ከስህተቱ የማይማር ቡድን ቢኖር የህወሓት ሽብተኛ ቡድን ብቻ ነው። ይህ ቡድን ሁሌም እሱ የሚለው ብቻ ነው ትክክል ብሎ የሚያምነው። የህዝብና የሌሎችን ወገኖች ሃሳብ ፈጸሞ አይቀበልም። ይልቁንስ ፈላጭ ቆራጭ፣ አድራጊ ፈጣሪ እኔ ብቻ ነኝ በሚል ራስ ወዳድነት ዘመናትን ተሻግሯል። ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረ ጊዜም የሌባና የማፍያ ስብስብም መሆኑን ጭምር በተግባር አሳይቷል። የአገር መርከብ ሰርቋል፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሌብነት ዋሻ አድርጎታል። የጋራ መኖሪያ ቤቶች ህንጻዎችን የት እንዳደረሳቸው አይታወቅም። በጥቅሉ ኢትዮጵያን ስጋዋን ግጦ አጥቷን ብቻ ነው ያስቀራት።
ይህ ቡድን ከፌዴራል መንግስቱ በህዝብና በለውጥ ሃይሉ ተገፍቶ ወደ መቀሌ ሲሸሽ ከስህተቱ የሚማርበትና ሰክኖ የሚያስብበት ዕድል ተሰጥቶት ነበር። ሆኖም የተሰጠውን ዕድል ሊጠቀምበት አልቻለም። ‹‹የበላይነት የለመደ እኩል ሁን ስትለው ያኮርፋል›› እንዲሉ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ወደ ባሰ ጥፋት ሊሸጋገር ችሏል። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ ሁሉ ይህ ቡድንም እኔ ያልመራዋት ኢትዮጵያ ትበታተን በሚል ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዘርና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶችን ሲጠምቅና ሲያቀጣጥል ቆይቷል።
ቡድኑ ከዚህ እኩይ ተግባሩ እንዲታቀብና ችግሮችም ካሉ በውይይት ለመፍታት በፌዴራል መንግስት በኩል በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። በሃይማኖት አባቶች፣ በዲፕሎማቶች፣ በታዋቂ ሰዎችና በአገር ሽማግሌዎች በኩል ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉት ጥረቶች በአሸባሪው ህወሓት ለስሜቱ በመገዛቱና ለራሱ የተሳሳተ ግምት በመስጠቱ ሳይሳኩ ቀርተዋል።
ቡድኑ ያሰበው ግብ ሳይሳካለትና ግጭቶቹም እየመከኑ ሲሄዱበት ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከፍቷል። ይህ ውለታ የማይገባውና ከስህተቱ የማይማረው ቡድን ጥቃት የከፈተባቸው የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የትግራይ ህዝብ ለ20 ዓመታት በምሽግ ውስጥ ሆነው ሲጠበቁ የነበሩ ናቸው። በዚህ ጨካኝ ተግባሩም ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ጡታቸውን በመቁረጥ በታንክ ጨፍልቋል። የአርሶ አደሩን ሰብል ሲሰበስቡ የዋሉትን የሰራዊት አባላት ተኩስ ከፍቶ ብዙዎቹን ረሽኗል። በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ድግሞ ሊነገር የማይችል ስቃይና ግፍ ፈጸሞባቸዋል።
በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የከፈተው ሽብርተኛ ቡድን በዚህ ብቻ ሳይወሰን የአማራን ህዝብ ለመውረርም ሙከራ አድርጓል አልተሳካለትም እንጂ። ይህን ተከትሎ መንግስት በትግራይ ክልል በወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ የአገር መከላከያ ሰራዊት በሶስት ሳምንት ነው መቐሌን የተቆጣጠረው። በተያያዘም በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ቡድኑ ወደ አስመራም ሚሳኤል በመተኮስ ኤርትራ ወደ ጦርነት እንድትገባ ጋብዟታል።
መንግስት በካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻም እንደ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ወልዱ፣ ቅዱሳን ነጋ፣ አባዲ ዘሙና ሎሎችም የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል። እነ አባይ ጸሀየ፣ ስዩም መስፍን፣አስመላሽ ወልደስላሴ፣ዘርአይ አስግዶምና ሌሎችም የሲቪልና ወታደራዊ መኮንኖች ተደምሰሰዋል። እንዲሁም ቡድኑ ይዟቸው የነበሩትን ከባድና ዘመናዊ መሳሪያዎችን ማስመለስና ሽብርተኛውን ቡድን አከርካሪውን መስበር ተችሏል።
በትግራይ ክልል የተካሄደው ግጭት በአገር ደህንነት ላይም ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል፣ በሰዎችና በአገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። በምዕራቡ የአገራችን ክፍል ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ የገባችውም የህግ ማስከበሩ ዘመቻ በተጀመረ ማግስት ነበር።
መንግስት ባለፉት ስምንት ወራትም ከ100 ቢሊዮን በላይ ብር ወጪ በማድረግ በትግራይ ክልል በግጭቱ ምክንያት የተጉዱትን እንደ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ ኤንተርኔትና መንገዶች ያሉ መሰረተ ልማቶችን ጠግኗል። ለህዝቡ የሰብዓዊ የእህልና የህክምና ቁሳቁስ ዕርዳታ አቅርቧል። ለአርሶ አደሩም ማዳበሪያ፣ ትራክተርና ምርጥ ዘር በወቅቱ አድርሷል። እንዲሁም ዕርዳታ ለሚያቀርቡ አካላትም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
በአንጻሩ አሻበሪው ሃይል በየስርቻው እየተወሸቀ አጋጣሚ ሲያገኘ እየወጣ ዕርዳታ የሚያደርሱ ሹፌሮችን፣ ኤሌክትሪክ የሚጠግኑ ሰራተኞችና ለሰብዓዊ ተግባር የተሰማሩ ባለሙያዎችን መግደልና ማፈን የየዕለት ተግባሩ ሆነ። ሽፍታው ቡድን እንደ እምነት አባት ጥምጣም አልብሶ ባሰማራቸው ሰዎች በሃይማኖት ቦታዎችና በገበያ ቦታዎች በመገኘት ተወረርክ፣ ተደፈርክና ተገደልክ እያለ ዘር ተኮር ቅስቀሳ በማካሄድ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ሰርቷል። ቡድኑ ሲቨል ለብሶ ወደ ከተሞች እየገባም በእምነት ቦታዎች ጉድጓድ ቆፍሮ የቀበራቸውን መሳሪያዎች እያወጣም ሲቪል በመምሰል በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ሲያደርስ ቆይቷል። የዕርዳታ እህል ለህብረተሰቡ እንዳይደርስ መሰናክልና ችግር ሲፈጥር ቆይቷል።
የዕርዳታ እህሉ ለህዝቡ እንዳይደርስ መሰናክል የሚፈጥረው ሽብተኛው ቡድን ሆኖ እያለ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በርካታ ወቀሳዎችን፣ ጫናዎችና ወከባዎችን የሚያደርጉት በመንግስት ላይ ነው። ሽብርተኛው ቡድን ሆን ብሎ የትግራይ ህዝብ ዕርዳታ እንዳያገኘና እንዲራብ በማድረግ ርሃብን ለቅስቀሳ ሲጠቀምበት ቆይቷል፤ እሱ ለሚፈጸመውን ወንጀል ሰበብ ላለመሆን፣ የትግራይ አርሶ አደር ያለ ስጋት እርሻውን እንዲያካሄድ፣ የትግራይ ህዝብ የመንግስትን ጥረት በጥሞና እንዲገነዘበውና ኢትዮጵያ ውጫዊ የደህነት ስጋት ስላለባት የአገር መካላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ ወጥቷል።
በቅርቡም መንግስት የተናጠል ባደረገው የተኩስ አቁም ውሳኔ መሰረትም የመከላከያ ሰራዊቱ ትግራይን ለቆ ከወጣ በኋላም በትግራይ ክልል በሽብርተኛው ቡድን አሁንም ንጹሀን ሰዎች እየተገደሉ ነው።ንጹሃን ሰዎች እየተገደሉ ነው ሲሉ የነበሩ አካላት ከእንግዲህ በኋላ ተጠያቂም ተወቃሽም ማድረግ ያለባቸው ሽብርተኛውን ቡድን ነው። ምክንያቱም በሀሰት ሲወቀስ የነበረው መከላከያ ሰራዊት ለዚህ ሰበብ ላለመሆን፣ ቡድኑ አሁን የአገር ስጋት ባለመሆኑና ሰላማዊ ሰዎች ተገን አድርጎ ጥቃት የሚፈጽም እንጂ ፊት ለፊት ለመግጠም አቅሙ የመከነ በመሆኑና የትግራይ አርሶ አደር ተረጋግቱ እርሻውን እንዲያርስ ለማድረግ የአገር መከላከያ ሰራዊት በመንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ ትግራይን ለቅቆ ወጥቷል።
ከአሁን በኋላ በትግራይ ቀውስ፣ ግድያ ካለና ሰብዓዊ ዕርዳታ ከተስተጓጎለ የሚወቀሰውና የሚጠየቀው ሽብርተኛው ቡድን መሆን አለበት። ዓለም አቀፉ ማህረሰብም ይህን ቡድን ተጠያቂ ማድረግ መልመድ ይኖርበታል። ለህዝቡ ዕርዳታ ለማድረስ ተቸግረናል በማለት ሰበብ ሲደረድሩና መከላከያ ሰራዊታችን ሲወቅሱ የቆዩ አካላትም የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ስለወጣ ያልተገደበና ተደራሽነት ያለው ዕርዳታ መስጠት ይችላሉ። ገብተው እንደፈለጉ ዕርዳታ መስጠት ይችላሉ።
የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ትግራይን ለቆ ቢወጣም አሁንም ሽብርተኛው ቡድን አማራንና ኤርትራን እወራለሁ ማለቱ ከስህተቱ የማይማር ሰይጣናዊ ቡድን መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።ሆኖም አሁንም ትንኮሳ አካሄዳለው ካለ የመከላከያ ሰራዊታችን እንደሚኮረኮም የታወቀ ነው። ምክንያቱም የመከላከያ ሰራዊታችን የህወሓትን ጁንታ ቡድን ሮኬት፣ ታንክና ሚሳኤል በነበረው ጊዜም እንኳ በሶስት ሳምንት መቐሌን በመቆጣጠር ጀግንነቱን አስመስክሯል። ስለዚህ ሽብርተኛው ቡድን አሁንም ዳግም የመማሪያ ዕድል ተሰጥቶታል። ከተጠቀምበት። በተለይም ደግሞ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የትግራይ ህዝብ ይህንን ቡድን በቃህ የሚልበት ወሳኝ ወቅት መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/ 2013