ሰሞኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ባለፉት ጊዜያት ከክልሉ ሕዝብ እና በተለያዩ ቦታዎች ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል።በዚህ ውይይት መነሻ በተሰበሰቡ ተጨባጭ ሀሳቦች መሰረት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለክልሉ ህዝብ ተጠቃሚነት ሲባል በጥንቃቄ በለያቸው ምክያቶች የተኩስ አቁም እንዲደረግ የፌደራል መንግስቱን በይፋ ጠይቀዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከሳምንት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ፣ በአሸባሪው የሕወሓት የጥፋት ኃይል ምክንያት የተፈጠረውን የትግራይን ችግር ለመፍታት ባቀረቡት ሐሳብ፣ የአሸባሪ ቡድኑ ዋና ዓላማ ሕዝቡን የጦርነት ጋሻ በማድረግ ለዘመናት በህዝቡ ውስጥ በዘረጋው የአፈና መዋቅር የሰላምና መረጋጋት ሥራውን ማደናቀፍ እንደሆነ አመልክተዋል።
የአሸባሪው ኃይል የክልሉን ህዝብ እንደመያዣ በማድረግ ህዝቡ በዘላቂነት እንዲራብ እና ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይደርሰው እንቅፋት መፍጠሩን በደብዳቤያቸው አመልክተዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በለያቸው 10 ምክንያቶች በትግራይና በመላው ሰላም ወዳድ ሕዝብ ስም የፌዴራል መንግሥቱ የተኩስ አቁም እንዲያደርግ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ የፌደራል መንግስቱም ለህዝብ ጥቅም ሲባል ገበሬው ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲከውን ትልቅ ውሳኔ ወስኗል።
በዋናነት ግን ይህ የመንግስት ትልቅ ህዝባዊነት የተላበሰ ውሳኔን በቅጡ የተረዱ የህወሓት ርዝራዥ አካላት ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ፤ በዚህም የጥፋት ኃይሉን የተከተሉ እንደገና ለማሰብና ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ ይታመናል።ይህ መንግስት ያስቀመጠው ውሳኔ ያለቅድመ ሁኔታ በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም የክልሉ ህዝብም ቢሆን በሚገባ ተገንዝቦ እድሉን በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባ የተለያዩ የአለም አገራት እና አለም አቀፍ ተቋማት የደገፉት ጉዳይ ነው።
ይሁን እንጂ የጁንታው ርዝራዥ ትናንት በተሟላ ትጥቅና ትዕቢት በሞከረው ጦርነት በ15 ቀናት ውስጥ እጅጉን እንዳይነሳ ሆኖ መመታቱን ማንም የሚዘነጋው ሀቅ አይደለም። እናም ይህ የመንግስት የተኩስ አቁም ውሳኔ ለጁንታው ርዝራዦች የሚሰጠው እድል ወደ ሰላም እንዲመጡ ማሰላሰያ ጊዜ እንጂ በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ‹‹አሸንፊያለሁ›› ብሎ ለዳግም ጥፋት ህዝብን የሚያታልልበት አለመሆኑ በአፅንኦት የተገለፀ ጉዳይ ነው።ምክንያቱም ይህ የተኩስ አቁም ከዚህ ዓላማ ውጭ ሆኖ ከተገኘ ስምምነቱ ፈርሶ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እወስዳለሁ ሲል ተናግሯል።
ቡድኑ እድሉን በማባከን እና በተሳሳተ ስሌት ህዝብን በተራ ‹‹የአአሸንፊያለሁ›› ወሬ ህዝቡን በዳንኪራ እና ፈንጠዝያ ውስጥ መክተት አይገባም፤ ህዝቡም ይህን በጉያው የያዘውን እሳት በቅጡ ማጥፋት እንጂ ለዳግም እልቂት እና ረሀብ ራሱን መስዋዕት ሊያደርግ መዘጋጀት የለበትም።
ይህን የመንግስት ቅን ውሳኔ በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ ዛሬም እንደ ትናንቱ ህዝብን እየማገዱ መጓዝ ባህሉ ያደረገው የጁንታው ርዝራዥ መቀሌን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የሚስተዋለው ዳንኪራና ፈንጠዝያ ከአንድ ቀን ሊያልፍ አልቻለም።ምክንያቱም በበቀል እና በትዕቢት የተሞላው የዚህ ርዝራዥ ቡድን አባላት የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈጠሩ ግድያ መፈፀም መጀመራቸው እየተነገረ ይገኛል።ለአብነትም አሲምባ የሚባል በክልሉ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ‹‹በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች የከፋ ግድያ እየተፈፀመ ነው›› ሲል መግለጫ ሰጥቷል።ይህ ደግሞ የጁንታውን ቡድን ‹‹አይጥ መንኩሳ አመሏን አትረሳ›› ሆኖ በገሀድ እየተስተዋለ ይገኛል።
የትግራይ ህዝብ ከትናንት በተለየ መልኩ ሊያጤናቸው የሚገቡ የቤት ስራዎች አሉበት።በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግስት መከላከያ ሰራዊቱ ከክልሉ እንዲወጣ የወሰነው ውሳኔ መሰረታዊ ምክንያት በጦርነት ስለተሸነፈ አለመሆኑን በተለይ የክልሉ ህዝብ ከመገንዘብ ያለፈ ሊያጤናቸው የሚገቡ ጉዳዮች ከፊቱ ተደንቅረዋል።ይብዛም ይነስ ርዝራዡም ሆነ የጁንታው አንዳንድ አባላት ክልሉን ተረክቧል።በአንጻሩ የጁንታው ርዝራዥ ከተራ ዳንኪራው ባለፈ የሚጠበቁ ፈጣን እና ወሳኝ ጉዳዮችን ሊያቀርብ የሚችልበት አደረጃጀትም ሆነ አቅም አለው ወይ? የሚለው ጥያቄ አሁንም ለገፈት ቀማሹ የትግራይ ህዝብ የተተወ ጥያቄ እንጂ ጁንታው ትናንትም አልመለሰው።ይህ በግልፅ ህዝቡ ልብ ሊለው የሚገባ ጉዳይ ነው።
ይህ ጊዜ ለትግራይ ህዝብ ከትናንት በባሰና በከፋ ሁኔታ የጁንታው ርዝራዥ ቡድን ዋጋ ሊያስከፍለው የሚችልበት ወቅት እንደሆነ ለማንም ሊሰወር የሚገባ አይደለም።ይህ ቡድን በአሁኑ ወቅት ለአንድ ቀንም ሆነ ለአንድ ሳምንት ክልሉን አሰተዳድራለሁ በሚል መዳከሩ አይቀርም።ይህ ግን በብዙ ምክንያቶች ዛሬም ህዝብን እንጂ ቡድኑን የሚያስከፍለው ዋጋ አይኖርም።
ጣት የማይሞሉት እነዚህ የቡድኑ ርዝራዦች መላው ክልሉን በተሟላ መልኩ ማስተዳደር በማይችሉበት በዚህ ወቅት የተሟላ አስተዳደራዊ ስራዎች ስለማይሰሩ ግድያውና ዝርፊያው ከዕለት ዕለት እየተባባሰ ይገኛል።ሌላው ትልቁ ጉዳይ ግን በአሁኑ ወቅት ቡድኑን የሚደግፉ እና በሚጠሉ መካከል ያለው የጠነከረ ልዩነት ቡድኑ መቀሌን ከረገጠበት ቀን ጀምሮ ግድያው በርትቷል።ይህን ቅሬታ በአግባቡ ለማስተካከል ደግሞ ቡድኑ እንኳን ዛሬ ትናንትም አልሆነለት።
ጁንታው በተሟላ ቁመና በነበረበት ወቅት ሳይቀር በክልሉ የነበረው ተረጂ ቁጥር ወደ ሁለት ሚሊየን የሚጠጋ ነበር።በአሁኑ ወቅት የተረጂዎች ቁጥር በሁለትና ሶስት እጥፍ ጨምሯል።ይህም እስከ ትናንት ድረስ የፌደራል መንግስቱ ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ጉሮሮ ነጥቆ የትግራይ ህዝብን እና ክልሉን ለማጠናከር ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ አስወጥቶታል።እናስ ይህን ሁሉ ክፍተት የመሙላት አቅሙ እና ወኔ የሌለው የጁንታው ርዝራዥ ዛሬም በህዝብ ህይወት እንዲቀልድ የትግራይ ህዝብ የሚፈቅድበት አሊያም ሁለንተናዊ ፈተና የሚፈተንበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።
እነዚህ ሁሉ እንቆቅልሾች ቡድኑ እግሩ መቀሌን ከረገጠበት ቀን ጀምሮ እየተስተዋለ ያለ ጉዳይ ነው። በመሆኑም በክልሉ ያለው ችግር ተጀመረ እንጂ አልተቋጨም።ሁኔታውን በሚገባ ለተገነዘበው አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በጁንታው ርዝራዥ የሚሞላ ሳይሆን ሁኔታው የሚባባስ እና ህዝቡን የከፋ ዋጋ የሚያስከፍለው ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች እየወጡ ይገኛሉ።
በመሆኑም የክልሉ ህዝብ በሚገባ ሊያገናዝባቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች አሉበት።የትናንቱን ከዛሬ በማወዳደር፤ ለክልሉ ህዝብ ማን ምን ያህል ዋጋ ከፈለ? የሚሉትን እና ሌሎች ቀጣይ ጥያቄዎች ለህልውናው ሲል የራሱን ውሳኔ እንደሚወስን ይጠበቃል።ህዝቡ የፌደራል መንግስቱ ለትግራይ ህዝብ ሲያደርጋቸው የነበሩ ጥቅሞችን መዘንጋት የለበትም።ይህ መንግስት ምን ያህል ዋጋ እየከፈለ እንደነበር ሊዘነጋው አይገባም።ይህ ጥቅም ነገ በማን ይሞላ ይሆን? የሚለው ጥያቄ በውል የሚመልሰውን አካል ዛሬ ማግኘት ቢያዳግትም።በእርግጥ ህዝብ በመንግስት በኩል የተሰጠን የማሰላሰያ ጊዜ በከንቱ በማበላሸት ራሱን ለቡድኑ ጥፋት የሚጠቀምበት እንደማይሆን የብዙዎች እምነት ነው።
እናት ከመሳለሚያ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም