ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ ዘመናትን ያስቆጠረው አሁንም የጀርባ አጥንት መሆኑን አጠናክሮ የቀጠለው የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኗል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለቡና ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱ ዘርፉ ከዕለት ዕለት እየተሻሻለ የመጣና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው መንገድ እየደገፈ ይገኛል። ቡናን በማልማት ከሚታወቁት በርካታ አርሶ አደሮች በተጨማሪም ጥቂት የማይባሉ ባለ ሃብቶችም በቡና ኢንቨስትመንት ተሰማርተው ጥሬ ቡናን ከመላክ ጀምሮ እሴት ጨምረው ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ። እነዚህ ባለሃብቶችም የሚያስገኙት የውጭ ምንዛሪ በሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ አለው።
በቡናው ዘርፍ ተሰማርተው ከፍተኛ ድርሻ እያበረከቱ ከሚገኙ ቡና አምራችና ላኪዎች መካከል ዶክተር ሁሴን አምቦ የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ናቸው። ዶክተር ሁሴን አምቦ የኢትዮጵያ ቡና አልሚዎች አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንትና የኢዩ ካፌ የግብርና ፕሮጀክት ኮሚቴ አባልም ናቸው። በግላቸው ቡናን ከማምረት ባለፈ በሙያቸው ዘርፉን በመደገፍ የጎላ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ። ዶክተር ሁሴን መሰረታቸው ቡና አብቃይ ከሆኑ የሀገሪቷ ክልሎች አንዱ በሆነው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ነው።
በቡና ውስጥ ተወልደው በቡና ውስጥ ያደጉት ዶክተር ሁሴን በቡናው ዘርፍ ጥልቅ ዕውቀትና ዘመን ያስቆጠረ ቁርኝት አላቸው። ከዚህ የተነሳም ቡናን በግላቸው አምርተው ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ በዘርፉ በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። በተለይም በሙያቸው የቡና ምርት እንዲጨምርና የገቢ ምንጭነቱን ዘለቄታዊ ባለው መንገድ መቀጠል እንዲችል ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው። በሙያቸው በሚያደርጉት ድጋፍም እርሳቸውን ጨምሮ ቡና አምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።
ቡና በስፋት በሚመረትበት አካባቢ ብሎም ቡና አምራች ከሆነ ቤተሰብ ተገኝተው በቡና ምርት ውስጥ ያደጉት ዶክተር ሁሴን ወላጅ አባታቸውን ተክተው ወደ ዘርፉ የተቀላቀሉት ከወጣትነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ነው። በአሁን ወቅትም በግላቸው የሚያመርቱትን ስፔሻሊቲ ቡና በቀጥታ ወደ ውጭ ሀገር ገበያ በመላክ ግብይት መፈጸም የቻሉ አምራችና የዘርፉ ባለሙያ ናቸው። በዘንድሮው ዓመት ብቻ በ90 ሄክታር መሬት ላይ ያመረቱት ስፔሻሊቲ ኮፊ በውጭ ገበያ በከፍተኛ ዋጋ መሸጥ ችሏል።
ዶክተር ሁሴን በሚያመርቱት ደረጃውን የጠበቀ ስፔሻሊቲ ቡና የውጭ ገበያውን ሰብረው መግባት ችለዋል። ቡና ውስጥ ተወልደው ቡና ውስጥ በማደጋቸው ስለ ቡና ምንነት በጥልቀት እንዲያውቁ አስችሏቸዋል። ስለሆነም ገበያው በሚፈልገው የጥራት ደረጃ የቡና ምርት ለማዘጋጀትና ቡናው ጥራቱን እንዲጠብቅ በማስቻል ስፔሻሊቲ ቡና ለውጭ ገበያ እያቀረቡም ይገኛሉ። በዘንድሮው ዓመትም አንድ ኮንቴነር ደረጃውን የጠበቀ ስፔሻሊቲ ቡና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የተሻለ ክፍያን አግኝተዋል። በዚህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን ከእርሳቸው አልፎም ሀገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት የድርሻቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በቡና እርሻ የተሰማሩት ዶክተር ሁሴን፤ በቡና ላይ ባላቸው የዳበረ ዕውቀት በሀገሪቱ የቡና ምርት እንዲሻሻልና በማንነቱ ዕውቅና አግኝቶ የጥራት ደረጃውን ከፍ ማድረግ እንዲችል የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉም ይገኛሉ። በዚህም የቡና ምርትና ምርታማነት ጨምሮ በከፍተኛ ጥራት ለዓለም ገበያ እንዲደርስ በተለይም ከግብርና ሚኒስቴር እና ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በጋራ በመሆን ይሰራሉ። በግላቸው ከሚያመርቱት ምርት በተጨማሪ እንደ ማህበሩ ሀላፊ ሙያቸውን ተጠቅመው በቅርበት ያገለግላሉ።
በተለይም በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ላይ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም እንዲታወቅ ገበሬዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የሚገባቸውን በሙሉ በማድረግ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። በመሆኑም በሀገሪቱ ያለው የቡና ምርት ጥራቱን ጨምሮ ማንነቱን ይዞ ለዓለም ገበያ ተደራሽ እየሆነ ይገኛል። በግላቸው በሚያመርቱት ምርት፣ የቡና እርሻ እንዲሁም በሙያቸው የሚያገለግሉት ዶክተር ሁሴን፤ በቋሚ እና በጊዜያዊ ከ200 በላይ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። የሥራ ዕድሉ በተመለከተ በኮንትራት የሚቀጥሩት የሠራተኛ ቁጥር በተለያየ ጊዜ ማለትም እሸት ቡና በሚለቀምበት እና በሚፈጭበት ወቅት የስራ እድሉ ሰፋ ይላል።
ከቡና ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ዶክተር ሁሴን፤ ቡናን አልምቶ ወደ ገበያ ከማቅረብ ባለፈም ያመረቱትን ቡና ሂደቱን አጠናቅቆ በቀጥታም ይሁን በምርት ገበያ አማካኝነት ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚያስችሉ ትላልቅ ማሽኖች አሏቸው። በመሆኑም የቡና መፍጫ ማሽኖችን ተጠቅመው ጀንፈል ቡና ወይም ደረቅ ቡናን ወደ ቀሽር ይቀይራሉ። ወይም ይፈጫሉ። የተፈጨው ወይም የተቀሸረው ቡናም ተለቅሞ ለጨረታ ይቀርባል። በዚህ ጊዜ በርካታ ጊዜያዊ ሰራተኞችን ያሳትፋሉ። ደረቅ ቡናን ወደ ቀሽር መቀየር በሚችለው ማሽን ሌሎች ቡና ነጋዴዎችም አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ጀንፈል ቡናን ሰብስበው በመፍጨት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን በዚህም ሌላ ገቢ ያገኛሉ።
ዶክተር ሁሴን ከገቢው በበለጠ የቡናው ዘርፍም ሂደቱን አጠናቅቆ ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ ገበያ እስኪቀርብ ድረስ ምን እንደሚያስፈልገው ያውቃሉ። በሂደቶች ውስጥም ጥራቱን ጠብቆ እንዲቀርብና የተሻለ ገቢ ማምጣት እንዲችል ሌሊት ከቀን በብርቱ ይተጋሉ። ዶክተር ሁሴን በዕድሜ ገፋ ያሉና ድካም የተጫናቸው ቢመስሉም ስለ ቡና ሲያነሱ እጅግ በላቀ ፍላጎት፣ ዕውቀትን መሰረት ባደረገና በተስፋ ተሞልተው ነው።
የግብርና ሥራን ከቤተሰብ የወረሱት ቢሆንም ባለቤታቸውም ጠንካራ ገበሬ መሆናቸውን ይናገራሉ። ይሁንና ባለቤታቸው የሚያመርቱት ከቡና ውጭ የተለያዩ ምርቶችን ሲሆን እርሳቸው ግን በ90 ሄክታር መሬት ላይ ቡና ብቻ ያመርታሉ። የእርሳቸው ልጆች ግን ወደ ግብርናው የመግባት ዝንባሌ የሌላቸው መሆኑን አጫውተውናል። ለዚህም ምክንያቱ የግብርና ሥራ አድካሚ በመሆኑና የዘመኑ ልጆች ደግሞ ብዙ ድካም ስለማይፈልጉ ነው ይላሉ።
የቡናው ዘርፍ አሁን ካለበት ደረጃ በበለጠ ከፍ ያለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችልና ሀገሪቷም ከዘርፉ በሚገባት መጠን መጠቀም እንድትችል ዶክተር ሁሴን ብዙ ጥረት ያደርጋሉ። የቡናው መስክ በአንዳንድ ክልሎችና በወረዳዎች እራሱን ችሎ ብቻውን የልማት ቢሮ ኖሮት እየተሰራ መሆኑንም ነግረውናል። ነገር ግን ጥቂት በሚባሉ አካባቢዎች ደግሞ በክልሎችም ይሁን በወረዳ በግብርና ሥር ተካትቶ ይሰራል። ይህ አሰራር ዘርፉ የሚፈልገውን ያህል ትኩረት ይነፍገዋል። ስለዚህ ቡናውን ከግብርናው ጋር በማዋሀድ ለቡናው መስክ ትኩረት ቢሰጥ እና አርሶ አደሩም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ይመክራሉ።
የቡና ሥራ በሀሳብ የሚሰራ ሳይሆን በተግባር በምርምር ተተርጉሞ የሚሰራ ነው የሚሉት ዶክተር ሁሴን፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለቡናው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በሙሉ በማሟላትና ሂደቱን ጠብቆ እንክብካቤ በማድረግ ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለውን የቡና ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንዲቻል ትኩረት ተሰጥቶት ቢሰራ መልካም እንደሆነ በማንሳት አርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የጎላ ነው ይላሉ ።
በደርግ ዘመነ መንግስት ቡናና ሻይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በነበረበት ወቅት ቡና ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ እንደነበር የሚያነሱት ዶክተር ሁሴን፤ ደርግ ከወደቀ በኋላ ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ ቡና እንደ አንድ ዘርፍ ለግብርና ተሰጠ። ግብርናውም ብዙም ትኩረት ያላገኘ ዘርፍ ስለነበር በወቅቱ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች በሙሉ አዝነው ነበር። አሁን ደግሞ ቡና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያ ላይ ያለውን አስተዋጽኦ በመረዳት ወደ ቀደመው ስሙ እየተመለሰ ይገኛል። በመሆኑም ቡናን በጥራት ለመጠበቅ፣ የቡናን ምርትና ምርታማነት ከፍ ለማድረግና በቡናው ዘርፍ የተሰማሩትን አርሶ አደሮች ኑሮን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የቡናን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ካሉት ሥራዎች መካከል፤ ግብርና ሚኒስቴርና ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከአውሮፓ ህብረት ጋር በጋራ በመሆን የሚሰሩት ፕሮጀክት አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ በተለይም ቡና አምራች ለሆኑ አርሶ አደሮች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። በቅርቡም 15 ሚሊዮን ዩሮ የሚሆን ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ በሀገሪቱ ቡና አምራች በሆኑ 28 ወረዳዎችን ያካተተ ፕሮጀክት ተቀርጾ የድጋፍ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል።
መንግስት ለቡናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት የሚበረታታ በመሆኑ ዘርፉ በተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። በተለይም በሀገሪቱ የሚገኙት ስድስት የቡና ማህበራት አንድ የኢትዮጵያ ቡና ማህበራትን መስርተው የግሉ ዘርፍም ወደታች ወርዶ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ጥራት ያለውን ቡና የማምረት የመጨረሻውን ግብ ማሳካት ይገባል። መንግስትም ሆነ ዩኒየኑ የሚፈልገው የግሉ ዘርፍ ተጠናክሮ በቡናው ምርት የተሻለ አምራች በመሆን ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ በመላክና እሴት በመጨመር ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።
መንግስትን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት በሚያደርገው ድጋፍ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ባሉበት በዚህ ጊዜ ቡና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዋልታና ማገር መሆኑን አረጋግጧል። ይህን አጠናክሮ በመቀጠል የአርሶ አደሮችን ሕይወት ማሻሻል ይገባል። ቡና የሀገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን የበለጠ ተሸክሞ እንደሚወጣ ያምናሉ።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ እንደመሆኗ ከስም ባለፈ በብዙ ልንጠቀምበት እንደሚገባና ለዛም በዘርፉ ሰፊ ሥራ መስራት የሚገባ እንደሆነ በማመን የሚንቀሳቀሱት ዶክተር ሁሴን፤ ኢትዮጵያ በቡና ከምትታወቅበት በላይ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንድትሆን መስራት ያስፈልጋል ይላሉ። በውጭው ዓለም የኢትዮጵያ ጥሬ ቡና እሴት ጨምሮ ስሙን ቀይሮ ለገበያ የሚሸጥ መሆኑ የሚቆጫቸው ዶክተር ሁሴን የቀጣይ ዕቅዳቸውም በማሳቸው ላይ የሚያመርቱትን ቡና እሴት ጨምረው በማዘጋጀት ወደ ውጭ ገበያ መላክ ነው። በዚህ ጊዜ ጥሬውን በመላካቸው ሲያጡት የነበረውንን መጠሪያ ስም ማስመለስ እንደሚቻል ያምናሉ። ከዚህም በላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ በመሆን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መደገፍ ይቻላል።
ዶክተር ሁሴን ተወልደው ባደጉበት ነንሰቦ ወረዳ ስፔሻሊቲ ቡና በከፍተኛ መጠን የሚመረትበት እንደመሆኑ አርሶ አደሩ ጥሬ ቡና ከመላክ ባለፈ እሴት ጨምሮ መላክ እንዲችል ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆኑን ይናገራሉ። ከእሳቸው እምነት ባለፈም የተማሩ አርሶ አደር እንደመሆናቸው በአካባቢያቸው ላሉ አርሶ አደሮች ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋሉ።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2013