ሰውዬው የቀብር ማስፈጽም ሥራን በመስራት የሚተዳደር ነው። እናት ልጅ ወልዳ ስትቀበል በእልልታ በመቀበል ደስታን እንገልጻለን። ሰው ሲሞት ደግሞ በሃዘን በመሸኘት ሃዘንን እንካፈላለን። የደስታና የሃዘንን ስሜት ለመለካት ግን በቁጥር አንችልም፤ የቀብር አስፈጻሚው ግለሰብ ግን ሁለቱ የተለያዩ ስሜቶች ይለካሉ ብሎ እንዴት መለካት እንደሚቻል ለማስረዳት የሚጥር ነው። የከበደው መጥቶ አደጋ እንዳይሆን ደስታንም ሃዘንንም መለኪያ ይኑራችሁ ይላል። የእርሱ መለኪያ ሚዛኑ “ቤተ-ሰብነት” ነው::
የቀብር አስፈጻሚው ግለሰብ በተገኘበት የማህበራዊ መድረክ ሁሉ ስለ ደስታና ሃዘን በቤተ-ሰብነት ውስጥ አድርጎ በመተንተን ልምዱ “ቤተሰብ” የተሰኘ ስምም ወጥቶለታል፤ በሰፊው ይታወቅበታልም። አደራ በምሞትበት ቀን በቤተ-ሰብነት ሸኙኝ ይላል፤ ሃዘን የሚደምቀው በቤተሰብነት ነው ብሎ ስለሚያምን። ቀጠል አድርጎም አውቃለሁ እንደምትወዱኝ ግን ፍቅራችሁን ልለካው ብችል በቤተ-ሰብነት ውስጥ ከሆነ እርሱ ከፍ ያለው ፍቅር ነው ይላል። “ፈላስፋው” እያሉ የሚጠሩት “ጀመረው ደግሞ መፈላሰፍ” በማለት በትንታኔው ላይ ሃሳብ ይሰጡበታል። ይህ ሰው ሁሌም ሃዘንን ለመለካት ይሞክራል፤ በሃዘኑ ልኬት ውስጥ ግን ቤተ-ሰብነትን ያነሳል። ግን ምን ማለት ነው? ዛሬ ሁላችንም ይህን እየጠየቅን ስለ ቤተ-ሰብ እናንሳ።
1. ቤተሰብነት
ባርባራ ቡሽ በቤተሰብ ዙሪያ የተናገሩት ጥቅስ አላቸው “ፍቅርን የሕይወትህ መሪ መርህ አድርገህ ኑር፤ ቤተሰብህን በመጠበቅ የቅርብ ጓደኞችህንም በቅርበት በመያዝ” የሚል። በእርሳቸው አገላለጽ ውስጥ ጓደኞችን መቅረብ ቦታ እንዳለው የተነሳ ሲሆን፤ ቤተሰብን ግን መቅረብ ሳይሆን መጠበቅ የሚለው ቃል ነው የሚገባው የሆነው።
ቤተሰብነት ግን ትርጉሙ ሰፋ ብሎ ለአንድ ሃሳብ የተሰለፉትንም ሲገልጽ ይሰማል። በተቋም ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እኛ የእዚህ ድርጅት ቤተሰብ ነን ሲሉ ቅርበታቸው ይታያል። የቡና ክለብ ቤተሰቦች፣ የጊዮርጊስ ክለብ ቤተሰቦች፣ ወዘተ ለአንድ ዓላማ መሰብሰባቸውን በቤተሰብነት ሲገልጹ የቃሉ ጥልቀት ታሳቢ ነው።
በአጭሩ ቤተሰብነት በብዙ መስተጋብሮች ውስጥ የሚጠራ፤ በቤተሳባዊ እሴት ውስጥ የሚፈለግ ብያኔ መሆኑን የሚክድ ያለ አይመስልም። ቤተሰብነትን ከደም ጋር አገናኝቶ ሲሆን ደግሞ ጥብቀቱ ደግሞም ክረቱ ይጎላል። ተፈጥሮ አጥብቃ ያሰረችው፤ ደግሞም ለሰዎች ውሳኔ የተወችውም አብረው በቤተሰብነት ባህር ውስጥ ይቀዝፋሉ። ቤተሰብነት! ቤተ-ሰብ!!
እዚህ ላይ ሰብን በሰው ስንተካው ቤተ-ሰብ ማለት የሰው መኖሪያ፤ የሰው መጠሊያ፤ የሰው ማደሪያ፤ የሰው በሰውነት ለመገኘት የሚያልፍበት ስፍራ ወዘተ ብለን ልንተረጉመው እንችላለን። ሰላም፣ መተሳሰብ፣ መቀባበል፣ አንዱ ለአንዱ ማሰብ ወዘተ ውስጥ በጥልቅ ተቆፍሮ የሚገኘ የማይዳሰሰው ሃብት በሰብ መኖሪያ ቤተ-ሰብ ውስጥ አለ።
ደቡብ አፍሪካ ከሰሞኑ
ሰሞኑን በደቡብ-አፍሪካ አንድ ወንድ ከአንድ በላይ ሚስትን በህጋዊነት ማግባት የሚችልበት ህጋዊ አሰራር መኖሩ በዜና አውታሮች እየተሰማ ነው። ይህ መብት ለምን ለወንዱ ብቻ ሴቷም ይኑራት እንጂ? ተብሎ ሙግት ተጀምሯል። በተመሳሳይ ሁኔት አንዲት ሴት ከአንድ በላይ ባሎች እንዲሯት የሚያደርግ ህግ የማርቀቅ ሂደትም ላይ ናቸው። ይህን መሰሉ ድንጋጌዎች፣ የተመሳሳይ ጾታን እንዲሁም ሌሎች መሰል ጉዳዮችን ገጣጥመን ስናየው ቤተ-ሰብ የተሰኘው ተቋም በዘመነ ስልጣኔ ጦርነት ውስጥ የገባ ይመስላል።
ቤተ-ሰብን ትርጉም የሚያሳጡ ህጋዊ ድንጋጌዎች በአለማችን ላይ እየበዙ በሄዱ ቁጥር እያንዳንዱ ሰው እንደሰው ሊኖርበት የተገባው የጥሞና ቤት እየፈረሰ፤ ቤት-አልባ ሰዎች እየበዙ፤ ዓለማችን መልከ-ጥፉ የግላዊነት መናኸሪያ ትሆናለች።
ልጆቻችን በመጀመሪያ ሳይክል የትምህርት ክፍል ውስጥ ስለቤተሰብ ሲማሩ ከሚነሱ የቤተሰብ አባላትን አንስተን እንመልከት። አባትንም እናስቀድም።
2. አባት – አባትነት
ከጠቢቡ ሰለሞን የምክር ቃሎች መካከል “እናንተ ልጆች፣ የአባትን ተግሣጽ ስሙ፤ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ” (ምሳሌ 4፡1) የሚለው ውስጥ “አባት” የሚለውን ቃል አስምረን እንነሳ። ይህ የጠቢቡ ምክር የሚገኝበት “መጽሐፈ ምሣሌ” ውስጥ ሌሎች አባቶችን ማእከል ያደረጉ የምክር ቃሎች አሉ። አንባቢው ፈልጎ ይማርባቸው ዘንድ እጋብዛለሁ።
በቤተሰብ ውስጥ “አባት” እና “አባትነት” ያላቸው ስፍራ ትልቅ ነው። አባትነት ሃላፊነት ነው፤ እያንዳንዱን የቤተሰብ አባላት ከራስ በላይ ተመልክቶ ዝቅ ብሎ የማገልገል ሃላፊነት። አባት በአባትነት ስፍራው ላይ ሳይገኝ ገንዘቡን ውጭ በትኖ፤ ትኩረቱን ከቤቱ አንስቶ ውጭ ውጩን ብቻ አድርጎ ቤቱ ውስጥ ቅዝቃዜ ቢገባ ከአባትነቱ ውስጥ የሚወጣ የምክር ቃል አቅም እንዳለው እንዴት ይታሰብ? እንዴ የትም!!
አባት ለመጪው ትውልድ ምሣሌ የሚሆን፣ የቤተሰቡ አመራርን ሃላፊነትን የተቀበለ፣ ቤተሰቡን ለመጠበቅና ለመከለል ቀዳሚው ሃላፊነት ያለበት ሆኖ እናገኘዋለን። “የአባቶች ቀን” ተብሎ የሚከበር ቀን ውስጥ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ምስላቸው የሚወጡ አባቶችን እናያለን። በአባቶች ቀን መልእክት በስፋት የሚያስተላልፉት የትዳር አጋሮች እና ልጆች ናቸው። ልጆች ከአባታቸው ያዩትን መልካም ነገር መነሻ በማድረግ ፍቅራቸውን ለአባታቸው ሲገልጹ ይስተዋላል። በተመሳሳይ ሁኔታ በአባታቸው ግብር እጅግ የሚያዝኑ ግፋ ሲልም የሚያፍሩ ልጆች በአደባባይም ባይሆን አባታቸውን በልባቸው ምንው ጨከንክብን ብለው ቀኑን ያስቡታል።
ሰው በሰውነት ሊገኝ ተገባበት ቤት የሆነው ቤተ-ሰብ የሞቀ፣ የጠበቀ፣ ለመጠለያ፣ ለመሰሪያ፣ ለመቀረጪያ፣ ወዘተ ይሆን ዘንድ አባትነት ትልቁን ሥራ ይሰራል። የሚመለከተው አባት እራሱን እየመረመረ እንደሆነ ጸሃፊው አስቦ ይቀጥል።
የአባትነት መንፈስን በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ስናመጣ የድርጅት መሪዎች፣ የእድር መሪዎች፣ የስፖርት መሪዎች፣ የሀገር መሪዎች ወዘተ የአባትነትን መንፈስ መላበስ የግድ ይላቸዋል። አባትነት ውስጥ ስለሌሎች ራስን አሳልፎ በመሰጠት ዝቅ ብሎ ሌሎችን ወደ ከፍታ የመምራት ሃላፊነት ነው። አባትነት ውስጥ ፍቅርን መስጠት መቻል አለ። አባትነት ውስጥ በቤተሰብ አባላት ውስጥ ያለውን እምቅ አቅም እንዲወጣ መንገዱን መጥረግ አለ። አባትነት ውስጥ መካሪነት አለ። አባትነት ውስጥ ከለላ መሆን አለ። አባትነት ውስጥ የወደፊቱን አሻግሮ ተመልክቶ የዛሬን አካሄድ ማስተካከል አለ። አባትነት፤ ሃላፊነትም ከህሊና ጀምሮ እስከ ፈጣሪ መዝገብ ተጠያቂነትም ያለበት ነው። ሰው በሰውነት እንዲገኝ የተሰራው ቤት ውስጥ አባትነት በብዙ ገጹ ይነሳል። እንቀጥል …
3. እናት – እናትነት
“እናትነት” በአርእያነት ውስጥ ከሁሉም የሚቀድም ጸጋ ነው። ሚሼል ኦባማ አርእያነትን የወላጅነት ሃላፊነት አድርገው በአንድ ወቅት ገልጸውታል። የትኛው ቃላችን፣ የትኛውም ተግባራችን ልጆቻችን ይመለከቱታል። እኛ ወላጆች የእነርሱ ዋና አርእያዎች ነን ሲሉ ነበር የተናገሩት። ስለ እናትነት ስናነሳ ግን የላቀው አርእያነት በእናትነት ውስጥ እንዳለ ብንጠቅስ አንሳሳትም። ከጽንስ ጀምሮ እስከ እድገት ድረስ “እናት” የልጅ የመጀመሪያው ቅርብ ሰው ስለሆነች።
ጠቢቡ ሰለሞንም … የእናትህንም ሕግ አትተው (ምሳሌ 6፡20) በማለት ከእናት የሚወሰደው ሕግ ሊከተሉት የተገባ መሆኑን ይገልጻል። ስለ እናት ምን ተብሎ ምን እንደሚተው ይቸግራል። እናት በየትኛውም መድረክ መልሶ “እናት” ከሚለው ቃል ውጪ ምንስ ሊገልጣት ይችላል? ምንም።
ዛሬ የቤተሰብ ህግ መልከ ብዙ ሆኖ የቤተሰብ ጣዕም እየደበዘዘ በሄደባቸው ሀገራትም ሳይቀር እናትነትን በምንም መተካት ያልተቻለ ሆኗል። እናትነት ውስጥ ሁሉም ነገር አለ። በእሳትም ሆነ በውሃ ውስጥ አልፋም ቢሆን ስለወለደችው ጥርሷን ነክሳ የምትራመድ የጽናት አርአያ፤ እናት ናት። እናት በፍጹም በምንም አትለካም፤ ደግሞም አትተካም።
እናትነትን እንደ ልዩ ሃላፊነት፣ ሁሌም እንደ ልዩ ጸጋ መቁጠር ይገባናል። እናትን መስማት ከምልዑ ፍቅር የሚወጣ ምክርን መስማት መሆኑ መካድ የለበትም። የዛሬ ወጣቶች፤ የዛሬ ልጆች የነገ አባቶችና እናቶች ናቸው። በእናትነት ውስጥ ያለውን ህግ መከተል ፍሬው ለመንገዳቸው ነው። ከፍቅር የሆነ ህግ በእናት በኩል አለ፤ እርሱም የሚያንጽ ነው፤ የሚሰራ ነው፤ የሚያበረታ ነው፤ ስንቅ የሚሆን ነው። ደመ-ሞቃት ሆኖ የእናትን ልብ ማክበድ ለጉዞ አይበጅምና ጆሮ ለእናት ይከፈት፤ ጆሮ ለአባት ይከፈት፤ ጆሮ የቀደሙትን ምክር ለመስማት ይከፈት።
እናት የሆንሽው ደስ ይበልሽ። አንቺ የከበረውን ሰው በመልካም የመቅረጽ እድል የሰጠሸ የሰው ቤት የሆነው ቤተሰብ መሰረት ነሽና። ዛሬን ነገን የምታገናኝ ድልድይ። ሰው የሚኖርበት ቤት ብርሃን! እቺ እናት ስፍራው መቼም የክብር መሆኑን አሻግሮ የተመለከተው ጠቢቡ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት (ምሳሌ 23፡22) ሲል ያሳስባል። ማሳሰቢያው ለልጅ ነው።
4. ልጅ – ልጅነት
በጠቀስናቸው የጠቢቡ ምክር ውስጥ ምክሩ ተደራሽ ያደረገው ልጅን ነበር። ልጅነት በአባትነት እናትነት መካከል የሚገኝ አስደናቂው የምድራችን ፍጡር ነው። ሰው ከአባትና እናት ይገኝ ዘንድ እርሱም ፈቃድ ያለው ሆኖ የሚኖር የነገ አባትና እናት ነው። ልጅነት ትርጉም እንዲኖረው የሰው መገኛ የሆነው ቤት ጤንነት በብዙ መጠበቅ አለበት።
ልጅነት ውስጥ ተማሪነት ገዝፎ ይታያል። ተማሪነቱ ከተሰመረው መደበኛ ትምህርት እስከ ኢ-መደበኛው ይዘልቃል። ከእናትና አባት እርምጃ የሚገኘው ትምህርት ደግሞ የምስክር ወረቀት የማይሰጠው የትምህርት ሁሉ የቀደመው ትምህርት ሆኖ ይገኛል። በልጅነት ሚዛን እየመዘኑ የሚቁጥሩ ቀናት ውስጥ ጥበብ የበዛ ስራን ትሰራለች። የልጅነት ዘመን ጥበብ መጉደል የሕይወት ዘመንን አቅጣጫ አስቶ መዳረሻን ጥያቄ ውስጥ ሊከት ይችላል።
አንተ ሰው ልጅ ነህ? አዎን ልጀነትህ በእድሜህ ቁጥር ውስጥ ትርጉም የማያጣ። የአንቺ ልጅነት በየትኛውም እድሜሽ ውስጥ ትርጉሙ ያው ነው። የበለጠ የእድሜ ቁጥር ግን እርሱ ከእናትና አባት ጋር በሆንባቸው ጊዜዎች ውስጥ ነው። ከአባትና እናት ግንኙነት የምንማርበት፣ ከእነርሱ ስኬት የምንማርበት፣ ከውድቀታቸው የምንማርበት፣ ከማህበራዊ መስተጋብራቸው የምንማርበት ከሁሉም ነገራቸው የምንማርበት ታላቁ ትምህርት ቤት በልጅነት ውስጥ አለ።
በልጅነት ውስጥ ባለመብትነት አለ። ባለመብት መሆን ብቻ ግን ስኬታማ አያደርግም፤ መብትን መጠቀም የሚያስችል አቅም ያስፈልገዋል። በሥራ ትጋታቸው የሚታወቁ ሃብትንም ያከማቹ አባትና እናት ከልጆቻቸው በሞትም ሆነ በሌላ ጉዳይ በማይቀጥሉበት ጊዜ ልጆች የቤተሰባቸውን ጥበብ ካለመውሰድ በእጃቸው ያለውን በትነው ሲታዩ ምን እናስተውላለን? ልጆች የዛሬውን ከመኖር ባሻገር ለነገው ባልተዘጋጁበት ልክ በነገ ውስጥ መቸገራቸው ይበዛል።
ልጅነትህ ልትክደው አትችልም። የልጅነትህን መብት ማወቅ፤ የልጅነትህን መብት መጠቀም በመቻል ጥበብ ውስጥ ማደጉን መርምር። ይህን ሃላፊነት በልጅነት ወራት መለማመድ እንዲቻል እድል የሚሰጥ ሁኔታ እርሱም ወንድምነትና እህትነት ነው። በወንድምነትና እህትነት ውስጥ የልጅነትን መብት መጠቀም የሚያስችል ልምምድ አለ፤ እንዲሁም የነገ አባትነትና እናትነት።
5. ወንድምነት – እህትነት
በፖለቲካው መድረክ ውስጥ ጎልተው ከሚሰሙ ከቤተሰብ የተወሰዱ ቃላት መካከል “ወንድማማችነት” ቀዳሚው ነው። በፈረንሳይ አብዮትም ሆነ በሌሎቹም ቃሉ ሥራ ላይ ቆይቶል፤ በሀገራችንም እንዲሁ። ወንድማማችነት ውስጥ ያለው እሴት በብዙ ተዘምሮለታል። ሥነ-ቃሎቻችንም የወንድምነት ጋሻነትን መስክረዋል።
በልጅነት ትርጉም ከእናትና አባት ጋር ቤተ-ሰባዊ ቁርኝት ሲኖረን በልጆች መካከል ወንድምነትና እህትነት የቁርኝቱ መጠሪያ ይሆናል። ልጅነት የአንዱን ግለሰብ እራስ ተኮር የሆነ ግላዊ ማንነትን የሚያሳይ ሲሆን ወንድምነትና እህትነት ግን ከሌሎች በልጅነት ትርጉም ውስጥ ካሉት ጋር የሚኖር መስተጋብርን ያሳያል።
ወንድምነት ውስጥ የነገ አባትነት፣ ሃላፊነት አለ። እህትነት ውስጥ ደግሞ የነገ እናትነት። ወንድምነት ለወንድሞችም ለእህቶችም ማሰብ አለ። አንዱ ልጅ ለሌላው ልጅ ሲያስብ ያኔ በመደጋገፍ ውስጥ እንደ አንድ ቤተሰብ የመተንፈስ እድልን ይፈጥራል። አባትና እናት ያልደረሱበትን ልጆች እርስ በርሳቸው የሚመካከሩበት የሚገሳጸጹበት መድረክ በወንድምነትና እህትነት ውስጥ አለ።
ወንድምነት ፍቅርን፣ እድገትን፣ መተጋገዝን፣ አንዱ የአንዱን ሸክም መሸከምን፣ አብሮ በሀዘንም በደስታም መቆምን ወዘተ የምናሳይበት እሴት ነው።
እህትነት ከፊል-እናትነት ሆኖ ይታያል። በኢትዮጵያ ውስጥ እህቶቻችን የእናቶችን ሸከም ተሸክመው ወንድሞቻቸውን ለማገልገል የቀደሙ ናቸው። በአኗኗር ለውጥ የቤተሰብ ሸክምን መጋራት የሚገባ መሆኑ በሰፊው ቢነገርም ዛሬም ክፍተቱ እንዳለ ነው። በእህትነት ውስጥ ያለው እናትነት ለነገ እናትነት መዘጋጃ መሆኑ አይካድም። ቤተ-ሰብነት ውስጥ የሰው ልጅ የሰላም እንቅልፉን የሚያንቀላፋበት ቤት ውስጥ የሚኖረውን ህይወት መመልከቻ።
ወንድሞቻቸውን ለማስተማር፣ ወንድሞቻቸውን ዳር ለማድረስ በብዙ የደከሙ እህቶች ምስክርነትን ለመስማት ብዙ መልፋት ለእኛ አያስፈልገንም፤ ሁላችንም በቤታችን የምናየው ነውና። እህትነትን እናመስግን። የራሱን ቀለም ለይተን እንንከባከበው። ይህንንም የምናደርገው እህትነት ያልተገባ ጫናን መሸከሚያ ቀንበር ከሆነ የነገዋ የቤተሰብ ምሰሶ ቤተሰብን በተሳሳተ መንገድ ተመልክታ ከቤተሰብ ምስረታ የምትሸሽ ልትሆን ትችላለችና ነው። እህት ከነጣቂ ተኩላ መጠበቅ ያለባት መሆኑን እንዲሁ ልብ እንበል።
የሰው መኖሪያ መጠሪያው ቤተ-ሰብ ውስጥ ያለውን መስተጋብር በአጭሩ መግለጽ ባይቻልም፤ ትኩረት ተደርጎበት የሰው የሰላም ቤት ይሆን ዘንድ ሁላችንም ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል። ከቤተሰብ ተነስተን ወደኋላ ስንሄድ መዳረሻችን አዳምና ሔዋን ይሆንና ከትንሹ ቤተሰባችን ባሻገር ዓለም ሁሉ የአንድ ወቅት የአንድ ቤተሰብ ውጤት መሆኑን እንረዳለን። በጊዜ ብዛት ቢሊዮኖች በአንድ ጊዜ የሚኖሩባት ምድር ውስጥ እንድንኖር ያደረገ ቤተሰብ፤ ወንድማማችነት፤ እህትማማችነት ቢሰፍን በአንጻራዊነት ትልቁ ቤተሰብ በሰላም ሊኖር የሚችልበት እድል ያለው።
ዛሬ በምድራችን በብሔር፣ በእምነት በሌሎች ምክንያቶችም የሚያነጋገሩን ነገሮች ከመነጋገር አልፈው መስመር እየሳቱ በሆኑ ቁጥር ቤተ-ሰብ ይፈርሳል። በሂደትም የሁሉንም ቤት የሚነካ። መፍትሄው ሁላችንም የአንድ ቤተሰብ ግኝት መሆናችንን ተረድተን ቤተሰባዊ ሃላፊነታችንን መወጣት ይሁን የሚል ነው። የቀብር አስፈጻሚ የደስታ የሰላም መለኪያው ቤተሰብ መደረጉ ምን ያህል ትክክል ነው የሚለውን ለእናንተ ትቼ ለመሰናበቻ ጥያቄ ላንሳ። አዳም፣ ሔዋን፣ አቤል፣ ቃየል፣ ሴት፣… የመጀመሪያው ቤተሰብ ዛሬ ወደ ምድር ቢመጡ ምን ይሰማቸው ይሆን?
ባላችሁበት ሰላም!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2013