
ሙስና እንደ ተላላፊ በሽታ አለምን ያዳረሰ መጥፎ ክስተት ቢሆንም በአህጉረ አፍሪካ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ግን የከፋ ነው:: የአፍሪካ እድገት በሚፈለገው ፍጥነት እንዳያድግ ከሚያደርጉት ተግዳሮቶች ሙስና አንዱና ዋነኛ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል::
ለሙስና መስፋፋት ጉልህ ሚና የሚጫወተው ሥልጣን መሆኑ ታምኖበታል:: አንዳንድ ባለሥልጣናት የተሰጣቸውን የሕዝብና የመንግሥት ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ራሳቸውን ወይም ዘመዳቸውን በሙስና ለማፈርጠም ሲፍጨረጨሩ ማየትና መስማት በተለይ በአፍሪካ የተለመደ ተግባር ሆኗል::
ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ የሙስና ቀውስ የዓለም መነጋገሪያ መሆኑን ቢቢሲ አስነብቧል :: የአገሪቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በፕሬዚዳትነት ዘመናቸው ሙስና ከሚገመተው በላይ እንደተንሰራፋ ይነገራል:: በዚህ ምክንያት አሁን ላይ በአገሪቱ የሙስና አሻራዎች ሁሉንም እንቅስቃሴዎችን ሽባ ከማድረጋቸውም በላይ የአገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባሉ የሚል ስጋት አስከትለዋል::
እንደ ዘገባው ከሆነ ፕሬዚዳንቱ በሙስና የተጨማለቁ ፈርጣማ ኩባንያዎችን በማበረታታቸው በአገሪቱ የመንግሥት መዋቅሮች በተለይ የሕግ አስፈጻሚ መዋቅሮች ከሥራ ውጭ እንዲሆኑ በማድረጋቸው በፍርድ ቤት እየተፈለጉ ይገኛሉ :: በእሳቸው ጊዜ በደቡብ አፍሪካ አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ወይም ወንጀል ከሰሩ በሕግ አግባብ መጠየቅ እምብዛም አልነበረም:: ይልቁንስ በሰሩት ወንጀል ለአገሪቱ የፖሊስ አካላት ገንዘብ ከሰጡ ተመሳሳይ ወንጀል ደግመው ቢሰሩ ማንም አይጠይቅም::
ሆኖም ግን ችግሩ ያንገሸገሻቸው፣ ፍትህን በገንዘብ መግዛት የማይችሉና ከሥልጣን ነጻ የሆኑት የአገሪቱ ሕዝብ ‘ሆ ብለው” በአደባባይ በመውጣት ባደረገው እልህ አስጨራሽ ተቃውሞ ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን ለማስወገድ ችሏል::
በተለይ ፕሬዚዳንቱ በዋናነት በሙስና የተከሰሱበት ጉዳይ በአገሪቱ ታዋቂውና ተጽዕኖ ፈጣሪው ጉፕታ የሚባለው ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያዎች ጋር ተያይዞ ነው:: ኩባንያዎቹ በአገሪቱ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩና እጅግ ትርፋማ እንደሆኑ ይነገራልና :: የኩባንያዎቹ ባለቤት የህንድ ዜጎች መሆናቸው በይፋ ቢነገርም በውስጥ አዋቂነት ትልቁን ድርሻ የያዙት ጃኮብ ዙማ መሆናቸው በክስ ፋይላቸው ላይ በግልጽ ሰፍሯል::
ከፕሬዚዳንቱ ሚስቶች አንዷ የሆነችው ቦንጊ ንገማ ዙማ በጊፕታ ቁጥጥር ስር በነበረው ጄ.አይ.ሲ የማዕድን አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሆና ስትሰራ በነበረችበት ወቅት በሙስና 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ራንድ ቢከፈላትም እሷ ግን ይህንን አስተባብላ ነበር:: በተመሳሳይ መልኩ የፕሬዚዳንቱ ሴት ልጅ ልክ አባቷ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ለስድስት ወራት ያህል የሰሃራ ኮምፒውተሮች ኩባንያ የሚባል ድርጅት በዳይሬክተርነት አገልግላለች:: በዚህ አላበቃም፣ የፕሬዚዳንቱ ወንድ ልጅም የጉፕታ ንብረት የሆኑ የተወሰኑ ኩባንያዎችን በዳይሬክተርነት ካገለገለ በኋላ በሕዝብ ግፊት ከስልጣን ሊወርድ ችሏል :: በጥቅሉ ፈርጣማ ኩባንያዎች በፕሬዚዳንቱና በፕሬዚዳንቱ ቤተሰብ ቁጥጥር ስለነበሩ የመንግስት መዋቅርን የማዳከም አቅማቸው ከፍተኛ ነበር::
ይህ ሁሉ ችግር ሲፈጠር ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ትንፍሽ ያሉበት ጊዜ አልነበረም:: ያሁኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበረውን የሙስና ቀውስ ጃኮብ ዙማ ቀርበው ግልጽ እንዲያደርጉ በአገሪቱ ፍርድ ቤት በኩል ትዕዛዝ ቢያቀርብም ጃኮብ ዙማ በተደበቁበት ቦታ ሆነው ማስተባበያና ንቀት ያዘለ ቀልድ መወርወር ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል::
ይባስ ብለው“የነጮች የበላይነት እንዲከስምና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን የታገልኩ ሰው ነኝ:: ታዲያ እኔ ባልሰራሁት ጥፋት ሙሰኛ ካደረጋችሁኝ ራሳችሁ ተወጡ” በማለት ለአገሪቱ ፍርድ ቤት ማስጠንቀቂያ አዘል ማስተባበያ ሲያሰሙ ተደምጠዋል::
የአገሪቱ ፍርድ ቤት ግን ፕሬዚዳንቱን ለፍርድ ለማቅረብ በልበ ሙሉነት መስራቱን ቀጥሏል:: ፕሬዚዳንቱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ባለማክበራቸው ብቻ የ15 ወራት እስራት በይኖባቸዋል :: ጃኮብ ዙማ ካሉበት በ5 ቀናት ውስጥ እጃቸውን ለፖሊስ እንዲሰጡም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል::
ሆኖም ግን የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች በኮሮና ምክንያት በብዛት ያለመሰብሰብ ሕግ ጥሰው የፕሬዚዳንቱ ቤት እንደ ንብ ከበዋል:: ፕሬዚዳንቱም የተሰበሰበውን ሕዝብ ተስፋ በማድረግ ፖሊስ በምንም መንገድ አልፈው እሳቸውን መያዝ እንደማይችሉ በመተማመን ገልጸዋል:: ይልቁንስ በእሳቸው ላይ የሚደርሰው ችግር አገሪቱ ወደ ጥፋት የሚወስድ ተቃውሞ እንዳያስነሳ አስጠንቅቀዋል::
በጥቅሉ በጃኮብ ዙማ የፕሬዚዳንትነት ዘመን በደቡብ አፍሪካ፣ ሥራ ለመግባት፣ የግል ጉዳይ ለማስፈጸም፣ የንግድና የሌሎች እድል ተጠቃሚ ለመሆን በአጠቃላይ ፍትህ ለማግኘት ዋናው መስፈርት ገንዘብ መስጠት እንደ ነበረ በዘገባው ተገልጿል:: በወቅቱ ስር የሰደደ ሙስና አሁን ላይ በአገሪቱ የሚደረገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አዳጋች አድርጓል :: ሰንሰለቱን ለመበጣጠስ ጊዜ የሚወስድ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ የጉዳዩ ባለቤትም ድምጹን አጥፍተዋል::
እንደ ተባለው ፕሬዚዳንቱ በአምስት ቀናት ውስጥ እጃቸውን ሰጥተው የሕግ የበላይነት ይረጋገጣል ወይስ በተቃውሞና በገንዘብ ጉልበት ፕሬዚዳንቱ ባሉበት ሆነው ፍትህ ይከስማል? ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ይሆናል::
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2013