ኢትዮጵያ ከደጋ እስከ ቆላ ለንብ ምርት ተስማሚ የሆነ ስነምህዳር እንዳላት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ስነምህዳሩ ለምግብና ለመድኃኒት የሚውሉ ምርቶችን ለማግኘት የሚያስችሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ በጣዕማቸውም ለገበያ ተመራጭ እንዲሆኑ አግዟል፡፡ተስማሚ ከሆነው ስነምህዳር ከግራር፣ ቀረሮና ገተን ከተባሉ ዕፅዋት የሚገኙት ምርቶች ጥቂቶቹ ይጠቀሳሉ፡፡ ማር በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተለይም ጥቅጥቅ ደን በሚገኝበት በምዕራብ ዞን ውስጥ ለየት ያለና ሰፊ የሆነ ጥናት የሚያስፈልገው የማር ምርት ከቡና ተክልም እየተመረተ መሆኑን የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ይገልጻሉ፡፡
የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አሚን ጀማል በጥቅጥቅ ደኑ ውስጥ የሚገኘው የዕፅዋት ባህሪና የሥነምህዳሩ ተጽዕኖ ከአካባቢው እርጥበት ጋር ተዳምሮ በአካባቢው የተለየ የማር ምርት እንዲገኝ አድርጓል፡፡ማሩ በጣም ጣፋጭና ቀጭን ነው፡፡ ስለማር የማያውቁ ሰዎች ውሃና ስኳር የተቀላቀለበት ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ይሄን የተፈጥሮ ማር የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ስኳር እንዳለው አረጋግጧል፡፡በተጨማሪ ምርምር በማካሄድ ጥራቱን የበለጠ ለማረጋገጥ ጥረት ቢደረግና የማስተዋወቅ ሥራ ቢሠራ ተደራሸ በማድረግ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ በክልሉ በተለይ በምዕራብ ዞኖች ከፋ፣ ሸካ፣ ቤንች፣ ማጂ፣ ሲዳማና ጌዶ ዞኖች ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የቡና ማር ሀብት ይገኛል፡፡ ከአካባቢዎቹ በ2009ዓ.ም 34ሺህ ቶን በ2010ዓ.ም ደግሞ 32ሺህ ቶን የማር ምርት ተሰብስቧል፡፡ አርሶአደሩ ከዘልማዳዊ የንብ ማነብ ዘዴ እንዲላቀቅ፣ ምርትን የሚጨምር የተሻሻለ ቀፎ እንዲጠቀም፣ በሞዴል አርሶአደሮች አማካኝነት የንብ ቤተሰብ ተባዝቶ ለአናቢው እንዲዳረስ በአጠቃላይ በተሻለ አያያዝ እንዲያመርት ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ በአቅም ግንባታና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ምርቱን በጥራትና በመጠን የማሳደግ ሥራ በመከናወን ላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ወደተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የማር ምርት በመላክ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ስታደርግ እንደነበርና በወቅቱም ወደ 54ሺህ ቶን ይመረት እንደነበር የኢትዮጵያ ማርና ሰም አምራች ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ውብሸት አዱኛ ያስረዳሉ፡፡ አገሪቷ የውጭ ገበያን ፍላጎት መሰረት ባደረገ በጠርሙስ አሽጎ የመላክ አቅም ባለመፍጠሯ በአንድ ጊዜ እስከ ሦስት መቶ ግራም ብቻ ነው ለተቀባይ አገሮች የምታቀርበው፡፡ተቀባዮቹ በጅምላ የገዙትን በተጠቃሚዎች ፍላጎት መጠን እያሸጉ ያቀርባሉ፡፡ በዚህ መልኩ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም ያላትን ሀብት ወደገንዘብ እየቀየረች ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል የውጭ ምንዛሪ እያገኘች አለመሆኑንም አቶ ውብሽት ይናገራሉ፡፡ ዓመታዊ ምርቷም ከአምስት መቶ ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ መሆን ሲገባው ከ51ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ሊሆን አልቻለም፡፡ የማር የወጪ ንግድ በተለይ እ.አ.አ. ከ2014 ወዲህ ተቀዛቅዟል፡፡
ምርቱ ከፍተኛ መሆኑና ለጥራትም ትኩረት መሰጠቱ በተደጋጋሚ ቢነገርም ለውጭ ቀርቦ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ቀርቶ የአገር ወስጥ ፍላጎትን በዋጋም በአቅርቦትም እያሟላ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡የአገር ውስጥ ተጠቃሚውም በዚህ በያዝነው በጥቅምትና ህዳር ወራት ውስጥ ነው ማር ለመጠቀም የሚነሳሳው፡፡ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻፀር ኢትዮጵያውያን ማር ተጠቃሚዎች ቁጥራቸው አነስተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡
አስተያየቱን የሚጋሩት የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ተቀባ እሸቴ በኢትዮጵያ የማር ነፍስ ወከፍ አጠቃቀም ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻፀር የመጨረሻ ደረጃን የያዘ ነው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት የመግዛት አቅም ያለውና የጤና ችግር ያጋጠመው ካልሆነ በስተቀር ማር ገዝቶ የሚጠቀም የለም፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ናቸው ገበያው ላይ በስፋት የሚቀርቡት፡፡ዋጋው ደግሞ ገበያተኛውን አይጋብዝም፡፡
ለማር አቅርቦት ማነስና የጥራት መጓደል ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም አስተያየት ሰጭዎቹ ሁለት ነጥቦችን ያነሳሉ፡፡አንዱ ዘርፉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመታገዙ የፈጠረው ክፍተት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ለዘርፉ ማደግ ፈጣን ምላሽ ከሚመለከተው አካል አለመሰጠቱ ነው፡፡
ዶክተር አሚን ጀማል እንዳሉት የማር ምርትን ለመጨመር አምራቹ ከባህላዊ የማነብ ዘዴ መላቀቅ አለበት፡፡አሁን ባለው አሰራር አገሪቷ የማር ጥራትን የምታረጋግጠው ምርቱን ውጭ አገር በመላክ ነው፡፡ይህ አሰራር ደግሞ በወጪም በጊዜም ተጠቃሚ አያደርጋትም፡፡ ክፍተቱን ተጠቅመው በህገወጥ ግብይት ውስጥ የሚገኙትንም ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ምርቱ በቅብብሎሽ ሂደት ወቅት ለጥራት መጓደል ይጋለጣል፡፡ ባዕድ ነገር ይጨመርበታል የሚል በተጠቃሚዎች የሚቀርበው የቅሬታ ምንጭም የገበያ ሥርዓቱ የሚፈጠረው ችግር ነው፡፡የገበያ ሥርዓቱን በህግ እንዲመራ ማድረግ ቢቻልና ማር በስፋት በሚያመርቱ አካባቢዎች የጥራት ማረጋገጫ ቤተ ሙከራ ቢቋቋም ችግሮቹን መቅረፍ ይቻላል፡፡
በክልላቸው አሁን ባለው ተሞክሮ ማር አምራቹ በማህበር ተደራጅቶ ምርቱን በማዕከል ለተደራጁ ዩኒየኖች ያስረከባሉ፡፡ ዩኒየኖቹ ደግሞ ለላኪዎች ያስረክባሉ፡፡የገበያ ሰንሰለቱ በዚህ መልኩ ቢከናወንም በህገወጥ ገበያው ውስጥ የሚገቡ በመኖራቸው ግብይቱ ከችግር የፀዳ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለችግሩ መፍትሄ የሚሆነው አገራዊ የሆነ የአሰራር ሥርዓት ሲዘረጋ ነው፡፡
አቶ ተቀባ እሸቴ በበኩላቸው ዘርፉ ወደከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገር በቴክኖሎጂ መታገዝ አለበት፡፡ የህግ ማዕቀፍ ኖሮ ቁጥጥሩን በማጠንከር ህግ አክባሪ እንዲኖር የማድረግ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ በዚህ በኩል መንግሥት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወጣ ቢሆንም በዘርፉ ላይ የሚገኙ በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ የአምራቹን ክህሎት ማሳደግ፣ በግብአት ማገዝ፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል፡፡ በዚህ በኩል ተቋማቸው የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እየሠራ ቢሆንም ለበለጠ ውጤታማነት የሌሎችም ባለድርሻ አካላት የጋራ እንቅስቃሴና መናበብ ያስፈልጋል፡፡ በዘርፉ ላይ ተደጋጋሚ ምክክር ይካሄዳል ያሉት አቶ ተቀባ ምክክሩ ለመነጋገር ብቻ መሆን እንደሌለበትና መተግበር እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
አቶ ውብሸት አዱኛ በበኩላቸው ማህበራቸው የኢትዮጵያ ማርና ሰም አምራች ላኪዎች በዘርፉ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ አባላት አሉት፡፡ አባላቱ ዕድሉን ካገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለመሳተፍ ፈቃደኞች ናቸው፡፡ አንዳንዶችም በሠርቶ ማሳያ ላይ ለአምራቹ ተሞክሮ በማካፈል አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በተጠናከረ መልኩ አቅማቸውን ለመጠቀም ሁኔታዎች ቢመቻቹ ችግሩን በጋራ መቅረፍ ይቻላል፡፡ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር ፣ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ተስማሚነት ምዘና፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቴክኖሎጂን በማመንጨት የሚያደርጉት ድጋፍ ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡
በተለይ የተሻሻለ ቀፎ በንብ ማነብ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አለው የሚሉት አቶ ውብሸት ከተሻሻለ አንድ ቀፎ 50 ኪሎግራምና ከዚያ በላይ ማምረት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው በአገር ውስጥ በአብዛኛው በባህላዊ የሚመረት ሲሆን፣ ከአንድ ቀፎም የሚመረተው ከአምስት ኪሎግራም አይበልጥም፡፡በዘመናዊ የታገዘውም ቢሆን ከፍተኛ የሚባል አይደለም፡፡ በቻይና ከአንድ ቀፎ 50ኪሎግራም በማምረት ገበያው ውስጥ በስፋት ማግኘት ይቻላል፡፡ የሌሎችንም ተሞክሮ ቀምሮ አሰራርን በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብሄራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ፍሰሐ እንደሚያስረዱት፤ ከጥራት ጋር በተያያዘ በተለያየ ጊዜ የተደረጉት ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የጥራት ጉድለቱም በወጪ ንግዱ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ እ.ኤ.እ. ከ2014 ወዲህ የወጪ ንግድ መቀዛቀዙ አገሪቷ አምርታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከማትችልበት ደረጃ ላይ መድረስዋ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ተጠቃሚውም ቢሆን ቅሬታ ያቀርባል፡፡ ለዚህም የጥራት ቁጥጥር ሥራ የሚያከናውኑ ተቋማት አቅም ማነስ፣ የሚሰጡት አገልግሎትም ዓለምአቀፍ ተቀባይነት አለማግኘቱና ውስን መሆኑ እንደ አንድ ምክንያት ይገለጻል፡፡በተጠቃሚው በኩልም የጥራት ጉዳይን የራስ አድርጎ አለማየት ለችግሩ መፈጠር የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ለጥራት የሚጨነቅ ማህበረሰብ መፍጠር ላይ ብዙ ሥራ ይቀራል፡፡ የጥራት ችግርንና የወንጀል ችግሮችንም ለይቶ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ በማድረግ ላይም ክፍተት መኖሩ ለዘርፉ ማነቆ ሆኗል፡፡መንግሥት ችግሩን ተገንዝቦ ከዓለም ባንክ ጋር በጋራ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ቀርፀው ለችግሩ መፍትሄ የሚሆኑ ሥራዎች በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በፕሮጀክቱ ክህሎትን የማሳደግ አንዱ ተግባር ሲሆን፣ ይህም እንደ ኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ያሉ የጥራት ቁጥጥር ሥራ ለሚያከናውኑ ተቋማት በአቅም ግንባታ ሥልጠና ማብቃትና የምክር አገልግሎት በመስጠት የሚደረገው ጥረት ይጠቀሳል፡፡ እንደአስፈላጊነቱም ለሥራው የሚያግዝ የመሣሪያ ግዥ በመፈፀም ድጋፍ ይደረጋል፡፡ በላኪው ዘንድ ስለጥራት ያለው ግንዛቤም አናሳ በመሆኑ የአቅራቢውን አቅም ከማጠናከር ጎን ለጎን በፕሮጀክቱ በማካተት ግንዛቤን የማዳበር ተግባር በመከናወን ላይ ነው፡፡
አምራቹና ላኪው ስለጥራት የጋራ ግንዛቤ ኖሯቸው ዓለም አቀፍ እውቅና ደረጃ ላይ ደርሰው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በሚደረገው ጥረት የአምስት ዓመቱ ፕሮጀክት አጋዥ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ወንድወሰን ፕሮጀክቱ ውስን የሆኑትን ብቻ ስለሚዳስስ ተከታታይነት ያለው ሰፊ ተግባር ማከናወን ይጠይቃል፡፡ እንደተባለው የዘርፉ ችግር ጥራትን ብቻ ሳይሆን የአሰራር፣ የክህሎት፣ የፖሊሲና ሌሎችን አሰራሮች ላይ ማሻሻል ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ የፕሮጀክቱ የመጨረሻ ግብም የአገሪቷ የማር ምርት መጠን ምን ያህል ደረሰ ? የወጪ ንግዱ በምን ያህል ጨመረ ? የሚል ውጤት ለማስገኘት በመሆኑ የተከናወኑ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየገመገሙ ውጤት ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
የጥራት መጓደል ችግርን በባለቤትነት የሚከታተለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወንድወሰን በፕሮጀክቱ ውስጥ ብሄራዊ የጥራት ቴክኒክ ኮሚቴ ፎረም አደረጃጀቶች አማካኝነት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ የተጀመረው እንቅስቃሴ ዘርፉን ወደኋላ ከጎተተው ችግር ያወጣው ይሆን?
ለምለም መንግሥቱ