የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ወጣቶች ቁጥር በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመረ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እንደገለጸው የመንፈስ ጭንቀት፣ “ከ10 እስከ 19 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ለሚያጋጥማቸው ሕመምና የአካል ጉዳት ዋነኛ መንስኤ” ነው።
የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች
የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች በጉርምስና ዕድሜ ሊታዩ የሚችሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የእንቅልፍ ወይም የአመጋገብ ልማድ መዛባት አሊያም የክብደት መጨመር ወይም መቀነስ ይገኙበታል። በተጨማሪም የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ወጣቶች ተስፋ ሊቆርጡ እንዲሁም የሐዘንና የዋጋ ቢስነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ከዚህም በላይ ራሳቸውን ሊያገልሉ፣ ትኩረት የመሰብሰብ ወይም የማስታወስ ችግር ሊያጋጥማቸው፣ ራሳቸውን ለማጥፋት ሊያስቡ ወይም ሙከራ ሊያደርጉ እንዲሁም በሕክምናው ዓለም በትክክል ያልታወቁ ሌሎች ምልክቶች ሊታዩባቸው ይችላል። የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች አንድ ሰው የመንፈስ ጭንቀት ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ የሚያውቁት የግለሰቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያውኩ ለሳምንታት የዘለቁ ምልክቶች መኖር አለመኖራቸውን በመመልከት ነው።
መንስኤው ምን ሊሆን ይችላል?
የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው “የመንፈስ ጭንቀት የማኅበራዊ፣ የሥነ ልቦናዊና የአካላዊ ችግሮች ድምር ውጤት ነው።” እስቲ እነዚህን ነገሮች በዝርዝር እንመልከት፦
• አካላዊ ችግር፦ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ በላይ ሰው የመንፈስ ጭንቀት ሊኖርበት ይችላል። ይህም የመንፈስ ጭንቀት በዘር ሊወረስ እንደሚችል ይጠቁማል። በአንጎል ውስጥ ባለው ኬሚካላዊ ሂደት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ችግሮች በዘር ሊተላለፉ ይችላሉ። በመንፈስ ጭንቀት የመያዝን አጋጣሚ ከፍ ከሚያደርጉ ሌሎች አካላዊ ችግሮች መካከል ከልብ ጋር የተያያዙ በሽታዎች፣ የሆርሞን መጠን መዛባት እንዲሁም ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ መጠቀም ይገኙበታል፤ አንድ ሰው ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን ለረጅም ጊዜ አላግባብ ከተጠቀመ የመንፈስ ጭንቀት ሊይዘው ወይም ሊባባስበት ይችላል።
• ውጥረት፦ በተወሰነ መጠን ውጥረት የሚሰማን መሆኑ ጤናማ ሊሆን ቢችልም ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ወይም ከመጠን ያለፈ ውጥረት ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊዳርገን ይችላል። በተጨማሪም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ከፍተኛ የሆርሞን ለውጥ ስለሚያጋጥማቸው በሚሰማቸው ውጥረት የተነሳ ለመንፈስ ጭንቀት ሊጋለጡ ይችላሉ። ሆኖም የመንፈስ ጭንቀት ትክክለኛ መንስኤ እስካሁን ድረስ በግልጽ አይታወቅም። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የመንፈስ ጭንቀት የተለያዩ ችግሮች ድምር ውጤት ሊሆን ይችላል።
የመንፈስ ጭንቀት እንዲከሰት ከሚያደርጉ፣ ከውጥረት ጋር ከተያያዙ መንስኤዎች መካከል የወላጆች መፋታት ወይም መለያየት፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት፣ አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት፣ ከባድ አደጋ እንዲሁም ሕመም ይገኙበታል፤ በተጨማሪም አንድ ልጅ ትምህርት የመቀበል ችግር ካለበትና በዚህም ምክንያት በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው የሚሰማው ከሆነ ለመንፈስ ጭንቀት ሊጋለጥ ይችላል። ወላጆች ልጆቻቸው በትምህርት ቤት ከአቅማቸው በላይ የሆነ ውጤት እንዲያመጡ የሚጠበቁባቸው ከሆነም ልጆቹ ለውጥረት ሊዳረጉ ይችላሉ። በተጨማሪም ወጣቶች ከጉልበተኞች የሚደርስባቸው ማስፈራሪያ፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰማቸው ስጋት፣ ከወላጆቻቸው አንዱ ባለበት የመንፈስ ጭንቀት የተነሳ ከእነሱ በስሜት መራቁ እንዲሁም ወላጆቻቸው ተለዋዋጭ ባሕርይ ያላቸው መሆኑ ለጭንቀት ሊያጋልጣቸው ይችላል።
በወጣት ሴቶች ላይ የሚከሰት የመንፈስ ጭንቀት
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ በመንፈስ ጭንቀት የተያዙ ሴት ልጆች ቁጥር ከወንዶቹ ይበልጣል። ምክንያቱም ስሜታዊ፣ አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት አሊያም ፆታዊ ትንኮሳ በአብዛኛው የሚደርሰው በሴት
ልጆች ላይ ነው፤ ይህ ደግሞ ውጥረት ይፈጥርባቸዋል። በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን “ቆንጆ” ብሎ የሚያቀርበው የሰውነት ቅርጽ፣ ሴት ልጆች ለራሳቸው ባላቸው አመለካከት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። አንዲት ልጅ ቆንጆ እንዳልሆነች የምታስብ ከሆነ ወይም በእኩዮቿ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ካላት በመንፈስ ጭንቀት የመያዝ አጋጣሚዋ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል። ለመሆኑ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ታዳጊ ወጣት (ሴትም ሆነ ወንድ) በመንፈስ ጭንቀት ከተያዘ ምን አይነት እርዳታ ሊደረግለት ይገባል?
ለአካልህና ለአእምሮህ እንክብካቤ ማድረግ
– መጠነኛም ሆነ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው አብዛኛውን ጊዜ መድኃኒት መውሰድ ወይም የአእምሮ ጤና ባለሙያ ማማከር ያስፈልገዋል። ሕመም ደግሞ አንጎላችንን ጨምሮ የትኛውንም የአካል ክፍላችንን ሊያጠቃ እንደሚችል የታወቀ ነው! የአኗኗር ለውጥ ማድረጋችንም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም አካላችንና አእምሯችን በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው።
– በመንፈስ ጭንቀት የምትሠቃይ ከሆነ አካላዊና አእምሯዊ ጤንነትህን ለመጠበቅ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል፣ ገንቢ ምግብ ተመገብ፤ በቂ እንቅልፍ ተኛ፤ እንዲሁም አዘውትረህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጥሩ ስሜት እንዲሰማ፣ የተሻለ ጥንካሬ እንዲኖር፤ እንዲሁም ጥሩ እንቅልፍ መተኛት እንዲቻል የሚያደርጉ ኬሚካሎች በሰውነት ውስጥ እንዲመነጩ ያደርጋል። የመንፈስ ጭንቀት እንዲነሳ የሚያደርጉ ነገሮችንና በመንፈስ ጭንቀት ልንዋጥ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶችን ለይቶ ለማወቅ መሞከር፤ ከዚያም ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች አስቀድሞ ማሰብ ይገባል ።
– የሚሰማንን ስሜት ለምናምነው ሰው መናገር ያስፈልጋል። ከጎናችን ሆነው ሊረዱን የሚችሉ ቤተሰቦችና ጓደኞች ካሉ የመንፈስ ጭንቀትን በተሻለ ሁኔታ መቋቋም ይቻላል። የሚሰማን ጭንቀትም ሊቀንስልህ ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎትን ለማሟላት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረግ መቻሉ ለሕይወት ጥሩ አመለካከት እንዲኖረን ሊያደርግ ይችላል።
የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ሣጥን ማዘጋጀት
በመንፈስ ጭንቀት የምትሠቃይ ከሆነ ስሜትህን ለማከም “የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ሣጥን” አዘጋጅ፤ ይህም ሐሳብህንና ስሜትህን ለመቆጣጠር ይረዳሃል። በሣጥኑ ውስጥ በዚህ ገጽ ላይ የሚገኙትን ነገሮች ማካተት የምትችል ሲሆን ካስፈለገም ሌሎች ነገሮችንም መጨመር ይቻላል።
፨ በጭንቀት ስትዋጥ ልትደውልላቸው
የምትችላቸው ሰዎች ስልክ ቁጥር፣
፨ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህና ዘና እንድትል የሚያደርጉህ ዘፈኖች ወይም መዝሙሮች፣
፨ ደስ የሚሉ አባባሎችን እንዲሁም የሚያበረታቱ ሐሳቦችን የያዙ ጽሑፎች፣
፨ የሚወዱህን ሰዎች እንድታስታውስ የሚያደርጉህ ነገሮች፣ እና
፨ አዎንታዊ ሐሳቦችንና ያጋጠሙህን አስደሳች ነገሮች የምትጽፍበት ማስታወሻ ደብተር።
ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ?
- የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች ስሜታቸውን መግለጽ ሊከብዳቸው ወይም ያሉበትን ሁኔታ በትክክል ላይረዱ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል። እነዚህ ልጆች የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች ምን እንደሆኑ እንኳ ላያውቁ ይችላሉ።
- በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ልጆች ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድ ከአዋቂዎች የተለየ ነው፤ ስለሆነም የልጃችሁ ባሕርይ፣ አመጋገብ፣ ስሜት፣ የእንቅልፍ ሰዓት ወይም ማኅበራዊ ግንኙነት እንደተለወጠ ካስተዋላችሁ ለጉዳዩ ትኩረት ስጡ። በተለይ ደግሞ ለውጡ ለሳምንታት የዘለቀ ከሆነ ይበልጥ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
- ልጃችሁ ራስን ስለ ማጥፋት ሲናገር ከሰማችሁ ወይም ራሱን ለማጥፋት እንዳሰበ የሚያሳይ ፍንጭ ካያችሁ ጉዳዩን አቅልላችሁ አትመልከቱ።
- ልጃችሁ የመንፈስ ጭንቀት (አልፎ አልፎ የሚታይና ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ የሐዘን ስሜትን አይጨምርም) እንዳለበት ከተጠራጠራችሁ የሕክምና ባለሙያ ጋር በመሄድ እንዲመረመር አድርጉ።
- ልጃችሁ ሐኪም ያዘዘለትን መድኃኒት በአግባቡ እንዲወስድ አድርጉ፤ መድኃኒቱን እየወሰደም ምንም መሻሻል ካላሳየ ወይም መድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት ካስከተለበት ሐኪሙን አማክሩ።
- ቤተሰባችሁ የሚመገብበት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርግበት እንዲሁም የሚተኛበት ቋሚ ፕሮግራም እንዲኖረው አድርጉ።
- ከልጃችሁ ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ፤ እንዲሁም የመንፈስ ጭንቀት ያለበት በመሆኑ እንዳይሸማቀቅ እርዱት።
የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው ብቸኛ እንደሆነና እንደማይረባ፤ እንዲሁም ዋጋ ቢስ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። በመሆኑም ለልጃችሁ አዘውትራችሁ ፍቅራችሁን ግለጹለት።
ምንጭ፦ ከጤና ማህበራዊ ገጽ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2013