የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሽንት ስርዓት አካላትን ማለትም (ኩላሊትን፣ የሽንት ፊኛን እና የላይኛውን እና የታችኛውን የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦዎች የሚያጠቃ የኢንፌክሽን አይነት ነው። ብዙዎቹ ኢንፌክሽኖች የታችኛውን የሽንት ቧንቧዎች እና የሽንት ፊኛን ያጠቃሉ። የኢንፌክሽን መምጫ መንስኤዎችን እንዲሁም የህክምና መንገዶችን በተመለከተ በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ጤና ጣቢያ ውስጥ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኢብራሂም ኤቦን አነጋግረናቸዋል።
ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው። ኢንፌክሽኖች ከሽንት ፊኛ አልፈው ወደ ኩላሊት ከተሻገሩ አሳሳቢ የጤና እክል ሊያስከትሉ ይችላሉ። ሃኪሞች የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን አንቲባይዎቲክ (ፀረ-ህዋስ) መድሃኒቶች በመስጠት ያክማሉ። ነገር ግን በሽታው ቀድሞ ሳይከሰት ራስን ከሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መጠበቅ ከበሽታው ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ ይጠቅማል።
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክቶች ምንድናቸው
- አንዳንዴ ምልክት ላያሳይ ይችላል፤ ካሳዩ ግን ምልክቶቹ እነዚህን ይመስላሉ።
- -በመጠን አነስተኛ ግን በተደጋጋሚ ሽንት መሽናት
- -ደመናማ የመሰለ የሽንት ከለር
- -የሽንት ከለር መቀየር – ቀይ፣ ሮዝ ወይም ጠቆር ያለ ሽንት – ከሽንት ጋር የደም ምልክት
- -ያልተለመደ ጠንከር ያለ የሽንት ሽታ
- -ማህፀን አካባቢ የሚሰማ የመጫን ህመም (ለሴቶች) ወይም ወንዶች ብልታቸው አካባቢ እና የሽንት ፊኛ አካባቢ የሚሰማ ህመም
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መንስኤዎች
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ባክቴሪያ ወደ ሽንት ቧንቧ ገብቶ በሚራባበት ጊዜ ነው። የሽንት ስርዓታችን በተፈጥሮ ባክቴሪያዎችን እንዲያስወግድ የተሰራ ቢሆንም አንዳንዴ ተፈጥሯዊው መከላከያ መንገድ አሰራሩን በማሸነፍ ባክቴሪያዎች ወደ ሰውነታችን ገብተው በሽታ ሊያመጡ ይችላሉ።
በተፈጥሮ የብልቶቻችን አቀማመጥ የተነሳ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የበለጠ የተጋለጡ ናቸው። የግብረ ስጋ ግንኙነት ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሴቶችን በተለይ የበለጠ ተጋላጭ ሊያደርግ ይችላል። ሴቶች በተለይ ባላቸው የሰውነት አቀማመጥ (Female anatomy) ምክንያት በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት፣ በማህፀን ውስጥ በሚቀመጡ አንዳንድ የወሊድ መከላከያዎች እንዲሁም የሴቶች ማረጥ (Menopause) ጊዜ የበለጠ ለሽንት ቧንቧ እንፌክሽን ከፍተኛ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
ሌሎች የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እንዲባባስ የሚያደርጉ ነገሮች
- ጤናማ ያልሆነ የሽንት ቧንቧ ኖሯቸው የሚወለዱ ህጻናት የሽንት ቧንቧ መደፈን፦ ይህም በኩላሊት ጠጠር ምክንያት ወይም መጠኑ ከፍ ያለ ፕሮስቴት (prostate) ምክንያት ሊመጣ ይችላል።
- የበሽታ መከላከያ ስርዓት መጎዳት፦ ለምሳሌ በስኳር በሽታ ምክንያት – ተፈጥሯዊው በሽታ መከላከያ ብቃት እንዲቀንስና ጀርሞችን እንዳንከላከል በማድረግ ለኢንፌክሽኑ ተጋላጭ እንድንሆን ያደርጋል።
- አርቴፊሻል የሽንት ቱቦ (ካቴተር) የሚጠቀሙ ህመምተኖች
- የሽንት ፊኛ፣ ፕሮስቴት ወይም የኩላሊት ቀዶ ጥገና ያደረጉ ሰዎች ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የበለጠ ተጋላጭ ናቸው ::
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ከበረታ ምን አይነት ችግር ሊያመጣ ይችላል?
የታችኛው የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በአግባቡና በጊዜ ከታከመ ለክፉ አይሰጥም። ካልታከመ ግን ከባድ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል። እነዚህም
- -ተደጋጋሚ ኢንፌክሽኖች
- -ከፍተኛ የሆነ የኩላሊት ኢንፌክሽን እና መዳከም
- -ነፍሰጡሮች ላይ ከተከሰተ ደግሞ የሚወለደው ህጻን መጠኑ ከሚገባው ያነሰ ወይም ያለጊዜው ሊወለድ ይችላል።
- -ለህይወት አስጊ የሆነ እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ኢንፌክሽን ነው፤ በተለይ ወደ ኩላሊት የሚዛመት ከሆነ። አደገኛ ሊሆን ይችላል።
ታድያ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መከላከያ መንገዶች ምን ምን ናቸው
-በቂ ውሃ መጠጣት። ውሃ መጠጣት ሽንትን ይበርዛል፤ እንዲሁም ቶሎ ቶሎ እንድንሸና በማድረግ ባክቴሪያው ኢንፌክሽን ሳያመጣ ከሽንት ቧንቧ እንዲወርድ ያረጋል።
-ሽንት ከሸናን በኋላ ከፊት ወደ ኋላ መጠረግ፦ ከተጸዳዳን በሁላ ከፊት ወደ ኋላ መጥረግ ባክቴሪያዎች ከመቀመጫ አካባቢ ወደ ብልት እንዳይሄድ ያደርጋል።
-ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ የሽንት ቧንቧ አካባቢን ማጽዳት፤ እንዲሁም አንድ ብርጭቆ ውሃ በመጠጣት ባክቴሪያው እንዲወገድ ማድረግ
-የሴቶች የተለያዩ የብልት ማጽጃዎች እንደ ዴዎድራንት ፓውደር እና ዶቸስ (douches) አለመጠቀም። እነዚህ አይነት ማፅጃዎች ባክቴሪያ ወደ ሽንት ቧንቧ እንዲገባ እድል ይፈጥራሉ፡፡
-የወሊድ መከላከያ መንገዶችን መቀየር ካለብዎት ከሐኪምዎ ጋር ይማከሩ፣ በተለይ ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሚያጠቃዎት ከሆነ። እንደ ዲያፍራም (Diaphragm) ወይም spermicide-treated ኮንደሞች ለባክቴሪያ እድገት አስተዋፅኦ አላቸው።
-በጊዜ ሐኪምዎን ያማክሩ፣ መድሃኒት ከታዘዘልዎት በአግባቡ ይውሰዱ ይላሉ።
ጤናችን በእጃችን ነውና መከላከያ መንገዶችን በመጠቀም ጤናችንን መጠበቅም ለሀገርም ሆነ ለግለሰቡ ጠቀሜታው የላቀ ነው።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2013