
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት 500 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡ ህብረተሰቡ በጁንታው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሳይደናገር የተጀመረውን የልማት፣ የሰላምና ሌሎች ስራዎችን አጠናክሮ ሊቀጠል እንደሚገባ አመለከቱ፡፡
“ክብር ለሀገራችን አንድነት እና አብሮነት ለቆሙ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን” በሚል የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳዮች፣ ለሰራዊቱ በሚደረጉ ድጋፎች፣ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ዙሪያ ትናንት ውይይት በተደረገበት ወቅት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች እንደገለፁት፤ የከተማ አስተዳደሩ ለመከላከያ ሰራዊቱ ደጀን በመሆን ሰራዊቱን ለመደገፍ የ500 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደርጋል።
ህብረተሰቡንም በማስተባበር ሰራዊቱን በገንዘብና በቁሳቁስ ለማጠናከር እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ አዳነች፣ ሕይወቱን ሰውቶ አገሪቱን በአሸባሪው ጁንታ ተደቅኖባት ከነበረው ስጋት በመታደግ ከደጀኑ የተጠጋውን ሠራዊት በእጅጉ እናከብረዋለን ብለዋል።
‹‹አሁን የሚቀረን ካሳለፍነው የባሳ አይደለም›› ያሉት ከንቲባዋ፤ ለመከላከያ ሀይላችን በተቀናጀ መልኩ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ህብረተሰቡ በጁንታው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሳይደናገር የተጀመረውን የልማት፣ የሰላም እና ሌሎች ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ መከላከያ አሸንፏል፤ ጁንታው ላይመለስ ተንኮታኩቷል›› ያሉት ወይዘሮ አዳነች፣ የፌዴራል መንግስት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ አቁም ትክክለኛ እና ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ የትግራይን ህዝብ ከጁንታው ጋር አንድ አድርገን አናየውም፣ ህዝቡ በተሳሳተ መልኩ እንዳይሄድ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የህዳሴ ግድባችን ሃይል ለማመንጫት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት ከንቲባዋ፤ የኢትዮጵያ የብልጽግና ተስፋ የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ለማጠናቀቅ ህዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠልና አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
ፀጋዬ ጥላሁን
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2013