“ዲፕ ፌክ” በቀጥታ ወደ አማርኛ ሲተረጎም ጥልቅ የሆነ በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ ማታለል ማለት ነው:: የዘመናችን እጅግ አሳሳቢ የሆነው ይህ የማታለል ዘዴ የአንድን ግለሰብ በተለይም ታዋቂ ሰዎች ቀድሞ የነበረ ምስል፣ ድምጽ ወይም ተንቀሳቃሽ ምስል በመጠቀም ያልተናገረውን ወይም ያልተናገረችውን ነገር እንደተናገረ ወይም እንደተናገረችው አስመስሎ የማቅረብ ዘዴ ነው:: ይህ በአለም ዙሪያ በርካታ ሰዎችን እያሳሰበ ይገኛል።
በሳይበር ዘርፍ ይዘት ማሳሳት የተለመደ ነው:: በተለይም ፎቶ ማስመሰል ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው:: መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የፎቶግራፍ ማጭበርበር የተለመደ ነበር:: ከጥቂት አስርት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ ማታለል (ዲፕፌክ)መተግበር እየተለመደ መጥቷል::
ቪዲዮ የማጭበርበር ቴክኖሎጂው በ20 ኛው ክፍለዘመን ውስጥ ያለማቋረጥ መሻሻል እያሳየ እና የእውነት እየመሰለ የመጣ ሲሆን በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዲጂታል ቪዲዮዎች መተዋወቃቸውን ተከትሎ በፍጥነት እየተሻሻለ መጥቷል:: በተለይ አሁን ላይ ሁለትና ከሁለት በላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ) ስልተ ቀመሮችን በአንድ ላይ በማጣመር እየተሰሩ ያሉ ዲፕፌኮችን ተራው ሰው ቀርቶ የዘርፉ ሊህቃን ጭምር ለመለየት እየከበዳቸው መጥቷል።
የዲፕፌክ ቴክኖሎጂ እ.ኤ.አ. ከ1990 ዎቹ ጀምሮ በአካዳሚክ ተቋማት ተመራማሪዎች እና በኋላም በማህበራዊ ሚዲያዎች ዘርፍ በተሰማሩት በተራው ግለሰቦች ጭምር መሰራት ጀምሯል:: በቅርቡ ደግሞ ዘዴዎቹን በኢንዱስትሪዎች ደረጃ ተወስደው እየተተገበሩ ነው:: ጥልቅ የሆነ በተንቀሳቃሽ ምስል ጋር የሚያያዝ የአካዳሚክ ምርምር በአብዛኛው በኮምፒተር መስክ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የኮምፒተር ሳይንስ ንዑስ ዘርፍ የሚዛመድ ነው ::
በዚህ ረገድ ቀደምት አስደናቂ ፕሮጀክት በ1997 የታተመ የቪዲዮ ዳግም መፃፍ ፕሮግራም ሲሆን ፣ አንድ የሚናገርን ሰው የሚያሳየውን የቪዲዮ ቀረፃ ቀይሮ በሌላ የድምፅ ትራክ ውስጥ የተካተቱትን ቃላቶች በአፍ ሲናገር የሚያሳይ ነው:: እንዲህ አይነት የማስመሰል ስራ ሲሰራ የመጀመሪያው ነበር:: የወቅቱ የአካዳሚክ ፕሮጀክቶች የበለጠ ተጨባጭ እና እውነተኛ የሚመስሉ ቪዲዮዎችን በመፍጠር እና ቴክኒኮችን በማሻሻል ላይ ያተኮሩ ናቸው::
እነዚህ የዲፕፌክ መስሪያ አፕሊኬሽኖች በቀላሉ በበይነ መረብ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ለእኩይ ዓላማ የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተበራከቱ መጥቷል:: ይህም ለሀገራት ከባድ ራስ ምታት ሆኗል:: ዲፕፌኮች አንዳንዴም አስገራሚ እና አስቂኝ ሲሆኑ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተዓማኒ ሚዲያዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች ተዓማኒነት ላይ ጭምር አደጋ ደቅነዋል::
የቢቢሲ ዘገባ እንዳስነበበው ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥልቅ የማታለል ተግባራት እየተበራከቱ እና እየተራቀቁ መምጣታቸውን ተከትሎ አንድን ምስል ወይም ቪዲዮ እውነተኛ ወይም ሀሰተኛ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ አዳጋች በመሆኑ እጅግ አደገኛ መዘዞችን ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ዲፕፌክ ለተለያዩ ዓላማዎች እየዋለም ይገኛል:: ለምሳሌ የአንድ ሀገር መሪ የሌላ ሀገር ስም የሚያጠፋ ነገር እንደሚናገር በማስመሰል ጥልቅ የማስመሰል ስራ የተሰራበት ቪዲዮ ቢለቀቅ በሀገራት መካከል ባላንጣነትን ብሎም ጦርነትን የማስከተል አቅም አለው::
በአሁኑ ወቅት ዲፕፌክ በሀሰተኛ ውንጀላዎች የሚከሰሱ ግለሰቦችን ለማጥቃት የሚያስችሉ የሀሰት ማስረጃዎችን ለማመንጨት ጭምር ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል:: ሆኖም ፣ ሐሰተኞቹን ማስረጃዎች ከእውነተኛ መለየት የሚቻልበት ሁኔታ ስላልነበረ የቀረበባቸው ማስረጃ የተጭበረበረ መሆኑን ለማስረዳት አዳጋች ነው::
ቴክኖሎጂ ሌሎች መልዕክቶችን እና ድርጊቶችን ለማጭበርበር የሚያገለግሉ ብቻ ሳይሆን የሞቱ ግለሰቦችን ጭምር ከሞት ተነስተው እንደተናገሩ አድርጎ ማቅረብ የሚያስችል መሆኑ ለዓለማችን ከባድ የቤት ስራ ሆኗል:: የዲፕፌክ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ ስልተ ቀመሮችን በማዋሃድ አዳዲስ ቪዲዮች ተሰርተው ብዙዎችን አስደምመዋል:: በአሜሪካን ሀገር የፓርክላንድ ተኩስ ሰለባ የሆነው ጆአኪን ኦሊቨር በዲፕፌክ ቴክኖሎጂ በህይወት እንዳለ አስመስሎ ቪዲዮ በመስራት የጠብመንጃ ደህንነት ዘመቻ ጥቅም ላይ ውለዋል:: የሟች ደጋፊዎች መንግስት በአሜሪካን ሀገር የጠብመንጃ ደህንነት ዙሪያ ጥብቅ ህግ እንዲያወጣ ጫና ለመፍጠር ተጠቅመውበታል::
“የዲፕፌክ” ቅንብሮች በተደራጁና ፕሮፌሽናል በሆኑ ሙያተኞች፣ አንዳንድ ጊዜም በመንግስታት ድጋፍ የሚደረግላቸው ቡድኖች የሚሠሩ በመሆኑ ሀገራዊ ምርጫን የሚያጠለሹና ህብረተሰቡን ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ እንዲያገኝ በማድረግ ወዳልተገባ ውዝግብ ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ::
ዲፕፌክ እየተበራከተ መምጣቱን ተከትሎ የሐሰተኛ ምስሎችን የተሳሳተ መረጃ ለማሰራጨት ተንኮል አድራጊ አካላት ሊጠቀሙበት ባለሙያዎች ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል:: ዲፕፌክ የሚያስከትለውን ችግር በመረዳት ሀያላን ሀገራት ሳይቀሩ ርብርብ ላይ ናቸው:: በአንድ በኩል የህግ ማዕቀፎችን እያዘጋጁ ዲፕ ፌክ መስራትን በወንጀልነት ከመፈረጅ አንስቶ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን እያዘጋጁ ነው:: በሌላ በኩል ዲፕ ፌክን የሚለዩ እና የዲፕፌኮችን ምንጭ መለየት የሚያስችሉ መተግበሪያዎች በማበልጸግ ላይ ላሉት የምርምር ተቋማትን ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል::
የቻይና እና የአሜሪካ መንግስታት ዲፕ ፌክን እንደ ትልቅ የስጋት ምንጭ በመቁጠር በደህንነት ፕሮግራሞቻቸው ላይ ቀርፀው አስቀምጠዋል። ለመከላከልም ጠንክረው በመስራት ላይ ናቸው:: በተለይ ቻይና ከሁለት ዓመት በፊት ነው ዲፕ ፌክን ሰርቶ ማሰራጨትን በግልፅ የከለከለችው። ይህም የችግርን አሳሳቢነት ደረጃ አመላካች ነው::
ኩባንያዎች ጥልቅ የሆነ በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ ማታለልን ለመከላከል በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል:: ሆኖም የማታለል ስራዎችን ለማጋለጥ ከሚንቀሳቀሱ ተቋማትን ግለሰቦች ባሻገር፤ ዲፕፌክን የበለጠ ለማሻሻል እና ወደ እውነተኛነት የቀረበ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱትም መኖራቸው ችግሩን ውስብስብ አድርጎ ቆይቷል::
ዲፕፌኮችን የመለየት ስራ ላይ ከተሰማሩት ተቋማት መካከል ፌስቡና ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሽ ናቸው:: ተቋማቱ በመተባበር በቅርቡ ዲፕፌኮችን የሚለይ ሶፍትዌር ይዘው ብቅ ብለዋል:: ተቋማቱ የሰሩት የመፍትሄ ስራ ዲፕፌኮችን ከመለየት ባሻገር የዲፕፌክ ቅንብሮችን ምንጫቸውንም መጠቆም የሚችል የሰው ሰራሽ አስተውሎት (የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ሶፍትዌር ማበልፀጋቸውን ይፋ ተደርጓል::
በፌስቡክ ተመራማሪ የሆኑት ታል ሀስነር እና ዢ ይን እንዳሉት የምርምር ቡድናቸው ከሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ነው በምልስ ምህንድስና (ሪቨርስ ኢንጂነርንግ) የዲፕፌክ ቅንብሮቹ እንዴት እንደተሰሩና መነሻቸውንም የሚያመለክት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሶፍትዌር ማበልፀጋቸውን ያብራሩት::
በጉዳዩ ዙሪያ ቴክ ኤክስፕሎር ሰሞኑን ያሰራቸው ዘገባ እንዳመላከተው፤ ሶፍትዌሩ በዲፕ ፌክ የተጠረጠሩ ስራዎች በዝግጅት ወቅት ቅንብሩ ላይ የሚስተዋል ስህተት በመመርመር የምስሉ/ቪዲዮው ዲጂታል አሻራ መቀየር አለመቀየሩን ያረጋግጣል:: የፎቶ ጥበብ አሁን ከደረሰበት ደረጃ አኳያ ዲጂታል አሻራን በመጠቀም ምስሉ የተዘጋጀበትን መሳሪያ ማወቅ ይቻላል::
በዚህ መልኩ የሚዘጋጁ ምስሎችም የራሳቸው የሆነ ልዩ አሻራ እንደሚኖራቸው ተመራማሪዎቹ የገለጹ ሲሆን ይህንንም በመጠቀም ምስሎቹ ከየት እንደመጡ መለየት እንደሚቻል ተመራማሪዎቹ አብራርተዋል:: አዲሱ ሶፍትዌር ዲፕፌክ ከመዝናኛነት አልፎ የዴሞክራሲ ፣ የጋዜጠኝነት እና የተግባቦት ዘርፎች አደጋ እንዳይሆን ይረዳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል::
በሀገራችን ጥልቅ የሆነ በፎቶ፣ በአውዲዮ እና በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ ማታለል ገና በጅምር ላይ ቢሆንም እየተተገበረ ይገኛል:: በተለይም በምርጫ መዳረሻ መራጮች የሚሰጡት ድምጽ ላይ ተጽዕኖ ለማሳረፍ በድምጽ፣ በፎቶ እንዲሁም በቪዲዮ የታገዘ የማታለል ሙከራዎች ታይተዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስለ ምርጫው እና ከምርጫው በኋላ ስለሚከናወነው ነገር ያልተናገሩትን እንደተናገሩት አድርጎ በማቅረብ በህዝቡ ዘንድ ግርታ ተፈጥሮ እንደነበር ታይቷል::
አሁን ላይ ዲፕ ፌክ በሁሉም ቦታ እየሆነ ነው:: ከዲፕ ፌክ የማምለጥ እድላችን በጣም አዳጋች ቢሆንም በሀገራችን ቀላል የፎቶ ቅንብሮችን የሚለየው እና በመተግበሪያዎች አማካኝነት የሚያጣራው ሰው በጣም ጥቂቱ ነው። አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ ፌስቡክ ላይ የተፃፈ እና ዩትዩብ ላይ የተወራ ሁሉ እውነት የሚመስለው እንደሆነ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል::
የዲፕ ፌክ ችግርን መቆጣጠር የሚቻለው ህብረተሰቡን በማንቃት ነው:: ህብረተሰቡ ከነቃ መተግበሪያዎችን በመጠቀም አጠራጣሪ የሆኑ ቪዲዮችን እና ፎቶዎችን በመተግበሪያዎች ውስጥ በማስገባት ማጣራት ይችላል:: ህብረተሰቡን የማንቃት ሀላፊነት ደግሞ የብዙሃን መገናኛዎች ነው:: ማንቃት የሚገባቸው ሚዲያዎች በዚህ ዙርያ ሲሰሩ ግን እምብዛም አይታዩም:: እንደውም አንዳንድ ሚዲያዎች የፎቶዎችን እና የቪዲዮዎችን እውነተኝነት ሳያረጋግጡ ራሳቸው ሀሰተኛ ምስሎችን እና መረጃዎችን አልፎ አልፎ ሲያጋሩ እናያለን።
በመሆኑም መንግስት በዲፕፌክ ዙሪያ ብዙኃን መገናኛዎች አስፈላጊውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት ሚዲያዎች ራሳቸው የጉዳዩን ምንነት፣ አሉታዊ ጎን እና መፍትሄዎችን አውቀው ለህብረተሰቡ እንዲያሳውቁ አስፈላጊውን ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል:: ከዚህ ጎን ለጎን በዘርፉ ፍላጎት እና እውቀት ያላቸው ግለሰቦች በጉዳዩ ዙሪያ እንዲሰሩ ማበረታታት እና መረጃ ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ማቅረብ ያስፈልጋል:: ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ አደገኛ ነው::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2013