
ቤት ከሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ቢሆንም ይህ ፍላጎት ቅንጦት ሆኖባቸው እንደናፈቁት በኪራይ ቤትና በጎዳና ላይ የሚኖሩ ብዙ ናቸው። በአለም ላይ ከተንሰራፉ ዋና ዋና ችግሮች መካከልም አንዱ ይኸው የመኖሪያ ቤት እጦት በመሆኑ በርካቶች የኔ የሚሉት ቤት ሳይኖራቸው ህይወታቸውን በድህነት ገፍተው ወደማይቀረው ዓለም ያሸልባሉ።
የበርካታ ሀገራት መሪዎች ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ለህዝቦቻቸው ቃል ከሚገቧቸው ጉዳዮች ውስጥም አንዱ ይኸው የፈረደበት የመኖሪያ ቤትን ለዜጎች የማዳረስ ዲስኩር ሲሆን ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ ግን በገቡት ቃል ልክ የዜጎችን መሰረታዊ የቤት ፍላጎት ጥያቄ ሲመልሱ አይታዩም ወይም ደግሞ በበቂ ሁኔታ ፍላጎታቸውን አያረኩም።
በኢትዮጵያም በከተሞች አካባቢ ከግዜ ወደ ግዜ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን ነዋሪ የቤት ፍላጎት ለመመለስ በተለያዩ ጊዜያት ጥረት ቢደረገም ጠብ የሚል ነገር እስካሁን አልመጣም። በግልም ሆነ በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶችም በአብዛኛው የሰውን ኪስ ያገናዘቡ ባለመሆናቸው ከነዚህ የቤት ልማት ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ሲሆን አይታይም።
በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በየአመቱ የግንባታ ወጪያቸው ስለሚጨምር ባለዕድለኛው ቤቱን የሚገዛበት ዋጋም አብሮ ያሻቅባል። በዚህም የቤቱን ቅድመ ክፍያ በመክፈልና ቀሪውን ደግሞ በወለድ በየወሩ በመክፈል ቤቱን የራሳቸው ለማድረግ በርካቶች ሲቸገሩ ይስተዋላል።
በተመሳሳይ ከመንግስት በተጨማሪ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በዋናነት መካከለኛና ከዛ በላይ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ለመጥቀም የተለያዩ የግል የመኖሪያ ቤት አልሚዎች ቢኖሩም ዋጋቸው ግን የሚቀመስ ሆኖ አልተገኘም። በየጊዜውም ገንብተው በሚያስረክቧቸው ቤቶችና አፓርትመንቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ ይስተዋላል።
ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ይዞት በወጣው መረጃ መሰረት ደግሞ ቻይና እንደራሷ ግዛት በምትቆጥራትና ራስ ገዝ በሆነችው ሆንግ ኮንግ የግል መኖሪያ ቤት ዋጋ ጣራ መንካቱን አስታውቋል። በዚህች የአለም ግዙፍ ኢኮኖሚ በሚንቀሳቀስባትና ከሰባት ሚሊዮን ህዝብ በላይ በሚኖርባት ከተማ የግል መኖሪያ ቤት ዋጋ ለተከታታይ አምስት ወራት የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ዘገባው አመልክቷል።
ዘገባው በሆንግ ኮንግ የግል መኖሪያ ቤት ዋጋ በአለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ውድና ለመግዛት የማይቀመስ መሆኑን የተናገረ ሲሆን ሰኞ እለት የወጡት የሃገሪቱ የተረጋገጡ መረጃዎች ደግሞ የመኖሪያ ቤት ዋጋው ለአምስት ተከታታይ ወራት ጭማሬ ማሳየቱን መግለፃቸውን ጠቁሟል።
በእነዚሁ መረጃዎች መሰረት በሚያዚያ ወር ከነበረው የ ዜሮ ነጥብ አራት ከመቶ ጋር ሲወዳደር ባለፈው ወር ብቻ የመኖሪያ ቤት ዋጋ በዜሮ ነጥብ ስድስት በመቶ ከፍ ማለቱንም ዘገባው ጠቅሷል። ይህ አሃዝ በዚህ ዓመት እስከ አሁን ድረስ ከሶስት ነጥብ ስድስት ከመቶ መሻገሩንና ይህም እ.ኤ.አ በ2019 ከነበረው ዜሮ ነጥብ ስምንት ከመቶ በላይ የሆነና ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ መሆኑንም አስታውቋል። የንብረት አማካሪዎች በሶሰተኛው ሩብ ዓመት የግል መኖሪያ ቤት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ሪከርዱን እንደሚሰብርና አሃዙ በሁለተኛው ግማሽ አመት ወደ አምስት ከመቶ እንደሚጠጋም በዘገባው ተመላክቷል።
በዚህ ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ላይ በሆንግኮንግ የድንበር ተሻጋሪ ጉዞዎች እንደገና በመጀመራቸው የዋና ቦታ ገዢዎች በአካባቢው ንብረት ላይ ተጨማሪ ሽያጭን ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም በዘገባው ተጠቅሷል። የንብረት ገበያው በፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱም የቤት ገንቢዎች አጠቃላይ የግብይቱን መጠን ከፍ እያደረጉ የአዳዲስ ጅምር ሥራዎችን በፍጥነት እያፋጠኑ እንደሚገኙም በዘገባው ተገልጿል።
በመጀመሪያው አመት አጋማሽ አጠቃላይ የቤት ግብይቶች ከ2012 ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እንደጨመረ ዘገባው የተናገረ ሲሆን የኒው ወርልድ ልማት የቤቶች ፕሮጀክት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በአዲስ የሆንግኮንግ ግዛቶች ውስጥ ከ30 ሺህ 600 በላይ የሚሆኑ ገዢዎች ፍላጎት ያላቸው ምዝገባዎችን መቀበሉንም ለአብነት አንስቷል። ይህም በሆንግ ኮንግ ውስጥ ከመቼውም ጊዜ የላቀ መሆኑን ተጠቁሟል።
በፕሮጀክቱ ውስጥ ባለ አራት መኝታ ቤት በአራት ካሬ ሜትር ዋጋ በአራት ሚሊዮን 508 ሺ ሰማኒያ ስድስት የአሜሪካን ዶላር በጨረታ መሸጡንና ይህም በከተማ ዳር አካባቢ እስካሁን ድረስ ከተሸጡ ቤቶች ውስጥ ከፍተኛው መሆኑን ዘገባው ገልጿል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2013