የ27 ዓመት ወጣት ነው። ትውልዱና እድገቱ በአማራ ክልል፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን፣ ደጀን ወረዳ፣ ጥቄት ኖራ በሚባል የገጠር መንደር ነው። ለእናቱ አንድ ነው። ልጅ እያለ እናቱ ያደርጉለት የነበረውን እንክብካቤ እንደህልም ያስታውሰዋል። የስድስትና የሰባት ዓመት ልጅ እያለ እናቱ በጠና ይታመማሉ። የህክምና ምርመራ ሲያደርጉ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ታማሚ እንደሆኑ ይነገራቸዋል። ጠላና አረቄ በመሸጥ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚኖሩት እናት ህመማቸው ሲጸናባቸው እየተኙ፤ ሻል ሲላቸው እየሠሩ እርሱን ለማሳደግ ይጥሩ እንደነበርና፤ ከራሳቸው አብልጠው ይጨነቁለት እንደነበር ያስታውሳል። የዛሬው እንግዳችን ሰለሞን ዘውዴ ይባላል፤ መልካም ቆይታ።
ሰለሞን ያኔ ስለእናቱ ህመም፣ ስለእለት ገቢያቸው፣ ስለኑሯቸው በሚረዳበት የእድሜ ክልል ላይ አልነበረም። በሽቦ መኪኖችን እየሰራ ከባልንጀሮቹ ጋር ይጫወታል። ጠዋት ቁርሱን በልቶ ይወጣል። ቀን ገብቶ ምሳውን ይበላና ተመልሶ ወደ ጨዋታው ይሄዳል። ማታ ለመኝታው ወደ ቤቱ ይገባል። ትምህርት ቤትም አልገባም ነበር።
እናቱ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒት ቀድመው ባለመጀመራቸው ምክንያት እራሳቸውን ካወቁ ከሶስት ዓመት በኋላ የአልጋ ቁራኛ ይሆናሉ። እሱን ለማሳደግ የሚያደርጉት ሩጫም ይገታል። ሰለሞንም እርሳቸውም የጎረቤት እጅ እያዩ መኖር ይጀምራሉ። ልክ ሰለሞን የአስር ዓመት ልጅ እያለ ታማሚዋ እናቱ ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ።
ብላቴናው ምድር ቁና ትሆንበታለች። የሚይዘውን የሚጨብጠውን ያጣል። እናቱን ከማጣቱ ባሻገር ብቻውን መቅረቱ ያስደነግጠዋል። ወላጅ አባቱን አያውቀውም፤ በአካባቢው ዘመድ አዝማድ የለውም። የመንደሩ ሰዎች ግን አልጣሉትም፤ ከልጆቻቸው ጋር እንዲኖር አቅፈውታል። ታዳጊው ልጅ ግን ጠዋት ማታ እናቱን እያስታወሰ ማልቀሱን አልተወም። የእናቱ ፍቅርና እንክብካቤ ትውስ ባለው ጊዜ እየተደበቀ ይንሰቀሰቃል። የአካባቢው ሰዎች እንዳይሰማውና ሀዘኑን እንዲረሳ መልካም ነገሮችን ሁሉ ቢያደርጉለትም እርሱ ግን ደስታ አይሰጠውም ነበር። ያ እየቦረቀ ያደገበት መንደር ከእናቱ ሞት በኋላ ጣዕሙ ጠፍቶበታል። እንደበፊቱ ከጓደኞቹ ጋር መጫወቱን ትቷል። በትንሽ በትልቁ ሆድ ይብሰው ጀምሯል።
ሰለሞን ከሁለትና ሶስት ዓመት በኋላ በአካልም በአስተሳሰቡም እያደገ ሲመጣ የኔ የሚለው ሰው በሌለበት መንደር የእናቱን መካነ መቃብር እያየ መሰቃየቱን ትቶ ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ ሰርቶ ለመኖር ይወስናል። ያኔ እድሜው አስራ ሶስት ዓመት ይሆናል።
በአንድ አጋጣሚ ለእንግድነት ወደሚኖርበት አካባቢ የመጣችን አንዲት ሴት ወደ አዲስ አበባ እንድትወስደው ይማጸናታል። በነገራት የህይወት ታሪኩ ውስጧ የተነካው ሴት ፈቃደኛ ሆና ይዛው ትመጣለች። ከዚያች ከገጠር መንደር ውጭ ወጥቶ የማያውቀው ብላቴና አዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ-ከተማ፣ መሳለሚያ አካባቢ በዝችው ሴት ቤት እየተላላከ መኖር ይጀምራል። ሁለት ሳምንት ያህል በሴትይቱ ቤት ከቆየ በኋላ አንድ ቀን ጠዋት ከቤት ወጥቶ አስፋልት ዳር እንደቆመ ከእርሱ አካባቢ ከመጡ ሰዎች ጋር በአጋጣሚ ይተዋወቃል። እናት አባት እንደሌለው እና ሥራ ሠርቶ ለመኖር ከሀገሩ መውጣቱን ነግሯቸው ሥራ የሚገኝበትን ቦታ እንዲያሳዩት ይጠይቃቸዋል። እነርሱም ፒያሳ አትክልት ተራ ቢሄድ የሰዎችን እቃ እየተሸከመ የእለት ጉርሱን ማግኘት እንደሚችል ይጠቁሙታል። ይዘውት ሄደው ቦታውን ካሳዩት በኋላ እነርሱ ወደ ግል ሥራቸው ይሄዳሉ።
ሰለሞን ፈራ ተባ እያለ እቃ ከሚገዙ ሰዎች ስር ስር በመሄድ እንዲያሠሩት ይጠይቃል። ጸጉረ ልውጥ መሆኑን ያዩ የአትክልት ተራ ተሸካሚዎች ሰለሞንን ይቀናቀኑታል። ግማሹ እየሰደበው፤ ግማሹም እያባረረው፤ ግማሹም እየፎገረው እንደምንም ብሎ የሸቃቀላትን ሳንቲም ይዞ ወደ ማረፊያ ቤቱ ለመመለስ ይሞክራል።
መሳለሚያ የሚለውን ያረፈበትን ሰፈር ስም ከማወቅ ባሻገር የት ጋር ታክሲ ይዞ፤ የት ጋር ወርዶ ወደ ማረፊያ ቤቱ መግባት እንዳለበት አያውቅም። ብቻ ግን አጠያይቆም ቢሆን የመሳለሚያ ታክሲን ተሳፍሮ ይሄዳል። ቀበሌውን፣ የመንደሩን ልዩ መጠሪያ፣ የቤት ቁጥሩን፤ ወይም የሰዎችን የስልክ ቁጥር አልያዘም ነበር። አንድ ሳምንት መሳለሚያ የተቀመጠበትን ቤት ልብ ብሎ ያስተዋለው የበሩን ቀለም ብቻ እንደነበር ይናገራል።
ታክሲው መሳለሚያ ካወረደው በኋላ አይኖቹ አረንጓዴ ቀለም የተቀባ ቤት መፈለግ ይጀምራሉ። በመሳለሚያ አካባቢ የሚገኙ በርካታ አረንጓዴ ቀለም የተቀቡ በሮችን ቢያዳርስም ያረፈባትን ቤት ማግኘት ሳይችል ይቀራል። የእከሌ ቤት እያለ ሲዞር ሌባ እየመሰላቸው ከበር ያባረሩት፤ ያመነጫጨቁትና ሊመቱት የተጋበዙት ብዙዎች እንደነበሩ ያስታውሳል።
ከአስራ አንድ ሰዓት የጀመረ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ሲኳትን ቢያመሽም ማረፊያ ቤቱን ማግኘት ያቅተዋል። መጨረሻ ተስፋ ቆርጦ በአንድ ግንብ አጥር ጥግ ቁጭ ይላል። ከቅርብ ርቀት አስፓልቱ ዳር እራፊ ጨርቅ፣ ላስቲክና የማዳበሪያ ከረጢት ፊታቸው ላይ ጣል ጣል አድርገው የተኙ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ያያል። ሊጠጋቸው አልፈለገም። እዚያችው ጭብጥ ብሎ ያድራል። ሲነጋም ተነስቶ መፈለጉን ይቀጥላል። ግን ሊያገኘው አልቻለም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰለሞን የጎዳና ህይወትን መለማመድ ግድ እንደሆነበት ይናገራል።
ለተለያዩ ሱሶች እንዳይጋለጥ እራሱን እየጠበቀ ለሰባት ዓመታት ያህል በጎዳና ላይ ይኖራል። በጎዳና ህይወቱ ሙያዎችን ለመማር ብዙ ጥረቶችን አድርጓል።
አንድ ቀን አንድ ሰው የጫማ ቀለምና ብሩሽ ይገዛለትና የሊስትሮ ሥራን ያስጀምረዋል። ሊስትሮነትን እየዞረ በሚሠራ ሰዓት ሰዎች አሮጌ እቃ ትጠግናለህ? ስቶቭ ትሰራለህ? ዣንጥላ ትጠግናለህ? የሚሉ ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ ሲጠይቁት የሰማው ወጣት በአገኘው አጋጣሚ እነዚህን ሙያዎች ለማወቅ ጥረት ያደርጋል። መርካቶ እየሄደ በዘርፉ የተሰማሩ ሙያተኞች የሚሠሯቸውን ሥራዎች በትኩረት ይከታተል ጀመር። ከዚያ በፊትም የጸጉር ማስተካከል፣ የእንጨት ሥራና የድለላ ሥራዎችን ሞካክሯል። በዋናነት ግን ጸጉር ቤት ተቀጥሮ መሥራትና ዣንጥላና ብረት ድስቶችን መጠገን ትኩረት የሰጣቸው ሥራዎች ነበሩ።
ሊስትሮነቱን ትቶ ሙሉ ለሙሉ በጸጉር ማስተካከል ሥራ ላይ ይሰማራል። ከዚያም ቤት ተከራይቶ መኖር ይጀምራል። የተቃራኒ ጾታ ጓደኛም ያፈራና እየተጋገዙ መኖር ይጀምራሉ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ይታመማል። ሥራውን አቋርጦ በተኛ ሰዓት የገቢ ምንጩ ስለነጠፈ መታከሚያ ያጣል። ኋላ ግን በሰዎች ብርታት ማዘር ትሬዛ የሚባል ድርጅት ይወሰድና የህክምና እርዳታ ይደርግለታል።
ድርጅቱ ባደረገለት የጤና ምርመራ ሰለሞን የኤች.አይ. ቪ/ኤድስ ቫይረስ በደሙ እንዳለበት ይነገረዋል። ወላጅ እናቱን በዚሁ በሽታ ያጣው ወጣት እርሱም የዚሁ በሽታ ሰለባ መሆኑ ለጊዜው ያስደነግጠዋል። ነገር ግን በህክምና ባለሙያዎች በተደረገለት የምክር አገልግሎት ይረጋጋል። ለተወሰኑ ወራት እዚያው ድርጅቱ እያስታመመው ይቆይና ቫይረሱ እንዳለበት የሚገልጽ ደብዳቤ ተጽፎለት ጤና ጣቢያዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የመድኃኒትና መሰል ድጋፎችን እንዲያደርጉለት ተብሎ ይሸኛል።
ሰለሞን በተደረገለት ህክምና እና የምክር አገልግሎት የአካልና የመንፈስ ጥንካሬ አግኝቶ በአዲስ መልክ ሠርቶ የመኖር ፍላጎቱን አለምልሞ ወደ ሥራ ይሰማራል። ቀደም ሲል በሚሞክራቸው ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሙያውን የበለጠ ማሳደግ ይጀምራል። ባለቤቱም እርሱም እየሠሩ ኑሯቸውን ይቀጥላሉ። በዚህ መሐል ሁለት ልጆችንም ይወልዳሉ። የሰለሞን ባለቤት በተደረገላት ምርመራ ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ ነጻ መሆኗ ቢነገራትም ከባለቤቷ ጋር በመሆን ልጆቻቸውን እያሳደጉ ለዓመታት ዘልቀዋል።
የተወለዱት ልጆችም እንዲሁ ከቫይረሱ ነጻ ተብለዋል። ሰለሞንና ባለቤቱ በተለያዩ ምክንያቶች መግባባት ባለመቻላቸው አሁን ተለያይተዋል። ባለቤቱ ልጆቹን ይዛ ክፍለ ሀገር ቤተሰቦቿ ጋር መኖር ጀምራለች። እርሱ ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ አምስት በቀድሞው ቀበሌ አስራ ስድስት አነስ ያለች ክፍል በአምስት መቶ ብር ተከራይቶ ይኖራል።
የብዙ ሙያዎች ባለቤት እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ሰለሞን ለዓመታት ጸጉር በማስተካከል ሥራ ተቀጥሮ ይሠራ እንደነበር ይገልጻል። በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት እያረፈደ ወደ ሥራ ስለሚገባ ከአሠሪዎቹ ጋር መግባባት አልቻለም። በዚህ የተነሳ የግል ሥራውን እየሠራ መኖርን መርጧል። ሰለሞን አሁን ዣንጥላና የተጎዱ መገልገያ እቃዎችን ማለትም እንደ ብረት ድስት፣ የሻይ ማንቆርቆሪያ፣ የልብስ መዘፍዘፊያ የመሳሰሉትን እየጠገነ በሚያገኛት ገቢ ይተዳደራል። በቅርቡ ደግሞ የእቃ መያዣ ቆርቆሮዎችን እየቀደደ በራሱ ዲዛይን አነስተኛ የዳቦ መጋገሪያ እየሠራ እንዳለ ይገልጻል። የሚሠራው የዳቦ መጋገሪያ ከላይና ከታች የፍም ማስቀመጫ ያለው ሆኖ መሀሉ ዳቦው የሚጋገርበት ቦታ ነው። በቀላሉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችልና በአንድ ጊዜ ስድስት ህብስቶችን መጋገር የሚያስችል ነው።
ሰለሞን ከሚኖርበት ሰፈር ማለዳ ተነስቶ በየመንደሩ በመዟዟር የሚጠገኑ እቃዎችን እየሠራ ውሎ ማታ ወደ ቤቱ ይገባል። ሥራውን ለማከናወንም በቀን በርካታ ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ እንደሚያደርግ ይናገራል። እንደዚያም ሆኖ በቀን ከሚያገኛት ገንዘብ ለራሱ እየተጠቀመ የተረፈችውን አጠራቅሞ ለልጆቹ ይልክላቸዋል። ካለበት የጤንነት ችግር አንጻር የተመረጡ ምግቦችን እንዲመገብ ቢነገረውም በአቅም ውስንነት ምክንያት እንደተባለው እያደረገ አይደለም። ነገር ግን የሱስ ተገዢ አለመሆኑ በሰላም ለመኖር እንደረዳው ይናገራል። አንዳንድ ጊዜ ቀን ቀን በሥራ ምክንያት እዚያው ምሳውን ገዝቶ ከሚበላው በስተቀር አብዛኛውን ጊዜ እቤቱ እያዘጋጀ እንደሚመገብ ይናገራል።
ሰለሞን ጎዳና ተዳዳሪ ሆኖ ተመላሽ ምግብ እየበላና ሳንቲም እየለመነ ያሳለፈው ህይወት ይቆጨዋል። አሁን ራሱንም ቤተሰቡንም ለማኖር በሚከፍለው ዋጋ ደስተኛ ነው። ይሁንና ከጤናው አንጻር እየተዟዟሩ መሥራት ፈተና እንደሆነበት ይናገራል። ከዚያ ይልቅ ሁኔታዎች ቢመቻቹለት አንድ ቦታ ሆኖ መሥራት የሚያስችለውን የጸጉር ሥራ ቢሠራ ይመርጣል። ያንንም መሞከሩ አልቀረም። ግን ችግር የሆነበት ቤት አከራዮች በአንድ ጊዜ የአራት የአምስት ወር የቤት ኪራይ ክፍያ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ መሆኑ ነው። እስከ አሁን ምንም አይነት ድርጅት ድጋፍ እንዳላደረገለት የሚናረው ሰለሞን አሁን ግን ብድር የሚሰጠው አካል ቢያገኝ ጸጉር ቤት ከፍቶ የመኖር ፍላጎት እንዳለው ይናገራል። ቀበሌ ድጋፍ እንዲያደርግለት በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ተደራጅ፣ ማመልከቻ ጻፍ፣ እዚህ ቦታ ሂድ፣ የሚለው ውጣ ውረድ የዕለት ጉርሱን ለመሸፈን የሚያደርገውን መሯሯጥ ስለሚያስተጓጉልበት ገፍቶ መሄድ አልቻለም። በየስድስት ወሩ ግን “ጥበብ በቀጨኔ” ከተባለ ጤና ጣቢያ የኤች. አይ.ቪ መድኃኒት ይሰጠዋል። ለዚህም ያመሰግናል። የጤና ችግር እያለበት ሠርቶ መብላት መቻሉ እርካታን እንደሰጠው የሚናገረው ወጣቱ ሙሉ አካል ይዘው በየጎዳናው የሚለምኑ ወጣቶች የሰው እጅ ከሚጠብቁ ሠርተው የሚኖሩበትን አማራጭ ቢፈልጉ የተሻለ መሆኑን ይመክራል።
ከጤና ችግር ጋር ሆኖ እየሠራ መኖር ለሚጥረው ወንድማችን መልካሙን ተመኘንለት። ሳምንት በሌላ ባለታሪክ ህይወት ዙሪያ እስከምንገናኝ ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2013