
አንድ ማኅበረሰብ የሚጠራባቸው እና የሚታወቅባቸው የራሴ የሚላቸው ባሕሎች፣ ወጎችና ልማዶች እሉት:: እነዚህን የባሕል፣ ወግ፣ ልማድ፣ ወዘተ፣ እሴቶቹን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላልፍ ኖሯል። እሴቶቹ አብሮነትን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን ይሰብካሉ:: ግጭት ቢነሳ ለመፍታት ትልቅ አቅም ሆነውም ሲያገለግሉ ኖረዋል::
የአያሌ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በእዚህ በኩል ምን ያህል ባለጸጋ ስለመሆኗ እነዚህ ያቀፈቻቸው ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው ያመለክታሉ:: በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእነዚህ እሴቶች ላይ ተመሥርተው የሚያከብሯቸው የዘመን መለወጫዎችን ለአብነት በመጥቀስ ብቻ ሀገሪቱ ምን ያህል በእነዚህ እሴቶች የተሞላች መሆኗን መረዳት ይቻላል::
የሀገሪቱ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በየዓመቱ የዘመን መለወጫ በዓላቸው እንደሚያከብሩ ይታወቃል:: ከእነዚህ ማኅበረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው በራሱ ባሕሎች ወጎችና ልማዶች በእጅጉ የሚታወቀው የሲዳማ ብሔረሰብም በየዓመቱ የዘመን መለወጫ በዓሉን ያከብራል:: ብሔረሰቡ ፍቼ ጨምበላላ በሚል በሚያከብረው በዚህ የዘመን መለወጫ ሥርዓትም ነው ወደ አዲስ ዓመት የሚሻገረው::
የዘመን መለወጫ በዓሉ በሲዳማ ብሔረሰብ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ በብሔረሰቡ ባሕላዊ መሪዎች /አያንቱዎች/ ይፋ እየተደረገ ሲከበር ኖሯል:: ብሔረሰቡ የዘመን ጥበብን፣ ሳይንሳዊ እውቀትን በመያዝና ተፈጥሮን ልቆ በመረዳት የዘመን መለወጫ በዓሉን /ፊቼ ጫምበላላን/ በየዓመቱ እነዚህ አባቶች በሚመዝኑት አቆጣጠር በሚያስቀምጡት ቀን ያከብራል::
የፍቼ ጫምበላላ በዓል በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል፤ በተለያዩ ባሕላዊ ክንዋኔዎችና ሌሎች ዝግጅቶችም ይከበራል:: የአደባባይ በዓል ከመሆኑ በተጨማሪም፣ ቤተሰብ በአንድ ላይ ሆኖ የሚያከብረው ሲሆን፣ ጎረቤት ከጎረቤት ጋር በመሆን ጭምር ይከበራል:: የብሔረሰቡ አባላት ይህን በማድረግ አዲሱን ዓመት የፍቅር ፣ የጥጋብ፣ የአብሮነት እንዲሆን ይመኛሉ::
በዓሉ በመላ ሲዳማ ክልል የሚከበር ሲሆን፣ የዘንድሮው የፍቼ ጨምበለላ በዓል እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በቅርቡ በሀዋሳ ከተማ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል:: በሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ በሚገኘው ሶሬሳ ጉዱማሌ በተሰኘ ሥፍራ በዓሉ በተከበረበት ወቅትም፤ በርካታ የሲዳማ ክልል ሕዝብ እንዲሁም እንግዶችና የክልሎችና የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል:: የተለያዩ ብሔረሰቦች አባላትና ቱሪስቶችም ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ይጠቀሳሉ::
የፍቼ ጨምበለላ በዓል ብዙ ባሕላዊ እሴቶች እንዳሉት ይታወቃል:: በመድረኩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ የሲዳማ ሕዝብ የዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓሉን የቱሪዝም መስህብ ጭምር ለማድረግ በማሰብ ሊያከብረው፣ በዚህም የቱሪዝም ዘርፉን እንቅስቃሴ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል::
የቱሪዝም ሚኒስትሯ የሲዳማ ክልል በተለያዩ ሀብቶች የታደለ መሆኑን ጠቅሰው፣ እንደ አብነት የሀዋሳ ሀይቅ እና የወንዶ ገነት የተፈጥሮ መስህቦችን አመልክተዋል:: የፍቼ ጫምበላላ በዓልን ከእነዚህ ሀብቶች ጋር በማቀናጀት የክልሉን የቱሪዝም ሀብት ማስፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ፍቼ ጫምበላላ በሲዳማ አባቶች ተጠብቆ እሴቶቹን እያንጸባረቀ እዚህ ደርሷል ሲሉ የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ባለው ትውፊታዊ ይዘትና ማኅበራዊ እሴት ዓለምን በማስደመም በዓለም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርትና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡንም አስታውሰዋል::
ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ያሏት የባሕልና የተፈጥሮ ብዝሀ ሀብቶች መድመቂያዋ ብቻ ሳይሆኑ እንደ ሀገር ለምናደርገው ቀጣዩ ጉዟችን ለቱሪዝም ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ስንቅ እንደሚሆኑም ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እነዚህ ባሕሎች እና የቱሪዝም ሀብቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ የማድረግና የማልማት ኃላፊነት አለበት ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህንንም ለማስቀጠል ከክልሉ ጋር አብሮ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
በዓሉ የብሔረሰቡን ባሕላዊ ሥርዓት በጠበቀ መልኩ በድምቀት መከበሩ ልዩ ስሜት እንዳሳደረባቸው ጎብኚዎችም አስታውቀዋል:: የእንግሊዝ ዜግነት ያለውና በአዲስ አበባ በሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ሠራተኛ መሆኑን የሚገልጸው ኬቨን፣ በዓሉን ሲታደም የመጀመሪያ ጊዜው ነው::
ኬቨን በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ በጋራ ሆኖ የሚያከብርበት መንገድ ይበልጥ እንዳስደነቀውም ገልጾ፣ ጎብኚው ከበዓሉ ክዋኔዎች ባለፈ የበዓሉ ተሳታፊዎች ባሕላዊ አለባበስ በይበልጥ እንደማረኩትም አስታውቋል። ይህም የባሕል አልባሳት ራሳቸውን የቻሉ የአንድን ሕዝብ ባሕል የሚያንጸባርቁ መገለጫዎች መሆናቸውን እንደሚያሳይ ጠቁሟል::
ኤቫ ሌላኛዋ በበዓሉ ወቅት ያነጋገርናት ጎብኚ ናት:: በፍቼ ጨምበላላ በዓል ላይ የተገኘችው በበዓሉ ላይ ጥናት ለማድረግ በማሰብ ነው:: በፍቼ ጨምበላላ በዓል ላይ ስትገኝም የመጀመሪያዋ ነው::
የፍቼ ጫምበላላ በዓልን ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አዋቂዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ እንደሚያከብሩት መረዳቷን ጠቅሳ፣ በዓሉ በሶሬሳ ጉዱማሌ ሲከበር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድነት ሆነው የሚያከናውኑት የቄጣላ (ጭፈራ) ሥርዓት ይበልጥ ዓይንን እንደሚስብ ገልጻለች::
ወጣቷ ኤቫም ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች በአንድነት ሆነው በሚያከናውኑት በዚህ የቄጣላ ሥነ-ሥርዓት መደነቋን ተናግራለች። የበዓሉ ተሳታፊዎች አለባበስ፣ በሕብረት የሚያዜሙበት እና ስሜታቸውን የሚገልፁበት መንገድ አስደሳች ነው ስትልም ገልጻለች።
በዘንድሮው የፍቼ ጫምበላላ ኹነት ላይም የአዲሱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሉ የጌዲኦ ዞን እንዲሁም የአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀላባ ዞን ተወካዮች መገኘታቸውን መመልከቷን ጠቅሳ፣ በዚህም ለብሔረሰቡ አጋርነታቸውንና የፍቼ ጨምበላላ የአብሮነት በዓል መሆኑን ስለማረጋገጣቸው መረዳት መቻሏን ገልጻለች።
የሲዳማ ሕዝብ በአያንቱዎች ትልልቅ አባቶች እየተመራ የሚያከብረው ይህ የዘመን መለወጫ በዓል ከመድረሱ በፊት ‹‹አፊኒ›› ትርጉሙም ሰምታችኋል ወይ በሚለው ሥርዓቱ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ወደ ቀጣዩ ዓመት ለመሻገር ዝግጅት ያደርጋል::
የሲዳማ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የባሕል ታሪክና ቅርስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሌዳሞ የታሪኩን መነሻ አስመልክቶ ሲያብራሩ እንዳሉት፤ አባቶች የጨረቃን ዑደት በማጥናት እና ከዋክብትን በመመልከት የፍቼ ጨምበላላ ቀንን ቆጥረው ይደርሱበታል:: ይህም በባለሙያዎች እና በምሁራን ተጠንቶ ለትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ እሴት ነው::
የፍቼ ጨምበላላ በዓል በዓለም የትምህርትና የሳይንስ ድርጅት /ዩኔስኮ/ የማይዳሰሱ ቅርሶች ሆኖ ተመዝግቧል። የሲዳማ ሕዝብ ይህንን ታላቅ ቅርስ ለዓለም ስለማበርከቱ በድርጅቱ ይፋ ከተደረገ 10 ዓመታትን ተቆጥረዋል። የጨምበላላ በዓልን የሲዳማ ሕዝብ በየቤቱም የሚያከብረው ሲሆን፣ በክልሉ ዋና ከተማ ሀዋሳ ሶሬሶ ጉዱማሌ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ደግሞ ከተለያዩ የክልሉ ዞኖች የተውጣጡ አባቶች እና ወጣቶች ቄጣላ (ጭፈራ) እያሰሙ ወደዚህ ሥፍራ መጥተው ያከብሩታል።
የጨምበላላ ክብረ በዓል ከመካሄዱ አስቀድሞ በርካታ የአብሮነት እሴትን የሚያንፀባርቁ፣ ሰላምን የሚሰብኩ፣ ሕዝቡ አንድነትን ፈላጊ መሆኑን የሚያስታውቁ ሥርዓቶች እስከ ዋዜማው እለት እንደሚከናወኑም አመልክተዋል።
አቶ ተፈራ አዲስ ዓመት ከመግባቱ አስቀድሞ ጪሜሳዎች (የበቁ የሲዳማ ብሔረሰብ አረጋውያን) ለ15 ቀናት ያህል በመጾምና በመጸለይ ወደ አዲሱ ዓመት በሰላም ይሻገሩ ዘንድ ስለሀገራቸው፣ ስለቤተሰቦቻቸው፣ ስለ ከብቶቻቸው ይፀልያሉ። በዓሉ አንድ ሳምንት ሲቀረውም የተቸገሩ ሰዎች በዓሉን ደስ ብሏቸው እንዲውሉ በማድረግ ፣ የተጣሉ ሰዎች አፊኒ (ሰማችሁ ወይ) ብለው ጉዳዩን በመዳኘት እና ሀላሌ (ሀቅን) በማውጣት የተጣላ እንዲታረቅ ያደርጋሉ።
የሲዳማ አባቶች ‹‹ሰፎተ ቄጣላ›› (የጭፈራ ሥነ ሥርዓት) ብለው አዲሱን ዓመት ሲያስረክቡ ወጣቶች ደግሞ ‹‹አዲቻ ቄጣላ›› ብለው ይረከባሉ፣ በዚህ ወቅት አባቶች ወጣቶች ምን አሉ የሚለውን ይሰማሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ይህ የዘመን መለወጫ በዓል ዋናና ፊጣራ በሚል ለየብቻም ይከበራል:: ሁለቱም የየራሳቸው ኩነቶች አሏቸው። በዋዜማው እለት ከስድስት ሰዓት በኋላ አዲስ ዓመት ነው ተብሎ የሚታሰብ በመሆኑ በፊጣራ እለት አባቶች በእርጥብ እንጨት ሁሉቃ (መሽሎኪያ) ሠርተው ቤተሰቦቻቸውን እና ከብቶቻቸውን በዚያ በማሳለፍ አዲሱን ዓመት በሰላም መሻገራቸውን ያበስራሉ።
ሌላኛው የዋዜማ ሥነ ሥርዓት የሻፌታ ሥነ ሥርዓት ነው፤ በዚህም ሁሉም በአንድነት ማዕድ ቀርበው ይቋደሳሉ:: በዚህ ሥነ ሥርዓት ከቆጮ እና ቅቤ የተዘጋጀ ባሕላዊ ምግብ ይቀርባል:: ሻፌታ ከመቆረሱ በፊት ግን አንድ ተግባር እንደሚቀድም ዳይሬክተሩ ያነሳሉ። እሱም ከሀዘን ጋር የተያያዘ ነው::
በሲዳማ ባሕል ሀዘን ጥልቅ ነገር ሲሆን ሀዘን የደረሰባት ሴት ለረጅም ጊዜ ራሷን የምትጥልበት ሁኔታ ሊገጥም ይችላል:: በፍቼ ጨምበላላ ወቅት ሀዘን ገጥሞ ከሆነ ግን የሀገር ሽማግሌዎች ወደዚህች ሴት ቤት በመሄድ አዲሱን ዓመት በሀዘን እንዳትሻገር ቤቷ ሄደው ቅቤ እንደሚቀቧት አቶ ተፈራ አብራርተዋል። የሻፌታ ቆረሳ ሥነ-ሥርዓቱም በጪሜሳዎች (በበቁ አባቶች) ቤት በማምራት አመሻሹን ይከናወናል።
በሌላው ጊዜ የአመጋገብ ሥርዓቱ በታላላቅ አባቶች የሚጀመር አልያም በእድሜ ቅደም ተከተል የሚከናወን ይሆናል፤ የሻፌታ ሥርዓት ግን ሁሉንም እኩል በማድረግ በጋራ የሚቆርስ ነው፤ ይህም የፍቅር ገበታ በመባል ይታወቃል።
ቀጣዩ የጨምበላላ ቀን የደስታ እና የፌሽታ የአዲስ ዓመት ብስራት በመሆኑ ሕፃናት ከብቶች ጥበቃ ወደ ሜዳ አይሰማሩም፣ እንስቶችም የሚያጌጡበት ፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት ቀን ይሆናል።
በጨምበላላ እለት ሥጋ አይበላም፤ ይህም የራሱ ምክንያት እንዳለው አቶ ተፈራ አብራርተዋል። በጨምበላላ እለት እንኳን ሰው ከብቶችም እረፍት ያገኛሉ ያሉት አቶ ተፈራ፣ እርድ የማይከናወንበት እና ከብቶች በቂ ግጦሽ ቀርቦላቸው ጠግበው እንዲውሉ የሚደረግበት ነው።
ተፈጥሮንም መጠበቅ በዚህ ቀን ማሳረፍ የሲዳማ ሕዝብ የሚከተለው ባሕላዊ ሥነ ሥርዓት በመሆኑ በጨምበላላ እንሰትም አይቆረጥም፣ መሬትን በጦር መውጋት ጭምር የተከለከለ ነው።
የሲዳማ ዘመን መለወጫ በዓል በሚከበርበት ወቅት የኢትዮጵያውያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለይም የቀድሞው የደቡብ ክልል ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሙዚቃዎችን በማጥናት ባሕላዊ ሙዚቃዎችን በመሥራት ድምፃዊ ተስፋዬ ታዬ ይጠቀሳል:: አርቲስቱ የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፍቼ ጨምበላላን አስመልክቶ በሠራው ሙዚቃ ይበልጥ ተወዳጅነት ማትረፉንም ይገልጻል።
የሲዳማ ሕዝብ የራሱ ባሕል እሴትና መገለጫዎች እንዳሉት የሚጠቅሰው ድምፃዊው፣ የራሱ ልዩ የዘመን አቆጣጠር እንዳለውም አመልክቷል። ድምፃዊው የሲዳማ አባቶች በፍቼ ጨምበላላ እለት የሚያደርጉት የቄጣላ ሥነ ሥርዓት ይበልጡኑ እንደሚማርከው ይናገራል።
ፍቼ ጨምበላላ የሲዳማ ቀደምት አባቶች ጠብቀው ለትውልድ ያስተላለፉት እሴት መሆኑን አስታውቆ፣ ኪነ-ጥበብ ይህንን ታላቅ ቅርስ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግሯል። የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ባሕሎችን በማስተዋወቅ የሚሠሯቸው ሥራዎች በራሳቸው ለቱሪዝም ዘርፍ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም አመልክቷል::
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ባስቀመጡት የዜማ ስልተምት፣ በሚያስተላልፉት መልዕክት ላይ ጥናት በማድረግና በዘመናዊ መንገድ ባሕልን ለመጪው ትውልድ ለማስቀመጥ ብሎም ባሕሉን ከትውልድ ወደትውልድ ለማስተላለፍ የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም ያስገነዘበው::
የቢሮው ባለሙያዎችና አመራሮች ዜማዎች ባሕሉን የጠበቁ እንዲሆኑ ሙያዊ እገዛ በማድረግ የኪነጥበብ ባለሙያውን ሊደግፉ እንደሚገባም ገልጾ፣ ባለሀብቶችም በዚህ ውስጥ ሊሳተፉ እንደሚገባ አመልክቷል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም