በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የህፃናት ስፔሻሊስት እና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ፋሲል መንበረ ስለህፃናት ሆድ ድርቀት ይሄንን ብለውናል። መልካም ንባብ።
ህፃናት ልክ እንደ መልካቸው ሁሉ የአንጀታቸው ባህሪ የተለያየ ነው። አንዳንድ ህፃናት በጠቡ ቁጥር ካካ ሲሉ አንዳንድ ህፃናት ደሞ ያለምንም ህመም በ7 ቀን ኖርማል ካካ ሊሉ ይቺላሉ። ይሄ ማለት ግን ድርቀት አለባቸው ማለት አይደለም። ብዙዎቹ ፍጹም ጤናማ ናቸው። የተወሰኑ ህፃናት ግን በትክክል ድርቀት አለባቸው። የተወሰኑ ህፃናት ደሞ ካካቸው ሳይደርቅ ረጅም ሰዓት ያምጣሉ፤ ያለቅሳሉ፤ ይንጠራራሉ፤ ሲወጣላቸው ግን ካካቸው ለስላሳ ነው። ይሄ ቺግር ድርቀት ሳይሆን ኢንፋንት ዲስኬዝያ በመባል ይታወቃል።
ኢንፋንት ዲስኬዝያ (Infant Dyschesia) ምንድነው?
ኢንፋንት ዲስኬዝያ ማለት እድሜያቸው ከ2 ሳምንት – 9 ወር ድረስ ያሉ ህፃናት ላይ የሚታይ የአንጀት ችግር (Functional GI disorder) ሲሆን ምክንያቱ ደሞ ህፃናት ካካ በሚሉበት ወቅት የአንጀት፣ የሆድ እና የፊንጢጣ ጡንቻዎች አለመናበብ (poor coordination) የሚያመጣው ህመም ነው። ይህ ችግር ያለባቸው ህፃናት ካካ ከማለታቸው በፊት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ማማጥ፣ መንጠራራት፣ የፊት መቅላት፣ ማልቀስ ወይም መነጫነጭ ሊኖራቸው ይችላል። በዓለም ላይ በተደረጉ ጥናቶች ከ5-10 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት ይሄ ችግር ያጋጥማቸዋል። በተለይ ደሞ የጣሳ ወተት የሚወስዱ ህፃናት ላይ ከፍ ብሎ ይታያል። ወላጆች ደሞ ይሄንን ሲያዩ ልጃቸው ድርቀት አለበት ብለው በማመን ሳሙና እና ሌሎች ባዕድ ነገሮችን ወደ ህፃኑ ፊንጢጣ ሲከቱ ይስተዋላሉ። ይሄ ተግባር የልጁን ህመም ከመጨመር ያለፈ ጥቅም የለውም።
ወላጆች አንድ ማወቅ ያለባቸው ነገር የሚያምጥ ህፃን ሁሉ ድርቀት አለው ማለት አለመሆኑን ነው።
ኢንፋንት ዲስኬዝያ (Infant Dyschesia) ሕክምናው ምንድነው?
ይህ በሽታ ምንም አይነት ህክምና አያስፈልገውም በራሱ ጊዜ ከ9 ወር በኋላ ይጠፋል።
የህፃናት ሆድ ድርቀት መንስኤው ምንድነው?
የህፃናት ሆድ ድርቀት መንስኤው እና ሕክምናው እንደ የእድሜያቸው ይለያያል። በጉዳዩ ላይ በተደረጉ ጥናቶች መሰረት አንድ ህፃን ልጅ በትክክል ሆድ ድርቀት አለው ብሎ ለመናገር ከሚከተሉት ምልክቶች ውስጥ ቢያንስ ሁለቱን ማየት ይኖርብናል።
1. በፊት ከነበረው የአንጀት እንቅስቃሴ (የአይነ ምድር ቁጥር) በጣም ከቀነሰ በተለይ በሳምንት ከ2 ጊዜ በታች ካካ የሚል ከሆነ፤
2. ከወትሮ የተለየ እና ድርቅ ያለ አይነ ምድር ካለው፤
3. ከ20 ደቂቃ በላይ የሚያምጥ ከሆነ እና ምንም አይነት አይነ ምድር ካልወጣለት፤
4. አይነ ምድሩ ሲወጣ አብሮ ደም ከወጣ፤
5. ተደጋጋሚ ትውከት ካለ፤
6. የሆድ መነፋት ወይም መጠንከር ካለ፤ እንዲሁም
7. የምግብ ፍላጎት መቀነስ ካለ ነው።
ከ1 ዓመት በታች ላሉ ህፃናት የሆድ ድርቀት መፍትሄ ዎች እና የቤት ውስጥ ሕክምናዎች ደግሞ
1. በመጀመሪያ የልጆዎን አመጋገብ ያስተካክሉ
• የእናት ጡት ወተት በበቂ መጠን መስጠት እና ልጅዎ በቂ የሆነ የጡት ወተት እያገኘ መሆኑን ማረጋገጥ፤
• የላም ወተት የሚጠቀም ከሆነ ሙሉ ለሙሉ አቁመው ሌላ ለህፃናት በእድሜያቸው የተዘጋጀ የጣሳ ወተት መጠቀም። የጣሳ ወተት የሚጠቀም ከሆነ ሌላ አይነት የጣሳ ወተት መቀየር እና ማየት፤ እድሜው ስድስት ወር ከሞላው ፋይበር ያላቸውን ምግቦችን መስጠት፤ ለምሳሌ የተፈጨ እና የበሰለ ጎመን፣ ቆስጣ፣ አበባ ጎመን፣ አቦካዶ፣ ፓፓያ፣ ያልተፈተጉ እህሎች፣ አትክልቶችን ፣ ፍራፍሬዎችን እና የመሳሰሉትን በደንብ መመገብ፤
• ህፃናት ለእያንዳንዱ 1000 ካሎሪ 15-20 ግራም ፋይበር ማግኘት አለባቸው። ፋይበር ማለት ሙሉ ለሙሉ ተፈጭቶ ወደ ሰውነት የማይዋሀድ ከአትክልቶች ፍራፍሬ እንዲሁም ካልተፈተጉ የእህል ዝርያዎች (ገብስ፣ አጃ፣ ስንዴ እና ከመሳሰሉት) የሚገኝ ጠቃሚ የምግብ አካል ነው።
• ስድስት ወር ከሞላው በቂ የሆነ ውሃ መስጠት
ከ6 – 12 ወር ያሉ ህፃናት በቀን 120 – 250 (ቢያንስ 1 ኩባያ) ውሃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ድርቀት ያለባቸው ህፃናት ደሞ ከዚህ በላይ ቢወስዱ ይመከራል። ከስድስት ወር በፊት ግን የእናት ጡት ወተት በቂ የሆነ ውሃ በውስጡ ስለሚገኝ ውሃ መስጠት አስፈላጊ አይደለም (ለአንጀት ኢንፌክሽንም ሊያጋልጣቸው ስለሚችል ማለት ነው)።
አንዳንድ ጥናቶች 3 ወር ለሞላው ልጅ በንጹህና የተዘጋጀ የአፕል ጁስ ማጠጣትን (10 – 30 ሚሊ ሊትር) እንደ አማራጭ ይመክራሉ። ምክንያቱም አፕል ውስጥ ያለው ሶርብቶል የሚባለው ንጥረ ነገር በአንጀት ስለማይፈጭ ሰገራውን አለስልሶ ሊወጣ ይችላል። ብዙ ህፃናት ላይ ተልባ ጥሩ ለውጥ ሲያመጣ ይታያል።
2. ልጆዎን የአካል እንቅስቃሴ ያስጀምሩት፤ የልጆትን እግር እጥፍ ዝርግት እያደረጉ እንቅስቃሴ ማድረግ ወይም ስፖርት ማሰራት ጉልበቱን በማጠፍ ቀስ ብሎ ወደ ሆዱ መግፋት ይሄን እንቅስቃሴ ደጋግሞ ማሰራት።
3. ማሳጅ ማድረግ
ቀስ ብሎ በጣትዎ ክብ (clockwise) እየሰሩ የሆድ ጡንቻዎችን ማሳጅ ማድረግ፤ ፊንጢጣው አካባቢ ቀስ ብሎ በክብ እንቅስቃሴ (clockwise) ማሳጅ ማድረግ፤
4. ለብ ባለ ውሃ ሰውነቱን ማጠብ
ከላይ ያሉትን መፍትሄዎች ተጠቅመው ለውጥ ካላዩ የህፃናት ስፔሻሊስት ሀኪም ቢያማክሩ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም