁለት ወለሎችም አሉት። 35 የሚደርሱ የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት መስመሮች እና 17 የሚሆኑ ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት ድርጅት መስመሮች በድምሩ 52 መስመሮች ላይ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ነው። ይሄ በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባውን መርካቶ ዘመናዊ የከተማ አውቶቡስ ተርሚናል ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዕቅዱ ይዞ በትራንስፖርት ዘርፉ እያከናወናቸው ከሚገኙ መሰረተ ልማት ማሟላት፣ ስምሪቱን በቴክኖሎጂ ማዘመንና ዘመናዊ አውቶቡሶችን ማስገባት ተግባር መካከል ይጠቀሳል።
የተርሚናሉ ዋና ዓላማ ቀልጣፋና ምቹ ዘመናዊ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት ነው። አገልግሎቱም ሕብረተሰቡን ታሳቢ ባደረገ በዝቅተኛ ዋጋ ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013