“አራት ኪሎ ፒያሳ” በሚል ታክሲ ውስጥ ነኝ። መነሻዬ ደግሞ መገናኛ። የፊት ወንበር ቀድሞ ስለተያዘ ከኋላ ጥጌን ይዤ ተቀምጬ መሄዳችንን እጠባበቃለሁ። በዚያኛው ዳር ደግሞ አንድ ሌላ ሰው ተቀምጧል። ብዙውን ጊዜ በታክሲ ውስጥ መሃል ላለመሆን የሚደረግ ከባድ ፉክክር አለ።
እውነት ነው መሃል በመሆን ብዙ ፈተናዎች ይገጥማሉ። ‹‹ሳንዱች›› ሆነህ ነው የምትደርሰው። ለዚያ ይመስለኛል ታክሲ ይ “እባክህ ረዳት ሆይ ቀጠን ያለ ሰው ጫን” የሚል ልምምጥ የሚበዛው። ደግሞ እኮ የሚኒባሶቹ መቀመጫ በቅቶ ቢሆን ችግር አልነበረውም። አንዳንዶቹ እኮ ወንበራቸው እንኳን ሶስትና አራት ሰው ሊይዝ ሁለት ሰውም በአግባቡ ማስቀመጥ አይችልም። ትንሽ ሰፋ ያለ ሰው ሲመጣ ጉድ ይፈላል። ወንበሮቹ በጣም የተቀራረቡ ስለሆኑ አንዳንዶች ለእግራቸው ስለማይመቻቸው መጪውን ተሳፋሪ እለፍ ብለው መንገድ ያመለክታሉ፤ እነሱ ዳር መቀመጥን ይመርጣሉ። ያዙልኝ እንግዲህ በዚህ ላይ ነው ሌላ ሰው መጨመር የሚፈለገው። አሻፈረኝ ብትል በራሰህ ነው የምትፈርደው፤ ፌንጣ ብትቆጣ ክንፏን ታጣ ነው የሚባለው። ረዳትና አሽከርካሪ ተባብረው በሆነ መልኩ ይጎዱሃል!
ታክሲው ከመነሳቱ በፊት አንዲት ቀጠን ቀላ ያለች ተማሪ ፈጠን ፈጠን እያለች ወደ ሚኒባሱ ገባች። ግራና ቀኝ ከተመለከች በኋላ የመጨረሻውን ወንበር አየችው። እኔም እንዳየኋት እፎይ አልኩ። ምክንያቱም ለእሷ የሚበቃ ቦታ አይጠፋም፤ ተመስገን። “ለትራንስፖርት ፀሎት” ይገርማል።
የመንግስት ትምህርት ቤት እንደምትማር ግልፅ ነው። የለበሰችው ዩኒፎርም ይገልጻታል። ዩኒፎርሙ አሳምሯቸዋል፤ አንድ አርጓቸዋል፤ በዩኒፎርም በኩል መንግስት ትልቅ ስራ ሰርቷል። በእዚህ የኑሮ ውድነት ህዝቡ ስለዩኒፎርምና ምግብ አስቦ እንዴት ይኮን ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ በኩል ሊመሰገን ይገባዋል።
ሹፌሩ ተማሪዋን እንዳሳፈረ ሞተሩን አስነስቶ ጉዞውን ቀጠለ። የሁልጊዜም ኡደታችን ነው። ታክሲ እንጠብቃለን። ተጉላልተን እናገኛለን። ተደራርበን እንቀመጣለን፤ ተጨማሪ ሰው አላስቀምጥም ቢሉ እንኳ ጥሩ ረዳት ከገጠሞት ቅርብ ወራጅ አለ፤ ተባበሩ ይልዎታል፤ ጋጠ ወጡ ከገጠመ ደግሞ መመናጨቅ ሊደርስቦት ይችላል። በስራ መውጪያም ይሄው ይደገማል፤ ቢሮ ደክሞን ደርሰን፣ ለአድካሚው ታክሲ ጥበቃ ደግሞ ከቢሮ እንወጣለን። ይሄኛው ደግሞ ከሰራ መግቢያ ሰዓቱም ሊከፋ ይችላል፤ ምሽት አለና፤ ይህ የእለት ተእለት ተግባር ሆኗል፤ እሽክርክሮሽ።
ተማሪዋ መረጋጋት አይታይባትም። ወደ ሹፌሩ አቅጣጫ አንገቷን አስግጋ ትመለከታለች። ትቁነጠነጣለች። በእጆቿ የሃምሳ ብር ኖት ይዛለች። ብሩን በፒራሚድ ቅርፅ አጣጥፋዋለች። የሆነ ነገር የምትፈልግ ነው የምትመስለው። ቀና ብላ ማየቱን ስታቆም ደግሞ ባጣጠፈችው ሃምሳ ብር የጣቶቿን ጥፍር ለማፅዳት ተሞክራለች። ጥፍሮቿ ግን ንፁሆች ናቸው። ሃሳብ የገባት ትመስላለች።
ሁኔታዋ ትንሽ ግራ ስለገባኝ ከሃሳብ ላወጣት ፈለኩ። ቀስ ብዬ “ኧረ ብሩን በጥፍርሽ እንዳትቀጅው” ብዬ ፈገግ አልኩ። መልስ አልሰጠችኝም። በቃ አንድ ሃሳብ ውስጧ ገብቶ እንደሚሆን ጠርጥሬ ዝም አልኳት። ሚኒባሱ ጉዞውን ቀጥሏል። ሾላ ደርሰናል። ብዙም ሳንቆይ ፈጠን ብላ “ሰዓት ስንት ነው” ስትል ጠየቀችኝ። እኔ እንዳንቺ አይደለሁም ብዬ ሰዓቱን ነገርኳት። ፈገግ አለች።
አሁንም መቁነጥነጧን አላቆመችም። “ወደ ትምህርት ቤት ነው? ፤ ስንተኛ ክፍል ነሽ ?” አልኳት ደግሜ። አሁንስ መለሰችልኝ “አዎ ታክሲ አጥቼ ነው የቆየሁት፤ 12ኛ ክፍል ነኝ፤ ረፍዶብኛል ፤ ፈተናም አለኝ” አለች በረጅሙ እየተነፈሰች። “ስንተኛ ክፍል ነሽ፤ ፈተናው ስንት ሰዓት ነው” ስላት ሁለት ተኩል ላይ መሆኑን ነገረችኝ፤ ትንሽ ሰዓት እንዳላት ተረዳሁ፤ ልጅ አይደለች ትደርሳለች ብዬ አሰብኩ። ታዲያ ምን አጨናነቃት ስል አሰብኩ።
የጋብቻ ቀለበት አድርጋለች። ለምንድነው ይህን ሁሉ የማያው ስል ለራሴ አሰብኩ። መቁነጥነጧ ይሆን? ያሳሰበኝ። አሁንም ግራ ተጋባሁ።
“ባለትዳር ነሽ” ስል ጠየቅሁዋት። ፈጠን ብላ “አዎ” አለችኝና ወዲያው ሳቀች። ግራ መጋባቴን ተመለክታ ወዲያው “አይ ሰው እንዳያስቸግረኝ ብዬ ነው ያደረኩት›› አለችኝ። ብልጠቷና ሁኔታዋ አሳቀኝ። ይገርማል። ይህ ምን ያህል ከአስቸጋሪ ሰው ያስጥላል ስል ጠየቅኋት። ቢሆንም ይሻላል ስትል መለሰችልኝ።
አሁን ነፃ እየሆነች መጥታለች፤ መቁነጥነጡንም አቁማለች። ወደ ፈተና እየሄደች መሆኑና ሰዓቱ ትንሽ መድረሱ ነበር ያስጨነቃት። ይገርማል።
እንዲህ ተወጥረው እና በብዙ ፈተና ውስጥ አልፈው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቀጥሎም በተለያዩ ችግሮች ሲፈተኑ እየተመለከትን ነው። ባለፉት ዓመታት ዩኒቨርሲቲዎች በዘረኝነት፣ በአክራሪነት ወይም ጠባብነት ሳቢያ ያዩት ፈተና ታወሰኝ። ዘረኞችና ዘረኝነትን እንደ ስልጣን መቆያ አርገው ይዘው የቆዩ እብሪተኞች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ብዙ ፈትነዋል ጎድተዋል። ሰሞኑንም በግጭት ምክንያት መውጫ ያጡ የአንድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይም ይህንኑ ያመለክታል።
የህይወት ፈተናው ይቀጥላል። ከፊት ምን ይገጥመኝ ይሆን አይባልም። ፈተናውን እያለፉ እየወደቁም መጓዝ ብቻ ነው። እርሷም የዚህ ትውልድ አካል ነች። ከአንዱ ወደሌላኛው ፈተና ተጓዥ።
ጭውውታችንን ቀጥለናል። ሚኒባሱ በተለምዶ “አበቤ ሱቅ” በሚባለው እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ ደርሷል። ከትንሽ ቆይታ በኋላ “ያው ፈተናው እኮ ብዙም አያሳስብም፤ ዋናው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ላይ ተፅእኖ የለውም። ሞዴል ያልተፈተንናቸውን ነው ዛሬ የምንፈተነው” አለችኝ። መልስ እንድሰጣት በሚፈልግ አኳኋን ቀና ብላ እየተመለከተችኝ።
“ታዲያ ለምን ቅድም እንደዛ ተጨነቅሽ” በማለት መልሼ ጠየኳት። ለትራንስክሪፕቷ ሰግታ መሆኑን ነገረችኝ። ትራንስክሪፕቱን የፈለገችው ደግሞ የውጪ የትምህርት እድል ምናልባት ቢያጋጥማት በሚል ነበር፤ ብልህ ነች። ይህቺን መሰል ፈጣን ወጣቶች አገሬ ያስፈልጓታል።
ተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ናት፤ እዚህ ዘርፍ ውስጥ የገባቸው ተሳስታ ነው፤ ሆቴል ማኔጅመንትና ቢዝነስ መማር ትፈልግ ነበር፤ አሁንም ግን ወደ አርት ትምህርት የመቀየር እድሉ እንዳላት ነገረችኝ። በእኛ ጊዜ ይህን ማድረግ አንችልም ነበር። የእውነትም ይህ አይነቱ እድል ካለ በጣም ጥሩ ነው። ተማሪዎች የሚያማክራቸው ከማጣታቸው የተነሳ መሰል ስህተት ስለሚሰሩ ማስተካከል የሚቻልበት እድል ካለ ለተማሪዎች ጥሩ አማራጭ ነው።
አራት ኪሎ ደረስን። ልትወርድ ነው። እንደተለመደው ፈጠን እያለች “ጫፍ ወራጅ አለ” ስትል ተጣራች። ይህን ያህል አውርተን ብዬ ስሜን ነገርኳት ፤ እሷም ወደኔ ዞር ብላ “እዚህ አደለህም እንዴ” ብላ ፈገግ አለች፤ ቀጠል አድርጋም ስሟን ነግራኝ ቻዎ ብላኝ ወረደች። መገናኛ ላይ ስትገባ እንጂ አራት ኪሎ ላይ ስትወርድ “ወደ ፈተና” የምትሄድ አትመስልም ነበር። እኔም “መልካም ፈተና” ብዬ ሞቅ ባለ ስሜት ተሰናበትኳት። ቸር ይግጠማት!
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2013