አንተነህ ቸሬ
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያን፣ በተለይም የትግራይን ሕዝብ ከጠላት በሚጠብቀውና ለትግራይ ሕዝብ ብዙ ውለታ በዋለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥትም ቡድኑን ለሕግ ለማቅረብ የሕግ ማስከበር ዕርምጃ መውሰዱ የሚታወስ ነው።
የሕግ ማስከበር ዕርምጃ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የታየው የመገናኛ ብዙኃን አሠራር እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነትና የፕሮፖጋንዳ ክዋኔ/አመራር ሰፋ ያለና ራሱን የቻለ ትንተና ያስፈልገዋል። የዛሬው ትዝብቴ ትኩረትም የዚህ ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ አካል የሆነውና ከመንግሥት መዋቅር ውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ የኅብረተሰብ ክፍል የህወሓታውያኑን ዘመቻ ለመመከት ባከናወናቸው ተግባራት ውስጥ በታዩ ድክመቶች ላይ የሚያጠነጥን ይሆናል። የህ.ወ.ሓ.ት ወዳጆች ዘመቻ የሕግ ማስከበር ዕርምጃው ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ (የውጭ) መገናኛ ብዙኃን ስለጉዳዩ የሚያሰራጩት ዘገባ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ተገቢ ያልሆነ ነው። ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ስለጉዳዩ ያላቸው ግንዛቤ ከእውነታው በእጅጉ የራቀ ሆኖ ታዝበናል። ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለጉዳዩ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ (እንዲኖረው) አድርጓል።
ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ጠላቶች ‹‹ኢትዮጵያን ለመበታተን ከዚህ የተሻለ ጊዜ/ዕድል አናገኝም›› ብለው ታጥቀው እንዲነሱና በረጅም ጊዜ ታሪኳ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን፤ ከኃይል ይልቅ ንግግርን ለማስቀደም እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ትብብርንና ወንድማማችነትን የሚያሰፍኑ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲመሰረቱና እንዲጠነከሩ ባላት ቁርጠኛ አቋም የምትታወቀው ኢትዮጵያ ስሟ እንዲጠለሽ በር ከፍቷል። ነገሩን ይበልጥ ለማፍታታት ስለህ.ወ.ሓ.ት ወዳጆች ዘመቻ በጥቂቱ እንመልከት።
የቀድሞ ወዳጃቸውን የህ.ወ.ሓ.ትን ‹‹ውድቀት›› አምኖ መቀበል ያቃታቸው ብዙ ምዕራባውያን መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን፣ ጋዜጠኞች፣ ተንታኝ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተብዬዎች በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት ዘመቻ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ‹‹ውሻ በበላበት ይጮሃል›› እንዲሉ ህ.ወ.ሓ.ት የኢትዮጵያ አድራጊ ፈጣሪ በሆነበት ወቅት የኢትዮጵያን ሀብት እንዳሻቸው እንዲዘርፉት የፈቀደላቸውና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘረፈው ገንዘብ እየመዥረጠ ያጎረሳቸው መንግሥታት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች [ውለታቸውን ለመመለስ አልያም ወዳጃቸውን ከሞት አስነስተው በድጋሜ ኢትዮጵያን ለመዝረፍ በማሰብ] ሐሰተኛና የጥላቻ መረጃዎችን፣ ወገንተኛ መግለጫዎችን እንዲሁም አሳፋሪ የክህደት ሪፖርቶችን ሲያወጡና ሲያሰራጩ ቆይተዋል፤ አሁንም ቀጥለውበታል።
ህ.ወ.ሓ.ት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ባሉ አጋሮቹ በኩል አገሪቱ ልትበታተን እንደሆነና የፌዴራሉ መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት እንዳወጀ አስመስሎ በርካታ የውሸት መረጃዎች እንዲሰራጩ አድርጓል። እነዚህን መረጃዎች ያዳመጡና የተመለከቱ ብዙ የውጭ አገራት ሰዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ መረጃዎቹን እንደወረዱ በመቀበል ከእውነት የራቀ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ተስተውለዋል።
አንድ ጊዜ ተንታኝ፣ ዲፕሎማት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛ፣ ሲያሻቸውም አማካሪ ወይም ተማራማሪ ሆነው የሚንቀሳቀሱት የህ.ወ.ሓ.ት ወዳጆች ያልተደረገውን ነገር እንደተደረገ አድርገው የ‹‹በሬ ወለደ›› ውሸት እያሰራጩ ቆይተዋል። እነዚህ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከህ.ወ.ሓ.ት ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ፀብ አለን›› የሚሉ፣ ራሳቸውን ተንታኝ፣ ዲፕሎማት፣ ጋዜጠኛ፣ አማካሪ ወይም ተማራማሪ ብለው የሾሙና በዚሁ ጭምብል የሚንቀሳቀሱ ጥራዝ ነጠቅ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አምባሳደሮች፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ እስከአሁን ድረስ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች እጅግ አሳዛኝም አሳፋሪም ናቸው። የሀገራችን ሰው ‹‹ነጭ ውሸት›› እንደሚለው ዓይነት መረጃ አሰራጭተዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበር ዘመቻው ዓላማ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ የእንግሊዝ መገናኛ ብዙኃንን ያህል የተቀናጀ ዘመቻ የከፈተ አካል የለም። ቢቢሲን ጨምሮ፣ ሮይተርስ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ዘ ቴሌግራፍ፣ ሜይል ኤንድ ጋርዲያን፣ ዘ ኢንዲፔንደንት እና ሌሎች በርካታ መገናኛ ብዙኃን (ድረ-ገፆችን ጨምሮ) … እነዚህ ሁሉ የውሸት ዜና በማሰራጨት ዘመቻ ተጠምደው ከርመዋል፤ አሁንም አላቆሙም።
ከእንግሊዝ በተጨማሪ የሌሎች አገራት መገናኛ ብዙኃንም በዚህ የፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል። በዚህ ረገድ የአሜሪካ፣ የአውስትራሊያና የአረብ አገራት መገናኛ ብዙኀን ቀዳሚ ተጠቃሾች ሆነው እናገኛቸዋለን። እነዚህ አገራት የእንግሊዝ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች እንደነበሩ ሲታወስ የእንግሊዝን ተልዕኮ ተቀብለው በፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻው ላይ ተሳታፊ መሆናቸው የሚያስደንቅ አይሆንም።
በአጠቃላይ የአብዛኞቹ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች በውሸት የተሞሉና ለንጹሐን ያሰቡ መስለው ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳዎችን አጭቀው የያዙ ናቸው። የእነዚህ ‹‹መገናኛ ብዙኀን›› የሐሰት ፕሮፓጋንዳና ውንጀላ ጠቅለል ያለ ምክንያት ‹‹አፍቅሮተ-ህ.ወ.ሓ.ት›› ወይም ‹‹ፀረ-ኢትዮጵያዊነት›› ነው። [በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ንፁሐን ዜጎችን መከራ ዝቅ አድርጎ የማየትም ሆነ ‹‹ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያቱ/ተጠያቂው ማን ነው?›› የሚለውን ጉዳይ አደባብሶ የማለፍ ፍላጎት የለኝም!
እነዚህ ህወሓታውያንና ፀረ-ኢትዮጵያውያን የህ.ወ.ሓ.ትን ወንጀል በመሸፈን ዓለም መላው ኢትዮጵያ ውያን ስለደገፉት የሕግ ማስከበር ዕርምጃ የተሳሳተ ግን ዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፤ አሁንም ይህንኑ እኩይ ተግባራቸው ቀጥለውበታል፤ ይኸው ድርጊታቸውም ፍሬ አፍርቶላቸዋል።
የኢትዮጵያውያን ምላሽና ቁመና ምን ይመስል እንደነበር የታዘብነውን በአጭሩ እንመልከት … በውጭ አገራት ከሚኖሩ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል የውጭ መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበሩ ዕርምጃ እውነተኛና ሚዛናዊ መረጃ እንዲኖራቸውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር እንደማይቀርብ የሞገቱ ባለስልጣናት፣ ተቋማት፣ ምሁራን፣ ቡድኖችና ግለሰቦች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው። በዚህ ረገድ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ማኅበራት ለመንግሥታትና ለዓለም አቀፍ ተቋማት የፃፏቸው ደብዳቤዎች፣ ያወጧቸው መግለጫዎች እንዲሁም ያደረጓቸው ሰልፎች ይጠቀሳሉ።
በውጭ አገራት ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ ባሻገር በሀገር ውስጥ ያለውም በጉዳዩ ላይ ያሳየው ተሳትፎ፣ ቅንጅትና ብስለት ለወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን ነው ለማለት አያስደፍርም። ከመንግሥት መዋቅር ውጪ ያለው ዜጋ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀንና ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ስለኢትዮጵያ የሚያሰራጯቸውን የሐሰት መረጃዎች በሚገባ በመመከት ረገድ ያከናወነው ተግባር አጥጋቢ አይደለም። በዚህ ተግባር ላይ ለመሳተፍ ፍላጎትና ተነሳሽነት ያሳዩ አካላት ጥቂት መሆናቸው የመጀመሪያው ሐቅ ነው። ከእነዚህ መካከል የክስተቶችን መነሻ በሚገባ ተገንዝበውና የጠላትን ዓላማ አውቀው የተሳካ ግብረ መልስ የሚሰጡት ደግሞ ጥቂቶቹ ናቸው። አብዛኞቹ ተዋንያን/ተሳታፊዎች እውነትም ይሁን ውሸት ከአንድ የመረጃ ምንጭ ያገኙትን ‹‹መረጃ›› በማባዛት የተጠመዱ ናቸው።
የሐሰት መረጃዎቹን ፉርሽ ለማድረግ የተተገበረው ዘዴም አዋጭነቱ አጠያያቂ ሆኖ ታይቷል። ‹‹ … ይህ መረጃ ሐሰት ነው …›› ብሎ ፌስቡክ ላይ በአማርኛ መፃፍ ለኢትዮጵያውያን መረጃ ከመስጠት አልፎ ለውጭው ዓለም (በተለይ ለምዕራባውያን) ተደራሽ ሊሆን አይችልም። ይህ ማለት ግን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀንና የህ.ወ.ሓ.ት ደጋፊዎች ስለሚያሰራጯቸው መረጃዎች ይዘት ለኢትዮጵያውያን ማሳወቅ ፋይዳ የለውም ማለት አይደለም። ትግሉ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግ በሚያስችል ቁመና ላይ የመገኘት ጉዳይ ነው።
ለነገሮች የተሰጠው የትኩረት ቅደም ተከተል ጉዳይም በዚሁ ዘርፍ ከተስተዋሉ ችግሮች መካከል የሚጠቀስ ነው። ዓለም አቀፍ መገናና ብዙኀንና ተቋማት ስለኢትዮጵያ የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ ኢትዮጵያውያን ግን ፋይዳቸው አነስተኛ በሆኑ ጉዳዮች ተጠምደው ሲከራከሩ ታዝበናል።
ይህ ሲባል ግን ከኢትዮጵያ ጥቅም በተቃራኒ ቆመው የውሸት መረጃ ሲያሰራጩ የነበሩትን አካላትን ለመመከት የተሠራ ምንም ሥራ አልነበረም ማለት ግን አይደለም። የሐሰት ውንጀላ ዘመቻውን ለመመከት የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ህወሓታውያን ካሰማሩት የቅስቀሳና ጫና ስልት መጠን አንፃር እነዚህ ጥረቶች በቂ አይደሉም! በፍፁም በቂ አይደሉም!
ህ.ወ.ሓ.ት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ወዳጆቹ በኩል ስለሕግ ማስከበር ዕርምጃው የተዛባ መረጃ አስተላልፏል፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይም ጫና ፈጥሯል። የህወሓታውያን የውሸት መረጃዎችና የሐሰት ዘመቻዎች ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ሲያሳስቱ በወገን በኩል የነበረው የቅድመ ጥንቃቄና የአፀፋ ዕርምጃ እጅግ ደካማ ሆኖ ታይቷል።
ታዲያ በሰው ልጅ ታሪክ ከተሰሙ የክህደት ተግባራት መካከል አንዱን (ከጠላት የሚጠብቀውንና ብዙ ድጋፍ የሚያደርግለትን የራሱን የመከላከያ ኃይል የመውጋት ክህደት) የፈፀመው ህ.ወ.ሓ.ት ዓይኑን በጨው አጥቦ ምንም ጥፋት እንዳልሠራ ሲያስመስልና ክህደቱን ለማስተባበልም ደጋፊዎቹን በየፊናው ሲያሰማራ ከመንግሥታዊ መዋቅር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን በተቀናጀ ዘመቻ የከሃዲውንና የደጋፊዎቹን አፍ ማዘጋት የተሳናቸው ለምን ይሆን?
ከመጀመሪያው ጀምሮ ይህ የውሸት መረጃን የማሰራጨትና የተሳሳተ ግንዛቤን የመያዝ ችግር የተፈጠረው በመንግሥት ድክመት እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀንና ተቋማት እንዲሁም በመንግሥታት ዓላማና የግል ፍላጎት ምክንያት ነው። መንግሥት ስለጉዳዩ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልፅ ከማሳወቅ አንፃር የሠራው ሥራ በቂ የሚባል አልነበረም (በእርግጥ መንግሥት ሁሉንም ኃላፊነት ብቻውን ሊወጣ አይችልም፤ አይገባምም። በተለይ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ የዘመቻና የቅስቀሳ ሥራ በሚፈልጉ ተግባራት ላይ የምሁራን፣ የተቋማት በአጠቃላይ የዜጎች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው)።
የውጭ መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀንና ተቋማት የየራሳቸው ዓላማ አላቸው። እነዚህ አካላት በሌሎች አገራት የሚፈጠሩ ክስተቶችን የሚመለከቱትና ብያኔ የሚሰጡት ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ወቅታዊ ሁኔታም የሚመዝኑት ዓላማቸውንና ጥቅማቸውን መሰረት አድርገው ነው።
ሕግ የማስከበሩ እንቅስቃሴ ብዙ የሴራ ትንታኔዎችን የሚጋብዝና ነገሩ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ስለሆነ ጠንካራ የመረጃ ዝግጅትና ጥንቃቄን የሚፈልግ ተግባር ነው። ስለሆነም ዕርምጃው ከመንግሥት ጥረት ባሻገር የምሁራንንና የዳያስፖራውን ኅብረተሰብ ጨምሮ የመላ ዜጎችን ተሳትፎና ንቅናቄ ይፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ ከመንግሥት መዋቅር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እንደተጠበቀው ሳይሆን መቅረቱን ታዝበናል።
ህወሓታውያን የቡድናቸውን ክህደት ክደውና የሀሰት መረጃ ይዘው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲፈጥሩ ‹‹ኢትዮጵያን እወዳለሁ … ኢትዮጵያ አገሬ/እናቴ …›› የሚለው ወገን በዚህ ደረጃ የተዳከመው ለምን እንደሆነ ማወቅ ያስቸግራል። ወትሮውንም ቢሆን ኢትዮጵያ የምትጎዳው በጠላቶቿ ጥንካሬ ሳይሆን ‹‹ኢትዮጵያን እንወዳለን … ባለቤት ነን›› በሚለው ወገን ደካማነት ነው!
በሕግ ማስከበር ዕርምጃው ወቅት የታየው የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን መረን የለቀቀ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ለዘመቻው የሰጠነው ደካማ ምላሽ፤ የዓለም ፖለቲካን፣ በተለይም ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን፣ የመረዳት ችሎታችንንና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያለንን ‹‹አቅም›› ያመላከተ ሆኗል። ስለሆነም ኢትዮጵያ ስሟን የሚያጠለሹና በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ አደጋ የሚደቅኑ ሐሰተኛ ውንጀላዎችን በብቃት ለመመከት ከዜጎቿ በእውቀትና በብስለት የተመራ አገራዊ ጥብቅናና አለኝታን ትሻለች!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም