አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርስቲ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ በእንዲህ እያለ ዘንድሮ አዲስ ከሚገቡ ተማሪዎቹ መካከል ከ23 ሺህ በላይ ተማሪዎች ቅሬታን እንዳስተናገደ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር። ከምደባ ጋር ተያይዞ ከቀረቡት አጠቃላይ ቅሬታዎች ከ1 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ የምደባ ማስተካከያ ተደርጎላቸዋል የሚለውን መረጃ ይዘን ወደ ዋናው ነጥባችን እንሻገር። አዲስ ገቢ በሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከምደባ ጋር ተያይዞ ቅሬታ እንዲያነሱ ያስገደዳቸው ምክንያት ምን ይሆን?
በሁላችንም አዕምሮ የሚመላለስ ጥያቄ መሆኑ አይቀሬ ነው።በዚህ ደረጃ ቅሬታዎች የተወለዱት በዩኒቨርሲቲዎች ከሚታዩ ተደጋጋሚ ግጭቶች እንደሆኑ በተለያየ መልኩ ያገኘኋቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። ታዲያ ዩኒቨርሲቲዎቻን በዚህ ደረጃ የጠፋውን እምነት ለመመለስ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ይጠበቃል።
በተቋማቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሠላማዊ ለማድረግ በቂ ዝግጅት አድርገናል! የሚሉ የጋዜጣዊ መግለጫዎች ጋጋታዎችን ሣይሆን ተጨባጭ ስራዎችን ሰርቶ ማሳየትን እንደሚጠይቅ እሙን ነው። ̋ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድብ ነውና ተረቱ፤ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ለመፍትሄው ትኩረት መስጠት ከቻሉ እንደ ተቋም ብቻ ሳይሆን ለሀገር የሚተርፍ ሠላም፣ ፍቅር፣ አንድነት የዋጀ እውቀትን በመስጠት ይኼንኑ የማሳየት አቅም አላቸው። ለዚህ ደግሞ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮ መውሰድ ይገባል። የዩኒቨርሲቲው ተሞክሮ በተመለከተ ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቤተሠብ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ታደሰ እንደሚከተለው ያስቃኙናል። መልካም ንባብ።
“የጎንደር ቤተሠብ ፕሮጀክት” ሀሳብ ውጥን በሀገር የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ ቢደረግ ትልቅ ውጤት ማምጣት የሚያስችል መሆኑን በተግባር የታየው “የጎንደር ቤተሠብ ፕሮጀክት” ሀሳብ ያመነጩት የቀድሞው የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ሥዩም ናቸው። ኢንጂር ማስተዋል የተለያዩ የውጪ ሀገራት ተሞክሮ ለትምህርት ሄደው የተመለከቱትን በእኛም ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ ብናደርግ? የሚል መነሻ ሀሳብ በጽሁፍ አዘጋጅተው አቀረቡ። ይኼ ዓይነት አሰራር በሌላው ዓለም በተለይም በአውሮፓ የቆየና የተለመደ አሰራር ነው።፡ በውጪ ሀገራት የሚማሩ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዎች ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ለተማሪዎቻቸው ወላጆች እንዲሰጣቸው በማድረግ ለተማሪዎች ድጋፍና ክትትል ያደርጉላቸዋል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው፣ ከአካባቢያቸው ርቀው የሄዱ ሳይመስላቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያግዛል። ኢንጂር ማስተዋል በውጪ ሀገር በትምህርት ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ፤ እንዲህ ዓይነቱን በጎ ልምድ ተግባራዊ ማድረግ ቢቻል መልካም እንደሆነ በማሰብ ንድፈ ሀሳብ አዘጋጁ። በጽሁፍ ያዘጋጁትን ንድፈ ሀሳብ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ አመራሩ አቀረቡ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በርካቶቹ በውጪ ሀገር የተማሩ እንደመሆናቸው ለሀሳቡ እንግዳ አልነበሩምና ኢንጂነር ማስተዋል ያቀረቡትን ንድፈ ሀሳብ በመቀበል ነበር ተግባራዊ ወደ ማድረጉ የተሸጋገረው። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቤተሠብ ፕሮጀክት ሃሳብና ውጥኑ ይህን በመሰለ መልኩ ተወጥኖ በ2012 ዓ.ም ተግባራዊ ሊደረግ የቻለው።
ፕሮጀክቱ ይዞ ት የተነሳው ዓላማ
“የጎንደር ቤተሠብ ፕሮጀክት” የተለያዩ ዓላማዎች የያዘ ሲሆን፤ በዋነኛነት በዩኒቨርሲቲው ምቹ፣ ሠላማዊና የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደትና የምርምር አካባቢን መፍጠር፤ ወደ ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች አካባቢዎች ለመጡ ተማሪዎች ‹‹የቃል ኪዳን ቤተሠብ›› በማገናኘት፣ ተማሪዎቹ ከአዳዲስ ቤተሠቦቻቸው ጋር ሆነው በጥሩ መንፈስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ ነው። ሌላው ዓላማ በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለውን የወንድማማችነት ትሥሥርን የማጠናከር ዓላማ ተሰንቆ ነበር ወደተግባር የተገባው።
በቅንጅት ወደ ተግባር ሽግግር በኢንጂር ማስተዋል የቀረበው ሀሳብ ተቀባይነት አገኘ። ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ ቀጣዩ ምዕራፍ የነበረው በምን መልኩ ተግባራዊ እናድርገው የሚለው ነበር። ከተማ አስተዳደሩና ዩኒቨርሲቲው በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገው፤በተቀናጀ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደረሰ። ሁለቱ አካላት የሥራ ድርሻ በመከፋፈል እንቅስቃሴው ተጀመረ። ለዚህም ደግሞ ኮሚቴ እንዲቋቋም አደረጉ።
በከተማ አስተዳደሩ በኩል ማሕበረሰቡን ለማስተባበር ከህብረተሰቡ አንድ ኮሚቴ፣ በተመሳሳይ ከዩነቪርሲቲው ማህበረሰብም አንድ ኮሚቴ እንዲዋቀር ተደረገ። በዚህ መሠረት የከተማው ኮሚቴ ኃላፊነት የሚሰማቸው የቃል ኪዳን ወላጆችን የመለየት ሥራ፣ የዩኒቨርስቲው ኮሚቴ ደግሞ ፈቃደኛ የሆኑና ዓላማውን የሚደግፉ ተማሪዎችን የመለየት ሥራዎች እንዲሰራ ተደረገ። የኮሚቴው የመጀመሪያ ተግባር የነበረው በፕሮጀክቱ የሚሳተፉ ቤተሠቦችን ለመመልመል የሚያስችለውን መስፈርት ማውጣት ነበር። በአቅጭር ጊዜ ውስጥ መስፈርቶቹን ያወጣ ሲሆን፤ ልጆች ያሏቸው መሆን፣ ባለትዳር የሆኑ፣ ቤተሠብ ያሏቸው፣ በሥነ – ምግባራቸው የታወቁ ሰዎች፣ አርዐያ የሆኑ ቤተሠቦች መሆን እንዳለባቸው በመስፈርትነት አስቀመጠ ። በመሆኑም ቀድመው ‹‹የቃል ኪዳን ልጅ እንፈልጋለን፣ ኃላፊነት እንወስዳለን›› ብለው የጠየቁ ቤተሠቦች ተመለመሉ። በተመሳሳይ የተቋቋመው ኮሚቴ የቃል ኪዳን ቤተሠብ ማፈላለግ እና ሌሎች በርካታ እልህ አስጨራሽ ስራዎች ተከናውነው ተጠናቀቁ። በዚህ መንፈስ ውስጥ በመሆን ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ.ም ላይ ደረሰ። ይህ እለት ደግሞ ተማሪዎች በቅርብ የሚያማክሯቸው፣ ለበዓላት እና ለእረፍት ቀናት የሚጠይቋቸው እና ምንም ዓይነት የደኅንነት ሥጋት ሳይገባቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ ከሚያደርጉላቸው ወላጆች ጋር የሚገናኙበት ነበር። በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የመጀመሪያ ዙር አዳዲስ ተማሪዎችን ለቤተሠቦች የመስጠት፣ የትውውቅና ርክክብ ሥነ ሥርዓት 1 ሺህ 500 ተማሪዎች ከአደራ ወላጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ተደረገ። ቀጣይ በተደረገ ሥነ ሥርዓት የቀሩትን 3 ሺህ 500 ተማሪዎችን ከአደራ ወላጆቻቸው ጋር በማገናኘት በ2012 ዓ.ም የገቡ አምስት ሺህ አዳዲስ ተማሪዎችን ከወላጅ ጋር በማገናኘት ስራውን በስኬት ማጠናቀቅ ተቻለ። በዚህ መልኩ ተማሪዎች ፕሮጀክት ከወረቀት ወደ መሬት ማውረድ ተቻለ።
የታየው ምላሽና የነበረው መልክ ቀጣዩ ምዕራፍ የነበረው የተማሪዎች እና የአደራ ቤተሠቦቹ ግንኙነት እንዲሁም የተማሪዎቹ ትክክለኛ ወላጆቻቸው መካከል ያለውን ሥሜት ምን እንደሚመስል ያስመለክተናል። ከተማሪዎች፣ ከተማሪዎቹ እውነተኛ ወላጆች፣ ከማሕበረሰቡ እንዲሁም ከመንግሥት በኩል አበረታች ምላሾች ተገኝቶበታል። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንድ ቤተሠብ ለአንድ ተማሪ ፕሮጀክትን ሲጀምር አምስት ሺህ አዳዲስ ተማሪዎችን በመቀበል እንደሆነ ይታወቃል።
ከአጠቃላይ ተማሪዎቹ መካከል ደግሞ 99 በመቶ ያህሉ፤ ከሌሎች የአገራችን አካባቢዎች የመጡ ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ከፀጥታ ጋር ተያይዞ ሥጋቶች የነበሩ እንደመሆኑ፤ ይህ አሰራር መዘርጋቱ ተማሪዎች ተረጋግተው እንዲማሩ አስችሏቸዋል።
ከአዲሶቹ ቤተሠቦቻቸው ጋር እየተገናኙና እየተወያዩ፣ ትምህርታቸውን በውጤት እንዲያጠናቅቁ በእጅጉ አግዟቸዋል።
በተጨማሪም ተማሪዎች ለአካባቢው እንግዳ እንደመሆናቸውና አዳዲስ ወላጅ ማግኘታቸው፣ አካባቢውን… ባህሉን… አመጋገቡን…
እንዲለምዱ ረድቷቸዋል። ዩኒቨርሲቲ ልጆችን ለመላክ ሲጨነቁና በከፍተኛ ሥጋት ለላኩ ወላጆች ትልቅ እፎይታን መፍጠር መቻሉም ሌላው በጎ ገጽታው ነበር። ስለዚህ ከተማሪዎች ሆነ ከቤተሠቦቻቸው በኩል የነበረው ምላሽ እጅግ የሚያበረታታ ነበር ። በተመሳሳይ ከማሕበረሰቡ በኩል በተመሳሳይ በጎ ምላሽ የተገኘ ሲሆን፤ ‹‹የቃል ኪዳን ወላጆችም›› ከእነዚህ ልጆቻቸው
አዳዲስ ባህሎችን እንዲያውቁ፣ እንዲማሩ ማድረጉን ለመረዳት ችለናል፡፡የፕሮጀክቱ ቀጣይነትና ሀገር አቀፋዊነት የጐንደር ከተማ ሕዝብም፣ ቃል ኪዳኑን ጠብቆ ልጆቹን ለውጤት አብቅቷል፡፡ ስለዚህ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንድ ቤተሠብ ለአንድ ተማሪ ፕሮጀክትን በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል እንደሚገባ ታምኗል።
በመሆኑም በ2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው አዲስ የተመደቡ ተማሪዎችን ለመቀበል ሲደረግ በነበረው ዝግጅት አንዱና ዋነኛው የትኩረት ማጠንጠኛ ነበር። ፕሮጀክቱን በተጠናከረ መልኩ ለመተግበር ከተማ አስተዳደሩ እና ዩኒቨርሲቲው በተቀናጀ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
በተለይ ወላጅ በማፈላለጉ ተግባር ላይ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነበር። በ2013 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲ አዲስ ለሚቀበላቸው ተማሪዎች የቃል ኪዳን ወላጅ ለመሆን 4 ሺህ 500 ወላጆች ማዘጋጀት ተችሏል። በዩኒቨርሲቲው አዲስ የተመደቡ ተማሪዎች 4500 ሲሆኑ፤ አንድ ወላጅ ለአንድ ተማሪ እንዲሆን በተማሪዎቹ ቁጥር ወላጅ እንዲዘጋጅ ተደርጓል። ይህም ዘንድሮ ፕሮጀክቱን ከአምና በተሻለና በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ያሳያል። በአጠቃላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንድ ወላጅ ለአንድ ተማሪ ፕሮጀክት ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ፤ በየዓመቱ የሚመጡትን ከወላጆች ጋር እያገናኘን መጨረሻ ላይ ሁሉም ተማሪ፣ የቃል ኪዳን ወላጅ ይኖረዋልማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምንም እንኳን በአገራችን የመጀመሪያ ቢሆንም፤ ይህን በተግባር ተፈትኖ ውጤት ያመጣውን ፕሮጀክት ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም መውሰድ ቢችሉ ሀገራዊ ትርፍይኖረዋል ባይ ነኝ።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2013