የእንስሳቱ ዘርፍ የዜጎችን የሥጋ፣የወተት፣ የወተት ተዋፅኦ እና ሌሎች ፍላጎቶችን በማሟላት የጎላ ሚና አላቸው። ይሄን ሚናቸውን ለማሳለጥና የተቀላጠፈ ለማድረግ እንደ ሀገር ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በምርምሩ ዘርፍ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል።በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርምር ዳይሬክተርና ተመራማሪ ዶክተር ፈቀደ ፈይሳ ፤ በእንስሳት ዝርያ እና ጤና ፣በበግ፣ በፍየል፣ በበሬ፣ በወተት ላም፣የሀገር ውስጥና የውጭ የእንስሳት ዝርያዎችን በማዳቀልና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማብዛት እንዲሁም በመኖ ዙሪያ የተሰሩት ሥራዎች በርካታ መሆናቸውን ነግረውናል።
ለዛሬው በተለይም በወተት ላም ምርምር ዙሪያ የተሰራውን ልናስቃኛችሁ ወድደናል። በሀገር ደረጃ የተሻሻሉ የወተት ላሞች ላይ የሚሰራው ሥራ አሁን ላይ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተውን የወተት እጥረት ለመቅረፍ ይረዳል ብለን በማመንም ነው ወደ ኢንስቲትዩቱ ያቀናነው።ታድያ ተመራማሪው ዶክተር ፈቀደ እንደሚናገሩት ከ50 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አርሶ አደሩ ምርምር ያፈራውን ዘመናዊ የወተት ከብት እርባታና ምርት አመራረት ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም እያደረገ መሆኑን ነግረውናል።
ኢንስቲትዩት በአጠቃላይ ሀገራዊ የእንስሳት ልማቱን ለማገዝ እያከናወነ ያለው ሦስቱን የኢንስቲትዩትን ተልዕኮዎች መሰረት አድርጎ ነው ።የኢንስቲትዩቱ አንደኛው ተልዕኮ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና ዕውቀቶችን ማመንጨት ነው።ከዚሁ ጋር በተያያዘም ምርትና ምርታማነትን፣ የምርት ጥራትንና የገበያ ተወዳዳሪነትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ዕውቀትና ቴክኖሎጂዎችን ማበልፀግ ላይ ያተኩራል።ሁለተኛው ተልዕኮው የሚመነጩ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅና በሕብረተሰቡ ዘንድ ፍላጎት መፍጠር ነው።ሦስተኛው ደግሞ ዘር አባዝቶ ማቅረብ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹የምርምር መስኩ ብዙ የሚቀሩና ያልተሰሩ የቤት ሥራዎች አሉበት›› ያሉት ተመራማሪው ዶክተር ፈቃደ ፈርጀ ብዙና ሰፋፊ የእንስሳት ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት የሚረዱ ምርምሮችን ማድረግ ቴክኖሎጂዎችንም ማፍለቅ ይጠበቅበታል ይላሉ። እንደ ተመራማሪው በዘርፉ አንኳር ተብለው የተለዩ ችግሮች እንኳን ቢጠቀሱ ብዙ ናቸው። ከነዚህ መካከል የእንስሳት ሀብቶቿን ለሕዝብ ጥቅም እንዲውሉ ለማድረግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ቢቀረፁም በአግባቡ አለመተግበራቸው፣የውጭ ምንዛሪ ምንጮች የሆኑ የግብርና ምርቶችን ሳያቀነባብሩ በጥሬያቸው ወደ ውጭ መላካቸው፣ በተለይም ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት በዓይነትና በጥራት አለመዘጋጀቱ፣ባልተቀነባበረ መልኩ የሚላኩትም ተገቢውን ዋጋ አለማግኘታቸው ፣የመኖ ዋጋ በየጊዜው መናር፣ የርቢ ላሞች፣ጊደሮች፣ጥጆች መታረዳቸው፣ ባልተገባ መንገድ የሚወልዱ ጊደሮች፣ ጥጆችና ላሞች ለእርድ እየዋሉ በመምጣታቸው ዘራቸው እየጠፋ መሆኑን ያነሳሉ።
እንዲሁም የሀገራችን እንስሳት አረባብ በዘመናዊና በሳይንሳዊ መንገድ አለመመራቱ ፣የእንስሳት ሀብትን ለእርሻ ሥራ ብቻ አጋዥ አድርጎ መቁጠርና ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አለመስራት፣ በኢትዮጵያ በተለይም በሦስቱ ዓመት የለውጥ ስርዓት ለሰብል የተሰጠው ትኩረት ለእንስሳት ሀብት አለመሰጠቱ፣በዘርፉ የተደረጉ በርካታ የምርምር ሥራዎችን መጠቀም አለመቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
‹‹ በአገሪቱ ያሉት የወተት ላሞች ምርታማነታቸው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች አነስተኛ ነበር›› የሚሉት ዶክተር ፈቀደ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞችን ማዳቀል በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ መንገድ ሳይጀመር ከአንድ እስከ ሁለት ሊትር ወተት ይሰጡ የነበሩ ላሞችን የማዳቀል ሥራው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ በቀን እስከ 15 ሊትር ወተት ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥራል። ሆኖም ይሄም ቢሆን ሀገራችን ላይ ካለው የተለያየ ምቹ ሁኔታ አንፃር አሁንም ቢሆን የወተት ላም ምርታማነት በሚፈለገው ደረጃ አደገ የሚያስብል አለመሆኑን ይጠቅሳሉ ። አሁን ላይ ያለውን የዜጎች የሀገር ውስጥ የወተት ፍላጎት መሟላት ያልተቻለውም በእነዚሁ ምክንያቶች ነው ።
ተመራማሪው ዶክተር ፈቀደ ይሄን ተግዳሮት ለመሻገር ወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርምር ባፈለቀው ቴክኖሎጂ እንዲታገዝና ውጤታማ እንዲሆን በኢንስቲትዩቱ የተከናወነው ሥራ ዘርፈ ብዙ መሆኑንም ይጠቁማሉ ። ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም በሰራቸው አያሌ የምርምር ሥራዎች በወተት ላም በኩል የተገኙ ውጤቶችም መኖራቸውን ይገልጻሉ ።
ምርታማ የወተት ላሞችን መጨመር አንዱ ተጠቃሽ ነው ። የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው ከብቶችን በሰው ሰራሽ መንገድ በማዳቀል የወተት ምርት በእጥፍ ለማሳደግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም ዶክተር ፈቀደ ያነሳሉ። የወተት ምርትና ምርታማነት በመጠኑም ቢሆን መጨመር የተቻለበት አለ ። ሰላሌ አካባቢ ያለው ተሞክሮ አርሶ አደሩ ከአንዲት ላም በቀን እስከ 40 ሊትር ወተት የሚሰጡ የተሻሻሉ የወተት ከብቶች ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል የምርምር ሥራ መሠራቱ ማሳያ መሆኑን ነው ተመራማሪው ዶክተር ፈቀደ የሚናገሩት።
የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የዳልጋ ከብት በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ መንገድ በማዳቀል ከፍተኛ መጠን ያለው የወተት ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን የማራባት ሥራ አሁንም በኢንስቲትዩቱ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የምርምር ተቋሞች የሚከናወንበትም ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ማላመድና ማፍለቅ ብዜትና የማስተዋወቅ ሥራዎችን እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ምርምሮችን የማስተባበርና ድጋፍ የመስጠት ሥራዎችን የሚያከናውነው በስሩ ካሉ 17 የምርምር ማዕከላት በተጨማሪም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከሌሎች ምርምር ተቋማት እና ከዓለም አቀፍ የምርምርና የትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ነው።ከነዚህ ጋር በመቀናጀት በነዚህ ሦስት የለውጥ ዓመታት ውስጥ የተሻለ ሥራ መሥራት ችሏል። ለአብነትም የለውጡ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሆነው በ2010 ዓ.ም በእንስሳት ምርምር ዘርፍም 21 ቴክኖሎጂዎችና 62 መረጃዎች ወጥተዋል። ከነዚህም መካከል የበግ ፣የፍየል፣ የግመልና የጋማ ከብት ምርትና ምርታማነትና ጥራትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎች የሚገኙበት ሲሆን የአገሪቱን የስጋና የወተት ምርት በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢም ለማሳደግ የሚረዱት ይጠቀሳሉ።
በእንስሳት ቴክኖሎጂ ብዜት 37 ኮርማዎች፣ 115 ጊደሮች፣ 231 በግና ፍየሎች፣ 849 ሺህ 750 ዓሳ ፣ 16ሺህ 500 የሐር ትል እንቁላሎች፣ 295 የንብ ቴክኖሎጂዎች፣ 251 ሺህ 540 ጫጩት ዶሮዎች፣ የዓሳ ግብርናን ሊያሳድጉ የሚችሉና የተፈጥሮ የውሃ አካላትና ትላልቅ ግድቦችን በመጠቀም ዓሳን በዘላቂነት ለማምረት የሚረዱ 11 መረጃዎች በምርምር የፈለቁበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ ። እነዚህም የዓሣ ተረፈ ምርት ብክነትን የሚቀንሱና የዓሣ መኖዎችን ለማዘጋጀት እንዲሁም የዓሣ ግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአግሮኢንዱስትሪውን ግብዓት ለማሳደግ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በተመሳሳይም ኢንስቲትዩቱ ሶስት የንብ መኖ ቴክኖሎጂን በማውጣት የንብ መኖ መጠንን ማሻሻል የሚያስችል ሥራ የሰራበት ሁኔታ አለ።
ኢንስቲትዩቱ በስሩ ካሉ የምርምር ማዕከላት እንዲሁም በትብብር ከሚሰሩ በሰባት የክልል ግብርና ምርምር ተቋማትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አማካኝነት በምርምር የወጡ ቴክኖሎጂዎችን በተለያየ መንገድ ለተጠቃሚው ሲያደርስ ቆይቷል።ቴክኖሎጂዎቹን የማስተዋወቅና ፍላጎት የመፍጠር ተግባርን የትኩረት አቅጣጫው በማድረግ እየሰራበት ይገኛል። በተለይ ፍላጎት የተፈጠረባቸውንና ተቀባይነት ያገኙትን ቴክኖሎጂዎች መነሻ ዘር ብዜት በማከናወን ለቴክኖሎጂ አባዥ ተቋማትና ተጠቃሚዎች እንዲደርስ ሲያደርግ ቆይቷል።
‹‹መኖ ለማንኛውም እንስሳት አስፈላጊ ነው። በተለይ የወተት ላም በእርግዝናዋ ጊዜ የምግብ ፍላጎት ባይኖራትም ለጥጃውም ለራስዋም ህልውና ሲባል በእርግዝናዋ ወቅት ከፊቱ የበለጠ መኖ እንዲቀርብላት ይደረጋል›› የሚሉት ተመራማሪው ዶክተር ፈቀደ ለወተት ላም ምርታማነት የመኖን አስፈላጊነትም ደጋግመው ይጠቅሳሉ።
በ2010 ዓ.ም በምርምር ማዕከላት በኩል ከተሰሩት ሥራዎች የመኖ ሰብል ርቢ ይጠቀሳል። 180 ሺህ የንብ መኖ ችግኞች፣ እንዲሁም በ26 ነጥብ 67 ሄክታር መሬት ላይ 201 ኩንታል 20 የሚሆኑ የመኖ ሰብል አራቢ፣ ቅድመ መስራችና መስራች ዘሮች የተባዙበት ሁኔታ መኖሩን ተመራማሪው ዶክተር ፈቀደ አብራርተዋል።
እንደ ተመራማሪው ዶክተር ፈቀደ የወተት አቅርቦት አዲስ አበባ ላይም ሆነ ሌሎች ከተሞች ላይ የሚያረካና ሌሎች ሀገሮች የደረሱበት ደረጃ የደረሰ አይደለም።ሆኖም ወደ ደጋው የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎችና ግለሰብ አርሶ አደሮች ላይ ለውጥ መታየት ችሏል። ከብቶቹን በደንብ የያዘ አርሶ አደር ሰላሌ ላይ ከአንድ ላም እስከ 40 ሊትር ወተት የሚገኝበት ሁኔታ ተፈጥራል። ይሁንና ከምርምሩ ጠቀሜታ አንፃር ቴክኖሎጂው የደረሳቸው አርሶ አደሮች ቢጠቀሙም ቁጥራቸው እጅግ ውሱን ነው።
ምክንያቱ ደግሞ አንዲት 12 ወይም 15 ሊትር ወተት የምትሰጥ ላም ካለች ይህችን ጊደር አባዝቶ ለተጠቃሚው በስፋት የሚያደርስ ተቋም አለመኖሩ ነው ።በውጪው ዓለም እነዚህ ተቋማት በስፋት አሉ።በመሆኑም በውጭው ዓለም በዓመት አንድ ሰው የሚያገኘው የወተት አቅርቦት 100 ሊትር ነው ።በእኛ ሀገር ግን 20 ሊትር ብቻ ነው የሚያገኘው።ይሄን 80 ሊትሩን ክፍተት ለመሙላት በቀን አምስት ሊትር ወተት የሚሰጡ ላሞች እንኳን መኖር አለባቸው።
በምርምር በሚፈልቁ ቴክኖሎጂዎች ተረድተን በቀን 15 ሊትር የሚሰጡ ሁለት ሚሊዮን የተሻሻሉ ላሞች ቢኖሩን ለእያንዳንዱ ዜጋ በዓመት መቶ ሊትር ወተት ማቅረብ የሚቻልበት አቅም ይኖረናል።እንደ ተመራማሪው ዶክተር ፈቀደ በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱን ጥቅም የምትሰጥ የወተት ላም ማግኘት ረጅም ጊዜና ቋሚ እንክብካቤ ይፈልጋል።ለእንስሳቱ የሚደረገው ክብካቤ ሳይቆራረጥ ነው። ለምሳሌ ፋብሪካ ግብዓቱ ከተቋረጠ ምርት እንደሚቆመው ሁሉ የወተት ላም መኖ፣ውሃ ፣ የጤና ክትትል ካልተደረገ እና ንጽህናው የተጠበቀ ቤት ውስጥ እንድትቀመጥ ካልተደረገ የሚፈለገውን ያክል ምርት ማግኘት አይቻልም። ወተት ለማምረት በቂ ግብዓቶች ያስፈልጋሉ። ለዚህ ነው ግብዓት ከተቋረጠ የወተት ምርቱ ወዲያውኑ ይቆማል የምንለው።
ተመራማሪው ከምርምር አንፃር የወተት ላሞችን ምርታማ ለማድረግ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ እየተሞከረ መገኘቱን ይናገራሉ።ሆኖም በምርምር ብቻ ምርታማ የወተት ላምን ማስፋት አይቻልም ባይ ናቸው። ምርጥ ዘር የሚባዛበትን መነሻ ሀሳብ በማቅረብና በምርምር ውጤቶች ብቻ ችግሮቹን መፍታትና መሻገር ስለማይቻል የግድ አባዝቶ የሚያቀርብ ተቋም መኖር ይኖርበታል። የገበያ ትስስሩና የህግ ማቀፉን ማበጀት ላይም ሥራ መሥራት ይገባል ሲሉ ምክረ ሀሳብ ያሉትን አስተያየት ሰጥተዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2013