
በአሁኑ ወቅት ተመራጭ የሆነውን የግንባታ ሥራ ወደ ጎን ማስፋት ሳይሆን ወደ ላይ መገንባት ነው::ለዚህም ከሚሰጡት ምክንያቶች መሬትን በአግባቡና በቁጠባ ለመጠቀም፣ ፍትሐዊነትንም ለማስፈን፣ ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ለመዘመን…. ከሚነሱት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው::በመሆኑም ለመኖሪያም ሆነ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ህንፃዎች በሥፋት እየተገነቡ ይገኛሉ ::
በመንግሥት ከተከናወነው የቤት ልማት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለአብነት የሚጠቀስ ሲሆን፣በግል ቤት አልሚዎችም በተመሳሳይ ተከናውኗል ። አሁንም በመሰራት ላይ ይገኛል :: ቀደም ሲልም በከተሞች የመኖሪያና ለአገልግሎት የሚውሉ ህንፃዎች ተሰርተው በአገልግሎት ላይ የዋሉ ቢሆኑም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ወደላይ የሚገነባው የህንፃ ግንባታ ሥራ በመሥፋት ላይ ይገኛል :: ነባራዊ ሁኔታውም የሚያሳየው በዚሁ እንደሚቀጥል ነው :: ወደላይ የሚገነባው የህንፃ ከፍታም ጨምሯል:: በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ህንፃ ተብሎ የሚጠቀሰውና የኪነህንፃ ጥበቡም የሚደነቀው ህንፃ ከዛሬ አምስት አመት በፊት ግንባታው የተጀመረውና አሁን በመጠናቀቅ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሲሆን፣ ከምድር በታች አራት ደረጃዎችና ወደላይ ደግሞ 46 ወለሎች(ፎቆች) ያለው ነው::ህንፃው የቢሮ፣ መዝናኛና ከተማዋን ለማየት በሚያስችል ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ የተሰራ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ :: ለከተማዋ ጥሩ ገጽታ እየሰጠ እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት የቀድሞውም ህንፃ ቢሆን ከአምስት አስርት አመታት በፊት ሲሰራ በተመሳሳይ ለከተማዋ ልዩ እና በዘመኑም ትልቁ ህንፃ እንደነበር ይነገርለታል::ተቋሙ በተለያየ ዘመን በህንፃ ከፍታውና የህንፃ ሥነጥበብ ባለታሪክ ሊሆን ችሏል::
ታዲያ የህንፃ ጥበብንም እያየንና እየተገለገልንበት ባለንበት በዚህ ዘመን መልካም ጎኑ የበዛ ቢሆንም ክፍተቶችንም ለማየት ችለናል :: በህንፃ ግንባታ ውስጥ ድምጽን፣ ፍሳሽንና ሽታን የሚቀንስ ቴክኖሎጂ አብሮ እንደሚሰራ ሲነገር ይሰማል:: ይሁን እንጂ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ተካትተው ስለመሰራታቸው በአንዳንድ አገልግሎት ላይ በዋሉ ሕንፃዎች ውስጥ የምንታዘባቸው ነገሮች ጥርጣሬ ውስጥ ይከቱናል:: በጋራ መኖሪያ ቤትም ሆነ የተለያየ አገልግሎት በሚሰጡ ህንፃዎች ውስጥ በፍሳሽ ምክንያት የህንፃዎቹ የውስጥ ክፍል ቀለማቸው ተለውጦና ወደሻጋታነት ተቀይሮ ይታያሉ::
ፍሳሹ ባስ ሲልም እንደዝናብ ይንጠባጠባል:: ከመፀዳጃ ቤት ውሃ ሲለቀቅ፣ ንጽህና ሲወሰድ፣እርምጃ ሳይቀር ድምጽ ይሰማል ከሚባለው በላይ ይረብሻል:: የጥገና ሥራ ሲከናወንማ ህንፃው የሚፈርስ እስኪመስል ስጋት ውስጥ ይጥላል :: ለተለያየ አገልግሎት የዋሉት ህንፃዎች (ሞል) ተብለው በሚጠሩት ውስጥ ያለው የድምጽ ብክለት ድብልቅልቅ ካለው የውስጥ አገልግሎታቸው ጋር ተደምሮ የመረበሽ ስሜት ይፈጥራል:: በአንድ በኩል የምግብ፣በሌላ በኩል የመጠጥ፣ የሻይና ቡና አገልግሎት ከሚሰጠው የሚለቀቀው ሙዚቃ ፣በሌላ በኩል የአካል ብቃት አገልግሎት ከሚሰጡና ስፖርት ዞን ከሚባሉት የሚወጣው ድምጽ፣ የተገልጋዩ ድምጽ ተደምሮ ወደነዚህ ህንፃ ውስጥ ሲገቡ የተረበሸ ከተማ ውስጥ ያሉ ያህል ይሰማል :: ወደነዚህ ህንፃዎች ውስጥ ለአገልግሎት የሚገቡ ሰዎች ከህፃን እስከ አዛውንት ናቸው::እነዚህን ሁሉ ባማከለ የድምጽ ልቀት ባለመኖሩ ክፍተቱ የበዛ ነው::ከዚህ ቀደም ከህንፃዎች ውጭ ከድምጽ ብክለት ጋር ተያይዞ ቅሬታ ይነሳ ነበር ::ለመሆኑ እንዲህ በህንፃዎች ውስጥ ስለሚስተዋሉ የድምጽ፣ የፍሳሽ፣ የሽታ ሁኔታና ክፍተቶቹን ለማስወገድ ስለሚረዳው ቴክኖሎጂ በግንባታ ዘርፉ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን ጠይቀናል::
ቴክኖሎጂውንና ያለውን ክፍተት መሠረት አድርገው ሀሳባቸውን ያካፈሉን ሌላው አመሐ ስሜ የህንፃ ሥራ ተቋራጭ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት ኢንጂነር አመሐ ስሜ ናቸው። ኢንጂነር አመሀ እንደሚሉት፤ ክፍተቱ ከሚገነባው ህንፃ ዕቅድ ይነሳል :: ህንፃው ከመገንባቱ በፊት ለምን አገልግሎት እንደሚውል የቅድመ ህንፃ አዋጭነት ጥናትና የህንፃ ንድፍ (ዲዛይን) ሲሰራ ሲከናወን ህንፃው ለምን አገልግሎት እንደሚውል፣ለሚገነባው ህንፃ የሚውለው የግንባታ ጥሬ ዕቃና ሌሎችንም አስፈላጊ ነገሮች ቀድሞ በማከናወን አሁን የሚነሱ የድምጽ፣ የፍሳሽና የሽታ ብክለት ስጋትንና ክፍተቶችን ማስቀረት ይቻላል :: ቴክኖሎጂው ሲታከልበት ደግሞ የበለጠ ውጤታማ መሆን ያስችላል:: ቴክኖሎጂው ቀደም ሲል በነበሩ የግንባታ ሂደቶችም ሆነ በአሁኑ ዘመን እየተሰራበት ነው :: አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የቅድመ ህንፃ ግንባታ ዕቅድ ችግር ነው ጎልቶ የታየውና ክፍተቱንም የፈጠረው :: ቅድመ ጥናት አዋጭነት ላይ ትኩረት ተደርጎ ካልተሰራና በጥናቱ መሰረት መተግበር ካልተቻለ ችግሩ ሊፈታ አይችልም :: ለመዝናኛና ለሆቴል አገልግሎት ተብለው የሚገነቡ ህንፃዎች ከታለመላቸው ውጭ አገልግሎት በመስጠት የተነሱት የብክለት አይነቶች ይስተዋልባቸዋል::
ከቅድመ ህንፃ አዋጭነት ጥናትና ንድፍ ቀጥሎ የሚመጣው በጥናቱ መሠረት መተግበሩን ክትትል ማድረግ ነው :: ክትትልና ቁጥጥሩ የጥራት መጓደልን ለማስቀረት ስለሚያግዝ ያለመታከት እስከ ግንባታው ማጠናቀቂያ መሰራት ይኖርበታል :: ይህ ደግሞ የአሰሪው ኃላፊነት ይሆናል :: አሰሪው ግለሰብም መንግሥት ሊሆን ይችላል :: ይህ ሲባል ግን ከአዋጭነት ጥናት ጀምሮ እስከግንባታው መጠናቀቅ ድረስ የሚሳተፈው ባለሙያ ኃላፊነት እንደሌለበት ተደርጎ መወሰድ የለበትም :: ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ-ምግባር ተከትሎ የመሥራት ትልቅ ኃላፊነት አለበት :: እላፊ የሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲባልና በግዴለሽነት የሚሰሩ ሥራዎች ሙያን፣በህንፃው የሚጠቀመውንና አገርን ስለሚጎዳ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን በኃላፊነት መወጣት ይጠበቃል ::
ኢንጂነር አመሐ በግንባታ ውስጥ የሚታዘቧቸውንና ያጋጠማቸውን አስመልክተው እንዳሉት ፤ግንባታው የሚከናወንበት ወይንም ህንፃው የሚያርፍበት ቦታ የመሬት አቀማመጥ ሁኔታ፣ የአካባቢው የአየር ንብረትና ሌሎችም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በቅድመ ህንፃ የአዋጭነት ጥናት ምቹነታቸውና ተስማሚነታቸው መለየት ይኖርበታል :: ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በቅድመ ጥናት አዋጭነት ጥናት ላይ ተሟልቶ እየተሰራ አይደለም :: ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ከነዚህ መካከል አንዱ የአሰሪው አካል ፍላጎት ጣልቃ ገብነት ነው:: ለአብነትም የአንድ ወቅት ገጠመኛቸውን ኢንጂነሩ እንደገለጹት፤በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የካ አባዶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የንድፍ (ዲዛይን)ሥራው ያለቀለት የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ለማከናወን የተዘጋጀው ቦታ ትክክል ሆኖ አላገኙትም :: በወቅቱ ባከናወኑት የቅየሳ ሥራ በቦታው ላይ የአራት ሜትር ከሃምሳ ሳንቲ ሜትር የከፍታ ልዩነት አገኙ :: ልዩነቱ ባመጣው ክፍተት ንድፍ(ዲዛይን)ሥራው ዳግመኛ መሰራት ነበረበት:: ምክንያቱም ለግንባታ ሥራው የተገባው ውል ልዩነቱን ሳያካትት ነበር ተቋራጩ በውሉ መሠረት ስለሚሰራ የተገኘው ትርፍ ቦታ ይባክናል:: ተቋራጩ ከውል ውጭ ቢሰራ ደግሞ ለኪሳራ ይዳረጋል:: በወቅቱ የነበረው ውሳኔ ንድፉን እንደገና መሥራት ነበር :: በድጋሚ ለመሥራት ሰባት ወራት ጊዜ ወስዷል :: መዘግየቱ በአሰሪውና በተቋራጩ ላይ የጊዜ ብክነት፣የገንዘብ ወጭና የተለያዩ ኪሳራዎችን አስከትሏል:: እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ለፕሮጀክቶች መጓተትም ምክንያት እየሆኑ ነው :: ክፍተቱም ይደጋገማል :: ቀድሞ በጥንቃቄ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ ግን የተፈጠሩትን ችግሮችም ማስቀረት ይቻላል :: ለዚህም ነው የአዋጭነት ጥናትና የንድፍ ሥራ በግንባታ ሥራ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ አላቸው የሚባለው :: ቅድመ ሥራው ተከናውኖ በተቋራጩ በኩል የሚፈጠሩ ችግሮች ካሉ ደግሞ የተጠናቀቀው ህንፃ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አለ ። በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በህንፃው ላይ የመሰንጠቅም ሆነ ሌሎች ችግሮች ከተስተዋሉ መልሶ የሚያርምባቸው አሰራሮች ስለተቀመጡ የእርማት ሥራው ይከናወናል::
መዘግየቱ በአሰሪውና በተቋራጩ ላይ የጊዜ ብክነት፣የገንዘብ ወጭና የተለያዩ ኪሳራዎችን አስከትሏል:: እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ለፕሮጀክቶች መጓተትም ምክንያት እየሆኑ ነው :: ክፍተቱም ይደጋገማል :: ቀድሞ በጥንቃቄ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ ግን የተፈጠሩትን ችግሮችም ማስቀረት ይቻላል :: ለዚህም ነው የአዋጭነት ጥናትና የንድፍ ሥራ በግንባታ ሥራ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ አላቸው የሚባለው :: ቅድመ ሥራው ተከናውኖ በተቋራጩ በኩል የሚፈጠሩ ችግሮች ካሉ ደግሞ የተጠናቀቀው ህንፃ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አለ ። በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በህንፃው ላይ የመሰንጠቅም ሆነ ሌሎች ችግሮች ከተስተዋሉ መልሶ የሚያርምባቸው አሰራሮች ስለተቀመጡ የእርማት ሥራው ይከናወናል::
ተቋራጩ የሰራውን ህንፃ አጠናቅቆ ሲያስረክብ ክፍተቶችን ለማረም የጊዜ ገደብ ተቀምጧል :: አሰሪው ከተቋራጩ የሚይዘውም ገንዘብ አለ :: ይሁን እንጂ በተግባር እየሆነ ነወይ የሚለው በተለይ በመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ያጠያይቃል :: በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት ላይ የቤት ዕድለኛው ቤቱን ከተረከበ በኋላ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ቤቱን ያስረከበው አካል እንዲያይለት ጥያቄ ሲያቀርብ ሂደቱ አመልካቹን የሚያሰለች በመሆኑ በራሱ ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ የአንዳንዶችን ገጠመኝ ማንሳት ይቻላል::እዚህ ላይም ኢንጂነር አመሐ የአሰሪው አካል ድክመት እንደሆነ ነው በአጭሩ ምላሽ የሰጡት :: በመልሶ ማስተካከል ላይ ግን ሁለት ነገሮች እንዳሉ አንስተዋል :: በድጋሚ የሚታየው ሥራ አሰሪውን ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል :: ይሄን ለማድረግ ደግሞ የማይቻልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል :: እንዲህ ያለው ነገር በአስፈፃሚው በኩል ችግር ለመፍታት የሚያነሳሳ ላይሆን ይችላል :: ይህ ተፈርቶ ደግሞ አለማስተካከሉ ተገቢ አይደለም :: በአጋጣሚም ተጨማሪ ወጪ ላይጠይቅ የሚችልበት አጋጣሚ በመኖሩ :: ኢንጂነር አመሐ፤የተነሳንበትን ርዕሰ ጉዳይ መሠረት አድርገው ሀሳባቸውን ሲያጠቃልሉ የተለያዩ ብክለቶችን ለመቀነስ በሚረዱ ቴክኖሎጂዎች ላይም ዘመኑ የሚጠይቀው አዳዲስ አሰራሮች እየመጡ ቢሆንም ከተለመደው ውጭ ለመንቀሳቀስ ያለው ፈቃደኝነትም እምብዛም እንዳልሆነ ተናግረዋል::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ የአርክቴክቸር ህንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት መምህርና የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ዋና ዳይሬክተር አርክቴክት ብሥራት ክፍሌ እንዳሉት ፤በግንባታው ዘርፍ ውስጥ የቅይጥ አገልግሎት የሚባል ነገር አለ :: ይሄ ከቃሉ ጀምሮ ችግር አለበት :: ከታች ሙዚቃ ቤት ፣ ከላይ ቤተ መጽሐፍት፣ ሌላው ክፍል መኖሪያና ጭፈራ፣ሌላው ጋር ሌላ ነገር :: ይሄ ቅይጥ ሳይሆን፣ረብሻ ነው የሚባለው :: አንድ ህንፃ በቅድመ ግንባታ ወቅት ምንና ምን ተጣጥመው መሰራት አለባቸው የሚለው መታየት አለበት ። እርሳቸው ባላቸው መረጃ አሁን ባለው ሕግና መመሪያ መሠረት በከተሞች እያንዳንዱ ህንፃ 40 በመቶ ወይንም 50 በመቶ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት እንዲውል ተደንግጓል :: ከታች እስከ አራተኛ ወለል ያለው ለንግድ አገልግሎት ይውላል ከዚያ በላይ ያለው ደግሞ ለመኖሪያ ቤት ይውላል :: ይሄ ለምን ሆነ ሲባል ከተማው ቀን ቀን ገበያ ካልሆነ የከተማው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ይዳከማል ከሚል በጎ እሳቤ የመነጨ ቢሆንም በራሱ ውጤት አያመጣም :: ምክንያቱም ከታች የተለያየ ድምጽ የሚያወጣ ነገር እያለ ከላይ ደግሞ ፀጥ ያለ መኖሪያ እንዲሆን ፈቅዶ ስለድምጽ ብክለት ማውራት ትርጉም የለውም :: ከዚህ ውጭ ለተለያየ ንግድ ተብለው የተገነቡትም ቢሆኑ ተመጋጋቢ ቢሆኑ ይመረጣል::
ለአብነትም የኢንዱስትሪ፣የግንባታ ግብአቶችና የተለያዩ አገልግሎቶች መነሻዎችን መለየት ቢቻል የተሻለ ነው :: ምክንያቱም አንዳንዶቹ አገልግሎቶች ድምጽ የሚያወጡና ተቀጣጣይ ነገር የሚያስከትሉ ሊሆኑ ስለሚችሉ እነዚህን ታሳቢ ያደረገ ግንባታ ቢከናወን የሚነሱ ስጋቶችን መቀነስ ይቻላል::ለአብነት ለህክምና አገልግሎት የሚውል ህንፃ ከሆነ የወለል፣የኮርኒስ፣የበር፣የመስኮት፣አይነት የቤቱ ስፋት ቀለም ጭምር መስፈርቶች አሉት :: በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግንባታዎች ለምን አገልግሎት እንደሚውሉ በቅድመ ግንባታ ወቅት ጥርት ያለ ነገር አለመኖር፣የግንባታ ግብአቶችንም እንደየአገልግሎቱ ለይቶ አለመጠቀም፣በህንፃው ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች አለመጣጣም ከክፍተቶቹ መካከል ጥቂቶቹ ይጠቀሳሉ::ህንፃው ተገንብቶ አገልግሎት ላይ ከዋለ በኋላም ውስጡን ለመከፋፈል በሚደረገው ጥረት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለማከፋፈል የዋለው ግብአትም ለብክለት መከሰት ተጨማሪ መንስኤዎች ናቸው::ሌላው አርክቴክቱ ያነሱት ለትምህርት ተቋማትና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ አካባቢዎችንም ለይቶ ማመቻቸት አልተለመደም :: በእርሳቸው እምነት መርካቶ ገበያ ላይ የመኖሪያ ቤት ሰርቶ የተቀላቀለ እድገት ለማምጣት በሚደረግ ጥረት ብክለትን ማስቀረት አይታሰብም :: እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ቢኖሩም መፍትሄዎችንም ስላሉ ጭልም ያለ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም ያሉት አርክቴክቱ ችግሩን ለመረዳት ዝግጁ መሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሲሆን፣ቀጥሎ በእርምጃ ማስተካከል ነው :: ቅድሚያ የሚሰጣቸውንና የትኛው ለየትኛው አገልግሎት ይዋል የሚለውን በጥናት በተደገፈ መተግበር ይጠይቃል::
የሙያ ሥነምግባሩ በድምጽ ብክለት መቀነስ ላይ ምን ይላል ለሚለው አርክቴክት ብሥራት እንዳስረዱት፤ድምጽን የሚስተጋባውን ለማስቀረት በግንባታው ዘርፍ ውስጥ በትኩረት ከሚሰራባቸው መካከል ሲኒማ ቤቶች፣የስብሰባ አዳራሾች፣በአጠቃላይ ብዙ ሕዝብ የሚስተናገድባቸው በንድፍ ወቅትም ሆነ ሲገነባ በትኩረት ይሰራሉ :: የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችንም በተመለከተ ከመታጠቢያና ከመፀዳጃ ቤቶች የሚወጡ ፍሳሾችንና የድምጽ ብክለትን ለመቀነስ አሁን አሁን ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች በግንባታው ወቅት መጠቀም እንደሚቻልም አስረድተዋል::ጥሩ የሚባሉ ተሞክሮዎችም መኖራቸውን ተናግረዋል::
የመከላከያ ግብአቶቹ ከውጭ የሚገቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በዋጋ መወደድ ጋር ተያይዞ ክፍተት እንዳይፈጠር በእጅ ላይ በሚገኝ ዘዴ ለመጠቀም መሞከር እንደሚገባም መክረዋል::የቦታና የክፍል አጠቃቀም ላይ እንዲሁም በህንፃዎቹ ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች ጋር የሚናበብ ሥራ ማከናወን ከመፍትሄዎቹ መካከል ጥቂቶቹ እንደሆኑም ጠቁመዋል::
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የቀደሙት ህንፃዎች ሲገነቡ የነበሩት የአገልግሎት ዘመናቸው እንዲረዝም ብቻ ሳይሆን ከተማዋን የሚመጥኑ መሆን እንዳለባቸው ታሳቢ በማድረግ ጭምር እንደሆነና የዕድሳት ሥራቸውም መጠነኛ ወጭን የሚጠይቁ በሆነ መልኩ እንደሆነም አስታውሰዋል :: የአሁን ከቀደመው ጋር ሲያነፃጽሩም የግንባታ ሥራው በቂ ጊዜ ሳይሰጠውና በበቂ ጥናትም ሳይዳብር ቶሎ ትርፍ በሚያስገኝ ነገር ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ታዝበዋል::
በህንፃ ግንባታ ውስጥ ያሉት አማካሪ ድርጅቶች ሚና ጉዳይም አርክቴክት ብሥራት ለቀረበላቸው ጥያቄ በግንዛቤ እጥረት፣ካለው ጫና በተለያየ ምክንያት አማካሪዎችም በጥፋቱ ውስጥ መኖራቸውን አልሸሸጉም:: በሌላው ዓለም አንድ አማካሪ በዓመት ቢበዛ ሁለት ህንፃዎች ቢሰራ ነው :: በቂ ጊዜና ተመጣጣኝ ክፍያ አግኝቶ ስለሚሰራ ጥሩ ነገር ያስረክባል::በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን የተሟላ ነገር የለም አማካሪው የሚከፈለው ክፍያ ከጎረቤት አገር ኬንያ ጋር እንኳን ሲነፃፀር አነስተኛ ነው:: ማማከርን መተዳደሪያው ላደረገ በሥራው ላይ የራሱ ተጽዕኖ አለው::
በመፍትሄነትም ከጠቀሷቸው መካከል አንዱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከሚያፈልቁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ቴክኖሎጂዎቹን በማላመድ መስራት ይጠበቃል:: ችግሮችን ወደሌላ ከመወርወር በጋራ ለመፍታት ጥረት መደረግ አለበት::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2013