አረጋውያን ለአንድ አገር በጎ ነገር ሰርተው ያለፉ የትውልድ ገፀ በረከት ናቸው። አረጋውያን በራሳቸው ለትውልድ የሚያስተላልፉት ታሪክ ያላቸው ሲሆን ይህንን ታሪክ የሚቀበልም ትውልድ የመፍጠርም ኃላፊነት አለባቸው። ነገር ግን አረጋውያን በየቦታው ወድቀው ደጋፊና ጧሪ ቀባሪ አጥተው ይገኛሉ። በተለያዩ አካባቢዎች አረጋውንን ለመጦር የተመሰረቱ በጎ አድራጎት ማህበራት ይገኛሉ። ለዛሬ በአዲስ አበባ በኮልፌ ቀራንዮ በወረዳ አምስት የሚገኘውን ውድ አረጋውያን የበጎ አድራጎት ማህበርን እንቃኛለን። ማህበሩን ለአምስት ሆነው ከአስር ዓመት በፊት የእናታቸውን ስራ ለማስቀጠል በማሰብ የተቋቋመ ነው። ከውድ አረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ውቤ ወልደ አማኑኤል ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
የማህበሩ አመሰራረት
ማህበሩ የተመሰረተው ከአስር አመት በፊት ሲሆን ማህበሩን ለመመስረት ያነሳሳቸው ለእናታቸው መታሰቢያ ለማድረግ አስበው ነበር። ውድ ሲባል አረጋውያን ውድ መሆናቸውን ለማመላከትና ለእናታቸው መታሰቢያ ለማድረግ ነው። ስራው ሲጀመር አስር አረጋውያንን በመደገፍ ነበር።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ በአስር አመት ውስጥ በአስር አረጋውያን የተጀመረውን የድጋፍ ስራ በኮልፌ ቀራንዮ በወረዳ አምስት ላይ ነበር። የማህበሩ የገቢ ምንጭ የነበረው የአባላት መዋጮ ስለነበር እንዲሁም በአካባቢው የሚታወቁ ለጋሽ ሰዎችን በመሰብሰብ የምክክር መድረክ ተካሄደ። በምክክር መድረኩ ማህበሩ የተመሰረተበትን አላማ በማስተዋወቅ እናታቸውን ካላቸው ቀንሰው በአካባቢው አረጋውያንን ይደግፉ እንደነበር። ይህን ስራ ለማስቀጠል ፍላጎት ስላለን ከአካባቢው ሰው ጋር በትብብር ለመስራት መዘጋጀታቸውን አሳወቁ።
ከውይይቱ በኋላ ከአርባ በላይ ሰዎች በቋሚነት አባል ለመሆኑ ፎርም ሞልተው ነበር። በዚህም በፈቃደኝነት አባል ከሆኑት ሰዎች መዋጮ በመሰብሰብ ተጀመረ። በወቅቱ ወርሃዊ መዋጮ ከአስር ብር ጀምሮ የነበረ ሲሆን አባሉ እስከቻለው ድረስ አስተዋፅኦ ለማድረግ ቃል ገቡ። በዚህ ሁኔታ በሚኖሩበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ቢሮ በመክፈት ለአረጋውያኑ ምገባ ተጀመረ። ከዚህም በኋላ ስራዎችን በማስፋት ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመሆን ድጋፍ የሚደረግላቸውን የአረጋውያን ቁጥር ከአስር ወደ ሰላሳና አርባ ከዛም ሃምሳ ማድረስ ተቻለ።
ለአረጋውያኑ የሚደረጉት ድጋፎች ለሶስት የተከፈሉ ሲሆን የመጀመሪው አቅማቸው በጣም የደከመውን ቤታቸው ድረስ በመሄድ ምግብ መስጠት፣ ወደ ማህበሩ እየመጡ መመገብ የሚችሉትን ደግሞ መመገብ ሲሆን ዋናው አላማ ከምግብ የበለጠ አረጋውያኑን የሚጎዳቸው መገለልና ብቸኝነት ነው። ሌላው ፍርሃትና ማን ይደግፈኛል የሚል ስጋት ነው። ነገር ግን በማህበሩ ግቢ ውስጥ መጥተው እንዲያውሩና እንዲወያዩ ተመቻችቶላቸዋል። ሌላው ደግሞ ከአንድ በጎ አድራጊ ማህበር በተገኘ ገንዘብ በየካና ጉለሌ ክፍለ ከተማዎች ድጋፍ ሲገኙ የነበሩ አረጋውያንን ወደ ማህበሩ እንዲጠቃለሉ ተደረገ። በዚህም አጠቃላይ ድጋፍ የሚደፈረግላቸው መቶ ሃምሳ ደረሰ።
በዋናነት የገቢ ምንጭ የሆነው የአባላት መዋጮ ነው። ከዛም በመቀጠል በየመስሪቤቱና ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል። በተለያዩ መድረኮች ግንዛቤ እያስጨበጠ እየተሰራ ሲሆን የማህበር፣ የተስካር፣ የልደት እንዲሁም ቀለበት ሲኖር በማህበሩ ግቢ ውስጥ ያከብራሉ። ማህበሩ በግቢ ውስጥ ለአረጋውያን ምንም አይነት መጠለያ አይሰጥም። አረጋውያኑ አስፈላጊ አገልግሎት አግኝተው ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ይደረጋል።
ለአረጋውያኑ የህክምና አገልግሎት የሚሰጣቸው ሲሆን ከተለያዩ የግል ህክምና መስጫዎችና ከመንግስት ሆስፒታሎች በነፃ ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል። የአለርት ሆስፒታል ለአረጋውያኑ ተከታታይ የሆነ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ነው። በተጨማሪም ከሆስፒታሉ የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍም ይደረጋል። በተለይ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ድጋፎች በመቀነሳቸው ችግር ተፈጥሮ ነበር። ተሸጠው ወደ ገንዘብ መቀየር የሚችሉ እቃዎች በድጋፍ መልክ ተገኝቷል። በተለይ አልባሳትና ሌሎች ንብረቶች በድጋፍ መልክ ከመስሪቤቶች ይገኛሉ። በአስር አመት ውስጥ በማህበሩ የተደገፉ ከአምስት መቶ በላይ ሲሆን አብዛኛው እየሞቱ፣ አካባቢ በመልቀቅና እንዲሁም ወደ አገራቸው እየተመለሱ ናቸው።
ሌላው ከአረጋውያን የሚኖሩ የልጅ ልጆችና ዘመዶቻቸውን የመደገፍ ስራ ማህበሩ ያከናውናል። ወደ ሰማንያ የሚሆኑ ሰዎች እገዛ ተደርጎላቸዋል። ቤታቸው ለፈረሰባቸው አረጋውያን የቤት ጥገና የሚደረግ ሲሆን ቤት ማደስ፣ የህክምና ድጋፍ ማድረግ፣ የአልባሳት ድጋፍ እንዲሁም ምገባ ይከናወናል። በየካና በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ አረጋውያን በየወሩ የምግብ አስቤዛ ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም የአልባሳት ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን የንፅህና መጠበቂያ እቃዎችንም ለአረጋውያኑ ይሰጣቸዋል። የሃይማኖት የበጎ አድራጎት ማህበራት አቅም ለሌላቸው አረጋውያኑ ድጋፍ የሚያደርጉ ሲሆን በርቀት የሚገኙ አረጋውያን ሲታመሙ በመንግስት ሆስፒታል ሄደው ታክመው መድኃኒት ሲታዘዝላቸው ደረሰኝ ሲያመጡ ያወራርዱላቸዋል። በተጨማሪም በዓመት አንድ ጊዜ አልባሳትን ይደግፏቸዋል።
ከቅርብ ጊዜ በኋላ ግን ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶች መቀነስ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። ውድ አረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር ቀድሞ የነበረው ቶታል ብስራተ ገብርኤል አካባቢ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ የዳቦ ቤት ባለቤት ብዛት ያላቸው ዳቦዎችን በድጋፍ መልክ ይሰጡ ነበር። ለአረጋውያኑ ተሰጥቶ የሚተርፈውን ዳቦ ለሱቆች በመሸጥ ገቢ ይገኝ ነበር። ሌሎችም ግለሰቦች ለበዓላት አረጋውያኑን ያበሉ ነበር።
የህብረተሰቡ አቀባበል
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ የህብረተሰቡ አቀባበል ግራ አጋቢ ነው። በአካባቢው የሚገኘው ህብረተሰብ የተወሰኑት አባል ሆኖ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን በተመሳሳይ ደግሞ የማህበሩን ስራ የሚቃወምና ስራዎችን የሚያጣጥል አለ። አረጋውያኖቹን በእናንተ ስም ገንዘብ እየተሰበሰበ የሚደረግላችሁ በቂ አይደለም እያሉ ውዥንብር እየፈጠሩ ናቸው። አባላት መዋጮ ሲያደርጉ አንዳንድ ሰዎች ሞኝ ናችሁ፣ እንዴት አባል ትሆናላችሁ ገንዘቡን ለራሳቸው ነው የሚያውሉት እያሉ የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ ነው።
በቶታል አካባቢ ማህበሩ ሲንቀሳቀስ እቃዎችን እንደልብ ማንቀሳቀስ አይቻልም ነበር። በድጋፍ መልክ የሚገኙ አልባሳትና ሌሎች እቃዎችን ለማውረድ በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች እክል ይፈጥሩ ነበር። እቃውን እኛ ነን የምናወርደው በማለት የመረበሽ ሁኔታዎች ነበሩ። ለአረጋውያኑ አልባሳትን ለመስጠት በተደረገ ስራ ላይ ከመኪና ላይ ሙሉ ማዳበሪያ ልብስ ጠፍቷል። በእንደዚህ አይነት ፈተናዎች ማህበሩ ይቸገር ነበር። ሌላው ደግሞ በጥበቃ ስራ ላይ የሚቀጠሩ ሰዎች በአግባቡ ስራቸውን ስለማይወጡ ስህተቶች ይፈጠሩ ነበር። ማህበሩ በቶታል አካባቢ ከባድ ሁኔታዎችን አሳልፏል። ነገር ግን በአካባቢው በሚገኙ ደጋግ ልቦች ለበዓላት አረጋውያኑን በየተራ ይመግቡ ነበር። በአሁኑ ወቅት ማህበሩ የሚገኝበት ቦታ ለደህንነት ምቹ የሆነ ቦታ በመሆኑ አስተማማኝ የሆነ ጥበቃ አለው።
ለማህበሩ ድጋፍ የሚሆኑ ያገለገሉ እቃዎችን ከመንግስት መስሪያቤት መሰብሰብ በጨረታ በመሸጥ ገንዘቡን ለአረጋውያን ድጋፍ እየዋለ ይገኛል። ገንዘቡ ለቤት ኪራይና ለሰራተኛ ደመወዝ እየተከፈለም ይገኛል። ይህን ስራ መስራት የተቻለው አሁን ማህበሩ የሚገኝበት ቦታ ምቹ በመሆኑ ነው። በበጎ ፈቃደኝነት የሚያገለግሉ ወጣቶች ማህበሩን እየደገፉ ነው። የአባላትን ቁጥር ለመጨመር ስራዎች እየተሰሩ ናቸው።
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ የበጀት እጥረት ከፍተኛ ፈተና ሆኖበታል። አረጋውያኑን ለመደገፍ የታቀደውን ያክል ለመስራት አልቻለም። ማህበሩ ውስጥ ያሉት አባላት እስከመጨረሻው ድረስ በትግስት አለመስራት ሌላኛው ችግር ነበር። በበጀት እጥረት ምክንያት ለሰራተኛ ደመወዝ መክፈል ባለመቻሉ ሰራተኞች እየተቀነሱ ይገኛሉ። ሰራተኞች በተቀነሱ ቁጥር ስራዎች ይስተጓጎላሉ። ሁሉም ሰው ቦታው ድረስ በመምጣትና በመጎብኘት ድጋፍ ማድረግ አለበት። ማህበሩ በቀጣይ ፈቃዱን ሲያድስ መቶ ሃምሳ የነበሩትን አረጋውያን ወደ ሶስት መቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዟል። ይህ እቅድ ሲያዝ ምንም አይነት በጀት በሌለበት ቢሆንም ህብረተሰቡን በማስተባበር ለማሳካት ታስቦ ነው።
ለማህበሩ ችግር እየሆነ የመጣው የተሳሳቱ መረጃዎች ሲሆኑ ህብረተሰቡ ከማየት ባለፈ እየመጣ መጠየቅ ይችላል። በግለሰብ ደረጃም እየመጡ አረጋውያንን በራሳቸው መንገድ መደገፍ ይችላሉ። በአሁን ወቅትም በዚህ መልኩ አረጋውያንን የሚደግፉ ሰዎች አሉ። አረጋውያኑ የሚያስፈልጓቸውን ነገር በመንገር ደጋፊ ሰዎቹ ያሟሉላቸዋል። ዋናው ነገር ለአረጋውኑ አለኝታ መሆን የሚያስፈልግ ሲሆን ቤት ለቤት በመሄድ ድጋፍ ይደረጋል። የበጀትና ሌሎች ወጪዎች መብዛት እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
የኢትዮጵያ ህዝብ አቅም የሌላቸውን ሰዎች እገዛ ማድረግ የሚፈልግ ህዝብ ቢሆንም በቀጥታ ገንዘብ መስጠት ሳይሆን በአይነት ለመደገፍ ፍላጎት አለው። ለአረጋውያኑ አልጋ፣ የሚለብሱትና የሚመገቡትን ምግብ በአይነት ድጋፍ የሚያደርጉ አሉ። በጤናው ዘርፍም አረጋውያን ለመደገፍ ታስቧል። አብዛኛው የአረጋውያን ችግር የኢኮኖሚና የጤና እክል ነው። በጤናው ዘርፍ ብዛት ያላቸውን አረጋውያንን ለመደገፍ ታስቧል። ሌላው ደግሞ አረጋውያኑን በገንዘብ ለመደገፍ ሀሳብ አለ። ምክንያቱም አረጋውያኑ ከምግብ በዘለለ ለእድር፣ ለቤት ኪራይና ለሰበካ ጉባኤ የሚከፍሉት ገንዘብ ይፈልጋሉ። ማህበሩ በቀጣይ የተወሰነ ክፍያ ለመስጠት ታስቧል። ለሰበካ ጉባኤ፣ ለውሃና ለመብራት ለመክፈል እቅድ አለ።
የገቢ ማስገኛ ስራዎች የተጀመሩ ሲሆን አቅም ያላቸውን አረጋውያን በመምረጥ ስራ ለማስጀመር የታሰበ ሲሆን የባልትና ውጤቶችን አዘጋጅቶ የመሸጥ ስራ ቀደም ብሎ የተጀመረ ተግባር ቢሆንም ቦታና ገንዘብ የሚጠይቅ ስራ በመሆኑ ማስቀጠል አልተቻለም። በቅርቡ የሲቪክ ማህበራት አዋጅ የተሻሻለ በመሆኑ ገቢ ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ማህበሩ በአይነት የሚያገኛቸውን ልገሳዎች በጨረታ በመሸጥ ገንዘቡን ለተለያዩ ስራዎች እያዋለ ይገኛል። በቀጣይ ስራዎችን ለማቀላጠፍ የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመተግበር ሀሳቦች አሉ።
የማህበሩ የአምስት አመት እቅድ እየተዘጋጀ ይገኛል። በእቅዱ ውስጥ የአበባ ተክሎችን በማልማት ውጤታማ ስራ ለማከናወን ሀሳብ አለ። በአሁን ወቅትም በማህበሩ ቢሮ ውስጥ አበባዎች ተተክለዋል። ነገር ግን ሰፊ ቦታ ባለመኖሩ የአበባ ማልማት ስራውን ለማስፋት እንቅፋት ፈጥሯል። ነገር ግን በተወሰነ መልኩ ስራውን በማስተዋወቅ ረገድ ስራዎች ተጀምረዋል። ሰፊ ቦታ ሲገኝ በተደራጀ መልኩ ለመስራት ሀሳብ አለ። ሌላው አረጋውያኑ የሚመገቡትን አትክልት እዛው ለማምረት የታሰበ ሲሆን ከሚለማው አትክልት የተወሰነውን ለገበያ ለማቅረብ ሀሳብ አለ። ለአትክልት ልማቱ ቦታ የተጠየቀ ቢሆንም ክፍት ቦታዎች ቢጠቆሙም እስካሁን ምላሽ አልተገኘም። ቦታው የሚገኝ ከሆነ ግን የአትክልት ስራዎችን ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2013