ክረምትና ቅኔዎቻችን፤
ሐምሌ፣ ነሐሴና ጳጉሚት ፊታቸውን አጨፍግገው ሊቀበሉን ዳር ዳር በሚሉበት በዚህ የሰኔ ወር መሰናበቻ ላይ ቆመን ስለ ብርሃናማው መስከረም መቀኘት አግባብ ባይመስልም አሻግሮ መመልከቱ የሰብዓዊ ባህርያችን አንዱ መገለጫ ስለሆነ ነገን ብንናፍቅ አይፈረድብንም። ስለዚህም እንቀጥል፤
ዝናቡም አለፈ፤ ጎርፉም ነዳ፣ ነዳ፣
ምን ቀረኝ ከእንግዲህ ቤቴን ላጸዳዳ።
አለች አሉ ስም የለሽ አዝማሪያችን። ማንነቷ ባይገለጥልንም፣ መቼ፣ የትና በምን ሁኔታ ላይ ሆና ይህንን ውብ ቅኔ እንደተቀኘች በቂ ማስረጃ ባይኖረንም የግጥሟ መልእክት ግን በእጅጉ አስተማሪ ሆኖልናልና አረሖኛችን ሆይ አልፈሽ ከሆነ ነፍስ ይማር! በሕይወት ካለሽም ክብረት ይስጥልን። አንድ ተጨማሪ ቅኔ እናክል፤
”እነሆ ክረምቱ አለፈ፤ ዝናቡም አልፎ ሄደ፣
አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣
የዜማም ጊዜ ደረሰ፣
የርግቦች ዝማሬ በምድራችን ላይ ተሰማ፣
በለሱ ማፍራት ጀምሯል፣
የወይን ተክሉም አብቧል፣
የአበባውም ሽታ ምድራችንን አውዶታል።‘
የዚህኛው ድንቅ ባለቅኔ ባለቤት ደግሞ ንጉሥ ሰሎሞን ነው። የመኃልየ መኃልዩ ደራሲ። ንጉሥ ሆይ ስለ ጥበባዊ አስተምህሮህ ምሥጋና ይድረስህ ።
ክረምት በጥሬ ትርጉሙ የዝናብና የልምላሜ ወራት ይሁን እንጂ በተለዋጭ የዘይቤ ስልት የሚጎላመሰው ግን በመልካም ፍቺው አይደለም። ጎርፍም እንደዚያው። የዛሬን አያድርገውና ክረምት ሲገባ ወንዞች ሁሉ ሲለሚሞሉ ወዳጅ ከወዳጁ በቀላሉ ስለማይገናኝ ወራቱ የሚመስለው በጨለማ ነው። “አባይም ቢሞላ፤ ዞረሽ ነይ በሌላ” እንዳለው ዜመኛ የወንዝ ሙላት ያዟዙራል፤ ሲበረታም ያቆራርጣል። ጎርፍም እንዲሁ ውክልናው ለመከራና ለችግር ነው። በአንጻሩም የመስከረም ወር የተስፋ ንጋት ተምሳሌት ተደርጎ ብዙ ተቀኝቶለታል፤ ብዙም ተዘምሮለታል።
መስከረም ሲጠባ፤ አደይ ሲፈነዳ፣
አንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ።
የተባለውን ሕዝባዊ ግጥም ማስታወሴ ብቻ ይበቃል።
የፖለቲካችን ክረምት፣ ጎርፍና መስከረም፤
የሀገራችን ፖለቲካ የተሻገራቸው የክረምትና የጎርፍ ወራት ጥለውብን ያለፉት ጠባሳዎች እንዲህ በቀላሉ የሚረሱ አይደሉም። ዛሬም ቢሆን ጎርፉና ክረምቱ ያስከተለብን አንዳንዱ ሀገራዊ የችግራችን ጠባሳ ሙሉ ለሙሉ ተፈውሶ ጠግጓል ማለት አይቻልም። እንዲያውም የሚቆጠቁጠው ቁስላችን እንደ አዲስ ደዌ ሲያመረቅዝና ሲያገረሽ እያስተዋልን ከመሳቀቅ ገና ነጻ ወጥተን አልተፈወስንም። በአጭሩ የፖለቲካው እባጭ ገና ተንፍሶ የወጣለት አይመስልም።
ኢኮኖሚያችንም ከልምሻው አገግሞ “የዕለት ማዕዳችንን ሳንሳቀቅ እንድንቆርስ” አላገዘንም። እንደ ቀትር እባብ እየተቅበዘበዙ በክፉ መርዛቸው ሀገሪቱን ሊያውኩ የሚሞክሩት አሸባሪ ቡድኖችም ተገቢው በትር ቢያርፍባቸውም ጭንቅላታቸው ስላልተመታ በየጊዜው አፈር እየላሱ በመነሳት ሲንደፋደፉ እያስተዋልን ነው። በማያገባቸው እየገቡ በሀገራዊ ሁለንተናዊ ጉዳያችን የሚፈተፍቱትም እጃቸውን በማስረዘም ሰላማችንን ከማወክ አልታቀቡም። እንዲያው በመደምሳሳው የችግሮቻችን ክረምቶችና ጎርፎች በሙሉ ተጠራርገውና አልፈው በደስታና ሃሴት፤
ክረምት አልፎ በጋ፤ መስከረም ሲጠባ፣
አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ሲተካ፣
በአበቦች መዓዛ ረክቷል ልባችሁ፣
ሕዝቦች ሁሉ በጣም እንኳን ደስ አላችሁ።
በማለት በዕልልታ ለማሸብሸብ የተጣቡን የችግር መዥገሮች በቀላሉ ተራግፈው አላለቁም። ነገን ተስፋ እያደረግን ያለነው የዛሬዎቹ ጨፍጋጋ ችግሮቻችን በሙሉ እንደሚቃለሉ ተስፋ በማድረግ እንጂ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነውልን “እፎይ” ለማለት ገና ትንፋሽ አልሰበሰብንም። ዳሩ ተስፋ አንሰንቅም ማለትስ ይቻላል። አይመስለኝም። ምክንያቱም፤ “የሰው ልጅ ያለምግብ ለአርባ ቀናት፣ ያለውሃ ለሦስት ቀናት፣ ያለ አየር ለስምንት ደቂቃ በአማካይ መኖር እንደሚቻል ተመራመርን ያሉ ጠቢባን የጽሑፍ ማስረጃ አቆይተውልናል። “ያለ ተስፋ ግን ለአንድ ሰከንድ እንኳን በፍጹም ለመኖር እንደማይቻልም” አስረግጠው ነግረውናል። ተመራማሪዎቹ ስለነገሩን ብቻም ሳይሆን የሰው ልጅ ያለ ተስፋ መኖር እንደማይችል ተፈጥሮ ራሷ እቅጩን አሳውቃናለች።
ሀገሬ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሻገረቻቸው ክረምቶችና ጎርፎች ብዛታቸው እንዲህና እንዲህ ተብለው የሚዘረዘሩ አይደሉም። የእንግዴ ልጆች ውጋትና የውጭ ጠላቶች ሴራ በትብብርና በመናበብ ቀስፈው እንዳስማጧት መች እንዘነጋለን። በወጀብና በአውሎ ነፋስ በሚመሰሉ የውስጥና የውጭ ችግሮች በርብርብ ሲንጡን መባጀታቸውንስ መች እንረሳዋለን። የንጹሐን ሞት፣ የዜጎች መፈናቀል፣ የግለሰቦችና የሀገር ሀብት ዘረፋና ውድመት በየተራ ተፈራርቀውብናል። ፖለቲካው ከርሮ ፖለቲከኞችም ጦዘዋል። በእነዚህ ሁሉ ወቅት ወለድ ሕመሞች የተሰቃየችው ሀገሬ ፊቷ ከስሎና በማዲያት ተዥጎርጉሮ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ!” እያለች በመቃተት እንባዋን እንደ ራሄል ወደ ፈጣሪዋ የረጨችባቸው ጊዜያት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።
አንዱ ሀገራዊ የችግር ቀዳዳ ሲደፈን ሌላው እያፈተለከ፣ አንዱ የፈተና ጎርፍ ሲገደብ ሌላኛው ፈንቅሎ እየወጣ አሳር መከራችንን ተግተናል። የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ያነሰን ይመስል በማሕበራዊ ሚዲያዎች ይርከፈከፍ የነበረው የክፋት ቤንዚልና ይጫር የነበረው የማቀጣጠያ ክብሪት ይበልጥ ሀገራዊ ችግራችንን እያባባሰና እያጋጋመ እንዳመሰንም አይካድም።
የጓዳችን ችግር ያነሰ ይመስል በባዕዳን አደባባዮችና ጎዳናዎች ላይ የራሳችን ውላጆች ይፈጽሙት የነበረው እኩይ ድርጊትና ተግባርም በታሪካችን ጥቁር መዝገብ ውስጥ በየዕለቱ እየተመዘገበ ይገኛል ባዕዳን መንግሥታትም ተቆርቋሪና አሳቢ መስለው በቁስላችን ላይ አሲድ ሲያፈሱ መክረማቸውም አይዘነጋም። ግብጽና ሱዳን ከአባሪ ተባባሪ መንግሥታት ጋር የህዳሴ ግድባችንን በተመለከተ ሴራ ሲሸርቡና እንቅልፍ ማጣታቸው በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው።
እኒህን ሁሉ ተግዳሮቶች እንደ ሀገር ለመቋቋም የተቻለው “ባህላችን የአደባባይ ምሥጋና ባያበረታታም” ከወጀቡና ከአውሎ ነፋሱ በስተማዶ ያለውን ጸጥታ ባስተዋሉ፣ ከጊዜያዊ ክረምቱ ባሻገር ያለው በጋ ፍንትው ብሎ በታያቸው የተፈተኑ መሪዎቻችን ጥበብና ማስተዋል ስለሆነ “ክብረት ይስጥልን” ብለን በሕዝብ ምርቃት ብንባርካቸው ያንስባቸው ካልሆነ በስተቀር አይበዛባቸውም። “ችግሮቻችን ሁሉ ተቃለዋል፣ አበሳዎቻችን ሁሉ ተወግደዋል” ብለን መኩራራት ደረጃ ላይ ባንደርስም እየተከናወኑ ያሉ ሀገራዊ ልማቶቻችን፣ እየተጠናቀቁ ያሉ ስኬቶቻችንንና የታቀዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶቻችንንና የዲፕሎማሲ ጥረታችንን ስናስብና ስናስተውል ግን ተስፋችን ፋፍቶ ሀሴት ማድረጋችን አልቀረም።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በድምጻችን የሚወለደው መንግሥት መንበረ ሥልጣኑን የሚረከበው በመስከረም ወር መሰናበቻ በጥቅምት ወር መባቻ 2014 ዓ.ም መሆኑን ሕገ መንግሥቱ ደንግጓል። በምልዓተ ሕዝቡ የእንደራሴነት ውክልና ተረክበው የፓርላማውን ደጃፍ ዘልቀው የሚገቡ ተወካዮቻችን የሚረከቧት ሀገር ከላይ ለመጠቋቆም እንደተሞከረው ለመስዋዕትነት የጠራቻቸው እንጂ ለጥቅማ ጥቅም ዳረጎት የተመረጡ እንዳልሆኑ መሃላቸውን ከወዲሁ ከህሊናቸው ጋር ጨርሰው ሊዘጋጁ ይገባል።
ያለመታደል ሆኖ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ የፓርላማችን ቤተኛና ባለጊዜዎች ገዢውን ፓርቲ እያወደሱ ገናናነቱን በመስበክ “ሺህ ዓመት እንዲነግሥ” አጎንብሰው የሚመርቁ እንጂ “መርጦናል” ለሚሉት አካባቢ “አፈ ሕዝብ” ለመሆን እንዳልታመኑ ያልመሸበት ታሪካችን ይመሰክርልናል። ታሪክን ለምስክርነት መጥራት ሳያስፈልግም ዕድሜውን ያደለን ወገኖች በእማኝነት ቃል የምንሰጥባቸውን በርካታ አብነቶች በድፍረት ማስታወስ አይገድም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እንኳን እንደ አንድ ተቆርቋሪ የሀገሪቱ ዜጋ በፓርላማችን ጉዳይ ላይ ያለመታከት በርካታ ጸሑፎችን በዚሁ ጋዜጣ ላይ በድፍረት ማስነበቡ አይዘነጋም።
ለቀጣዩ አዲስ መንግሥት “የሥልጣን መገለጫ ተምሳሌት የሆነውን መዶሻ” ሊያስረክብ ቤቱን እያጸዳዳ ያለው ነባሩ ፓርላማ ጥርስ አብቅሎ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ህልውና ላይ መወሰን የጀመረው “በስተ እርጅና” የመጨረሻው ዕድሜ ላይ እያለ ስለመሆኑ የሚካድ አይደለም። እውነቱን ለመካድ የሚዳዳቸው ካሉም ትዝብት እንጂ ሰሚ ጆሮ የሚሰጣቸው ዜጋ ሊያገኙ አይችሉም።
ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ አይሳካም እያሉ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሲያሟርቱ የነበሩት ሁሉ የሕዝባችንን ልብ ስለማያውቁት ቢዘላብዱም እውነቱ እነርሱ እንደጠበቁት ሳይሆን ቀርቶ “ሙያ በልብ ነው” ብሎ በሚያምነው ኢትዮጵያዊ ወገን የተሰራውን ትንግርት ተመልክተው እጃቸውን በአፋቸው ላይ እስከ መጫን ደርሰዋል።
የመከራ ክረምት ለማዝነብ የሚሞክሩትን የሴረኞች ተንኮል በተመለከተም ሕዝቡ በልብ ስፋት ሁሉንም ችሎ አሳልፏል። አውሎ ነፋስ አነሳስተው በወጀብ ሊያጥለቀልቁን ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። በምርጫው ቢያሟርቱም ሟርታቸው ረከሰ እንጂ አልያዘላቸውም። የህዳሴ ግድባችንን ተስፋ ለማምከን ቢፍጨረጨሩም ተዋረዱ እንጂ አላተረፉበትም። ደግነቱ የቀጣዩን የመንግሥት ወር ተራ የሚረከበው ፓርላማ ሥራ የሚጀምረው እኒህን መሰሎቹ የሀገራዊ ፈተናችን ክረምትና ጎርፍ እየቀለሉ በመሄድ ላይ ስለሆኑ እድለኛ ነው ማለት ይቻላል። በሌላ አንጻርም ከትናንት የተሻለ ሆኖ ባይገኝ የሚያርፍበት የሕዝብ የቁጣ በትር በቀላሉ የሚሰነዘርበት ስለማይሆን ከወዲሁ ምሎና ተማምሎ በፀና ኪዳን ወንበሩ ላይ ሊቀመጥ ይገባዋል።
እስኪመረጡ ድረስ በመሽቆጥቆጥ፤ ከተመረጡ በኋላ ደግሞ “እሽ አትበሉን የሹም ዶሮ ነን!” የሚል ባህርይ የሚስተዋልባቸው “እንደራሴዎችም” ነገ ዛሬን እንደማይሆን በሚገባ ተገንዝበው የወከላቸውን ሕዝብ ከልብ በመሰጠት ዝቅ ብለው ሊያገለግሎት ይገባል። በተዘወተረ የባለሀገር ምሥጢራዊ የአዝመራ ወቅት እንጉርጉሮ እንሰነባበት። “በመስከረም ደረሰልኝ ገብሴ፣ በጥቅምት እላለሁ ጥቂት፣ በህዳር እላለሁ ዳር ዳር፣ በትሣሥ እጅንፉ ድረስ . . .” ልብ ያለው ልብ ያድርግ። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2013