
ጎንደር:- ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጅን በሚገኙ ጎንደርና ደብረታቦር ከተሞች ላይ የላቀ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን የ4 ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ አገልግሎት አስጀመረ ። በሁለት ወራት ውስጥ ስድስት ሚሊዮን የቴሌ ብር ኤሌክትሮኒክስ ግብይት ደንበኞች ማፍራቱም ገለጸ።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለጹት፤ የ4 ጂ አገልግሎት የላቀ ፍጥነትና አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ደንበኞች አገልግሎታቸውን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ፣ምርታማነትን ለማሳደግና በአጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ላይ ያላቸውን ተሞክሮ ለማሳደግ ያግዛቸዋል ።
ተቋሙ እያደገ የመጣውን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ፍላጎት ለማርካት መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አስታውቀው፤ ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የቆየውን የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ አገልግሎት በክልል ከተሞችም ለማዳረስ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ትናንት ይፋ የተደረገው የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ አገልግሎት በሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጅን የሚገኙ 361 ሺ ደምበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ነው ያሉት ወይዘሪት ፍሬሕይወት፤ በአሁኑ ጊዜ የስማርት ስልክ ተጠቃሚ የሆኑ 72ሺ ሰዎች አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ገልጸዋል።
በሁለት ወራት ጊዜ ብቻ ስድስት ሚሊዮን የቴሌ ብር ኤሌክትሮኒክስ የግብይት ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን ጠቁመው፤ የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ አገልግሎት መጀመር ቴሌ ብርን ለመጠቀም ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም እስካሁን ድረስ የዛሬውን ጨምሮ 67 ከተሞችን የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን የጠቆሙት ወይዘሪት ፍሬሕይወት ፤ ኩባንያው የዳታ ትራፊክ እድገትና ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚያከናውነው የማስፋፊያ ስራ ሲጠናቀቅ በመላው አገሪቱ የሚገኙ 103 ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም