የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዓመቱን ሙሉ ጎብኝዎችን በማስተናገድ ገቢ እንዲያመነጭ ይጠበቃል:: ሆኖም ግን ሥራው ወቅታዊ ነው እየተባለ ተለምዷዊ አሠራር ለዘመናት ሲሰራበት መቆየቱ ይታወቃል:: በመሆኑም ሽርጉዱ ወይም እንቅስቃሴው የሚጀመረው በዚሁ በሚጠበቅበት ወቅት ብቻ ነው:: በዘርፉ ላይ በሚኒስቴር፣ በቢሮ ደረጃ ተቋቁመው የሚሰሩ ተቋማትም ሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱት በዓመት ውስጥ ውስን በሆኑት ቀናት ውስጥ ነው። ይህ ተለምዶ በመቀጠሉ ዛሬ ዓለምን ስጋት ላይ የጣለው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የውጭውን ጎብኚ ሲያስቀረው ዘርፉን በማዳከም ትልቅ ተጽዕኖ ፈጥሯል። አሁን ኪሳራውን ለማካካስ ዋጋ እያስከፈለ ነው:: እንዲህ ያለው ተለምዶ ኮቪድ ተጨምሮበት በተለይም በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ተጽዕኖው ከፍ ያለ ነው:: ቱሪስት ሲባል የውጭው ዜጋ (ፎሪነር) ብቻ ነው የሚለው እሳቤም እንዲሁ ዘርፉን ጎድቶታል::
ቀድሞ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችንና በተለያየ ዓለም የሚኖሩትን ትውልደ ኢትጵያውያንን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቢሆን ኖሮ ተጽዕኖው የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ባልሆነ ነበር:: በኮቪድም ሆነ በተለያየ ምክንያት የውጭ ዜጋው ቢቀር ትውልደ ኢትጵያውያውያኑና ኢትዮጵያውያኑ ዕትብታቸው ከተቀበረበት ትውልድ ሀገራቸው አይቀሩም:: ቤተሰቦቻቸውንና ሀገራቸውን ለማየት ይመላለሳሉ:: ከቆይታቸው ጊዜ የሀገሬውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ቃኝተው፣ የተሰራውንም ሥራ አድንቀው፣ ሀገራቸው ውስጥ በተሰራው ኮርተው፣ ተዝናንተው፣ ለተዝናኑበት በሚያወጡት ወጪ ደግሞ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ አበርክተው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ ቢሰራ ጥቅሙ የጋራ ነው:: ዜጎቹ በሚኖሩባቸው ሀገራት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ያስችላቸዋል:: የሀገራቸው አምባሣደር ሆነውም ለዘርፉ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ:: የውጭ ዜጋ ብቻ በመጠበቅ የሚንቀሳቀሰው የቱሪዝም ኢንዱስትሪም አማራጭ ያገኛል:: በዚህ እሳቤ መንቀሳቀሱ እንደሚጠቅም ብዙዎች ይስማሙበታል::
በተለምዶው አሠራር በአሁኑ ወቅቱ ቱሪስት የሚጠበቅበት ጊዜ አይደለም:: ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታም አልተወገደም:: በጀት ዓመቱም በመገባደድ ላይ ይገኛል:: ያለፈው ተሞክሮ ለአዲስ በጀት ዓመት ምን ዓይነት ትምህርት እንደሰጠ፣ ከወቅታዊው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለመውጣትና ለቀጣይ በጀት ዓመት የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከወዲሁ ስላለው ዕቅድና በተለይም የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማስፋፋት፣ በዓለም ላይ የሚገኙ ኢትጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ማዕከል ያደረገ ሥራ ለመሥራት የታቀዱ ሥራዎችን በተመለከተ በዘርፉ ላይ የሚሰሩትንና ለዲያስፖራው ተደራሽ የሆኑትን አነጋግረናል::
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ግርማ በዚህ ላይ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ከዓለም አቀፉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ፣ ከኮቪድና ከሌሎችም የተለያዩ ምክንያቶች ጋር ተያይዞ እንቅስቃሴው ተገትቶ የቆየው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲነቃቃ ተቋማቸው የነበሩትን ተግዳራቶች መነሻ በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማካሄድ የማርኬቲንግ ስትራቴጅ ቀርጿል::
የስትራቴጂው አንዱ የትኩረት አቅጣጫ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲሆን፤ ሌላው የቀጠናውን ቱሪዝም በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ሥራዎች እንዲሰሩ ነው ምክረ ሀሳብ የተቀመጠው:: በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በመላው ዓለም ካሉት ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ እንዲሁም መጥተው እንዲጎበኙና በዘርፉም እንዲሳተፉ ወይንም ኢንቨስት ኢንዲያደርጉ የሚሉ መሠረታዊ ሀሳቦችን የያዘ ነው:: ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በመላው ዓለም የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ (ብራንድ) የምድረ ቀደምት አምባሣደር የምልመላ ሥራ ተጀምሯል:: ይኼ በተለያየ ዓለም የሚኖሩ ዲያስፖራዎችን አቅም፣ ዕውቀትና ክህሎት፣ ዕውቅና በመጠቀም የሚከናወን ሲሆን፤ እንቅስቃሴውም የኢትጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ጥሩ አቅም ከሚፈጥሩ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል። የምድረ ቀደምት የምልመላ
መሥፈርት አሥር በሚሆኑ መለኪያዎች የተከናወነ ሲሆን፤ በምልመላው መሥፈርት መሠረት ሀገራቸውን የሚወዱ፣ የሀገራቸውን ክብርና ኩራት ለመላው ዓለም ማህበረሰብ ማስረጽ የሚችሉ፣ በሚኖሩበት አካባቢ በሕዝብ ዕውቅና ያላቸው፣ ታዋቂ የምግብ ባለሙያ፣ ፓለቲከኛ፣ ስፖርተኛ፣ ተመራማሪ፣ ሳይንቲስት፣ የቱሪዝም ባለሙያ ሌላም ሙያ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ:: ከዚህ ውስጥም የተሻለ አፈጻፀም ያላቸው ናቸው የተመረጡት::
ቱሪዝምን በማስተዋወቅ ከፍ ያለ ሚና እንዲወጡ በሀገር ቤትም ቋሚ የሆነ የመረጃ መለዋወጫ በመዘርጋት በየዕለቱ አዳዲስ መረጃዎችን በመስጠት በጋራ ይሰራል:: የማርኬት ስትራቴጂውም በርካታ ነገሮችን ይዟል:: በተጨማሪም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከአስጎብኝ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን አንድ የማስተዋወቂያ መድረክ ለማዘጋጀትም በድርጅቱ ታቅዷል:: ድርጅቱ ለተከታታይ ጊዜም በበይነ መረብ (ኦንላይን) ሥልጠናዎች ሰጥቷል::
እንደ አቶ ስለሽ ማብራሪያ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ተሰርተዋል:: አዲሶቹንና ነባሮቹን የቱሪስት መዳረሻዎች በማስተዋወቅ ቱሪስቶችን በመሳብ ለመጠቀም በተለያዩ የውጭ ዓለማት ከተወከሉት አምባሣደሮችና ቆንስላዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር ሥራዎች ተጀምሯል:: ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን፣ በያሉባቸው ሀገሮች በሚዘጋጁ ኮንፈረንሶች፣ ባዛሮችና በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ፀጋዎች እንዲያስተዋውቁ የሚረዳ የተለያዩ መረጃዎችን የያዙ በራሪ ጽሁፎች ለማስተዋወቂያ ተልከዋል:: በተጨማሪም በቴክኖሎጂ የታገዘ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ መረጃ የሚሰጥና የማስተዋወቅ ሥራ ለማከናወን በቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት አዳዲስ ድረ ገጾች ተከፍተው መረጃዎች እንዲደርሱና ገጽታ የመገንባት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።
ለቱሪዝሙ ዘርፍ ሥጋት የነበሩት ኮቪድ፣ ሀገራዊ ምርጫ፣ ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ስጋት መሆናቸው ቀርቶ ቱሪዝሙን ለማነቃቃት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል::በመሆኑም ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችንም ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተሰራ ነው:: በሀገር ውስጥም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄዱ ኮንፈረንሶችና ስብሰባዎች በቱሪዝም መዳረሻዎች ውስጥ እንዲካሄዱ በቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት በኩል በደብዳቤ የማሳወቅ ሥራ ተሰርቷል:: ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ አንጻራዊ ሠላም ተፈጥሯል:: ከምርጫው ጋር ተያይዞ የነበረው ሥጋትም ምርጫው በሠላማዊ መንገድ ተከናውኗል:: ኮቪድን ለመከላከልም ክትባት በስፋት እየተሰጠ ይገኛል:: ኢትዮጵያም በተመሳሳይ እየተገበረች በመሆኑ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መነቃቃት የተሻለ ጊዜ እየተፈጠረ ነው::
ዲያስፖራው በተለያየ ዘርፍ ለሀገሩ የድርሻውን ለማበርከት እንዲያስችለው በሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ተቋቁሟል:: ኤጀንሲው በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ እያከናወነ ስላለው እንቅስቃሴ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬከተር ወይዘሮ ሠላማዊት ዳዊት አስረድተዋል::
እርሳቸው እንዳሉት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን ዲያስፖራው ይገነዘባል:: ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፉ ተጎድቶ የቆየ ቢሆንም በተለያየ ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገሩ መመላለሱን አላቆመም:: አብዛኞቹም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለይ አዳዲሶቹን ፓርኮች አንድነት፣ ወዳጅነትና እንጦጦ በመጎብኘት ትልቅ ሚና ነበራቸው::
ኤጀንሲው በሀገር ውስጥ ያሉትም ሆኑ በውጭ የሚሰሩ አስጎብኝ ድርጅቶች የቱሪዝም መዳረሻዎቹን ለገበያ የሚያቀርብበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ጥረት አድርጓል::ዲያስፖራው ሀገሩ ቤተሠብ ያለውና ለልጆቹም ሀገሩን ማሳየት የሚፈልግ በመሆኑ ከሌላው ቱሪስት በተለየ ሁኔታ ነው መስተናገድ ያለበት:: እንዲዝናና ብቻ ሣይሆን ሀገራዊ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ይጠበቃል:: እየተዝናኑ እግረ መንገዳቸውን የበጎ አድራጎት ተግባርና ሕክምናም እንዲሰጡ አብሮ በማቀናጀት ውጤታማ ሥራ መሥራት ይቻላል::
ዲያስፖራው በሀገሩ ሊኖረው የሚችለውን ተሳትፎ ማሳደግ ከተልኮዎቹ መካከል አንዱ ሲሆን፤ ቱሪዝም ከሚያሳትፍባቸው ዘርፎች መካከል ይጠቀሳል:: በሆቴልና ቱሪዝም ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ባለው ላይ እንዲሳተፉ፣ ቱሪስት ሆነው በመምጣት ደስታን አግኝተው ሀገራቸውንም በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው:: ኤጀንሲው በተለያየ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ቱሪዝም በ2014 ዓ.ም በተሻለ ለመሥራት በተለይም በሀገር ውስጥ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ውስጥ ከሚገኙ አስጎብኝ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለዲያስፖራው በሚመች መልኩ የቱሪዝም ገበያ እንዲያቀርቡ ለማድረግ ዝግጅት አድርጓል::
ኤጀንሲው ዲያስፖራውን ተደራሽ የሚያደርግበት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ከሚያናውነው ተግባር በተጨማሪ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋርም ግንኙነት በመፍጠር ኢትዮጵያን በተለያየ መንገድ በማስተዋወቅ እየሰራ ይገኛል::
የቱሪዝም መዳረሻዎችን መጎብኘት በኢትዮጵያውያን ብዙም የተለመደ ባለመሆኑ ዲያስፖራውም የወጣው ከዚሁ ማህበረሰብ በመሆኑ በውጭ ስላለው ልምድ ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ሀሳብ እንዲያካፍሉ ወይዘሮ ሠላማዊት ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በውጭው ዓለም ዓመቱን በሥራ ላይ የቆየውም ሆነ ተማሪው ጊዜያቸውን በመዝናኛ ቦታዎች በማሳለፍ አዕምሯቸውን እንዲያዝናኑ ይበረታታሉ:: በመሆኑም ዲያስፖራዎችም ይህን ተሞክሮ ይተገብራሉ::
ዲያስፖራው በሀገሩ የቱሪዝም ኢንዱደስትሪው ላይ ሚና እንዲኖረው በማድረግ ረገድም የመገናኛ ብዙሃን ስለነበራቸው ሚና እና ወደፊት ማድረግ ስላለባቸውም እንቅስቃሴ የማውንቴንስ ሚዲያ ባለቤት ጋዜጠኛ አስቻለው ጌታቸው እንዳለው በሀገር ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ኃይማኖታዊ ጉዞ ነው። ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የሆኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን የመጎብኘት ባህል አልዳበረም:: በመሆኑም ከሀይማኖታዊ ጉዞ ጎን ለጎን ቱሪስት ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ የማድረግ ባህሉን ማዳበር የሚቻልበትን ዕድል መፍጠር ይቻላል:: ለአብነትም ወደ ላልይበላ መንፈሣዊ ጉዞ የሚያደርገውን ደሴ ላይ የንጉሥ ሚካኤል ቤተመንግሥትን እንዲጎበኝ ማድረግ ነው:: መንፈሣዊ ጉዞው አሥር ቀንና ከዚያም በላይ ስለሚፈጅ አጋጣሚውን በመጠቀም ታሪካቸውንና ባህላቸውን በማወቅና በመዝናናት እንዲያሳልፉ ማድረግ ይቻል ነበር:: ነገር ግን ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር አንጻር በቱሪዝሙ ላይ እንዲሳተፍ የማድረግ ሥራ አልተሰራም:: በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቀውን ያህል አለመሥራታቸው እንደ አንድ ክፍተት ይወሰዳል:: ሕዝቡ ሀገሩን እንዲያውቅና እንዲጎበኝ የማድረግ ሥራ ተሰርቶ ቢሆን፣ምናልባትም የውጭው ቱሪስት እንደተጨማሪ አቅም የሚታይበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር:: ከመገናኛ ብዙሃን ከሚጠበቀው ሚና በተጨማሪ በዘርፉ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ኃይማኖታዊ ጉዞ ከሚያዘጋጁት ጋር በቅንጅት የሚሰሩበትን ማመቻቸት ይኖርባቸዋል::
እንደጋዜጠኛ አስቻለው ማብራሪያ በተለያየ ዓለም የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም እንደላልይበላ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶች ካልሆኑ በስተቀር ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዲያውቁና እንዲጎበኙ የተሰራው ሥራም አናሳ ነው:: በአሁኑ ጊዜም በከተሞች ሙዚየሞች በስፋት በመሰራት ላይ በመሆናቸው ሙዚየሞቹን ዲያስፖራው ወደ ሀገሩ ሲመጣ ሙዚየሞቹን ሳያይ እንዳይመለስ በሚያደርግ መልኩ ማስተዋወቅ ይቻላል::መገናኛ ብዙሃን እንደመስቀል ያሉ ታዋቂ በዓላት ላይ ትኩረት አድርጎ ከመሥራት መውጣት ይኖርባቸዋል:: በከተሞች ዘመናዊ የታክሲ አገልግሎቶች እየተለመዱ በመምጣታቸው ዲያስፖራው በነዚህ አገልግሎቶች ተጠቅሞ በከተሞች ያሉ የቱሪስት መደረሻዎችን እንዴት ማየት እንደሚችል መንገዶችን በማሳየትና መዳረሻዎችንም በማስተዋወቅ ቀድሞ መሥራት መለመድ አለበት:: እንዲህ ያለውን እንቅስቃሴ ማውንቴንስ ሚዲያ በ2013 ዓ.ም ላይ ጀምሯል:: ይህን በማስቀጠል የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችንና የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግና ለማነሳሳት ጥረት ያደርጋል:: ለውጤታማነቱ ሁሉም የድርሻውን በመወጣት ከተንቀሳቀሰ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው የተሻለ ውጤት እንደሚመዘገብ ተስፋ እናደርጋለን::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2013