
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር በመሆን ትታወቃለች። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ከምትታወቅበት ባህላዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህሎቿ መካከል ቡና ቀዳሚው ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ቡና በዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የሚታወቅና በእጅጉ የሚወደድ ሆኖ ቀጥሏል። ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያገኘው የኢትዮጵያ ቡና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆን ይታወቃል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘርፉ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከመሆኑም በላይ ተፈላጊነቱ በእጅጉ እየጨመረ ይገኛል።
ቡና አብቃይ በሆኑ የሀገሪቱ ክልሎች የሚገኙ አርሶ አደሮችም ካለፈው ጊዜ በተሻለ ደረጃ እያመረቱ የሚገኙ ሲሆን በምርቱም ተጠቃሚነታቸው እያደገ መጥቷል። ከአርሶ አደሩ በተጨማሪም በዘርፉ የተሳተፉ አልሚዎችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኘው የዘርፉ ተዋናዮች ጠንክሮ መስራት ሲችሉ ቡናውን በስፋት የማስተዋወቅና በአለም አቀፍ ጨረታ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገ ነው።
በተለይም በአሁን ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የቡናን ዘርፍ በማነቃቃት፣ አርሶ አደሩንም ተጠቃሚ በማድረግ ጉልህ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው የባለልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር አንዱ ነው። ባለፈው ዓመት የተጀመረው የባለልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ላይ የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች ተወካዮች እና ሌሎች ዓለምአቀፍና የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የሚገኙበት በመሆኑ የኢትዮጵያን ቡና በስፋት ለማስተዋወቅ ያለው አበርክቶ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
ባለፉት ዓመታት ለኢንቨስትመንቱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ቡና በግብርና ሚኒስቴር እንደ አንድ ዘርፍ የገባና ተደብቆ የቆየ ስለመሆኑ ብዙዎች ያነሳሉ። ነገር ግን በአሁን ወቅት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ ያለው ቡና በተሰጠው ትኩረት ትርጉም ባለው መንገድ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። ለዚህም በዘርፉ የተሰሩና አሁንም በስራ ላይ ያሉ በርካታ ተግባራት አሉ። እነዚህን ተግባራት አጠናክሮ በመቀጠል ኢንቨስትመንቱን ማሳደግና ሀገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት በቡናና ሻይ ባለስልጣን የኢዩ ካፌ ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ፍቅሩ አመኑ ናቸው።
እንደሳቸው ማብራሪያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት የቡና ዘርፍን ለማሳደግ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛሉ። በተለይም ቡና አብቃይ በሆኑ ክልሎች፣ ወረዳዎችና ዞኖች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ተገቢውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል። አሁን ላይ ያለው የገበያ ዕድልም ተስፋ ሰጪና አበረታች ነው።
የቡና ልማትን ለማሻሻል የአውሮፓ ህብረት ግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በጋራ በሚሰራው ሥራ በርካታ ድጋፎች ተገኝተዋል። በቅርቡም የቡናን ምርታማነት ለመጨመር ዓላማ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የአውሮፓ ህብረት 800 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ወይንም 15 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ፋይናንስን ወጪ በመመደብ የቡና ልማቱን የሚያግዝ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በተለይም ቡና አምራች በሆኑ ወረዳዎች አካባቢ የቡና ሥራውን ለማቀላጠፍ የሚያስችላቸውን የትራንስፖርት ድጋፍ በማድረግ 42 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አድርገዋል። ይህም ምርታማነትን ለመጨመር አንዱ መሳሪያ ሲሆን ወረዳ ላይ ያለው አመራር ታች ያለው አርሶ አደሩ ጋር ወርዶ ድጋፍ ለማድረግ ይረዳል። ተሽከርካሪዎቹም ለአራት ክልሎች የተከፋፈሉ ሲሆን፤ ኦሮሚያ ክልል 18፣ ደቡብ ክልል 9፣ ሲዳማ ክልል 3 እና አማራ ክልል 3 ተሽከርካሪዎችን አግኝተዋል።
ህብረቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ በኢትዮጵያ የቡና ምርትን ለማሳደግና አገሪቱ ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል መሆኑን ያነሱት አቶ ፍቅሩ፤ በዘርፉ በተለይ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲቻል ተሽከርካሪዎቹን ለታለመላቸው የቡና ልማት ማዋል አስፈላጊ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የቡና ኤክስቴንሽንን ለማሳለጥ፣ የቡና ችግኝ በብዛት ለማዘጋጀት፣ ቴክኖሎጂን በስፋት ተደራሽ ለማድረግና የምርምር ስራዎችን ለማከናወን ተሽከርካሪዎቹ በእጅጉ አጋዥ ናቸው።
የአውሮፓ ህብረት የመሰረተ ልማትና የኢኮኖሚ ቡድን ህብረቱ በቡና ልማት በተለይም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ በግብርናው ዘርፍም ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ባለፉት 40 ዓመታትም የቡና ልማትን ለመደግፍ ከ122 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ኢንቨስት በማድረግ የቡናውን ዘርፍ ደግፏል።
በኢትዮጵያ ለአራት ዓመታት የሚቆውየው የ15 ሚሊዮን ዩሮ የቡና ልማት ፕሮጀክት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ ውጤታማ መሆን ችለዋል። በተለይም በአሁን ወቅት ህብረቱ በ28 ወረዳዎችና በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በጅማ የምርምር ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን እየሰራ ይገኛል። በዋናነት ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አማራና ሲዳማ ክልሎች ተጠቃሚዎች ናቸው።
ከእነዚህ ክልሎች የተሻሉ ወረዳዎች ተመርጠው ድጋፍ እያገኙ ሲሆን ወረዳዎቹ የተመረጡበት መስፈርትም ከዚህ ቀደም በነበራቸው ልምድ፣ በቡና ምርታቸው፣ ለዓለም ገበያ በሚያቀርቡት የቡና ምርት መጠንና የቡና ምርት መተዳደሪያቸው መሆኑ ተለይቶ ነው።
ከዚህ ቀደም አጠቃላይ በፕሮጀክቱ የተቃኙ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም በአሁን ወቅት የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎችን በማሟላት የእርሻ ግብዓቶችን የአርሶ አደር የስልጠና ማዕከላትን በማቋቋም የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች ተሰርተው ሞዴል በመሆንም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ከፍ አድርገዋል። የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከመረጋገጡ ባለፈም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት ተችሏል።
የፕሮጀክቱ የልማት ቡድኖች እርስ በእርስ ተቀናጅተው የሚሰሩበትን መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮች የተመቻቹ ናቸው። በቀጣይም አርሶ አደሮቹ በቴክኖሎጂ ተቀናጅተው በገበያ መረጃ በመስራት በመማማር እራሳቸውን ብቁ ከማድረግ ባለፈ ሌሎች አርሶ አደሮችን ከማፍራት ባለፈ ምርትና ምርታማነት ያድጋል ግብዓት ይሻሻላል። ከዚህ በተጨማሪም ከሚሸጠው ቡና የእያንዳንዱ አርሶ አደር ገቢ በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ ያስችላል የሚል ዓላማን ሰንቀው እየሰሩ ስለመሆኑ አቶ ፍቅሩ አስረድተዋል።
አራት አመት በሚቆየው ፕሮጀክትም መቶ ሺ የሚደርሱ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተደራሽ በማድረግ እነሱ ደግሞ አንዱ ቀበሌ ለሌላው ቀበሌ በሚያደርገው ድጋፍ ተሞክሮን በማስፋት ሌሎች በመቶ ሺ የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ማሰልጠን ያስችላል። አርሶ አደሩ በየጊዜው በሚያገኘው ስልጠና በልማቱ የሚገጥመውን ማንኛውም ችግር በራሱ መፍትሔ እየፈለገ ለመሄድ ያስችለዋል።
የአውሮፓ ህብረት ለቡናው ዘርፍ እያደረገ ባለው ድጋፍ ለውጥ ለማምጣት በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በአሁን ወቅትም በተመረጡት ክልሎች የተለያዩ ግብዓቶችን ከቦታ ቦታ ለማመላለስና ባለሙያዎችም ተንቀሳቅሰው መስራት እንዲችሉ የሚያግዙ እያንዳንዳቸው 10 ኩንታል ድረስ መጫን የሚችሉ መኪኖችን በግዢ አቅርቧል። መኪኖቹም የቡናውን ዘርፍ በመደገፍ የሚኖራቸው ፋይዳ የጎላ ነው።
የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ላይ የሚሰሩ ስራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፍና ክትትሎችን አጠናክሮ በመቀጠል የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ የማስተዋወቅ ሥራ መስራት ተገቢ ነው። የኢትዮጵያ ቡና በአሁን ወቅት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ከመሆን አልፎ ተመራጭና ከፍተኛ ገቢ እያስገኘ ያለ ኢንቨስትመንት በመሆኑ ለዘርፉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
በሀገሪቱ የሚገኙ የቡና ምርቶችን ከአምራች አካባቢዎች ጋር መለያ በመስጠት ተመዝግቦ ስመ ጥር ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነና ለዚህም እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አቶ ፍቅሩ አንስተው፤ ጥራት ባለውና ደረጃውን የጠበቀ ቡና ለአለም ገበያ በማቅረብ መታወቅ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ መጠን ያግዛል ።ከዚህም በላይ እውቅናን ማትረፍ ይቻላል። በአሁን ወቅትም እየተሰራ ያለው የኢትዮጵያ ቡና የሚገኝባቸውን አካባቢዎች በማስጠራት ምን አይነት ቡና ከየት አካባቢ እንደሚገኝ ጭምር ማስተዋወቅና መለያ መስጠት ነው።
በሀገር ውስጥ ባሉት ባለሙያዎች በቡናው ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑ ስልጠናዎችን መስጠትና የቡና ኤክስቴሽን ሥራዎችን ማሳለጥ ኢንቨስትመንቱን ከሚያሳድጉ ተግባራት አንዱ ነው። በተለይም በአሁን ወቅት ለቡናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሄድ እየተደረገ ይገኛል። በመሆኑም ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ቡና እንደ አንድ ስፔሻላይዜሽን እንዲሆን እየተሰራ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ክልሎች በቢሊዮን የሚቆጠር የቡና ችግኞችን እያዘጋጁ የአፈር አሲዲቲ ባለበት ቦታ ቡናን በስፋት እያለሙ ነው። በተለይም የአውሮፓ ህብረት የተሽከርካሪ ድጋፍ ባደረገበት 28 ወረዳዎች ውስጥ ማሳያ መሆን የሚችል ሁሉን አቀፍ የሆነ ቴክኖሎጂን በማቅረብ የሰው ሀይል ግንባታውን አጠናክሮ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሚሰራ ይሆናል። በቀጣይም በወረዳ ደረጃ መሰራት የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች በመኖራቸው ድጋፉ ቀጣይነት ይኖረዋል። ክልሎችም ይህንኑ የመደገፍ ሥራ ይሰራሉ።
የአውሮፓ ህብረት ዩኒየን ወይም ኢዩ ካፌ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ቡና ምርትን ለማሻሻል ብሎም ኢንቨስትመንቱን ለመሳብ የአራት አመት ኮንትራት ይዞ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በቀጣይነት ማስቀጠል የሚቻለው ድጋፉን በአግባቡ መጠቀም ሲቻል ነው። ነገር ግን በአሁን ወቅት ኢዩ ካፌ ለልማቱ የመደበውን 15 ሚሊዮን ዩሮ መጠቀም ካልተቻለ በቀጣይ ድጋፍ ማግኘት አይቻልም። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ መሰል ፕሮጀክቶችን በማፈላለግ የቡና ልማቱን ለመደገፍና ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ ይሰራል።
ከዚህ ቀደም የቡና ዋጋ ሲወድቅ እንዲሁም ገበሬው ቡናው አረጀ በማለት ተስፋ ቆርጦ በቆሎ መዝራት የጀምረበት ወቅት እንደነበር ያነሱት አቶ ፍቅሩ፤ በአሁን ወቅት በቡና ምርምር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነና ያረጁ ቡናዎችንም በጉንደላ እንዲሁም ነቅሎ በመተካት ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል። በምርምር ደረጃ ምርታማነትን በማሳደግ ለአብነትም ከአንድ እግር ቡና አንድ ኪሎ አገኛለሁ ያለ አንድ አርሶ አደር እንደየአካባቢው እስከ አራት ሺ አምስት መቶ እግር ቡና ይተክላሉ ። በመሆኑም ሶስት ሺ እግር ቡና የተከለ ሶስት ሺ ኪሎ ግራም ወይም 30 ኩንታል ቡና ያገኛል ማለት ነው።
በአጠቃላይ የቡና ምርታማነት እንዲጨምር እየተደረገ ያለው የሀገር ውስጥና የውጭ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሀገሪቷም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷ ትርጉም ባለው መንገድ ቀጣይነት እንዲኖረው በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ሥልጠናዎችን ለአርሶ አደሩ መስጠትና የተለያዩ ንቅናቄዎች በመፍጠር ያረጁ ቡናዎችን በመንቀል በጉንደላ ወዘተ ምርቱን ማሻሻል ተችሏል። በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል። በዘንድሮው ዓመትም ካለፉት ዓመታት እጅግ በተሻለ መጠን ቡናን ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2013