
ሰላማዊት ውቤ
በእጅጉ እየበረታ የመጣው የኑሮ ውድነት ከምግብ ሰብል እስከ አትክልትና ፍራፍሬ አልባሳትን ጨምሮ እየናረ ይገኛል። የፍራፍሬ ዋጋ ንረት በተለይም በብርቱካን ላይ በርትቶ ሰንብቷል። የአንድ ኪሎ ብርቱካን ዋጋ ባለፉት ወራት እስከ 120 ብር የደረሰ ሲሆን፤ ፓፓያ፣ አቡካዶ፣ አናናስ፣ መንደሪን ያልጨመረ የፍራፍሬ ዓይነት አልነበረም። ዋጋው በመዋዠቁ የማይታወቀው ሙዝ እንኳን ከነበረበት 20 እና 25 ብር 30 ብር ገብቶ እንደነበር ይታወሳል።
አትክልትም ቢሆን ቀላል የማይባል ዋጋ ጨምሯል። ከውድነቱ የተነሳ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የማህበረሰብ ክፍል የሚጠቀምበት ችርቻሮ የአትክልት ገበያ አልነበረም። አትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴዎች እንደሚሉት የዋጋው ንረትና እጥረት ምክንያቱ ደግሞ የአትክልትና ፍራፍሬ ተጠቃሚ ቁጥር መጨመሩ ነው። ለጤና ጠቃሚ የመሆን ጥቅሙም ታይቷል። ወቅታዊ የመሆኑም ጉዳይ ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተለይም በጾም ወቅት አብዝቶ መፈለጉ ካለፈው ከአብይ ጾም ጋር ተያይዞ ለተከሰተው የአትክልትና ፍራፍሬ እጥረትና የዋጋ ንረት ማሳያ ይሆናል። የፍራፍሬ ምርት የሚመጣባቸው ቦታዎች ውስን መሆናቸውና የአምራችነት ሥራ ባህላችን ደካማ መሆኑ ለችግሩ ምንጭ እንደሆነም ይነገራል።
አትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ መናርን አስመልክቶም ሀሳባቸውን ካካፈሉን ተጠቃሚዎች መካከል አቶ ናሆም ፀደቀ አንዱ ናቸው። አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዮቶር ጭማቂና ፍራፍሬ መሸጫ ሲገበዩ አግኝተናቸዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ቤተሰቦቻቸው አዝወትረው አትክልትና ፍራፍሬ ይጠቀማሉ። ምክንያቱም አትክልትንና ፍራፍሬን አዝወትሮ መመገብ ለስኳር በሽታ የመጋለጥ ዕድልን ከመቀነስ ባሻገር ብዙ የጤና ጥቅሞች እንዳሉት ያውቃሉ። ሆኖም ባለፈው ጊዜ ዋጋው አልቀመስ ማለቱ ለተወሰነ ጊዜ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያቆሙ አድርጓቸው ቆይቶ ነበር።
ወጣት ሀና ከበደ በዚሁ አካባቢ በሚገኘው ባርኮት ፍሬሽ ጁስ ውስጥ ነው የምትሰራው። እንደምትለው ሙዝ ሳይበዛ በቀን ሁለት ለልብ ህመምና ምግብን ለማንሸራሸር ቢበላ በጤና ባለሙያዎች ይመከራል። እሷም ከምግብ በኋላ በቀን ሁለት ሙዝ ትመገባለች። አቅሟ የሚችለው ሙዝ ቢሆንም ሌሎች ፍራፍሬዎችን ለመመገብ ትሞክራለች። ነገር ግን ዋጋቸው አልቀመስ በማለቱ ተቸግራ ቆይታለች። ሆኖም የሙዝ ዋጋ ብዙም ጭማሪ ባለማሳየቱ አልከበዳትም። ወይዘሪት ኤምራኬብ ዮናስ ፒያሳ አትክልት ስትሸምት ያገኘናት። ‹‹ካሮት፣ ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ አበባ ጎመን፣ ቀይ ስር፣ ጎመን፣ ባሮ ሽንኩርት ምን ያልጨመረ ነበር›› ብላናለች አሁን ላይ ቀድሞ ሲሸጥበት በነበረ ዋጋ ባይሸጥም ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ማሳየቱን በማከል፤ ቀድሞ እስር ጎመን እስከ መቶ ብር የገዛችበት ሁኔታ መኖሩንም አስታውሳለች።
ይሁንና አሁን ላይ ጎመን አርባ ብር መግዛቷንና የአትክልት ገበያ ዋጋም እንዲሁ ወደፊት ይቀንሳል የሚል ተስፋ እንዳላት ተናግራለች። የፍራፍሬ ተጠቃሚ መሆኗን የጠቆመችው ኤምራኬብ ዘንድሮ መንግስት እንዳስቀመጠው አቅጣጫ ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ተያይዞ ፍራፍሬና ሌሎች ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ተክሎች መልማታቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋን ማረጋጋት የሚያስችልና ጠቃሚ እንደሆነም ገልፃልናለች።
የባርኮት ፍሬሽ ጁስና ፍራፍሬ ቤት ባለቤት ልጅ የሆነው ወጣት ኤፍሬም ኤርሚያስ በኤሌክትሪካል ኢንጅነር ቢመረቅም እዚህ መሥራት መርጦ እየሰራ ይገኛል። በአሁኑ ሰዓት ሕብረተሰቡ አትክልትና ፍራፍሬ ለጤና ያለውን ከፍተኛ ጥቅም ተረድቷል። ‹‹አልኮል ከመጠጣት ይልቅ ፍራፍሬ መመገብ ይመረጣል›› የሚለው ኤፍሬም በጁስ መልክ፣ በአትክልት፣ በፍሩት ፓንቺ እዛው የሚጠቀም፤ በጥሬው ሸምቶ የሚወስድ ብዙ ደንበኛ ያለው መሆኑ ለዚህ ማሳያ እንደሆነ ይናገራል።
ባለፉት ወራት ዋጋ በመጨመሩ ተጠቃሚው ተቸግሮ ነበር። ቢሆንም ገበያው አልቀነሰም በውድም ቢሆን ገዝተው የሚጠቀሙ ደንበኞቹ አራቁትም። ጥራት ያለውን የየረር ብርቱካን 120 ብር አውጥተው የሚገዙ ብዙ ነበሩ። አሁን ብርቱካን ቀንሶ 80 ብር ገብቷል። ቫሊሽያ የተሰኘው ብርቱካን 65 ብር ነው። የፍራፍሬ ዋጋ በአንፃራዊነት መሻሻል አሳይቷል። በዚህም ቀደም ባሉት ወራቶች በዋጋ ውድነት አንዳንድ ሲርቁ የነበሩ ደንበኞቹም እየተመለሱ ነው።
ሙዝ 30፣ ብርቱካን 80፣ ፓፓያ 50፣ አቡካዶ 50፣ አናናስ 50፣ ቴምር 130፣ መንደሪን 70፣ ሀባብ 30፣ ማንጎ ትልቁ 70 ማንጎ ትንሹ 50፣ ግሪፕ ፍሩት 70፣ አፕል 130፣ አፕል 150፣ ወይን 400 የሚል የዋጋ ዝርዝር የተለጠፈበት ደግሞ ዮቶር ጭማቂና ፍራፍሬ ቤት ነው። ባለቤቱ አቶ ታደለ ፈቃዱ እንደሚናገረው የፍራፍሬ ዋጋ በመቀነስ መሻሻል አሳይቷል። ፍራፍሬ ወቅት ስላለው በዚህ ጊዜ የሚወደድበትና እጥረት የሚኖርበት ጊዜ አለ። አሁን ማንጎ ከገበያ እየወጣ ነው። በዚህ ወቅት ተፈላጊነቱ ስለሚጨምር አርሶ አደሩ ዋጋውን ያስወድዳል። ክረምት ሲሆን ሥራው ይቀንሳል። አርሶ አደሩም እንዳይበላሽበት ቶሎ አውጥቶ ይሸጣል።
አቶ ታደለም ሆኑ ወጣት ኤፍሬም እንደነገሩን ፓፓያ ከስልሳ እስከ 70 ብር አካባቢ ነበር አሁን ሙዝና አፕል ብዙም የዋጋ ለውጥ የላቸውም። ዋጋቸው አይቀያየርም። በእርግጥ አፕል ሲዊስ ካናል የተዘጋ ጊዜ ስለማይገባ ጨምሮ ነበር። በገበያው መካከል ብዙ ደላሎች በመኖራቸው አንዳንድ አካባቢ የፍራፍሬ መሸጫ ቤት ኪራይ ዋጋ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ይሄን ይሄን ለማካካስ ሲባል ነጋዴው ዋጋ የሚጨምርባቸው ሁኔታዎች አሉ። ማንጎ ከአሶሳ ሙዝ ደግሞ ከአርባ ምንጭ ይገባል። የሚመጡበት ቦታም ከጥራት አንፃር ለዋጋ መጨመር አስተዋጽኦ አለው። በዚህ በኩል ፍራፍሬና አትክልት በሁሉም አካባቢዎች የሚመረቱበትን ሁኔታ መንግስት ማመቻቸት አለበት። ዜጎችም በተለይ ወጣቶች አላስፈላጊ ነገሮች ውስጥ እየገቡ ጊዜያቸውን ከማባከን ይልቅ በዚህ በኩል ቢሳተፉ የሥራ ዕድል ከመፍጠርና የሥራ ባህላቸውን ከማሻሻል ባሻገር ምርቱ ተደራሽ የሚሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም