የተወለደው ባሌ ጎባ ነው:: ያደገው ደግሞ ደብረ ዘይት ከተማ። ሥራና ኑሮው ደግሞ አዲስ አበባ:: እስከ ስድስት ዓመቱ እንደማንኛውም ታዳጊ ህጻን ቦርቋል፤ ተጫውቷል:: ከጊዜ በኋላ ግን በስህተት ታፋዋው ላይ በተወጋ መርፌ ምክንያት እግሮቹ ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆኑ::
ከዚህ በኋላም ከባዱን የህይወት ውጣ ውረድ ተያያዘው:: በሁለት ክራንች መጓዙና አካል ጉዳተኝነቱ የልጅነት ሕልሙን እንዳያሳካ ሳይገድቡት ዛሬ ላይ ለሌሎች ምሣሌ ሆኖ ከበሬታን ባተረፈለት ሙያ አገርንንና ሕዝብን እያገለገለ ይገኛል:: ትንታጉ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረማርያም::
ልጅነትና ያልታሰበ ፈተና
አካል ጉዳተኛ የሆነው ከስድስት ዓመቱ ጀምሮ እንደሆነ የሚናገረው ጋዜጠኛ ተስፋዬ፤ በልጅነቱ እናቱ የሰው ዓይን ውስጥ እንዳይገባ እያሉ በርሜል ውስጥና መኝታ ቤት ይደብቁት ነበር። ተደብቆ የሚቀር የለምና የኋላ ኋላ ግን ከቤት መውጣት እንደጀመረና በዚህም በአንድ አጋጣሚ ሕመም ተሰምቶት ወደ ሕክምና ተወስዶ በሕክምናው ላይም የተሳሳተ መርፌ ተወግቶ ለአካል ጉዳት መዳረጉን ይናገራል::
ይህ ደግሞ በጊዜው ቤተሠቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳረፈ:: አካል ጉዳት ከደረሰበት በኋላ በቤተሠቡ ላይ የመጣውን ትልቅ ፈተና መቋቋም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበርም ያስታውሳል:: ምክንያቱም ተስፋዬ ለቤተሠቦቹ የመጀመሪያ ልጅ ነበር:: ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ብዙ ቦታ ሄዱ:: ነገር ግን ሊሳካላቸው አልቻለም:: እንዲያውም ቤተሠቦቹ ነገሩን የፈጣሪ ቁጣ አድርገው ይቆጥሩት ነበር ሲል ይገልጻል::
አካል ጉዳቱ ከደረሰበት በኋላ መራመድ አለመቻልን ጨምሮ ብዙ ፈተና አጋጠመው:: በመጨረሻም ወደእምነት ሥፍራ በመሄድ ጤናው ቢመለስለትም እንደማንኛውም ሰው እንዴት መራመድ ይችላል የሚለው ሌላኛው ፈተና ነበር:: ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ ሆስፒታል ሄዶ ለሁለቱም እግሮቹ ቀዶ ሕክምና ተደረገለት:: ከዚህ በኋላ ጠዋት ታስሮ ማታ የሚፈታ የብረት ጫማ እንዲገጠምለት ተደረገ:: ከዚያም ክራንች ይዞ መንቀሳቀስ ጀመረ::
መንሳቀሱ በቤተሠቡ ላይ እፎይታን ቢፈጥርም ፈተናው ግን በቀላሉ የሚገለጽ አልነበረም:: ትምህርት ቤት ገብቶ አጥጋቢ የሚባል ውጤት ማምጣት ተሳነው:: ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቤተሠብ እርሱን ትምህርት ቤት ከመላክ ባሻገር ፍላጎቱ ምን እንደሆነ በትኩረት አለመከታተሉ ነበር:: በተለይ ከትምህርት ጎን ለጎን ያለውን ፍላጎቱን አልተረዱለት:: እርሱ ግን ይህ ለምን ሆነ ብሎ ተሥፋ ሳይቀርጥ ሁሉንም ፈተናዎች እየተቋቋመ ስድስተኛ ክፍል ሲደርስ የአማርኛ ቋንቋ መምህሩ በድምጹ ምክንያት “ጋዜጠኛ እንደሚሆን የተነበዩለት ንግግር እውን ለማድረግ አስቸጋሪውን የሕይወት መስመር በትግል አለፈ::
በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርቱን ተከታትሎ ከጨረሰ በኋላ ራዲዮ ጣቢያዎች ላይ መሥራትና ጋዜጦችና መጽሔቶችን ማዘጋጀት ቻለ:: ከተስፋዬ በኋላ ልጅ አንወልድም ብለው የነበሩት ቤተሠቦቹ ሁለት ወንድሞች ወልደውለታል:: የእርሱን ዓላማና ራዕይ ተረድተው በደስታ ተቀብለውታል::
እርሱም ሕልሙን በመከተል የአካል ጉዳተኞች ድምጽ በመሆን ከአገር ውስጥ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭ ሆኗል:: ለመጀመሪያ ጊዜ የአካል ጉዳተኞችን ደምጽ በፋና ኤፍ ኤም 98.1 ላይ “አንድ ድምጽ” የተሰኘ የአካል ጉዳተኞች የሬዲዮ ፕሮግራምን ለመፍጠር በቅቷል::
ከፋና ወጥቶ ረጅም ዓመት የቆየው ደግሞ ዛሜ 90.7 (የአሁኑ አዋሽ 90.7) “ድርሻችን” የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ነው:: በዚህ ጣቢያ በሣምንት ሁለት ቀናት ፕሮግራም እያሰናዳ ለስምንት ዓመታት ያህል ሰርቷል:: የቦታው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆን ተስፋዬን ቢፈትነውም እጅ ግን አልሰጠም:: እነዚህን ሁሉ ዓመታት ደረጃውን እየወጣና እየወረዳ በጽናት ሥራውን ማከናወን ችሏል::
በጋዜጠኝነት ሙያ ከተለያዩ የህትመት ሚዲያ እስከ ኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለረጅም ዓመታት የሰራው ተስፋዬ፤ በአሁኑ ወቅት በአሃዱ ሬዲዮ 94.3 የአካል ጉዳተኞች የሬዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ሆኖ ይሰራል::
የቲኤፍቲ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተርም ነው:: አብዛኛውን የሚዲያ ሥራ በቅጥር ሣይሆን በራሱ ጥረት የአየር ሰዓት ገዝቶ ነው ሲሰራ የቆየው:: ለዚህ ተስፋዬ ሾው የተሰኘውን በጄ ቲቪ ሲቀርብ የነበረ ፕሮግራም ለአብነት መጥቀስ ይቻላል:: በዚህ ሣይገደብ አንድ የተለየ የአካል ጉዳተኞች ድርጅት የማቋቋምና አካል ጉዳተኞች እንደ ጉዳታቸው ድጋፍ የሚያገኙበትና ሕይወታቸው ተለውጦ የሚያይበት ራዕይ አለው:: ለዚህም ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ገልፆልናል።
የተስፋዬ ውሎ
ብዙውን ጊዜ እረፍቱን ለማንበብ ይጠቀማል:: የሚያነባቸው መጻህፍት ደግሞ እውቀት የሚጨምሩ መሆን እንዳለባቸው ያምናል:: በተለይም መንፈሣዊና ሥነ ልቦና ላይ የሚያጠነጥኑና አነቃቂ መጻሕፍት የጋዜጠኛ ተስፋዬ ምርጫዎች ናቸው:: በሰው ልጅ አዕምሮ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖን በማሳረፍ ሀይል ሊሆኑ የሚችሉ ከአገር ቤት እስከ ዓለም አቀፍ ያሉ መጻህፍትን በማንበብ ጥሩ ጊዜ ያሳልፋል::
ከዚያ ውጭ የእረፍት ጊዜውን ከቤተሠቡ ጋር ማሳለፍም ምርጫው ነው:: “ከቤት መውጣት አልወድም፤ ብዙ ጊዜ ከቤተሠብ ጋር ተቀምጠን ቴሌቪዥን እንመለከታለን:: የምንመለከተው ደግሞ መርጠን ነው:: ለኛ ሊጠቅሙ የሚችሉ ነገሮችን እንጂ አሰስ ገሰሱን አናይም::” ይላል::
ከዚህም ባሻገር ተስፋዬ ያለውን ትርፍ ጊዜ በጎ ነገሮችን በማከናወን ያሳልፋል:: በተለይም ክራንችና ዌልቸር የሚያስፈልጋቸው አካል ጉዳተኞች ይኼን የሚያገኙበትን መንገድ ሳይታክት በመፈለግ ያላቸውን ችግር ከመፍታት አንጻር ሰፊ ሥራዎችን ይሰራል::
ከጓደኞቹ ጋር ስለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በማውጋት ሀሳቦችን መለዋወጥ ተስፋዬ በእረፍቱ ውሎ ውስጥ ከሚያዘወትራቸው ተግባራት ውስጥ ይጠቀሳሉ:: አንዳንድ ጊዜም ከመኖሪያው አዲስ አበባ ከተማ ወጣ ብሎ ዝምታ በሰፈነበት አካባቢ በመሆን ተፈጥሮን በማድነቅ ራስን የማዳመጥ ልምድም አለው:: ይህ ለእርሱ ልዩ መዝናኛው ነው::
“አዕምሯችን ውስጥ መልካም ዘር ከዘራን እናሸንፋለን:: ነገር ግን ሁልጊዜ አካል ጉዳተኝነትን ሰበብ በማድረግ ነገሮችን ወደ መንግሥትና ማህበረሰብ ማላከክ የትም አያደርስም” ይላል:: ትልቁ ነገር አካል ጉዳተኛው ስኬታማ መሆን የሚችለው ከራሱ ጋር ጦርነት ሲከፍት እንደሆነም በመግለጽ ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፎ ሃሳቡን ያጠቃልላል::
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2013