የዓባይን ውሃ በበላይነት ስትጠቀም የኖረችው ግብጽ፣ የታላቁ የኢትዮጵያን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግንባታውን ስትቃወም፣ የሐሰት መረጃዎችን ስታሰራጭ፣ ኢትዮጵያን ስትከስና ስታስፈራራ ቆይታ ዛሬ ላይ ደርሳለች፤ የውሸት መረጃዎቿ፣ ኢ-ፍትሐዊ ክሷና ማስፈራሪያዋ ዛሬም ቀጥሏል።ፍትሐዊነትንና የጋራ ተጠቃሚነት መርሆችን የማታውቀው ግብጽ ‹‹ … ኢትዮጵያ የግብጽን ሕዝብ በውሃ ጥም ልትገድል ነው …›› ከሚለው ተራ የሀሰት ወሬዋ ‹‹ማንኛውንም ዓይነት አማራጭና እርምጃ እወስዳለሁ›› እስከሚለው ዛቻዋ ድረስ የተለጠጠ ማጭበርበሪያና ማስፈራሪያን ስታራግብ ቆይታለች።
በእርግጥም ግብጽ የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ያልሞከረችው ዓይነት አማራጭ የለም።ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለግድቡ የተሳሳተ መረጃ እንዲይዝና በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥር ለማድረግ ላይ ታች ስትል ኖራለች። ከዚህ አልፎም ፖለቲከኞቿን ሰብስባና ምዕራባውያን አጋሮቿን ይዛ ‹‹በግድቡ ላይ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ›› ብላ ነበር።ሰሞኑን የግድቡን ጉዳይ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት (Security Council) በመውሰድ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ እንዲወያይ የማድረጓ ነገርም የዚሁ ጥረቷ አካል ነው።
ከግብጽ በተጨማሪም ጎረቤት ሱዳንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የግብጽ ጋሻ ጃግሬ ሆና ተከስታለች። የሱዳን አቋም አስገራሚ ከመሆን አልፎ አስቂኝ ነው።የኦማር ሐሰን አል-በሺር አገዛዝ ከተገረሰሰ በኋላ መንበሩን የተቆናጠጠው የወታደሮች ስብስብ የሚተነፍሰው በፈርኦኖቹ ሳንባ ስለሆነ የካይሮ አለቆቹ ያዘዙትን ከመፈፀም ውጭ ሌላ አማራጭ ያለው ስላልመሰለውና ሲጠሩት ‹‹አቤት››፤ ሲልኩት ‹‹ወዴት?›› ብቻ የሚል በመሆኑ የአለቆቹን አቋም እያንፀባረቀ ነው።የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ከሚጠቅመው ባላነሰ ሁኔታ ሱዳንንም እንደሚጠቅም ኢትዮጵያም፣ ሱዳንም ግብጽም በደንብ ያውቃሉ።በአጭሩ የሱዳንን ነገር ‹‹ውስጡን ለቄስ›› በሚባለው የአገራችን ተረት እንለፈው።
ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ያሳዩት ትብብርና ድጋፍ በኢትዮጵያ ታሪክ በደማቅ ቀለም ከሚፃፉ አስደናቂ ታሪኮች መካከል አንዱ ነው።በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ፣ በሁሉም የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ፣ በመላው የዓለም ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮያጵውያን የግድቡ ግንባታ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ ለግንባታው ዘርፍ ብዙ ድጋፍ አድርገዋል፤ በአንድነት ቆመዋል።ፖለቲከኞች እንኳ ፖለቲካዊ ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በግድቡ ጉዳይ ላይ ልዩነት አልነበራቸውም።
ሰሞኑን ግብጽ የግድቡን ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት በመውሰድ ግድቡ የቀጣናዊ ብሎም የዓለም አቀፍ የደህንነት ጉዳይ እንደሆነ ለማስመሰል ባደረገችው ጥረት ኢትዮጵያውያን ያሳዩት ትብብር በግድቡ ላይ ያላቸውን አንድነት ካሳዩበት ብዙ አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ሆኖ ታይቷል። ግብጽ ጉዳዩን ወደ ምክር ቤቱ የመውሰድ እቅድ እንዳላት ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ጉዳዩ ግብጽ እንደምትለው የዓለም ሰላምና ፀጥታ አጀንዳ ሳይሆን የኢትዮጵያ ፍትሐዊ የመልማት ጥያቄ እንደሆነ ሞግተዋል፤ ውይይት ይደረግ ከተባለ እንኳ የጉዳዩ ባለቤት በሆኑ አገራት መካከል እንጂ የግድቡን ጉዳይ ወደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት መውሰድ ተገቢ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አሳስበዋል። የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመምከር ማሰቡ በራሱ ተገቢነት የሌለው እርምጃ እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ከቀናት በፊት የፀጥታው ምክር ቤት በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርጎ ነበር።በውይይቱ ላይ ግብጽ የተለመደውን የውሸት ክሷን ጮሃለች … ሱዳንም ከአለቃዋ የተቀበለችውን ቅጥፈት አስተጋብታለች … ፍትሐዊ ጥያቄና እውነት ያላት ኢትዮጵያም ሴራና ውሸት ያልታከለበትን እውነተኛና ሐቀኛ ድምጿን አሰምታለች።ግብጽ የተለመደ ትርኪ ምርኪ ውሸቷን በተናገረችበት መድረክ ላይ ኢትዮጵያ በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሯ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በኩል እውነተኛውን ነገር አቅርባለች።
ሚኒስትሩ በንግግራቸው ‹‹ … የሕዳሴ ግድብ በዓለምም በአህጉራችንም ታሪክ የመጀመሪያው የልማት ፕሮጀክት አይደለም። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገበሬዎች፣ የቀን ሰራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ምሁራን፣ ህፃናት፣ ወጣቶች እና በሁሉም ዘርፎች ያሉ ኢትዮጵያዊያን አሻራቸውን እያሳረፉበት ያለ የልማት ፕሮጀክት ነው። የሕዳሴ ግድብ በመላው ኢትዮጵያውያን ደም፣ እንባ እና ላብ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ነው። እንደ ሕዳሴ ግድብ አይነት ፕሮጀክቶችን መገንባት ተሰደው ከሄዱበት ሃገር በባዶ እግራቸው የሚባረሩ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የሚቀይርም ነው።
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የምትገነባው ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን ወጣት ህዝቧን የኢኮኖሚ ፍላጎቶች ለማሟላት ነው፤ የሥራ ዕድል ፍለጋ በተለያዩ ሀገራት ተሰደው የሚሰቃዩ የኢትዮጵያ ወጣቶች በሀገራቸው ተስፋ ማድረግ እንዲጀምሩ ነው። የህዳሴ ግድብ ያሉብንን የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ለመመለስ ወሳኝ መሳሪያ ነው።
ዛሬ እዚህ ተሰብስበን ያለነው ግብፅ እና ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ላይ ተቃውሞ በማቅረባቸው ነው። እነዚህ ሁለት ጎረቤቶቻችን በዓባይ ወንዝ ላይ ትልልቅ እና መካከለኛ ግድቦችን ገንብተው እየተጠቀሙ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ግብፅ እና ሱዳን ከዓባይ ወንዝ በተጨማሪ ሌላ የውሃ ምንጮችና ክምችት የላትም። የሕዳሴውን ግድብ ስንገነባ ሱዳንንና ግብፅን የመጉዳት አላማ ፈፅሞ የለንም። እኛ ኢትዮጵያውያን ዓባይ ወንዝ ካስተሳሰረን ሱዳናውያን እና ግብፃውያን ወንድሞቻችን ጋር በፍትሐዊነት እንዲሁም በጋራ መርህ ለማደግ የምንሻ ህዝብ ነን። ለናይል ወንዝ ከ77 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሀ አስተዋፅኦ የምታደርግ ሀገር ለኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ጥቂት የውሀ መጠን ሙሌት ብታከናውን የሚገርም አይደለም። ለግብፅ እና ሱዳንም የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲያልቅ የሚያገኙትን ጥቅም በተደጋጋሚ ከማስረዳታችን በላይ ሌላ አሳማኝ ነገር ሊኖር አይችልም።
የቅኝ ግዛት አስተሳሰቦችና ውሎች የአፍሪካን ህዝብ የወደፊት ተስፋ በእጅጉ የሚያጨልሙ ናቸው። የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራትም ይህንን ችግር ተረድተው መፍትሔ ለማበጀት ተንቀሳቅ ሰዋል። የዓባይ ወንዝ ባለቤቶች ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ናቸው። የዓባይ ውሀ ለሁላችንም በቂ ነው። በመሆኑም የግብፅ እና ሱዳን ወንድሞቼን የዓባይን ወንዝ አስመልክቶ ከዚህ የፀጥታ ምክር ቤት ምንም አይነት ውሳኔ እንደማያገኙ ልነግራቸው እወዳለሁ። የሚሻለው ነገር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርቶ ከሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ጋር መወያየት ብቻ ነው።
ግብፅ እና ሱዳን ላለፈው አንድ አመት በህዳሴ ግድብ ላይ የተደረጉ 11 ውይይቶች ላይ አልተሳተፉም። ኢትዮጵያ ግን ዓለም አቀፍ ጫናዎች እየበረቱባትም ቢሆን በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ መድረኮች ላይ ተሳትፋለች። ወደድንም ጠላንም ከአንድ ወንዝ እንደሚጠጡ ጎረቤታሞች በትብብር መስራትን መልመድ አለብን። የሱዳን ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም ሲሉ እንደነበረው የሕዳሴው ግድብ ለሱዳን በእጅጉ የሚጠቅም ነው፤ ለግብፆችም የሚጠቅም መሆኑ ይታወቃል። አንድ ማወቅ ያለብን ነገር አንዳችን እየጠጣን ሌሎቻችን መጠማት የማይገባን መሆኑን ነው።
የፀጥታው ምክር ቤት በልማት እና በኃይል ማመንጫ ጉዳይ ላይ ሲወያይ ይህ የመጀመያው ነው። የምክር ቤቱ ኃላፊነት የፖለቲካና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ መምከር ነው። ቴክኒካዊ የውሀ ጉዳዮችን በዚህ የፖለቲካ ምክር ቤት መወያየት የማይጠቅም እና የተሳሳተ አካሄድ ነው። ይህ ምክር ቤት እንዲወያይ እየተጠየቀ ያለው ‹‹ኢትዮጵያውያን የዓባይን ወንዝ የመጠቀም መብት አላቸው ወይስ የላቸውም?›› የሚለውን ጉዳይ ነው። እስኪ ልጠይቃችሁ፤ ኢትዮጵያውያን ከዓባይ ወንዝ ላይ ውሀ የመጠጣት መብት አላቸው ወይስ የላቸውም?
የአፍሪካ ኅብረት በሕዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገውን የሦስትዮሽ ውይይት በብቃት እያሳለጠ ባለበት በዚህ ወቅት ግብፅ እና ሱዳን ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዳቸው የሚያስገርም ነው። ኢትዮጵያ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግሮች በራሳቸው ለመፍታት ብቃቱ አላቸው ብላ ስለምታምን በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት የሚደረጉ የትብብር ማዕቀፎች ላይ በቁርጠኝነት እየተሳተፈች ነው። በኅብረቱ አደራዳሪነት እየተደረገ ያለውን የሶስትዮሽ ድርድር ትቀጥልበታለች። ከድርድሩም ሁላችንንም የሚያስማማ ነገር እንደምናገኝ እናምናለን … ›› በማለት የሀገራቸውን የኢትዮጵያን አቋም ያስረዱት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ‹‹ … የፀጥታው ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ጣልቃ መግባት የለበትም። ምክር ቤቱ የግብፅና ሱዳንን ጥያቄ ተቀብሎ በሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ በሁሉም ሀገራት መካከል ባሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት ይኖርበታል ማለት ነው። የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ በሕዳሴው ግድብ ላይ የሚያደርገው ስብሰባ የመጨረሻው ስብሰባ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። የፀጥታው ምክር ቤት በአህጉራዊ ተቋም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን የድርድር ሂደት ጣልቃ በመግባት ማደናቀፍ የለበትም … ›› በማለት ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲመለስ በአፅንዖት አሳስበዋል። ከስብሰባው ቀደም ብሎም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳላትና የፀጥታው ምክር ቤት በዓባይ ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጉ ኢ-ፍትሐዊ እርምጃ እንደሆነ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገልፀዋል።
የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሚኒስትሩ ላደረጉት ገለፃ ምስጋናቸውንና አድናቆ ታቸውን ገልፀዋል። የግብጽንና የሱዳንን ኢ-ፍትሐዊ ጥያቄንም በእጅጉ ኮንነዋል።በእውነቱ እንዲህ ዓይነቱ አንድነትና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የመቆም ባሕል የሚመሰገንና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው።ይህ የሚኒስትሩ ማብራሪያና የኢትዮጵያውያን አንድነት የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራት ከውይይታቸው በኋላ ስለጉዳዩ ለሰጡት ምክረ ሃሳብና ለያዙት አቋም መነሻ እንደሆነ አያዳግትም።አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች የምክር ቤቱ አባል አገራት በግድቡ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች በውይይት መፈታት እንዳለባቸውና ሀገራቱ ልዩነቶቻቸውን በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በተጀመረው ድርድር ሊጨርሱ እንደሚገባ ገልፀዋል። ድርድሩ ሶስቱ ሀገራት በ2015 በካርቱም በተፈራረሙት የመርሆዎች ስምምነት መሰረት ሊመራ እንደሚገባም መክረዋል።
በእርግጥ የግድቡ ጉዳይ ውዥንብር የሚፈ ጥር፣ ሴራን የሚጋብዝና ውሸት የሚወራበት አጀንዳ ስላልሆነ ኢትዮጵያ በወንዟ ላይ ግድብ መገንባቷ ይህን ያህል ትግል አያስፈልገውም ነበር። በግድቡ ላይ ፍላጎት (Interest) አለን ያሉት ግብጽና ሱዳን ግን ስለፍትሐዊነት የማያውቁ፣ ከሳይንሳዊ ትንታኔና ማስረጃ ይልቅ ለተራ ምቀኝነትና ሴራ ቦታ የሚሰጡ እንዲሁም የሦስተኛ ወገን ፍላጎትን የተሸከሙ በመሆናቸው ብዙም ጥያቄ ማስነሳት ያልነበረበት ግድብ እስከፀጥታው ምክር ቤት ድረስ አጀንዳ ለመሆን በቃ።ኢትዮጵያውያንም በዚህ ሁሉ የትግል ሂደት ያሳዩት አንድነት የሚደነቅና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መደገም ያለበት ነው።
ከዚህ የግድቡ ትግል መማር የሚቻለው ኢትዮጵያውያን በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይም በጋራና በጽናት ተባብረው መታገል እንደሚገባቸው ነው።ኢትዮጵያውያን በግድቡ ግንባታ ሂደት ያሳዩትን ተሳትፎ እንዲሁም ከግብጽና አጋሮቿ በኩል ስለግድቡ የሚነገረውን አሉባልታ በመቃወም ያደረጉትን ትግል በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይም መድገም ይኖርባቸዋል። ከፖለቲካ ልዩነቶች የላቁ ብዙ አገራዊ ጉዳዮች አሉ። የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ትብብርና አንድነት በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ መተባበርና በአንድነት መቆም ትርፉ ከግለሰቦችና ከቡድኖች በላይ የሆነችውን አገር አሸናፊ ማድረግ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2013