አንዳንድ ተፈጥሯዊ ባህሪዎቻችን በእያንዳንዱ ሰው ላይ የሚንጸባረቁበት ደረጃ የተለያየ ነው። ይህም ሆኖ እነዚህ ባህሪዎቻችን ከልክ በላይ ሲሆኑና ወደሌሎች ሲሸጋገሩ እኛንም ሌሎችንም ለችግር የሚዳርጉበት አጋጣሚ አለ። ለመሆኑ ንዴት ምንድን ነው ? በውስጣችን የሚፈጠርን ንዴት እንዴት መቆጣጠር እንችላለን? ስንል የዘወትር ተባባሪያችን የሆኑትን የማህበራዊ ሳይንስ አመራርና ባለሙያ አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ቁጣ ከመበሳጨት ቀድሞ የሚፈጠር ሲሆን ከስሜታዊ መሆን፣ ከአካላዊ መረጃ መጠንና አይነት አንጻር የሚሰፈር ነው፡፡ ስለዚህ ለማንፈልገውና ለምንጠላው ነገርና ሁኔታ አልያም ለሆነውና ለሚሆነው የምናሳየው ግብረ መልስ የቁጣ ስሜት ይባላል፡፡ ቱግ ያልንበት ወይም ፈንድቶ ድንገት የተፈጠረው ቁጣችን ደግሞ ቆይታው ረዝሞ ሲነድ ወደ ንዴትነት ያድጋል፡፡ ንዴታችን ደግሞ በእውቀት፣ በምክንያትና በተሞክሮ ተደግፎ በውስጣችን ሲቆይ በውጤቱ ብስጭትን ይወልዳል፡፡ በዚህም ቁጣችን ሲነድ ንዴትን ሲወልድ፤ ንዴታችን ደግሞ ሰንብቶ ብስጭትን መበሳጨትን ያመጣብናል፡፡ እናም ቁጣ ወደ ንዴት፤ ንዴት ደግሞ ወደ ብስጭት ያድጋል ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ቁጣ ጠቃሚ የስሜት ዓይነት ሲሆን፤ ለምሳሌ ነገሮችን ወይም ሁኔታን ለማስተካከል፣ ለመመለስ ወይም ለመቀየር ያገለግላል፡፡ ይህም ልጆችን ለማሳደግ፣ ቤተሰብን መልክና ስርዓት ለማስያዝ ወዘተ ይጠቅማል ማለት ነው፡፡ ሆኖም ትልቁ ችግር ቁጣን ሳንቆጣጠረው ከመጠን አልፎ ንዴትና ከዚያም ብስጭትን ሲወልድ ነው፡፡
መንስኤዎች
የህክምናው ሳይንስ የቁጣ መንስኤዎችን ውጫዊና ውስጣዊ በማለት ለሁለት ይከፍላቸዋል። ለውስጣዊ መንስኤ የጭንቀት ስሜት፣ የረሃብ ስሜት፣ ከአሰቃቂ ገጠመኝ በኋላ የሚፈጠር ጭንቀት፣ ከፍተኛ ድካም፣ አልኮልና አደገኛ እጽ አለአግባብ መውሰድ፣ ራስን መግለጽ አለመቻል፣ የአንጎል ተግባራት ሚዛን መዛባት፣ ፊዚዮሎጂያዊ – ብዙውን ጊዜ ለሴቶች በወር አበባ ጊዜ፣ በእርግዝና ወቅት፣ የድህረ ወሊድ ሁኔታ፣ ማረጥ፣ ከቪታሚኖች እጥረት፣ በነርቭ ስርዓት ላይ ከመጠን በላይ ተጽዕኖ ሲደርስ፣ የምንጠቀመው መድሃኒት የጎንዮሽ ተፅዕኖ ወዘተ የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ውጫዊ መንስኤ የሚባሉት ደግሞ የተሳሳቱ የሰዎች ዕርምጃዎች፣ የትራፊክ መጨናነቅ፣ እልቂት ወይም መጎዳት/ መበደል፣ ጫና ሲደረግብን፣ በስህተት ስንወቀስ፣ የዓለምን እውነታዎች መቀበል ካለመቻል፣ ማህበራዊ ችግሮችን መቋቋም አለመቻል፣ ድንገተኛ የአየር ለውጥ፣ አለአግባብ የሆነ ትችት፣ ቅናት ወይም ምቀኝነት፣ የቤተሰብ ችግር፣ የተደበቀ ግጭትና የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡
በተጨማሪም ሌሎች የህክምና ጠበብት ብስጭት በስነልቦናዊ እና አካላዊ መንስኤዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ያስቀምጣሉ። ስነ ልቦናዊ መንስኤ የሚባሉት ጭንቀት፣ ውጥረት፣ ኦቲዝም፣ ድብርት፣ ባይፖላር ዲስኦርደር፣ ስኪዞፈሪንያ ወዘተ ናቸው፡፡ አካላዊ መንስኤ የሚባሉት ደግሞ እንቅልፍ ማጣት፣ ዝቅተኛ የደም ስኳር፣ የጆሮ በሽታ፣ የጥርስ ህመም፣ አንዳንድ የስኳር በሽታ ነክ ምልክቶች፣ የተወሰኑ የመተንፈሻ አካላት ችግር፣ ጉንፋን ወዘተ ናቸው፡፡
ምልክቶች
የድምፅ መጠን መለወጥና መጨመር፣ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ጥርት ያሉ ይሆናሉ፣ የዓይኖች ኳስ እንቅስቃሴ መፋጠንና መቅላት፣ የአፍ ውስጥ ምሰሶ መዳከም፣ የምራቅ መድረቅ፣ መዳፍንና አንዳንድ ቦታዎች ለምሳሌ አፍንጫን ማላብ፣ የአተነፋፈስ ስርዓት ለውጥ በማድረግ በጣም መፍጠን፣ የአካል መንቀጥቀጥ፣ የፊት ቆዳ መንጣት ወይም ፍም መስሎ መቅላት፣ መናገር አለመቻል ወይም ንግግርን ማቆም፣ ማቅለሽለሽ፣ ለሴቶች ያልተለመደ የወር አበባ ኡደትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ጉዳቱ
ስር የሰደደ የህመም መባባስ፣ እንቅልፍ እጦት፣ የሆርሞናዊ ዳራ መለወጥ መጀመር፣ በሽታ የመከላከል አቅም መቀነስ፣ አለርጂ፣ ኢንፌክሽኖች፣ የምግብ አለመቻቻል፣ የአዕምሮ ህመም፣ ስትሮክ፣የቆዳ በሽታ፣ ከፍተኛ የራስ ምታት ህመም፣ ነስር በአፍና በአፍንጫ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት ወይም ማነስ፣ ወንጀል ለመፈጸም ይዳርጋል፣ ግንኝነትን ያበላሻል፣ ቶሎ ለማርጀት ይዳርጋል፣ የጀርባ ህመም፣ የልብ ድካም ወዘተ በሚቆጣው ሰው ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ናቸው፡፡
በተጨማሪ በምንቆጣቸው ሰዎች ላይ ደግሞ ጥላቻ፣ አብረውን መሆን አለመፈለግ፣ ሃሳባቸውን መደበቅ፣ ይቆጡናል ብለው ስለሚያስቡ አስመሳይ እንዲሆኑ መዳረግ፣ በተለይ ሕፃናት ወይም ልጆች ለወላጆቻቸው ግልጽና በፊታቸው ነፃ መሆን እንዲሳናቸው ያደርጋል፡፡ ይህም ልጆች አስተዳደግ ላይ አሉታዊ ጉዳት ማስከተሉ የማይቀር ነው፡፡
መፍትሔ
- ከመጠን በላይና በመደበኛነት ተናዳጅ መሆንዎን ከተገነዘቡ ቴራፒስት ጋር መሄድ ይገባዎታል፡፡ እንዲሁም የመበሳጨት መንስኤን ሙሉ በሙሉ ከተገነዘቡ ወይም በቁጣ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ይህንን ችግር በተናጥል መፍታት ይችላሉ፡፡ በመጀመሪያ ለቁጣ መንስኤ የሚሆኑ ሁኔታዎችን ለማስወገድ መሞከር እንዲሁም በውስጣችሁ አሉታዊ ስሜቶችን ከሚያስከትሉ ሰዎች ጋር መገናኝት የማቆም፡፡
- ዮጋ (ምሥራቃዊ ቴክኒኮችን መለማመድ)፣ ማሰላሰልና ራስን- ማሰልጠን የአዕምሮን ሚዛን በማረጋጋት ቁጣን ለመቋቋም ይረዳሉ፡፡
- ተለዋጭ ሥራ ውስጥ መሳተፍ፣ በቂ እንቅልፍ ማገኘት፣ ብዙ ውሃ መጠጣት፣ በቂ አየር ባሉበት ቦታ ማገኘት፣ ጤናማ ምግቦችን መመገብ፣ ቤት ከሆኑ ሲሠሩ ፅዳት ወይም ምግብ ማብሰል የሚችሉ ሲሆን፤ ቢሮ ከሆኑ ደግሞ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ በቀዝቃዛ ውሃ ፊትን መታጠብ፣ገላን መታጠብ፣ ዕረፍት መውሰድ፡፡
- ቂምና በቀልን በመተው ይቅርታ እና ምህረት ማድረግ መቻል ተመካሪ ነው፡፡
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2013