በአካባቢያችንና በመንገዳችን ላይ የምግብና የተለያዩ ሸቀጦች፣ አልባሳትና ሌሎችም አገልግሎቶች እንደምናገኘውና እንደምንሸምተው ሁሉ ለግቢ፣ ለቤት ውስጥ፣ ለበረንዳ፣ለአጥር ማስዋቢያና ለምግብ የሚውሉ የአበባና የዛፍ ችግኞች በቅርበት እየቀረቡ ይገኛሉ።በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም አቅጣጫዎች የማግኘት ዕድሉ እየሰፋና ገበያውም እየተለመደ መጥቷል። ለመግዛት ሀሳብ የሌለው ሰው እንኳን በችግኞቹ አጠገብ ሲያልፍ የአበባው የአረንጓዴ ተክሉ ቀልብ ስለሚስብ ጎሮ ለማለት ያስገድዳሉ። በተለይም የአንዳንዶቹ የችግኝ አቀራረብ እጅግ ማራኪ ነው። በመሬት ላይ ከተደረደሩት በተጨማሪ በመትከያ ዕቃዎች በማንጠልጠያ ተሰቅለው የሚታዩት ትኩረትን ይስባሉ። በዚህ ወቅት ቤትዎንና ግቢዎን በአይነህሊናዎ በመሳል የሚስማማውን የችግኝ አይነት ይመርጣሉ። አቅራቢዎቹ ወይንም ነጋዴዎቹ ደግሞ ሲያግባቡ ቦታ እንኳን ባይኖርዎ በደጃፍዎ ላይ በዕቃ ለመትከል ፍላጎት ይቀሰቅሳሉ።
‹‹ግዴለም በዱቤም ቢሆን እንሰጣለን። ይምጡና ይውሰዱ›› ብለው ቀልጠፍ ብለው የሚቀርቡ ነጋዴዎች ሲያጋጥምዎ አያልፉም። ነጋዴዎቹ የመትከያ ዕቃውንም አብረው ያቀርብሎዎታል። በከተሞች አልፎ አልፎ በደጃፎቻቸው ላይ ጤና አዳምና አንዳንድ ለውበት የሚሆኑ የአበባ ዕፅዋት ካልሆነ በስተቀር በአረንጓዴ ማስዋብ የተለመደ አይደለም።አንዳንዶችም ችግሩን ከቦታ ጥበት ጋር ያያይዙታል።
ግቢያቸው መለስተኛ የአረንጓዴ መናፈሻ እስኪመስል ድረስ ለውበት፣ ለመድኃኒትና ለጥላ የሚውሉ ዕፅዋቶችን በመትከልና በመንከባከብ የሚመሰገኑ የከተማ ነዋሪዎችም አይዘነጉም።ግን ደግሞ አቅርቦት መኖሩ እንደሚያነሳሳ መረዳት የሚቻለው በየአካባቢው የዕፅዋት ችግኞች መቅረብ መጀመራቸው ብዙዎች እንዲተከሉ በማድረግ ላይ ይገኛል። የችግኝ አቅርቦት የሥራ ዕድል በመፍጠርም የሚያበረክተው አስተዋፆኦ ከፍ እያለ ነው። የችግኝ አቅርቦት የሥራ መስክ ሆኖ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ግምት ውስጥ አልገባም ነበር።
ችግኝ በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች በሚያገኙት ገቢ ቤተሰብ እያስተዳደሩ ማህበረሰቡ ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት እንዲሰጥ እያነሳሱ ነው። የራሳቸውን አሻራ በማስቀመጥ ላይ ናቸው። የምንገኝበት ወቅት ‹‹ኢትዮጵያን እናልብሳት›› በሚል መርሃ ግብር ሶስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ የሚካሄድበትና ክረምት በመሆኑ ትኩረት በመስጠት የችግኝ ገበያውንና ሸማቹን ለመቃኘት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ውስጥ በማህበር ተደራጅተው ችግኝ በማፍላትና ለገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኙት ጋር ጎራ በማለት ያለውን ሁኔታ ዳስሰናል።
ማህበራቱ ችግኞቻቸውን ለገበያ የሚያቀርቡበት ሥፍራ መንገድ ዳር ላይ በመሆኑ እግረኛውም ሆነ ባለመኪናው ሳይጎበኛቸው አያልፍም። እነርሱም ተሽቀዳድመው ገበያ ለመሳብ የሚያደርጉት ጥረት ራሳቸውንና ሸማቹንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ታዝቤያለሁ። በችግኝ ሽያጩ ላይ የተሰማሩት አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። በሥራው ላይ ሴቶች ቢኖሩም የወንዶቹ ቁጥር ከፍ ያለ ነው። ጠዋት ረፋድ ላይ በሥፍራው በደረስኩ ጊዜ ዋጋ በመጠየቅና በመግዛት ላይ የነበሩ ሸማቾችም አግኝቻለሁ። መኪናቸውን አቁመው በአንዱ የችግኝ መሸጫ ውስጥ ያገኘኋቸው መካኒሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ጅማ ከአንድ ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ለውበትና ለጥላ የሚሆን የዛፍ ችግኞችን ነበር የገዙት። የገዟቸው ችግኞች እርሳቸው የመረጧቸውንና ችግኝ ነጋዴዎቹ ይሻላል ያሏቸውን እንደ ሸውሸዌ፣ ግራቪያ የተባለ ዝርያ ያላቸው ሲሆኑ፣ አብዝተው የገዙት ግን የዛፍ ችግኞችን ነው። ቀደም ሲል በግቢያቸው ውስጥ የተከሏቸው የተለያዩ ዕፅዋቶች ቢኖሩም ተጨማሪ ችግኞችን መትከል አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል።
አቶ ዮሐንስ ግቢያቸውን በአረንጓዴ የማስዋብ ልምዱ ቢኖራቸውም አሁን እንደሀገር የተፈጠረው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ደግሞ የበለጠ አነቃቅቷቸዋል። ብዙዎች በዚህ ስሜት ውስጥ እንደሆኑም ይገምታሉ። በተግባር ለማሳየትም ከራሳቸው ግቢ በመጀመር በማጠናከር ላይ ይገኛሉ። ግቢያቸው ሰፊ በመሆኑ ለውበትና ለጥላ ከሚውሉ የዛፍ ችግኞች በተጨማሪ ለምግብ የሚውሉ አትክልቶችንም ለማልማት ቦታ አዘጋጅተዋል። አቶ ዮሐንስ ግቢያቸውን በተለያየ የዕፅዋት አይነትና በአትክልት በማስዋብ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት ሲያደርጉ እግረ መንገዳቸውንም የአረንጓዴ ልማት አስፈላጊነትን ለልጆቻቸው በማስተማር እነርሱም እንዲያስቀጥሉ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ልጆቻቸው ገና ታዳጊ ቢሆኑም በአቅማቸው የሚችሉትን በማድረግ እየተንከባከቡ ፍላጎቱ እንዲያድርባቸው መስመር እያስያዝዋቸው ነው።
የችግኝ ገበያው ዋጋ ተመጣጣኝ መሆኑን ይናገራሉ። እርሳቸው መርጠው የገዟቸው የአንድ ችግኝ ዋጋ አንድ መቶ ብር ነው። ችግኞቹ ከሚሰጡት ዘላቂ ጥቅም አንጻር ለአንድ ጊዜ ግዥ የሚወጣው ገንዘብ አይጎዳም የሚል ሀሳብ አላቸው። ሰዎች ብዙ ርቀት ሳይሄዱ በአካባቢያቸው ላይ ችግኝ ማግኘት መቻላቸው በራሱ በጊዜም በዋጋም ተጠቃሚ ማድረጉንና መነሳሳት ለመፍጠርም ጥሩ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ችግኝ ለሚገዙ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ ያገኘኋቸው አቶ ባዬ ተሰማ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ከያዙት መኪና ለመረዳት እንደቻልኩት ብዛት ያላቸው ችግኞች ለመጫን የመጡ ናቸው። የተወሰኑ ችግኞች በመኪና ላይ ተጭነው ተጨማሪ እየጠበቁ ነበር።
አቶ ባዬ በመግዛቱ ለምን እንዳልተሳተፉ በጠየኳቸው ጊዜ እንደነገሩኝ፤ ነዋሪነታቸው ከአዲስ አበባ ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ደቡብ ምዕራብ ሸዋ አስጎሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመሆኑ ችግኞችን በቅርበት ያገኛሉ። ሀገር በቀል ዛፎች፣ ለውበት የሚሆኑ ዕፅዋቶችና ለምግብ የሚውሉ አረንጓዴ ተክሎች በግቢያቸው ውስጥ መኖራቸውንና በየክረምቱ አዳዲስ ዝርያዎች በመትከል በልማቱ ሥራ ላይ ከራሳቸው ጀምረዋል። እርሳቸው ባሉበት አካባቢ ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በተሻለ ለአረንጓዴ ልማቱ ግንዛቤ መኖሩን በማስታወስ፣ አሁን የተፈጠረው ሀገራዊ ንቅናቄ ግን ከገጠር እስከ ከተማ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ኢትዮጵያንበደን ልማት ማልበስ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት አላቸው።
የዛፍ ችግኞችን ከመትከል ጎን ለጎን ለምግብ የሚሆኑ የጓሮ አትክልቶችን ማልማት እየተወደደ የመጣውን የጎመን፣ ቲማቲም፣ ድንች የመሳሰሉትን አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ዋጋ ለማውረድም ሆነ ትኩስ የሆነ አቅርቦት ለማግኘት እንደሚያግዝ ሀሳብ ሰጥተዋል።
ችግኝ በማፍላትና በመሸጥ ከተሰማሩትና ካነጋገርኳቸው መካከል ወይዘሮ ዙልፋ አስማራ አንዷ ስትሆን ‹‹መሐመድና ዋቢ ጓደኞቻቸው ችግኝ ማፍላትና መሸጥ››በሚል ስያሜ የሚጠራው ማህበር አባል ናት። በማህበሩ አራት ሴቶችና አራት ወንዶች ሆነው ነው የሚሰሩት። በሥራው ላይ አራት አመት ቆይተዋል። በተለይ ሴት አባላቱ ሥራውን መርጠው ነው በማህበሩ የተደራጁት። በግሏም ፍላጎቱ ስለነበራት ሥራው ላይ ከተሰማራች በኋላ በደስታ ነው የምትሰራው። ከምታገኘው ጥቅም ጎን ለጎን አረንጓዴ ሥፍራ ላይ መዋሏ የመንፈስ እርካታ አስገኝቶላታል። ችግኞች መንከባከቡን ከልጅ ማሳደግ ጋር በማያያዝ እየሰራች መሆኑን ትገልጻለች። ገበያውን ደግሞ ተለዋዋጭ ነው። ሲገኝ በቀን እስከ ሶስት ሺህ ብር ይሸጣል።ለሁለትና ሶስት ቀናት ገበያ የማይገኝበት ሁኔታ ያጋጥማል። ሆኖም ግን ገበያ የለውም በሚያስብል ደረጃ አይደለም። በተለይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ የችግኝ ሽያጭ ጨምሯል።
በተያዘው የክረምት ወቅት ከሌሎች የዕፅዋት ተክሎች የዛፍ ችግኞች የሚፈለግ በመሆኑ ገበያው የተሻለ ነው። በበጋ ወቅት ደግሞ ሰፊ ገበያ ያላቸው ለቤት ውስጥ ማስዋቢያ የሚውሉ የዕፅዋት አይነቶች ናቸው። ‹‹የችግኝ ዋጋ ውድ ነው የሚሉ ሰዎችም ያጋጥማሉ።ሰዎች ከገቢያቸው አንፃር ስለዋጋ ውድነት ቢያነሱ ልክ ናቸው። ግን ቢያንስ በአቅማቸው አያጡም። በመጎብኘት ያለውን ነባራዊ ሁኔታም ቢያዩ የተሻለ ነው›› የምትለው ወይዘሮ ዙልፋ የእነርሱ የችግኝ አቅርቦት በገንዘብ ቢሆንም ለአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ መዘንጋት የለበትም ስትል ትገልጻለች።
ችግኞችን መሸጥ ብቻ ሳይሆን ለደንበኞቻቸው ሙያዊ ምክር በመስጠትም እገዛ እንደሚያደርጉ የነገረችኝ ወይዘሮ ዙልፋ፣ በተለይ በችግኝ መትከያ ዕቃ ላይ የሚተክሉ ደንበኞች ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረግ ችግኙ የመድረቅና የተለያየ ጉዳት ደርሶበት አልፀድቅ ሲላቸው ለወቀሳ ስለሚመለሱ ቀድመው በማስገንዘብና ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ችግሩን ለመከላከል ጥረት እንደሚያደርጉ ነው ያጫወተችኝ። በተቻለ መጠንም ደንበኛውም እነርሱም እኩል ደስ ብሎአቸው ተጠቃሚ ቢሆኑ ጥቅሙ የጋራ ነው። ለአረንጓዴ አሻራ የሚኖረውም አስተዋጽኦ ከፍ ይላል።
የማህበር አባላትም ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት መሠረታዊ ሥልጠና በማግኘታቸው ድጋፍ ለማድረግ እንደማይቸገሩ ነው የገለጸችልኝ። ገበያ ለማግኘት ስለሚያደርጉት ጥረትም እንደነገረችኝ፤ ገዥ ሲመጣ ብቻ ሳይሆን አባላቱ በተለያየ ቦታ በመዟዟርና በተለያየ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ በመሳተፍ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት ያደርጋሉ።
ሌላው በዚያው ሥፍራ የሚገኙት ‹‹ጊፍትና ተባረክ ችግኝ ማፍላትና መሸጥ›› ማህበር አባላት ከሆኑት መካከልም አቶ ተባረክ ኑሩ፣ ነጅቡ ዐረብና ሰባዐረብ መሐመድ፤ ዊር፣ ጋራቪሊያ፣ወተርብሩሽ፣ ሚም፣ ኦሜድላ፣ ፊከስ የተባሉ፣ ከፍራፍሬ ደግሞ ማንጎ፣ አቡካዶ፣ ወይንና ሌሎችንም የዕፅዋት ተክሎች ነው ይዘው የቀረቡት። ከያዟቸው የተለያዩ የዕፅዋት ችግኞች መካከል ደግሞ በዚህ ወቅት ሰፊ ገበያ እያገኙ ያሉት ለዛፍ የሚሆኑና የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው። ለበረንዳና ለቤት ውስጥ የሚሆኑት ተክሎች የሚፈለጉት በበጋ ወቅት ነው። በዋጋም ተመጣጣኝ እንደሆነ አባላቱ ይናገራሉ።
እነርሱ እንዳሉት አነስተኛው ዋጋ 40 ብር ነው። ከፍተኛው ደግሞ እስከ ሁለት ሺ ብር የሚያወጣ ሲሆን፣ ኪከስ፣ አቡካሪያ የተባሉ የዛፍ ችግኝ ተክሎች ናቸው። ዋጋ መጠየቅና ማየት የሚወዱ ሰዎች መኖራቸውንና አንዳንዶችም ግቢ ሲኖራቸው እንደሚገዙና አስተያየት እንደሚሰጧቸውም ነግረውኛል።
አባላቱ በሥራው ላይ ሥለሚያጋጥማቸው ችግርና ከመንግሥት ስለሚፈልጉት ድጋፍም እንደገለጹልኝ፣ ለችግኞቹ እንክብካቤ ለማድረግ ሰፊ ቦታ ያስፈልጋል። በተለይ በዚህ የክረምት ወቅት ለውበት የሚሆኑ ዕፅዋቶች በበረዶ ሲመቱ ይበላሻሉ። ሰሞኑንም በጣለው በረዶ ብዙ ችግኞች ከጥቅም ውጭ ሆነውባቸዋል። በበጋ ደግሞ በቂ ውሃ ያስፈልጋል። ውሃ በግዥ ስለሚቀርብ ዕፅዋቶቹ የሚፈልጉትን መጠን እያገኙ አይደለም። ማዳበሪያና አፈር ለመቀየርም እንዲሁ በቂ ቦታ ባለመኖሩ በሚፈልጉት ልክ ለመጠቀም ተቸግረዋል። ችግኞችን ውሃ ለማጠጣት በአካባቢው ውሃ ባለመኖሩም ተቸግረዋል። ለውሃ ግዥ የሚያወጡት ገንዘብም ትርፋቸውን እየወሰደባቸው በመሆኑ ተማርረዋል። ማህበራቸው ሽያጩንም በደረሰኝ የማከናወን ፍላጎት አላቸው። ለሥራ የተሰጣቸው ቦታ ጊዜያዊ ከመሆን ጋር ተያይዞ ከሚመለከተው አካል ምላሽ ማግኘት አልቻሉም። እነዚህ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ቢያገኙ ሥራው እጅግ በጣም ጥሩ እንደሆነና ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ።
ወደ ሥራው ከገቡት የማህበሩ አባላት አንዳንዶቹ በቅጥር በሥራው ላይ የቆዩ ሲሆኑ፣አንዳንዶቹም ለሥራው አዲስ ናቸው። አልባሌ ቦታ ከመዋል ለሀገር በሚጠቅም ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ወደውታል። ሥራቸው ለአረንጓዴ አሻራ የማነሳሳት ዓላማ ስላለው እንዲህ ባለው ሀገርን በሚጠቅም ሥራ ላይ መሰማራታቸውን እንደበጎ ወስደውታል።አስተያየታቸውን ከሰጡኝ እንደተረዳሁት አንዳንዶቹ የስልጠና ክፍሎችና ብድር የተመቻቸላቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ሁለቱንም ያላገኙ ናቸው። ሁሉም ግን የመስሪያና የችግኝ ማፍያ ቦታ ተመቻችቶላቸዋል። በዚህ መልኩ እየሰሩ ተጠቃሚ ቢሆኑም በአካባቢው ግንባታ ስለሚከናወን ቦታው ይወሰዳል የሚል ስጋትም አድሮባቸዋል።በአጠቃላይ ክትትልና ድጋፍ እንደሚፈልግ ነው ከአስተያየት ሰጭዎቹ የተረዳሁት።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በማህበር ተደራጅተው በችግኝ ማፍላትና ገበያ ላይ የተሰማሩት አባላት ክፍለ ከተማው አካባቢና ጥበቃ አረንጓዴ ልማት ክትትልና ድጋፍ ይደረግላቸዋል። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የአረንጓዴና ደን ቦታ አያያዝ ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ ወይዘሮ ይርጋለም ታምሩ በክፍላቸው እየተከናወነ ስላለው ሥራ እንደገለጹት፣ በማህበር በማደራጀት የሥራ ዕድል እየፈጠረ ካለው ከወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ጋር በቅንጅት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ ማህበራቱም ለችግኝ ማፍላቱ ሥራ ምቹ እንዲሆንላቸው የወንዝ ዳር፣ እንዲሁም ለመሸጫ የሚሆን ሥፍራ በመሥጠት እያገዟቸው ይገኛል። የሚሰጣቸው ቦታም እንደ አባላቶቻቸው ብዛት የሚወሰን ሲሆን፣ እስከ 230 ካሬ ሜትር ይሰጣቸዋል። ማህበራቱ ለገበያ የሚያቀርቧቸው ችግኞች በዋጋ ውድ እንደሆነ ከሸማቹ የሚሰማውን መሠረት በማድረግ ማህበራቱን ለማነጋገር በተደረገው ጥረት ማህበራቱ እነርሱ በሚያዋጣቸው ማቅረብ ካልቻሉ ኪሳራ ላይ እንደሚወድቁ ነው ምላሻቸው። በአሁኑ ጊዜ በወረዳው በችግኝ ማፍላትና መሸጥ ሥራ ላይ የተሰማሩት ማህበራት ብዛት አሥራ አንድ ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ማህበራት ከአምስት እስከ ስድስት አባላቶች አሏቸው። ከማህበራቱ የሚነሱ ችግሮች እየፈቱና ተናብቦ መሥራት ከተቻለ የዕፅዋት ችግኝ አቅርቦቱ ለተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ህብረተሰቡ ለአረንጓዴ ልማት ያለው ፍላጎት እንዲጨምርና እንዲነቃቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2013